የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለና በመንግሥትና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ከታክስ ጋር በተያያዙ የሚነሱ አመግባባቶችን የሚመለከት ተቋም ነው፡፡ ግለሰቦችና ነጋዴዎች በጉምሩክና በገቢዎች የተጣሉ ታክሶች ላይ የሚያቀርቡትን ይግባኝ የሚመለከት የራሱ ችሎትም አለው፡፡ ኮሚሽኑ በ2015 ዓ.ም. የመጀመርያው ሩብ ዓመት ብቻ 1.26 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን ላላቸው 202 መዝገቦች ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከኮሚሽኑ መቋቋም ጀምሮ ፕሬዚዳንት ሆነው ተቋሙን እየመሩ ያሉት አቶ ሙሉጌታ አያሌው ስለተቋሙ ሥራዎች ተደራሽነት፣ የገለልተኝነት ጉዳይና ከአገሪቱ የታክስ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከአማኑኤል ይልቃል ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በ2008 ዓ.ም. ራሱን ችሎ እንዲቋቋም በአዋጅ ከተደነገገ በኋላ፣ ተግባራዊነቱ ቢዘገይም በይፋ ሥራውን ከጀመረ አራት ዓመታት ሆኖታል፡፡ የኮሚሽኑ ሥራ ግን በንግድ ማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ዕቅውና እምብዛም ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ራሱን ችሎ ከመውጣቱ በፊት በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የግብር ይባኝ ሰሚ ጉባዔ ተብሎ ይታወቅ ነበር፡፡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ለብዙ ጊዜያት ቆይቷል፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር እያለ ሥራውን ሲሠራ የነበረው ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከንግዱ ማኅበረሰብና ከፍትሕ ሚኒስቴር በተወጣጡ የትርፍ ጊዜ አባላት ነበር፡፡ ሥራው የሚሠራው እነዚህ ሰዎች ከተገናኙ ነበር እንጂ፣ እንዲገናኙ የሚያስገድዳቸው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች አቤቱታ አቅርበው ውሳኔ ሳይሰጥ ረዥም ጊዜ እንደሚቆይ ያውቁ ነበር፡፡ የኮሚቴው አባላት በሚገናኙ ጊዜም ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ፣ በፍትሕ ሚኒስቴርና በንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች መካከል ክርክር ሲደረግ ነበር የሚውለው፡፡ ሁለቱም ለወከላቸው አካል ያደሉ ነበር፡፡ ሰዎቹ ባለመገናኘታቸውና ክርክር ሲደረግ ውሳኔ ባለመሰጠቱ፣ ሰዎች ተስፋ በመቁረጥ ውሳኔ አናገኝም በሚል መንፈስ ትኩረት አይሰጡትም ነበር፡፡
የሚነሱ ቅሬታዎች እየበዙ ሲመጡ መንግሥት ይህንን ጉዳይ የተረዳው ይመስለኛል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ፓርላማው ለዕረፍት ከወጣበት ተጠርቶ ነበር የገቢ ግብር አዋጁን የታክስ አስተዳደር አዋጅ እንዲፀድቅ የተደረገው፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጁ በአንቀጽ 86 ይህንን ኮሚሽን ሲያቋቁም፣ በጣም ትኩረት እንደተሰጠው የሚያሳየው ተጠሪነቱ ራሱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ብዙ የሚከታተላቸው ተቋማት ስላሉና በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን እንዲከታተሉ የሚፈቅድ ስላልነበረ፣ በ2011 ዓ.ም. የፌዴራል አስፈጸሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ሲወጣ ተጠሪነቱ ወደ አሁኑ ፍትሕ ሚኒስቴር ተዛውሯል፡፡ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም በአዋጅ የተደነገገው በ2008 ዓ.ም. ቢሆንም፣ የተቋቋመው ግን ከለውጡ በኋላ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው ትኩረት ሰጥተው፣ ለአምስት ዳኞችና ለፕሬዚዳንቱ ሹመት ሰጥተው እንዲቋቋም ያደረጉት፡፡
በወቅቱ ሥራ ስንጀምር 719 ውዝፍ መዝገብ ነበር፡፡ መጀመሪያ ከፍትሕ ሚኒስቴር ኮሚቴ አቋቁመን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችን ቅጥር እንዲፈጽም አድርገን፣ እኔን ጨምሮ የተሾሙት ዳኞች ይህንን ውዝፍ መዝገብ የማጥራት ሥራ መሥራት ነበር፡፡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ የተደረሰው የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት እነዚህን መዝገቦች ለማጠናቀቅ ጥረት አድርገን ነው፡፡ ለዚያ ነው ኮሚሽኑ አይታወቅም፣ ተደራሽም አልነበረም፣ ሰውም ቢመጣ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ አልነበረም ብለን የምንገልጸው፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ አሁንስ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው?
