Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

ቀን:

አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር ዛፍ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ የማገዶ ፍጆታ እንጨት የተቸገሩት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ (1881-1906) መፍትሔ ያገኙት በአማካሪያቸው አልፍሬድ ኢልግ አማካይነት ‹‹ኢካለፕተስ›› የተሰኘውን የዛፍ ችግኝ ከአውስትራሊያ ማስመጣታቸው ነው፡፡ ከባህር ማዶ ስለመጣም ስሙም ‹‹የባህር ዛፍ›› ተባለ፡፡

በሌላ አንፃር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከስድሳ ስድስት ዓመታት በፊት በወርኃ ኅዳር በአውስትራሊያዋ የሜልቦርን ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙት ከተማዋ 16ኛውን ኦሊምፒያድ ከኅዳር 13  እስከ ኅዳር 29 ቀን 1949 ዓ.ም.  (22 ኖቬምበር1956 – 8 ዲሴምበር 1956) ባስተናገደች ጊዜ ነበር፡፡ ከተካፋዮቹ 72 አገሮች በተለይ ኢትዮጵያን በልዩነት ያነሳት አትሌቶቹ እነ ማሞ ወልዴ፣ ገረመው ደንቦባ ወደ ውድድሩ ስፍራ በዳኮታ አውሮፕላን ለአንድ ሳምንት ያህል ተጉዘው መድረሳቸው መነጋገርያ መሆኑ ነበር፡፡ ውጤት ባይቀናቸውም ለአገራቸው የኦሊምፒክ ፋና ወጊ ሆነው መመለሳቸው ነው፡፡

ከስድስት አሠርታት በኋላ በተመሳሳይ በዚሁ ኅዳር ወር በሜልቦርን ከተማ ስመ ጥሩው የክላሲካል ፒያኖ ሙዚቃ ተጫዋቹ ግርማ ይፍራሸዋ፣ ‹‹አዲሱ የአፍሪካ ፒያኒዝም ፋና ወጊ›› የተባለበትን ሥራዎቹን ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› (The Spirit of the Nile) በሚል መጠርያ በኮንሰርት ማቅረቡን የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡

የግርማን ሥራዎች በባህል በዜማ ኢትዮጵያዊ፣ ሲኒማዊ ዕይታንና ውበታዊ ጥልቀትን የተጎናፀፈ፣ ድርሰቶቹ በብሉይ (ክላሲካል) እና በጃዝ መካከል ሆኖ እጅግ በጣም የሚደመጥ ‹‹ልዕለ ኵሉ›› የሆነ ሲል የገለጸው በሙዚቃ፣ በጥበባትና በባህል ላይ የሚያተኩረው ላይም ላይት ማጋዚን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊውን የሙዚቃ ትውፊት ከምዕራባዊው የሙዚቃ ጥበብ ቅርፀት (ፎርማት) ጋር በማስማማት፣ ብሂልን ከባህል ማዛመዱ ነው ግርማ ይፍራሸዋን አዲሱ የአፍሪካ ፒያኒዝም ፋና ወጊ ያደረገው።

የክላሲካል ሙዚቃ ፒያኖኛ ግርማ በተለያዩ የሜልቦርን መድረኮች የምዕራባውያኑንና የኢትዮጵያን ረቂቅ ሙዚቃዎች አዋድዶ እንዲያቀርብ፣ ከአውስትራሊያ የባህል ተቋማት ጋር በመተባበር ያመቻቸው ጃአዝማሪ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ጃአዝማሪ በታዋቂው የፒያኖ ተጫዋች፣ የሙዚቃ ቀማሪና አቀናባሪ ዳንኤል አጥላው ሰይፉ የተመሠረተ ነው፡፡

ጃአዝማሪ ከግርማ ይፍራሸዋ በፊት ማህሙድ አህመድን፣ ዓሊ ቢራን፣ ዓለማየሁ እሸቴንና እንዳልካቸው የኔይሁንን (2ፓክ) በመጋበዝ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለዳያስፖራውና ለአውስትራሊያውያን ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡

