Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

ቀን:

በፍቅር አበበ

የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ በአገር አቀፍ ደረጃ በ2006 ዓ.ም. የተጀመረው የትምህርት ኢንስፔክሽን፣ ከትምህርት ቤት የቁጥጥር ሥርዓት አንዱ ነው፡፡

ኢንስፔክሽን የእያንዳንዱን ትምህርት ቤት የትምህርት ግብዓት፣ ሒደትና ውጤት በመመዘንና ባለ አራት ደረጃ የመለኪያ መሥፈርት በማውጣት ለትምህርት ቤቶች ከአንድ እስከ አራት ደረጃዎች የሚሰጥበት የመመርመር ሒደት ነው፡፡

የግብዓት መሥፈርት የመማርያ አካባቢ፣ የትምህርት ቤት አመራርና አስተዳደር የሚመዘንበት ሲሆን፣ ሒደት ደግሞ የመማርና ማስተማር ሒደቱ የሚለካበት ነው፡፡ ውጤት ትምህርት ቤቱ ከወላጆችና ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት፣ የተማሪዎች ውጤትና ሥነ ምግባር የሚለካበት ነው፡፡

ይህንን መሠረት አድርጎ በ2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኙ በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአማራጭ መሠረታዊ ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች፣ በኦ-ክፍሎች፣ በቅድመ አንደኛ ክፍሎች፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ተከናውኗል፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣንም የተገኘውን ውጤት ባለፈው ሳምንት ለሚመለከታው አካላት ይፋ አድርጓል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ከታዩት 57 ኦ ክፍሎች 19.3 በመቶ ደረጃ አንድ ማለትም ደረጃውን ያላሟሉ፣ 77.2 በመቶ ደረጃ ሁለት ማለትም በመሻሻል ላይ ያለ እንዲሁም 3.5 በመቶ ደረጃ ሦስት ደረጃውን አሟልተው ተገኝተዋል፡፡

ኢንስፔክት ከተደረጉ 71 አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ቤቶች 32.4 በመቶ ደረጃ አንድ፣ 67.6 በመቶ ደረጃ ሁለት ሆነው ሲገኙ፣ ኢንስፔክት ከተደረጉ 453 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 24.5 በመቶ ደረጃውን ያሟሉ ሲሆኑ፣ እነዚህም 26 የመንግሥትና 85 የግል ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ከደረጃ በታች ከሆኑት 75.49 በመቶ ትምህርት ቤቶች 75 የመንግሥትና 267 የግል ሲሆኑ፣ 340 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 40.6 በመቶ ደረጃውን ያሟሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

59.4 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሲሆኑ፣ ኢንስፔክት ከተደረጉ 120 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 51.7 በመቶ ደረጃውን አሟልተው ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም 24 የመንግሥትና 38 የግል ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡

ደረጃቸውን ያሻሻሉ 132፣ ደረጃቸውን ያላሻሻሉ 643፣ ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ያሉ 128 እና በበጀት ዓመቱ እንደ አዲስ የታዩ 130 መሆናቸውን የኢንስፔክሽኑ ሪፖርት ያሳያል፡፡

በግብዓት መለኪያ መሠረት፣ ትምህርት ቤቶች ለደረጃው የሚመጥኑ የሰው ኃይል በስታንዳርዱ መሠረት ማሟላት አለመቻላቸው የታየ ክፍተት ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች በተለይም የመንግሥት ቅድመ አንደኛ የመማር ማስተማሩን ሒደት ለማሻሻል ላቀዳቸውና ቅድሚያ ለሰጣቸው ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውል ሀብት ማሟላት አለመቻላቸውም ታይቷል፡፡

በሒደት መለኪያ ደግሞ በትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርቱ ተገቢነት ያለው፣ አሳታፊና የሕፃናትን የዕድገት ደረጃ፣ ፍላጎቶችና ልዩነት ያገናዘበ መሆኑን መምህራንና ረዳት መምህራን የሚገመገሙበትና ግብረ መልስ የሚሰጡበት ሒደት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች ሆኖ መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

ትምህርት ቤቶች የሰው፣ የገንዘብና የንብረት ሀብት አጠቃቀም ሥርዓት ተዘርግተው ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሥርዓት ደካማ መሆንና መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ መርሀ ግብርን ተግባራዊ ማድረግ ላይ በተለይም በግል ትምህርት ተቋማት ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩ ታይቷል፡፡

