Sunday, July 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓባይ ባንክ 1.3 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት 70 ቅርንጫፎቹ ከአገልግሎት ውጪ ሆነው የቆዩበት ዓባይ ባንክ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.3 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና የካፒታል መጠኑን ወደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ 

ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት ክንውኑና የድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔውን አስመልክቶ ባፈለው ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፣ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም፣ አብዛኛዎቹ የባንኩ የሥራ አፈጻጸሞች ውጤታማ እንደነበሩ አስታውቋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ በመላ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ቅርንጫፎች ውስጥ 25 በመቶ ወይም 70 ቅርንጫፎች በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከስድስት ወራት በላይ ከአገልግሎት ውጪ ሆነው መቆየታቸው፣ በባንኩ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን የባንኩ የስትራቴጂና ማርኬቲንግ ዋና መኮንን አቶ ወንድይፍራው ታደሰ ገልጸዋል፡፡ 

ቅርንጫፎቹ ከስድስት ወራት በላይ ምንም ዓይነት አገልግሎት የማይሰጡ ሆነው በመቆየታቸው፣ የተሰጡ ብድሮችን ለማስመለስ ትልቅ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቅርንጫፎቹ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብና መልሰው ለማበደር አለመቻላቸው በራሱ የባንኩ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላሳረፈ ዓመታዊ ትርፉ ላይ ጫና ማሳደሩን አቶ ወንድይፍራው ተናግረዋል፡፡  

ይህም ቢሆን ግን ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ13 በመቶ ብልጫ በማሳየት ከታክስ በፊት ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ ችሏል፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት 1.15 ቢሊዮን ብር አትርፎ ነበር፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ በሆኑት ቅርንጫፎቹ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት ብድር መስጠቱን የገለጸው፣ ዓባይ ባንክ ለዚህ ብድር የያዘው መጠባበቂያ የባንኩ ትርፍ በሚጠበቀው ልክ ከፍ እንዲል ማድረጉን አሳውቋል።

ይህም የባንኩን የተበላሸ የብድር መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከፍ እንዳደረገው አመልክቷል። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ጣሪያ አንፃር ሲታይ የባንኩ የብድር ክምችት ጤናማ መሆኑን እንደሚያሳይ አስታውቋል፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን 1.5 በመቶ ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. ግን ወደ 3 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡   

ቅርንጫፎቹ ከሥራ ውጪ ባይሆኑና ሌሎች አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮች ባይከሰቱ ባንኩ ከዚህም በላይ ሊያተርፍ ይችል እንደነበርም ተገልጿል፡፡ 

በርካታ ቅርንጫፎቹ ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸው ከፈጠረው ተግዳሮት ባሻገር፣ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የዋጋ ንረትና ተያያዥ ጉዳዮችም በባንኩ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ ስለማሳደሩም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ኢትዮጵያ ታደሰ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከዋጋ ንረቱ በተጨማሪ፣ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሻሻል ባለመቻሉ የባንክ ኢንዱስትሪው ላይ የራሱ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰዋል።  

ከሰሜኑ ግጭት ጋር በተያያዘ 25 በመቶ የሚሆኑ የባንካችን ቅርጫፎች ለስድስት ወራት ያህል አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ አስታውሰው፣ ይሁንና የደረሱትን ጉዳቶች በመጠገን፣ እንዲሁም የጠፉና ከጥቅም ውጪ የሆኑ ንብረቶች በመተካት በሚቻለው ፍጥነት ቅርንጫፎቹን ወደ ሥራ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንደተደረገ የቦርድ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን ነባራዊ ሁኔታው ለሥራ ምቹ ከባቢ የፈጠረ ባይሆንም፣ ባንካችን ከበርካታ መለኪያዎች አንፃር በዓመቱ ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል፤›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ በምሳሌ የጠቀሱት ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 8.5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ነው፡፡ ይህም የ35 በመቶ ዕድገት እንደነበረው አመልክተዋል፡፡ 

አቶ ወንድወሰን ይፍራው በበኩላቸው፣ በሒሳብ ዓመቱ የነበሩ ጫናዎች በትርፍ ዕድገቱ ላይ የተወሰነ ጫና ከማሳደሩ በውጪ በሌሎች የባንኩ አፈጻጸሞች ግን ከ30 እስከ 40 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 32 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን፣ ይህንን ስኬት ለማስመዝገብም ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ የከፈታቸው 87 አዳዲስ ቅርንጫፎች ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