በአንድ ሐተታ ላይ እንደተከተበው፣አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደው ግርማ ይፍራሸዋ  ከፒያኖ ጋር ያለው ጥብቅ ትስስር ከኢትዮጵያዊቷ ፒያኖ ተጫዋችና አቀናባሪ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ አገራዊውን “ፔንታቶኒክ ስኬል” ከምዕራባዊው ጥበበ ሙዚቃ ፎርማት አያይዞ መጠቀሙ ደግሞ ድርሰቶቹ አካዴሚያዊ ዕይታ ካላቸው ሥራዎች ጋር እንዲታይ ያደርገዋል።

ፒያኖ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃዊ ቅርስ ባይሆንም የሙዚቃን አዲስ ገጽታ በማሳየት በኩል የቅርብ ዘመናት ትውልድ ሙዚቀኞችን መሳቡ አልቀረም፡፡ ከእነዚህም መካከል ከአገሩም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፒያኖ ረቂቅ ሙዚቃ ተጫዋችነቱ ግርማ ይፍራሸዋ ይጠቀሳል፡፡

ከእርሱ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት አሠርታት በላይ ዝናቸው የናኘው መኖሪያቸውን በኢየሩሳሌም (እስራኤል) ያደረጉት የ99 ዓመቷ የዕድሜ ባለፀጋ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ግርማ የርሳቸውን ፈለግ በመከተል በተለያዩ አገሮች ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ አውስትራሊያ የፒያኖ ኮንሰርቱን አቅርቧል፡፡ ብሉይ (ክላሲካል) ሙዚቃን ከኢትዮጵያ ትውፊት/አላባ ጋር በማስተሳሰር የራሱን ቱባ ሙዚቃ በመሥራትና በመቀመርም ይጠቀሳል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ተወልዶ ያደገው ሙዚቀኛው የፒያኖ ጌታ ግርማ ይፍራሸዋ በገጸ ታሪኩ እንደተመለከተው፣ የሙዚቃ ሕይወቱን አሐዱ ብሎ የጀመረው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ የሆነውን ክራር በመጫወት ነው፡፡

በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲማር በኋላ ላይ ለተጠበበበት ለብሉይ ሙዚቃ (ክላሲካል) ተጫዋችነት ካበቃበት ፒያኖ ጋር ተዋውቋል፡፡ ከፍተኛ ትምህርቱን በቡልጋሪያ ሶፊያ ስቴት ኮንሰርቫቶሪ ኦቭ ሙዚቃ በመከታተል ተመርቋል፡፡ በተከታታይም በለንደን የሮያል ሙዚቃ አካዴሚና በላይፕዚንግ የሙዚቃና ቴአትር ተቋም ብሉይ ሙዚቃን ለመቅሰም ችሏል፡፡

በቡልጋሪያ የታላላቅ ሙዚቀኞችን የነሞዛርት፣ ቤቶቨን፣ ሹማን፣ ሹበርት፣ ቾፒንና ዴቡሲ ሥራዎች በማቅረብም አድናቆትን አትርፏል፡፡

በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ፒያኖን ያስተማረው ግርማ፣ አገራዊ ሙዚቃንና ብሉይ ሙዚቃን አስተሳስሮ፣ ብሂልን ከባህል አዛምዶ በአገር ውስጥ በውጭ አገሮች ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡

ካሳተማቸው የክላሲካል (ብሉይ) ሙዚቃ አልበሞቹ መካከል ‹‹ሼፈርድ ዊዝ ዘ ፍሉት›› (ባለዋሽንቱ ዕረኛ)፣ ‹‹ላቭ ኤንድ ፒስ›› (ፍቅርና ሰላም)፣ መለያ ቀለሜ (ከሚካኤል በላይነህ ጋር)፣ ሰመመን፣ እልልታ ይገኙበታል፡፡

የታዋቂውን ገጣሚና ሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹ሀገሬ›› ግጥምን በፒያኖ አቀናብሮ በማቅረቡም አድናቆትን ማትረፉ ይታወሳል፡፡

በቅርቡ በአሜሪካው ቤተስዳ ብሉዝ ኤንድ ጃዝ ሱፐር ክለብ ሙዚቃዎቹን ያስደመጠው ግርማ፣ በአይኤስ በግፍ ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ የሚሆን ሙዚቃም ተጫውቷል፡፡ ከወራት በፊት የለቀቀው አልበም ‹‹ፒስ ኤንድ ላቭ›› በዛው አሜሪካ ሪከርድ የያዘ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ‹‹ሰመመን›› የተሰኘው ሙዚቃ የዓመቱ ምርጥ የክላሲካልና ብሉዝ ሙዚቃ ሆኗል፡፡

