Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአንጋጠው ከተጓዙ የእንቅፋትን ማንጎል አይወቅሱም (ክፍል አንድ)

አንጋጠው ከተጓዙ የእንቅፋትን ማንጎል አይወቅሱም (ክፍል አንድ)

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

አጥር ግቢ ከተውተፈተፈ ከውጭ ልሹለክ ባይ አይጠፋም፡፡ አንጋጠው ከሄዱም እንቅፋት ለምን መትቶኝ ሊባል አይችልም፡፡

የአፍሪካ ቀንድ የአሁን ካርታ (ከሰሜን ቀይ ባህር አንስቶ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ ኢትዮጵያ ከባህር የታጠረችበት ካርታ) አገነባብ ከንግድ ቁጥጥር ትግል ጋር፣ ከጠረፋማ ማኅበራዊ ጥንቅር አዝጋሚ ለውጥ ጋር፣ ከመንግሥት ኃያልነትና ከጠረፋማ ግዛት ጥበቃ መድከም ጋር ውስብስብ መስተጋብር ያለው ነው፡፡ ይህን ብዙ የውስጥና የውጭ ሰበዞች የተወሳሰቡበትን ታሪክ ጥንት ድረስ ሄዶ ከሰባተኛ ክፍለ ዘመን ከዓረቦች መስፋፋትና ከአክሱም መንግሥት እየደከመ መምጣት ጋር ሁሉ ማያያዝ ይቻላል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በቀይ ባህር ንግድ ቁጥጥርና ሽሚያ ውስጥ ኢትዮጵያ የነበራት ሚና እየደከመ ሄዷል፡፡ በአፍሪካ ሰሜንና ምሥራቃዊ ግርጌ በተለያየ ጊዜ የኦቶማን ቱርክ፣ የግብፅና የአውሮፓውያን መስፋፋትም የኢትዮጵያ መንግሥታት በጊዜያት ውስጥ ከነበራቸው የአቅምና የውዝግብ ጣጣዎች ጋር የሚገናዘብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥታዊ ውጥን ህልውናና ግንባታ ታሪክ ጥንታዊ ሥር ያለው ይሁን እንጂ፣ ግንባታው በ20ኛው ክፍለ ዘመንም በአግባቡ አልተጠናቀቀም ነበር፡፡ ኦቶማን ቱርክ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ምፅዋን በያዘ ጊዜ ዝም አልተባለም፡፡ ከምፅዋና አከባቢው ቱርክን ለመንቀል ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ ግን ከቱርክ ጋር የኢትዮጵያ ባህር ነጋሽ ተሻርኮ ጥረቱን ያከሸፈበትም ታሪክ ታይቷል (ዘውዴ ገብረ ሥላሴ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት መንስዔና መፍትሔ፣ ገጽ 88)፡፡ ይህ አፈንጋጭነት እንደ ምን ሊከሰት እንደቻለ መረዳት የምንችለው ያ ዘመን ራሱ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ግብግባዊ መስተጋብር ውስጥ (በደገኞቹ ገዥዎችና በምሥራቃዊ ቆላማ ገዥዎች የመዋዋጥ/የበላይነት ትግል ውስጥ የነበረ) መሆኑን ስናስተውል ነው፡፡ ደገኞቹንና የምሥራቆቹን በመደገፍ ፓርቱጋሎችና ቱርኮች የኃይል ሚዛን መገለባበጥ የፈጠረ ሚና ሊጫወቱ ችለዋል፡፡ ተፋላሚዎቹ ሰሜነኞችና የደቡብ ምሥራቅ ገዥዎችም ዝለው፣ የኦሮሞ መስፋፋት በኢትዮጵያ ታሪክ የኅብረተሰብና የአገረ መንግሥት ግንባታን ወሳኝ የአሻራ ታሪክ ይዞ ይመጣል፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ መኮማተርና የንጉሠ ነገሥት ኃያልነት መሰልሰል (ዘመነ መሳፍንት)፣ ኃያል ንጉሠ ነገሥታዊ የሥልጣንና የግዛት ማስፋት ትግል እንደገና ማንሰራራት ሁሉ ይከተላል፡፡