የአስቀማጭ ደንበኞቹ ቁጥርም በሒሳብ ዓመቱ በ470 ሺሕ በማደግ ወደ 1.6 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የገለጹት አቶ ወንድይፍራው፣ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠንም በ34 በመቶ ጭማሪ በማሳየት አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት 27 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የተከፈለ ካፒታልንም በማሳደግ ረገድ በሒሳብ ዓመቱ የተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወንድይፍራው፣ በአንድ ዓመት ውስጥ የተከፈለ ካፒታል መጠኑን በአንድ ቢሊዮን ብር በማሳደግ አራት ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን ደግሞ የ35 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል። 

በርካታ አዳዲስ ባንኮች የባንክ ኢንዱስትሪውን እየተቀላቀሉና ዘርፉ እየሰፋ መምጣቱን አስመልክቶ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠ መጪውን ውድድር ለመቋቋም የሚያስችል ዝግጅት መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የባንክ ኢንዱስትሪው እየሰፋ ከመምጣቱ በተጨማሪ ከተለመዱት የባንክ ተቋማት ባሻገርም፣ ኢትዮ ቴሌኮምና በርካታ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ዘርፉን በመቀላቀል ላይ እንደሚገኝ አቶ የኋላ ጠቅሰዋል፡፡ ዘርፉን ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ክፍት ለማድረግ ከሚደረገው የመንግሥት ጥረት ጋር ተያይዞ፣ ውድድሩ የበለጠ እየጠነከረ እንደሚሄድ እንደሚጠበቅም ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል፡፡ በዓመቱ ከታዩ ሌሎች ተጠቃሽ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች መካከል በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያን ለማቋቋም መንግሥት የአክሲዮን ገበያ አዋጅን ከማስፀደቅ አንስቶ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያን ለመመሥረት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች የባንክ ኢንዱስትሪው እየተለወጠ ስለመሄዱ አመላካች ነው ብለዋል፡፡ 

ዓባይ ባንክ ከወቅታዊ የፋይናንስ ዘርፉ ውድድር አንፃር አዲስ ስትራቴጂ እየቀረፀ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድይፍራው ደግሞ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ የሚመጣውን ውድድር ተቋቁሞ ለመቀጠል የሚያስችል ስትራቴጂ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የባንክ ገበያ ውስጥ መከፈት ዘርፉን የሚያጠናክርና የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል፡፡ 

የውጭ ባንኮች መግባት ምናልባትም ባንኮች እንዲዋሃዱ የሚያስገድድ ሁኔታን ቢፈጥር፣ ዓባይ ባንክ ከሌሎች ባንኮች ጋር ተዋህዶ መሥራት ይችል እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የባንኮች ውህደት በተቆጣጣረው መሥሪያ ቤት (ብሔራዊ ባንክ) ውሳኔ ወይም ሁኔታው ራሱ ገፊ ሆኖ ሊተገበር የሚችል እንደሆነ እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እንደ ባንክ እኛ ራሳችንን የምናየው አንደኛ በራሳችንና በምንችለው ሞዴል ፈጣነን የምንሠራውን ሥራ በጥሩ ሁኔታ ለመሥራት እንሞክራለን፡፡ በራሳችን የምናደርገውን ጥረት የሚቀድም ፈጣን ለውጥ የሚመጣ ከሆነ መዋሃድ አማራጭ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ጉዳይ ባንኩ አሁን እየቀረፀ ባለው ስትራቴጂ ውስጥ እንደ አንድ ጉዳይ የተያዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድይፍራው፣ የባንኩን ዕድገት በፍጥነት ማረጋገጥ ከተቻለ ውህደት እንደ አማራጭ የሚታይ አይሆንም ብለዋል። ውህደት አማራጭ ከሆነ ደግሞ በሰፊ ጥናት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ውህደቶች ውጤታማ ስለማይሆኑ ትክክለኛ ውህደት እንዲኖር ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓባይ ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩን አራት ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ወደ 12 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስኗል። ዓባይ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ4,327 በላይ ባለአክሲዮኖች እንዳሉትና የሠራተኞቹን ቁጥር ደግሞ ከ6,990 በላይ ሲሆኑ፣ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ደግሞ ወደ 372 ማሳደግ ችሏል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች