ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የሰሊጥ ግብይት የዋጋ ጣሪያ ገደብ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመነሳቱ ሳቢያ፣ ላኪዎች ሰሊጥ ከአገር ውስጥ የሚገዙበት ዋጋ በእጅጉ በመጨመር ከዓለም ገበያ በላይ እየተሸጠ መሆኑን ላኪዎች ተናገሩ፡፡
ከኅዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወሰነው መሠረት፣ በምርት ገበያ አማካይነት ይወጣ የነበረው የግብይት ዋጋ ጣሪያ የተነሳ ሲሆን፣ ላኪዎችም በገበያው አቅርቦትና ፍላጎት መሠረት በገበያ ዋጋ እንዲገበያዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም በጊዜው በምርት ገበያ የአንድ ኩንታል ሰሊጥ የመጨረሻ ዋጋ 8,870 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በምርት ገበያ እስከ 11,138 ብር ደርሷል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ላኪዎች ማኅበር ኃላፊዎች ገለጻ፣ ከምርት ገበያ ውጪ የሚካሄደው ግብይት እጅግ ከፍ ብሎ ከዓለም ገበያ በላይ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ ነው፡፡ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳዎ አብዲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዓለም ገበያ የዋጋ ለውጥ ካለመኖሩም በላይ እንዲያውም ቅናሽ ታይቷል፡፡
‹‹ነጋዴው ያላግባብ ውድድርና ክምችት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ይህ የአገርን ምርት ማባከንና ምርት በማከማቸት ሊገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ማሳጣት ነው፤›› ሲሉ አቶ ኤዳዎ ተናግረዋል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ከነጋዴዎች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ዋጋ አውጪ ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ኤዳዎ፣ በአቅርቦትና በፍላጎት መመጣጠን መሠረት ዋጋ ሁልጊዜም በገበያ መመራትና ከመንግሥትም በኩል የዋጋ ጣሪያ መቅረብ እንዳልነበረበት ገልጸው፣ አሁን ግን መንግሥት የዋጋ ጣሪያውን ሲያነሳ ዓለም አቀፉ ፍላጎት ብዙም ባልጨመረበት ሁኔታ በነጋዴዎች ፍላጎት ብቻ ዋጋው እንዲህ መወደድ አልነበረበትም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከዚህ በፊትም በጥቅምት ወር መጀመርያ ይህ የግብይት ጣሪያ ገደብ ተነስቶ እንደነበር ያስተወሱት የምርት ገበያው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ነፃነት ተስፋዬ፣ ይህን የማድረግ ኃላፊነትም ሥልጣንም ያለው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው ብለዋል፡፡ በምርት ገበያ በኩል ግን ግብይቱ መቀጠሉን፣ የፍላጎትና የአቅርቦት መመጣጠንን በማገናዘብ እያገበያዩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በየሳምንቱ በሚያወጣው የዓለም ዋጋን ያገናዘበ የምርቶች ዋጋ ማነፃፀሪያ መሠረት፣ የሰሊጥ ዋጋ በከንታል ከ1,600 እስከ 1,700 ዶላር የሚሸጥ ሲሆን፣ ይህም ከ165 ዶላር ያልዘለለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዋጋው በኩንታል ከ8,500 ብር ሊበልጥ እንደማይችልና የዓለም ዋጋ ይህ በሆነበት ሁኔታ በአገር ውስጥ ግን ላኪዎች በኩንታል የሚገዙት ከ2,000 ብር በላይ እየከሰሩ መሆኑን ነው የሚነገሩት፡፡
ከሌሎች በተመሳሳይ ከሚያመርቱ የዓለም አገሮች ጋር ከተወዳዳሪነት እንደሚያስወጣ፣ እንዲሁም በአምራች ገበሬዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ግንዛቤ እንደሚፈጥርና ምርቱ ከሚገባው በላይ ዋጋ ያወጣል በሚል የማከማቸት ልምድም እንደሚከሰት አቶ ኤዳዎ ተናግረዋል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፈው ዓመት በላኪዎች በርካታ ወደ ውጭ መላክ የነበረባቸው ምርቶችን በተደጋጋሚ እንደያዘ፣ ላኪዎችም እንዲልኩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ምርት የማከማቸት ልምድ በዚህኛው የምርት ዓመት እንዳይደገም፣ የንግድና ቀጣናዎች ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው ኅዳር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ላኪዎች የሚልኩትን እህል አቅደው እንዲያስገቡ ማስታወቂያ አውጥቷል፡፡
በማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከኅዳር እስከ ሚያዝያ ወር ድረስ የስድስት ወራት የኤክስፖርት ዕቅዳቸውን እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርቡ አዟል፡፡
ወደ 40 የሚሆኑ የምርት ዓይነቶችን ዘርዝሮ በየወሩ የሚላክ ዕቅዳቸውን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲያስገቡ ባሳወቀበት ፎርም ላይ እንዳሳሰበው፣ ሚኒስቴሩ ዕቅድ ይዘውና አስፈላጊውን ጥራት ጠብቀው ምርቱን ወደ ውጭ በማይልኩ ድርጅት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡
የማኅበሩ ዋና ፕሬዚዳንት አቶ ሲሳይ አስማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህንን ዕቅድ ማውጣት ምንም ችግር እንደሌለውና ላኪዎችም ምርት ይዘው የዋጋ መወደድን በመጠበቅ፣ መንግሥት ያወጣውን የውጭ ምንዛሪ አወሳሰድ መመርያ መቀየር በመጠበቅ ምርት ከመያዝ ይቆጠባሉ፡፡