አቶ ሙሉጌታ፡- አሁን ያለንበት ሁኔታ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ አሁን ለሥራው የሚያስፈልጉ 39 የድጋፍ ሠራተኞችን እኔን ጨምሮ ሰባት ዳኞች አሉን፡፡ ቁጥራችን ጥሩ ነው፡፡ መዝገቦችም በተያዘላቸው ቀጠሮ ውሳኔ እያገኙ የሚወጡበት አሠራር ተጀምሯል፡፡ በተጨማሪም ማንም ቅሬታ ያለው አካል ቢሯችን በአካል ተገኝቶ ፋይል መክፈት ይችላል፡፡ በአካል ባይገኝም ባለበት ቦታ ሆኖ መመዝገብ እንዲችል ሁሉ ነገር ተሟልቷል፡፡ ሰዎች ስለማያውቁ ይኼንን አያደርጉም፡፡ እዚህ ከመጡ በኋላ ነው እዚሁ አካባቢ ቁጭ ብለው በኢንተርኔት ምዝገባ እየፈጸሙ ያሉት፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ በጉምሩክና በገቢዎች የሚጣሉ ታክሶች ላይ የሚቀርቡ ይግባኞችን የሚመለከት እንደመሆኑ ጥቅሙ ለንግዱ ማኅበረሰብ ያደላል፡፡ ይሁንና የንግዱ ማኅበረሰብ ወደ ኮሚሽኑ ለይግባኝ እምብዛም የማይመጣው ከገለልተኝነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሊኖረው ስለሚችል ነው የሚል ዕሳቤ የላችሁም? ምን ያህል ገለልተኛ ናችሁ?
አቶ ሙሉጌታ፡- የዳኝነት ሥራ በባህሪው ገለልተኝነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ገለልተኛ ካልሆንክ ከመጀመሪያውኑ ዳኝነት የሚባለው ጉዳይ የለም፡፡ ዳኝነት በሁለት ተከራካሪ ወገኖች መካከል ሆነህ በገለልተኝነት ውሳኔ የምትሰጥበት ነው፡፡ ከመጀመሪያው አንድ ወገን ጋር ከሆንህ ዳኝነት የሚባለው ነገር የለም፡፡ ገቢዎች በቅርንጫፍና በዋና መሥሪያ ቤት አቤቱታ አጣሪ ያላቸው፣ አቤቱታ አጣሪዎች ውሳኔ ሰጥተው ነው ወደ እኛ የሚመጣው፡፡ ግን አቤቱታ አጣሪው የተቋቋመው በገቢዎች በኩል ነው፡፡ የተደራጁት በአስፈጻሚው መሥሪያ ቤት ሥር ስለሆነ፣ ሰዎችም ገለልተኛ ናቸው ብሎ አይጠብቁም፡፡ አቤቱታዎችን እዚህ ጋ ማጠናቀቅ ይቻል ነበር፡፡ መንግሥት ግን ይህንን አልፈለገም፡፡ መንግሥት የፈለገው ውሳኔዎቹ በየተቋማቱ ይታዩ፣ ሰውም ዕድል ያግኝ፣ ነገር ግን በየተቋማቱ የሚሰጠው ውሳኔ ካላረካው ሚዛናዊና ገለልተኛ ሆኖ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችል ሌላ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ነው፡፡ አዋጁ በራሱ ኮሚሽኑን ሲያቋቁም፣ ገለልተኝነቱን ለማስጠበቅ ሲል የሚሾሙ ሰዎች በጉምሩክ ወይም በገቢዎች ውስጥ የማይሠሩና ከእነዚህ ተቋማት ከወጡ ከሁለት ዓመታት በላይ የሆናቸው መሆን እንዳለባቸው አስቀምጧል፡፡ የሚሾመው ሰው ከሁለት ዓመታት በፊት እንኳን ከሠራ፣ የወሰናቸው ውሳኔዎች ወደ ኮሚሽኑ ሊመጡ ስለሚችሉ ተፅዕኖ እንዳያድር በሚል ነው፡፡ የሚሾሙት ዳኞች ገለልተኛ የሆኑ የሕግና የሒሳብ ዕውቀት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ አዋጁ የገለልተኝነትን ጉዳይ በግልጽ ነው ያስቀመጠው፡፡ ሥራችንንም ስንሠራ እንደዚህ ዓይነት ነገር አያጋጥምም፡፡
እርግጥ ነው ከጉምሩክና ከገቢዎች ጋር ተቀራርበን የምንሠራባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህም ግን የሚሰጡ ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ለነጋዴው ውሳኔ ከወሰንን ውሳኔው በ30 ቀናት ውስጥ መፈጸም ስላለበት ውሳኔውን እንዲፈጽሙ የጋራ ግንኙነት እናደርጋለን፡፡ በኮሚሽናችን አሠራር ላይ የተገልጋዮችን እርካታ ለመመዘን ብለን ለ1,104 ሰዎች ጥያቄ አቀርበን ነበር፣ በገለልተኛ አካል ባይጠናም፡፡ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች ውስጥ 1,077 ሰዎች ረክተናል፡፡ ተቋሙ ገለልተኛ ነው የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡ 49 ሰዎች ገለልተኛነቱን የማይቀበሉ ሰዎች አሉ፡፡ ከአብዛኛው ሰው ግን ገለልተኛ ነው፣ ረክተንበታል፡፡ ጥሩ ውሳኔ ነው የተሰጠው የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው፡፡
ሪፖርተር፡- በ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ውሳኔ ከተሰጠባቸው 202 መዝገቦች ውስጥ 146 መዝገቦች ባሉበት የፀኑ ናቸው፡፡ እነዚህ መዝገቦች ባሉበት የፀኑት ከመጀመሪያውም ውሳኔው ትክክል ስለሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ በንግዱ ማኅበረሰብ በኩል ግን ‹‹ኮሚሽኑ የሚሰጠው አብዛኛው ውሳኔ ባለበት የሚፀና ነው›› በሚል ሥጋት ቢነሳ ምላሽዎ ምን ይሆናል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ብዙ ሰው መረዳት ያለበት ይህንን ጥያቄ ነው፡፡ ውሳኔዎቹ በአብዛኛው የሚፀኑት ለምንድነው? ለምንድነው የማይሻሩት? የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ እኛ ይግባኝ ሰሚዎች ነን፡፡ እኛ ይግባኝ ሰሚ ሆንን ማለት ከዚህ በፊት የመጀመሪያ ደረጃ ሥልጣን ያለው ውሳኔ የሚሰጥ አካል አለ ማለት ነው፡፡ ይህ አካል ከቅርንጫፍ ይጀምራል፡፡ ቅርንጫፍ ላይ መጀመሪያ ኦዲተሩ ሒሳብ ሠርቶ ለኃላፊዎች ያቀርብና በኃላፊው በኩል ይህንን ያህል ግብር አለብህ ክፈል ተብሎ የውሳኔ ማስታወቂያ ይሰጣል፡፡ ቅሬታ ከተሰማው እዚያው ላለው ቅርንጫፍ ቅሬታውን ያቀርባል፡፡ ቅሬታው ሲቀርብ እነዚህ ነገሮች ተሻሽለው ባለበት ፀንቷል የሚል ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ይህንን ይዞ ደግሞ ዋናው መሥሪያ ቤት ቅሬታ አጣሪ ጋ ሲያቀርብ ይኼ፣ ይኼ ይሻሻል፡፡ ይኼ ደግሞ ይጥና ተብሎ የውሳኔ ማሻሻያ ተደርጎበት ይመጣል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሙሉ በሙሉ አልተሻረልኝም ተብሎ እኛ ጋ የሚመጣው፡፡ ከእኛ በፊት ጉዳዩ ሁለት ጊዜ ስለሚታይ ጉዳዩ አልቆ ነው የሚመጣው ማለት ይቻላል፡፡ እኛ ጋ የሚመጣው ይግባኝም ስለሆነ መሠረታዊ ነገሮች ካላጋጠሙ በስተቀር፣ ራሱ ተቋሙ ውሳኔዎችን የሚያሻሽልበትን ሁኔታ ዓይተናል፡፡ አቤቱታ አጣሪዎቻቸው በቂ ግንዛቤ ያላቸው፣ በሙያው ላይም የተሻለ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ተቋማቸው የወሰነው ጉዳይ ላይ እንኳን ይኼ ይኼ ይስተካከል ብለው ይልኩታል፡፡
እኛ ጋ ከመጡት መዝገቦች ውስጥ 15 በግልጽ ሲሻሩ፣ ሦስት ተመልሰዋል፣ 13 ተዘግተዋል፣ 26 ደግሞ ተሻሽለዋል፡፡ እነዚህ መዝገቦች መጠነኛ ነገር ተብለው ነው እንጂ፣ ብዙዎቹ ከታች ባለው የሚወሰኑ ስለሚሆኑ ነው፡፡ በሩብ ዓመቱ ውሳኔ ከሰጠንባቸው 202 መዝገቦች ውስጥ፣ ውሳኔ ያፀናንባቸው 132 ሰዎች ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንጠይቃለን፣ መዝገቡን ስጡን ብለው ወስደዋል፡፡ በውሳኔያችን አልተስማሙም፡፡ ሲሄዱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አየና ከ132 መዝገቦች 11 መዝገቦች ብቻ ያስቀርባሉ አለ፡፡ አሥራ አንዱም ደግሞ ወደ እኛ ነው የተመለሱት፡፡ ምስክር እያለ ብትሰሙ ኖሮ ወይም እንዲህ ዓይነት ማስረጃ አለኝ እያላችሁ ማስረጃውን ሳታዩ ለምን ውሳኔውን ሰጣችሁ የሚል ነው፡፡ አንዳንዱ ማስረጃ አለኝ ይልና ማስረጃውን አምጣ ብለህ አንድ ወርና ሁለት ወራት ጊዜ ትሰጠዋለህ፣ ግን ማስረጃውን አያመጣም፡፡ አዋጁ በ120 ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንዲሰጥ ያዛል፡፡ ግለሰቡ እስከ ስምንት ወራትና አንድ ዓመት ሊያቆይ ሲል እናቋርጥና ውሳኔ እንሰጣለን፡፡ ግን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመደመጥ ዕድል አለው፣ እንደገና አዳምጡ ይልና ይመልሳል፡፡ አሁን ከተመለሱት 11 መዝገቦች ውስጥም አንድ ሁለት ካልሆነ በቀር ጠብቀናል፣ ዓይተናል፡፡ ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻለ ነው ተብሎ ተመልሶ የሚሄዱ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑን ያቋቋመው አዋጅ አቤቱታዎች ወደ ኮሚሽኑ በመጡ በ120 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ማግኘት እንዳለባቸው፣ ውሳኔ ከተሰጠም በኋላ የተሰጠው ውሳኔ በ30 ቀናት ውስጥ መፈጸም እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ይሁንና የተሻሻሉ ወይም የተሻሩ ውሳኔዎች ማስፈጸምን በተመለከተ በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል ተግዳሮቶች እንዳሉ ይነሳል፡፡ ብዛት ያላቸው የአፈጻጸም አቤቱታዎች ወደ ኮሚሽኑ እየመጡ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ አፈጻጸም ላይ ያለው ችግር ከምን የሚነሳ ነው? ምን ዓይነት ዕርምጃዎችን እየወሰዳችሁ ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- ሕጉ አፈጻጸምን እኛ እንድናይ ብሎ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ የእኛ ሥራ ውሳኔ መስጠት ስለሆነ፣ የተወሰነለት ሰው ለአፈጻጸሙ በፍርድ ቤት መዝገብ ሊከፍት ይችላል፡፡ አሊያም ሕጉ በ30 ቀናት መፈጸም እንዳለበት መደንገጉን ጠቅሶ ለአመራሮች ሊያመለክት ይችላል፡፡ ግን እዚያ አካባቢ በዚህ አካሄድ የሚፈጸም የለም፡፡ እናንተ ከወሰናችሁልን በኋላ የሚል ሐሳብ ስለሚመጣ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ጋር እንነጋገራለን፡፡ ግንኙነት ስናደርግ የተነጋገርነው ይግባኝ ጠይቃችሁ ከፍርድ ቤት ዕግድ ካላመጣችሁ በስተቀር፣ አዋጁ እንደሚለው በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔው መፈጸም አለበት የሚለውን ነው፡፡ ከጉምሩክ በኩል ለምሳሌ በቅርቡ አንድ ውሳኔን ያልፈጸሙት ውሳኔውን ለማስፈጸም ቅንነት ጎድሏቸው ሳይሆን፣ ተይዞ የነበረው ዕቃ በአጋጣሚ ስለጠፋ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ቢጠፋም ግን የዕቃው የገበያ ዋጋ ታይቶ በገንዘብ ተቀይሮ ይሰጣል፡፡
መኪና የሚወረስባቸው ጊዜያት ላይ ደግሞ እኛ መኪናው መመለስ አለበት ብለን ልንወስን እንችላለን፡፡ ግን ብዙውን ጊዜ መኪና በውርስ ተይዞ ሲቆም አፈር ስለሚበላውና ስለሚበላሽ፣ ጉምሩክ ኮሚሽን መኪናውን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላልፋል፡፡ እንደሚታወቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢትዮጵያም ስላለ ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ የተቀበለውን መኪና ለመንግሥት ተቋማት ያከፋፍላል፡፡ ስለዚህ ገንዘቡ ተተምኖ ለግለሰቡ ይመለሳል፡፡ ገንዘቡን ለማስመለስም ቀድሞ ይህንን ያህል ገንዘብ በክርክር ላይ አለ፣ ሊመለስ ይችላል ተብሎ በጀት መያዝ አለበት፡፡ ውሳኔ ሲሰጥ ነው ገንዘብ ሚኒስቴርን እንደ አዲስ ተመላሽ ገንዘብ የሚጠይቁት፡፡ ይህንን ገንዘብ ለመቀበል ሒደቱ ጊዜ ስለሚወስድ ውሳኔ የተወሰነለት ሰው ጥያቄ ወደ እኛ ያመጣል፡፡ አንዳንዴ ግን የቅንነት መጓደል የሚታይባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በአስቸኳይ እንዲታረሙ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት የገቢዎች ሚኒስትር ጋር ንግግር አድርገን፣ እኛ ዘንድ የቀረቡትን የአፈጻጸም መዝገቦች በቶሎ ዓይተው እንዲፈጸም ሰብስበን ሰጥተናቸዋል፡፡ የእነሱ ጥያቄ እንዲያውም ውሳኔ አሰጣጡ ይፍጠንልን የሚል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከታክስ ጋር የተያያዙ ብዙ ይግባኞችን ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥና የሚመጡ መዝገቦችን በመመልከት በኢትዮጵያ የታክስ ሥርዓት ውስጥ ምን አስተዋላችሁ?
አቶ ሙሉጌታ፡- በሁለት ለይተን ነው የምንመለከተው፡፡ ጉምሩክ አካባቢ በየጊዜው የሚያዘጋጁት የዋጋ ማደራጃ ዳታ ቤዝ አለ፡፡ ከሦስት ወራት በፊት የገባ አንድ መኪና በ60 ሺሕ ዶላር ነው የገባው ተብሎ ይመጣል፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ ደግሞ ራሱ መኪና በ40 ሺሕ ዶላር የተገዛ ነው ተብሎ ይመጣል፡፡ የጉምሩክ ሰዎች ወደ ዳታ ቤዛቸው ሄደው መኪናው ተመሳሳይ መሆኑን አረጋግጠው ቀደም ሲል በገባበት 60 ሺሕ ብር ይገምቱታል፡፡ በዚህ ጊዜ ባለንብረቱ ኢንቮይስ አለኝ ብሎ ቅሬታ ያቀርባል፡፡ እዚህ ላይ እኛ የምናየው ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ነው፡፡ ለምሳሌ መጀመሪያ መኪና ያመጣው ሰው የገዛው አንድ መኪና ከሆነና በኋላ የመጣው በብዛት ገዝቶ ከሆነ፣ የዋጋ ቅናሽ አግኝቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ለምን ከግምት ውስጥ አላስገባችሁም ብለን ልንወስን እንችላለን፡፡ ከግምት ውስጥ የሚገቡ እንዲህ ዓይነት ምክንያቶች ከሌሉ ግን ባለበት እናፀናለን፡፡
ቀጥሎ ያለው የታሪፍ ጉዳይ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዕቃ ሲመጣ ምን ላይ ነው የሚያርፈው? የሚለውን የያዘ የታሪፍ መጽሐፍ አለ፡፡ ዘመናዊ የሆነ የታሪፍ አመዳደብ ያለው ለሚያየው ሰው ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ነው፡፡ ግን የታሪፍ ዋጋ አመዳደብ ላይ ብዛት ያላቸው ክርክሮች ወደ እኛ ይመጣሉ፡፡ ከመኪና፣ ከወርቅና ከከበሩ ማዕድናት መያዝ ጋር፣ እንዲሁም በኮንትሮባንድ ከሚገቡ ዕቃዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ገቢዎች ጋ ሲመጣ ከንግድ ትርፍ ግብር ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ወጪያቸውንም ገቢያቸውንም በሒሳብ መዝገብ ላይ ጽፈው እንዲይዙ ይገደዳሉ፡፡ ገቢዎች ይህንን መዝገብ ያይና ወጪው ተጋነነ፣ ገቢው ደግሞ አነሰ ብሎ የሒሳብ መዝገቡን ውድቅ ያደርገዋል፡፡ የዚያ ተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት የሒሳብ መዝገብን እንደ መነሻ ይወስዳል፣ ወይም የትርፍ ኅዳግ አለ፡፡ በየዘርፉ ወጪና ገቢ ይህንን ያህል ነው ተብሎ የተቀመጠበት እሱ ይወሰዳል፡፡ የግል ተቋማት ወጪያችን በዚህ ዓመት ከፍ ብሎ ነበር ሒሳብ መዝገባችን ይያዝልን ብለው ክርክር ይነሳል፡፡
በከፈሉት የንግድ ትርፍ ግብር ልክ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይከፈል ቀርቶም ክርክር ይነሳል፡፡ መንግሥት የሰበሰብክልኝን ተጨማሪ እሴት ታክስ አምጣ ይላል፡፡ ማስረዳት ካልቻለ ውሳኔ ይፀናል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ቢራ አምራቾች ለማስታወቂያ በነፃ ቢራ ይሰጣሉ፡፡ ይህ የተሸጠ ስላልሆነ የንግድ ትርፍ ግብር አይጠየቅበትም፡፡ ተጨማሪ እሴት ታክሱን ግን መክፈል አለባቸው፡፡ መንግሥት አይከፍልላቸውም ለማስታወቂያ ብለው የሰጡት ራሳቸው ናቸው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፈሉ ሲባሉ የንግድ ትርፍ ግብር አልከፈልንበትም ይላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ ጉዳዮች ሲጠቀለሉ ብዙው ችግር ሕግን ካለማወቅና ከታክስ ማጭበርበር ጋር ተያያዘ ነው ማለት ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ታክስ የመክፈል ልምድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ግብር ግዴታዬ ነው መባል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካገኘሁት ገቢ ላይ ግብር መክፈል አለብኝ የሚለው አስተሳሰብ ብዙ ይቀረዋል፡፡ የታክስ መሠረቱም ቢሆን አልሰፋም፡፡ ትኩረት የተደረገው ቀድመው የታወቁና የተያዙት ላይ ነው፡፡ በየጊዜው በሚፈጠሩ አዳዲስ መስኮች የሚሠሩ፣ ነገር ግን ግብር የማይከፍሉ አሉ፡፡ ማጭበርበሩም ቢሆን በግልጽ ይታያል፡፡ በቅርቡ የገጠመን ዕቃው የተገዛው መርካቶ ነው፡፡ ደረሰኝ የሚወሰደው መገናኛ ነው፡፡ ያ ተቋም ደረሰኝ ብቻ ነው የሚሸጠው ማለት ነው፡፡ ያወጣችሁት ወጪ እንዲያዝ የገዛችሁት ዕቃ ክምችት ውስጥ ገብቶ የወጣበትን ሒደት አሳዩን እንላለን፡፡ የሁለት ሚሊዮን ብር ዕቃ ገዝቻለሁ ይልህና ገንዘቡ የተዘዋወረበት የባንክ ደረሰኝ አምጣ ስንል በጥሬ ነው የከፈልኩት ይላል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ብር በምን ዓይነት መንገድ ተወስዶ ነው በጥሬ የሚከፈለው? ስለዚህ በሐሰተኛ ሰነድ ነው የተገዛው ማለት እንችላለን፡፡ እኛ በተቻለን መጠን ፍትሐዊ ውሳኔ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡
ሪፖርተር፡- የታክስ ሥርዓቱ ላይ ከሚነሱ ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው የታክስ መረብ ውስጥ አዳዲስ ግብር ከፋዮች አይካተቱም፣ ያሉት ብቻ ናቸው ግብር እንዲከፍሉ የሚጠበቀው የሚል ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለው አቅምና በሚንቀሳቀሰው ልክ የሚሆን ግብር እያመነጨ አይደለም የሚል ቅሬታ ከመንግሥት ይነሳል፡፡
አቶ ሙሉጌታ፡- ይኼ ትክክለኛ ቅሬታ ነው፡፡ ጎረቤታችንን ሩዋንዳን ብትወስድ በሕዝብ ብዛት የኢትዮጵያ አንድ አራተኛ የማይሞላ ሕዝብ ነው ያላት፡፡ በሚሰበሰብ ታክስ ግን ትበልጠናለች፡፡ ይህንን የሚወስነው የታክስ መረቡ ውስጥ ያለው ግብር ከፋይ ቁጥር ነው፡፡ ዝም ተብሎ ከጉሊቱም፣ ከምኑም ይሰብሰብ ማለት አይደለም፡፡ ግን መደበኛ ንግድ የሚነግደው አካል መለየትና መታወቅ አለበት፡፡ ኢኮኖሚውን በመምራት ላይ የሚገኙት የመንግሥት ተቋማት ቀጣይ ሥራ መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ ቅርጫቱ ውስጥ ያሉት ቀድሞውንም ስለሚታወቁ ገቢያቸው እንዲሰፋ ዕገዛ እያደረጉ፣ የሚከፍሉትን ግብር ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ አገር ውስጥ ሥራ እየሠሩ ግብር የማይከፍሉ ሰዎች የሉም ወይ? ለዚህ የታክስ መሠረቱን ማስፋት ይጠይቃል፡፡ ይህ አንዱ የገቢዎች ትልቅ ተልዕኮ ሆኖ ሊሠራበት ይገባል፡፡
ጉምሩክ ላይም ኮንትሮባንዱን መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ በቦሌና ኬላዎች ባሉባቸው ቦታዎች የሚገባው ነው እየተቀረጠ ያለው፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገባውስ? የሚያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃ ሲታይ ያስደነግጣል፡፡ ባለፈው ዓመት ከኮንትሮባንድ 50 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል፡፡ ያልተያዘውስ? ከ50 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ደግሞ ሳይያዝ ገብቷል ማለት ነው፡፡ በቀጥታ ቀረጥ እየተከፈለበት ቢገባ የገቢ መጠናችን ይጨምራል ማለት ነው፡፡ ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ በቅርቡ በኦንላይን መዝገብ መክፈት የሚቻልበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ ይህ የኮሚሽኑን ተደራሽነት እንደሚያሰፋ ቢጠበቅም፣ በተለይ ከጉምሩክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጠረፍ አካባቢ ኬላዎች ላይ ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በኦንላይን የተከፈተው መዝገብ ላይ ለመከራከር ወደ አዲስ አበባ መምጣት ይጠይቃል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሎች ቅርንጫፍ የመክፈት ሐሳብ አለው?
አቶ ሙሉጌታ፡- እኛ የምንመራው በአቋቋመን አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 86 እና በተከታዮቹ አንቀጾች ነው፡፡ አዋጁ የሚለው የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ጉዳዮችን ለማየት ለክልሎች ውክልና ሊሰጥ ይችላል ነው፡፡ መስጠት አለበት አይልም፡፡ አዋጁ ቅርንጫፍ ይከፍታል ቢል ጥሩ ነበር፡፡ ግን ጉዳዩን ክልሎች እንዲይዙት አድርጎ ኃላፊነት ሰጥተህ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ከራሳቸው ሾመው ሊሠራ ይችላል፡፡ አብዛኛው ግብር የራሳቸው ስለሚሆን የፌዴራሉንም ደርበው ያዩልን ነበር፡፡ ግን የተፈለገው የፌዴራሉን ጉዳይ ፌዴራሉ እንዲይዘው ነው፡፡ ለክልሎች ውክልና ስንሰጥ ሊያዩት የሚችሉት እንደ ሁለተኛ ሥራ ነው፡፡ ዋነኛ ሥራቸው የራሳቸውን ገቢ መሰብሰብና ቅሬታ መፍታት ስለሆነ፡፡ በውክልና የሚጡ ሥራዎች በየቀኑ ክትትልና ቁጥጥር ይፈልጋሉ፡፡
እኛ ያሰብነውና ከገቢዎች ጋር ንግግር የጀመርንበት ጉዳይ ተዘዋዋሪ ችሎት ቢኖረን የሚል ነው፡፡ ሦስት ዳኞች መርጠን ከሩቅ ቦታዎች በኦንላይን የተመዘገቡ ሰዎች ለቃል ክርክር እዚህ ድረስ እንዳይመጡ አካባቢ ላይ ያለውን ጉዳይ ጠርቀም እያደረጉ አንዴ መፍታት ይቻላል፡፡ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ ብሎ በአራት ከፍሎ እያንዳንዱ ቦታ በዓመት አንዴ ችሎት እንዲቻልበት ማድረግ ቢቻል በቀላሉ መፍታት ይቻላል፡፡ ይህንን እያሰብን ነው፡፡ ይህንኑ ችሎት ሦስት ዳኞችንና አንድ የመዝገብ ሠራተኛን ጨምሮ ለተመዘገቡት መዝገቦች ችሎት ማስቻል ነው፡፡ የሚያስቸግር ነገር የለውም፡፡ እኛ ጋ ያለው ትልቅ ችግር በጀት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ለማድረግ የበጀት እጥረት አለበት፡፡ ሥራው ተሠርቶ ከታየ ግን ተጨማሪ በጀት የማይመደብበት ምክንያት የለም፡፡