በውጤት መለኪያ መሠረት ደግሞ፣ ትምህርት ቤቶች ከወላጆች (ከአሳዳጊዎች)፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠርን ባቀዱት ልክ ማሳካት አለመቻላቸውና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የክፍል፣ የብሔራዊ ፈተና ውጤቶች ከሚጠበቀው አገራዊና ክልላዊ መመዘኛ ጋር ሲነጻጸር በሚጠበቀው ደረጃ ልክ አለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ 

በ2014 ዓ.ም. የኢንስፔክሽን አገልግሎት ካገኙ 128 የኦ ክፍል እና አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት መስጫ ተቋማት 126 (98.43 በመቶ) ተቋማት ከደረጃ በታች በመሆናቸው ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግም የባለሥልጣኑ የአጠቃላይ ኢንስፔክሽን ቡድን መሪ ሲሳይ ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም የኢንስፔክሽን አገልግሎት ካገኙት 913 የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ውስጥ 8 (0.09 በመቶ) ደረጃ 1 (ደረጃውን ያላሟሉ)፣ 594 (65.1 በመቶ) ደረጃ 2 (በመሻሻል ላይ የሚገኙ)፣ 310 (34 በመቶ) ደረጃ 3 (ስታንዳርዱን ያሟሉ) እና 1 (0.09 በመቶ) ደረጃ 4 (ደረጃቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሟላ) መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የ2014 ዓ.ም. የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኢንስፔክሽን ውጤት ከ2013 ዓ.ም. የኢንስፔክሽን አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ደረጃቸውን ያሟሉ ትምህርት ተቋማት በመንግሥት 2.6 በመቶና በግል 2 በመቶ ያህል መሻሻል ታይቶባቸዋል፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኢንስፔክሽን ውጤት ከ2013 ዓ.ም አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ደረጃቸውን ያሟሉ ትምህርት ተቋማት በመንግሥት 25.81 በመቶና በግል 15 በመቶ መሻሻል ማሳየታቸውን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኢንስፔክሽን ውጤት ከ2013 ዓ.ም. የኢንስፔክሽን አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር፣ ደረጃቸውን ያሟሉ ትምህርት ተቋማት በመንግሥት 25.81 በመቶና በግል 15 በመቶ መሻሻሉን፣ ከ2013 ዓ.ም. የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ውጤት ጋር ሲነጻጸር ደረጃውን ያሟሉ የትምህርት ተቋማት ከ22.9 በመቶ ወደ 29.9 በመቶ ማደጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ምን መደረግ አለበት?

የትምህርት ሥራ የብዙ ባለድረሻ አካላትን ተሳትፎ፣ በቅንጅት መሥራትንና አገርን የመገንባት ከፍተኛ የኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም ትምህርት ቤቶች በተለይም የመንግሥት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማሻሻል ራሳቸው በጀት የሚያንቀሳቅሱበትን ሥርዓት መፍጠር እንዳለባቸው አቶ ሲሳይ አክለዋል፡፡

በደረጃው መሠረት የሠለጠነ የሰው ኃይል በተለይም በቅድመ አንደኛ ደረጃ የመምህራን እጥረት የከተማው የትምህርት ዘርፍ ቁልፍ ችግር መሆኑን ግኝቱ አሳይቷል፡፡ ትምህርት ቤቶች ለደረጃው የሚመጥን ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራንና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎችን በገበያው ላይ እያገኙ ባለመሆኑ ትምህርት ቢሮ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ስልት ነድፎ ሊሠራ ይገባልም ተብሏል፡፡

መምህራንና የትምህርት ቤት አመራር፣ በሥርዓተ ትምህርት ግምገማ መሳተፍ የሚችሉበትን ሥርዓት በሚገባ መተግበር፣ የድጋፍና ክትትል ሥርዓትን ከትምህርት ቢሮ እስከ ትምህርት ቤት አመራር ድረስ በዕቅድ መምራትና ውጤት ተኮር እንዲሆን ማድረግ፣ ወላጅንና የአካባቢን ማኅበረሰብ ከድጋፍ ባለፈ በተማሪ ውጤትና ሥነ ምግባር ዘርፍ መሳተፍ የሚችሉበት ሥልት መቀየስና መተግበር እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...