ዋሽንግተን ፖስት ግርማ ሙዚቃውን ስላቀረበበት የሙዚቃ ኮንሰርት በዝርዝር ዘግቧል፡፡ ‹‹ከዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ኮንሰርቶች አንዱ በሆነው ዝግጅት የአውሮፓውያን ፒያኖ ጨዋታ ተሞክሮውን በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ አሳይቷል፤›› ብሏል፡፡ የቾፒንና ሹማን ሙዚቃዎች ላይ ልዩ ሪትም ጨምሮበት ማስደመጡ የሙዚቃውን ውበት እንዳጐላው ተገልጿል፡፡ ‹‹ኦተም›› የተሰኘውን የቲቻኮቮስኪ፣ የሊስዝትን ‹‹ኮንሶሌሽን ነምበር 3›› እና የጄምስ ሊ ‹‹ሜሞሪስ ኦፍ አክሱም›› እንዲሁም ራሱ ያቀናበራቸውን ሙዚቃዎች ተጫውቷል፡፡

በዕለቱ ‹‹ላቭ ኤንድ ፒስ›› ከተሰኘው አልበሙ መርጦ ካቀረባቸው ሙዚቃዎቹ መካከል በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ላይ ተመሥርተው በአውሮፓ ቴክኒክ የቀረቡት ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹እልልታ›› እና ‹‹ባለ ዋሽንቱ እረኛ›› ከቀረቡት ሙ.ዚቃዎች መካከል ሲሆኑ፣ ‹‹አምባሰል›› ባህላዊ ሙዚቃን በቤትሆቨን ዘዬ ማቅረቡም ተመልክቷል፡፡

ግርማ ምሽቱን ያደመቁና ተወዳጅ ድባብ የፈጠሩ ሙዚቃዎችን እንዳቀረበ በመዘርዘር ‹‹አውሮፓ ውስጥ ሙዚቃ ያጠናውና አሜሪካ ውስጥ ኮንሰርት ያቀረበው ሙዚቀኛ በርካታ አስገራሚ ሥራዎች አስደምጧል፤›› መባሉም አይዘነጋም፡፡ 

ማስተር ፒያኒስት ግርማ በፒያኖ ረቂቅ ሙዚቃ ሙያው ላበረከተው ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ከወር በፊት የጣሊያን መንግሥት ‹‹ኤ ግራንድ ፕሬዚዳንሻል አዋርድ-ዘ ኦርደር ኦቭ ዘስታር ኦቭ ኢታሊ›› የተሰኘውን ፕሬዚዳንታዊ ሽልማትን ሲሰጠው ባሰማው ዲስኩር፣ ‹‹ለሙዚቃ የከፈልኩትን የፍቅር ዋጋ [ሽልማቱ] ከፍሎልኛል ብዬ አስባለሁ፤›› ማለቱ ይታወሳል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በአውስትራሊያ ኮንሰርቱን ያቀረበው የፒያኖው ጌታ (ማስተር) ግርማ ይፍራሸዋ ከኮንሰርቱ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ የሜልቦርን የናይል /ዓባይ መንፈስ ኮንሰርት ፍሬያማና መሳጭ ትውስታዎችን የያዘ ዑደት መሆኑን በመግለጽ ለዝግጅቱ ስኬት የተባበሩትን አመስግኗል፡፡

በዋናነት የቀድሞ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪና የብሔራዊ ቴአትር ሙዚቀኛ ዳንኤል አጥላው ሰይፉ፣ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ ከአውስትራሊያ የባህል ተቋማት ጋር በመተባበር ላደረገው ቁርጠኝነት ልባዊ አድናቆትና ምስጋናውን ያቀረበው ግርማ፣ በሁሉም ኮንሰርቶች የተገኙት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብንም በትልቅ አክብሮት ያወደሰው  ለወደፊቱ  ተጨማሪ የባህል ማስተዋወቅ እንደሚኖር ተስፋ በማድረግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...