ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ አንደኛው ነው፡፡ በማኅበረሰብ ደረጃ መሠረታዊ የሆነው ልብስ አግባብነት ያለውና ጊዜውን የዋጀ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ቅር ማሰኘቱ አይቀሬ ነው፡፡
ልብስ ለሁሉም የሰው ልጆች አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ለልብስ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል፡፡
በሰላም ዕጦት፣ በኢኮኖሚያዊና በሌሎችም ችግሮች ምክንያት ልብስና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በተለይ የሚያጡት እንስቶች ናቸው፡፡ ቀልድ የሚመስል ነገር ግን የልብስ ዋጋ እየተወደደ መምጣቱም አቅም ፈትኗል፡፡
በተደጋጋሚ አንድ ልብስ በመልበሳቸው ምክንያት የሚሳቅቁም አሉ፡፡ ቅያሪ ልብስ አጥተው ሳይወዱ በግዳቸው ራሳቸውን ከማኅበራዊ ግንኙነት የሚያገሉም አይጠፉም፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የ‹‹ንጉሡ ሴት ልጆች›› ተቋም ‹‹ልብሴን ለእህቴ›› የተሰኘ አዲስ ንቅናቄ ጀምረዋል፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት የተጀመረው ‹‹ልብሴን ለእህቴ – ‹እኔ ልብሴን ለእህቴ እሰጣለሁ› አንቺስ?›› በሚል መሪ ቃል ልብስ የመሰብሰብ ዘመቻ ሲሆን፣ ማንም ሴት በልባሽ ጨርቅ ምክንያት ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል የለባትም የሚል ዓላማን ሰንቋል፡፡
የ‹‹ንጉሡ ሴት ልጆች›› በሴቶች ላይ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ወ/ሪት ዘመነ መሣፍንት ደግሞ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እንደ ቀልድ ሴቶች ላይ የሚታይ የልብስ ችግር ወደ ሥራ ገበታቸውና ወደ ማኅበረሰቡ እንዳይቀላቀሉ እንደሚያደርግ ወ/ሪት ዘመነ ይናገራሉ፡፡
ከጓደኞቸው ጋር ለመገናኘትና ማኅበራዊ ሕይወትን ለመምራት ምን ለብሼ ልሂድ፣ ቦታውን የሚመጥን ልብስ የለኝም፣ ስለዚህ ብቀር ይሻላል የሚሉ ሴቶች አይታጡም ይላሉ፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ በታክሲ፣ በአውቶቡስ፣ በባቡር ትራንስፖርት ሲጠቀም ሴቶችን ቢቃኝ ጥቂት የማይባሉት እንስቶች በቅያሪ ልብስ ዕጦት መሰቃየታቸውን ማየት እንደሚቻል ሥራ አስኪያጇ ይገልጻሉ፡፡
ይህ ሁኔታ ‹‹ጆሮ ዳባ›› ተብሎ የተደበቀና በግልጽ የማይነገር በመሆኑ፣ በንጉሡ ሴት ልጆች መሥራች በወ/ሮ ፌቨን ጋሻው ሐሳብ አመንጪነት ሴቶችን ለማገዝ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ችግሩ ጥናትና ምርምር ባይደረግበትም በአካባቢያችን የምንቃኘው ነው፣ ለዚህም ልብሴን ለእህቴ በሚል ንቅናቄ፣ የልብስ ማስቀመጫ ቁም ሳጥናቸው በማይለብሱት ልብስ የተጨናነቀባቸው ሴቶች፣ ለሌላቸው የማከፋፈልና የመስጠት ዘመቻን እንዲቀላቀሉ እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዘመቻ ለ500 ሴቶች ልብስ፣ ጫማና ቦርሳ እንዲያገኙ የሚያደርጉ መሆኑን፣ ይህም የተወሰኑ እንስቶችን ችግር ይቀርፋል የሚል እምነት እንዳላቸው፣ የሚሰባሰቡት ልብሶችም እህቶች ሳይሳቀቁ ማኅበራዊ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ለማድረግ እንደሆነ አክለዋል፡፡
‹‹ልብሴን ለእህቴ›› ንቅናቄ የመጀመርያው ዙር እስከ ኅዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ እንደሆነና በዓመት አራት ጊዜ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
ዕገዛ የሚደረገው በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ሴቶች መሆኑን፣ በከተማም አስተዳደራዊ መዋቅር መሠረት ታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ተብለው ለተለዩት ሴቶች ዕገዛው እንደሚደረግ ወ/ሪት ዘመነ ተናግረዋል፡፡
አሁን በማኅበራዊ ትስስርና ገጻቸው ጭምር እኔም ልብስ እፈልጋለሁ? የሚሉ ጥያቄዎች እየመጣላቸው መሆኑንና የእርጉዝ ልብሶች፣ ቦርሳዎች፣ ጫማዎችና ሌሎችም የሴቶች መገልገያዎችን ለእንስቶች ለማዳረስ እየሠሩ መሆኑን፣ ዕገዛ እየተደረገ ያለው የልብስ ዓይነቶች ሊለበስ የሚችልና ንፁህ እንደሆነ፣ በተጨማሪም ጫዎችና ቦርሳዎችም የሚለግሱ መኖራቸውን፣ በዋናነት ዕገዛ የሚደረግላቸው ደግሞ ገቢያቸው ከምግብና ከቤት ኪራይ አልፎ ልብስ መግዛት ለማይችሉ ሴቶች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአገር ባህል ልብሶች፣ ጋቢዎች፣ የአዋቂና የወጣት ሴት ልብሶች እየተሰበሰቡ ከሚገኙ የልብስ ዓይነቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ከልብስ ማሰባሰብ ባሻገር የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ለመሰብሰብ ዕቅድ እንዳላቸውና በዘመቻው አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እየተሳተፉበት እንደሚገኙና ‹‹ማንም ሴት በልብስ እጦት ምክንያት ከማኅበራዊ ሕይወት አትገለል!›› በሚል ንቅናቄው መጀመሩ ታውቋል፡፡
‹‹የንጉሡ ሴት ልጆች ወርቃማ መንገዶች›› የተሰኘ አዲስ መጻሕፍ የጻፉት ወ/ሮ ፌቨን፣ ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ የተሰናዳ መሆኑን፣ ተቋማቸውም ወጣት ሴቶችን በተፈጠሩበት ማንነት ልክ እንዲኖሩ በማገዝ፣ በማንቃት፣ በማማከር፣ ሥልጠና በመስጠትና የትምህርት ዕድሎችን በማመቻቸት እንደሚሠራ ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