ይህን ሁሉ አንካሴና ደፋ ቀና ስናስተውል ነው ኢትዮጵያ ለከበባና ለአፈና ለምን እንደተጋለጠች የሚገባን፡፡ ከ16ኛው አጋማሽ አንስቶ ቱርክ ምፅዋን ይዞ ሦስት መቶ ዓመት ያህል መቆየት እንደምን እንደቀለለው፣ በ1857 ቱርክ ከግብፅ ግብር እየተቀበለ ምፅዋን ለግብፅ አሳልፎ መስጠቱ፣ ጁሴፔ ሳፔቶ የዳግማዊ ቴዎድሮስ ዘመን ባበቃ በዓመቱ አሰብን በአንድ ኩባንያ ስም ያለ ችግር መግዛት መቻሉ፣ ከአሥር ዓመት በኋላም ለጣሊያን መንግሥት አስተላልፎ መሸጥ መቻሉ፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በፊት በምሥራቅ አፋር ጠረፍ ምድር የፈረንሣይ ሥር ለማበጀት መብቃት፣ የግብፅ ተሳፋፊዎች በሰሜን ምፅዋ በኩልና በደቡብ ምሥራቅ ባደረጉት መስፋፋት ሳይመጠኑ፣ ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠር በምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ያደርጉት የነበረ ጦርነትና የማስገበር ትግል ውስጥ መግባት፣ በስተኋላም በግብፅ ተስፋፊነት ጀርባ ቅኛዊ ጥቅም የነበራት ብሪታኒያ ግብፅን በ1874 ከተቆጣጠረች በኋላ በኢትዮጵያ ጦርና በሱዳን አማፂያን ወጥመድ ውስጥ የነበረውን የግብፅ ጦር እንድታስመልጥ፣ ለዚያም ውለታ ከረን (ቦጎስ)ንና ምፅዋን ለመመለስ የተስማማችው ብሪታኒያ ውሏን በከፊል ለመሸፈጥና ምፅዋን አሳልፎ ለጣሊያን በ1877 ለመስጠት መድፈር እንደምን እንደቀለላት የምንረዳው፣ የአካባቢ ገዥዎችን በማይዋዥቅ አኳኋን አስገብሮ ንጉሠ ነገሥታዊ ሥልጣንና ግዛታዊ ይዞታን የማፅናቱ ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ ገና ዋላላ እንደነበር ማየት ስንችል ነው፡፡ በአፄ ቴድዎድሮስ ጊዜም ሆነ በአፄ ዮሐንስ ጊዜ የነበረው የሥልጣን ትግል፣ የውጭ ኃይል ድጋፍን ምርኩዝ እስከ ማድረግ ድረስ የሄደ የመጣጣል የሥልጣን ትግል የነበር መሆኑ አስገራሚ የማይሆንብን፣ በውስጥ ያለው የአካባቢ ገዥዎች የአፄውን (ንጉሠ ነገሥታዊ) ሥልጣን የማይዳፈሩበት የሥልጣን ኃያልነትና ዕርጋታ አለመፈጠሩ፣ የአፄያዊ ትግሉ በውስጥ ጣጣዎች ውስጥ በመትረክረክ መጣበቡ፣ ከውጭ የሚተነኩሳቸውን/በር የሚይዙባቸውንም ሆነ በመሣሪያ ዕገዛ እያባበሉ የሚንፏቀቁትን ኃይሎች መሰሪ ባህርይ ባህር በተሻገረ መስተጋብር ለማወቅ አላስቻላቸውም፡፡ ዲፕሎማሲያቸው አውሮፓ ገብ በሆነ ብስል መረጃ ላይ ያልተመሠረተ የዋህነት የሚያጠቀው መንግሥታዊ ባህርይን ከመታወቂያ ሃይማኖት ጋር የሚያሳክር አድርጎታል፡፡ ይህም ጥቅማቸውን በብልህነት ለማስከበር ላለመቻል ድክመት አጋልጧቸዋል፡፡ ምኒልክ ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችን ተቀናቅኖ ሰፊ ግዛት ለመያዝ መቻሉን እፁብ የሚያሰኘውም፣ የጠቃቀሳናቸው ዘርፈ ብዙ የጀርባ ድክመቶች ለራሱ ለምኒልክም ሩቅ ስላልነበሩ ነው፡፡

የቴዎድሮስ ዘመንን ይዞ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የነበረችበት ሁኔታ ምን ያህል ከጃፓን የጊዜው እውነታ የተለየ እንደነበረ የተረዳ አዕምሮም፣ የጃፓንን ምዕራብ ቀመስ አሠለጣጠንን በኢትዮጵያ ታሪክም ውስጥ የነበረ ዕድል አድርጎ አይለጥፍም፡፡ ጃፓን ገና በ16ኛው ክፍለ ዘመን ማክተሚያ ላይ ሰላምንና አንድነቷን የተቀዳጀች አገር ነበረች፡፡ ከዚያ ወዲህ ከ200 ዓመታት በላይ ከዓለም ራሷን ዘግታ በቆየችበት ወታደራዊ አስተዳደር ጊዜም የውስጥ ባህልና ጥበባዊ ቅርሷን አበልፅጋለች፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ጃፓን ወደቦቿን ለአሜሪካ መርከቦች እንድትከፍት ለማድረግ፣ የአሜሪካ ዘጠኝ የጦር መርከቦች የመጡበት ጊዜ ስለምዕራባዊ ግስጋሴ ለጃፓኖች ዓይን ገላጭ ሆኗቸው፣ ከአሜሪካና ከአውሮፓ አገሮች ጋር ግንኙነት ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ በመጣው ዝመና (በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በባህር ኃይል፣ በምድር ጦር፣ ወዘተ) ዋና መሪ የነበረው የሜጂ ንጉሣዊ ሥርወ መንግሥት ነበር፡፡ በንጉሣዊ ቤተሰቦችና በመሳፍንት ዘንድ የተከማቸ መሬትን ፈቅደው እየለቀቁና እየተከፋፈለ (በዚህም ፊዩዳላዊው ሥርዓት እንዲሰናበት) መሳፍንትና ባለፀጎቹም የለውጡ አካል ሆነው፣ በንግድና በኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ መንገድ ቀዳጆች እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ ወደ አውሮፓ ይላኩ የነበሩ ጃፓናውያንም በዚሁ በአገራቸው የለውጥ ጉዞ ውስጥ በየፈርጁ የተፈለጉ ጥበቦችን እየቀሰሙ ወደ ጃፓን እንዲያስገቡ ዓላማ አንግበው የሚሄዱና ይህንኑ የማሳካት ሚና መጫወት የቻሉ ነበሩ፡፡ በጃፓን የነበረው የሜጂ ንጉሣዊ መንግሥት የለውጥ ቁርጠኝነት፣ በመሳፍንቱና በሌሎቹም የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የነበረው ተሰሚነት፣ በዝመና ጉዳይ ላይ በጥቅሉ የነበረው የንጉስ የመሳፍንትና የተማሩ ባለሙያዎች ሥምረትና በጊዜው የነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ፣ በእኛ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ይቅርና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የቅድመ ጣሊያን ፋሽስት ጊዜም ሆነ የጣሊያን ወራሪ ከተባረረም በኋላ አልነበረም፡፡

ይህ ግን ከዓድዋ ድል በኋላ የአውሮፓውያንን ዘረኝነትና የዓድዋ ድልን ቂም በዘዴ ተቋቁሞና በዓድዋ ድል መኩሪያነት አማካይነት፣ ከባህር ማዶ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሊሳብ የሚችለውን ጥበብ እየሳቡ ከተሞካከረው የሰፋና የጠለቀ ልማት ማካሄድ አይቻልም ነበር ማለት አልነበረም፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከጣሊያን ወረራ ማክተምና ከስደት መልስ ወዲህ ለለውጥ ቁርጠኛ ሆኖ፣ በንጉሣውያን ቤተሰብ የተግበሰበሰውን መሬት ለአራሾች እንዲከፋፋል አርዓያ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ቢያንስ በመሬት ሥሪት ጥገናዊ ለውጥ መሳፍንቱንና ባለርስቶችን መግራትና በዚህም የሁለገብ ልማትን በር መክፈት በቻለ ነበር፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ብርሃንነት ዳፍንትም የነበረበት ባይሆን ኖሮ፣ የመሬት ሥሪት ማሻሻያ የአፄው የተዋረደ አወዳደቅ ድረስ ባልዘገየ (አወዳደቁም ባማረ) ነበር፡፡ ከስደት መልስ በነበረ ዘመን አፄው ፈር ቀዳጅ ሆኖ ቢሆን በነበረው ግለሰባዊ ተወዳሽነቱ ላይ ሊመጣ ይችል የነበረውን የመላ ኢትዮጵያ ኅብረተሰብን ድጋፍ፣ የጥቂት መሳፍንትና ባለርስት ቅዋሜ ፈፅሞ የሚያስቆመው አይሆንም ነበር፡፡

ከአፄ ኃይለ ሥላሴ በኋላ የመጣው የደርግ መንግሥት ያልገባውን የሚሠራ (የግል አልሚነትን በገደብ ያነቀ፣ ንቅዘትና ተባይ ከላይ እስከ ታች የወረሰው፣ ሥራ ሞቅ ያለበትን የግል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አይዞህ በርታ ከማለት ይልቅ መውረስ የሚያምረው) የልማት ማስፈራሪያ ዓይነት ነበር፡፡ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዙሪያ ከነበሩት ሹሞች አንድ ሦስቱ ከመዝናናት መልስ ፊኛቸውን ሲያስተነፍሱ፣ በአጋጣሚ አንዱ የሌላውን ዕቃ ያይና ‹‹አንተ ምን ያህላል ነገርዬህ›› ይላል፡፡ ‹‹ባለ ነገርዬው›› ኩራት አልተሰማውም፡፡ ‹‹በል በል ዝም በል፣ ወሬ ሊቀመንበሩ ጋ ደርሶ እንደታስወርሰኝ!›› አለ ይባላል፡፡ ይህ ቀልድ ሥርዓቱ ምን ያህል የሥራ ከፈታና የፈጠራ ፀር እንደነበር ለመግለጽ በቂ ይመስለኛል፡፡

የሕወሓት ኢሕአዴግ መንግሥትም የተወሰኑ ነገሮች ቢሞካክርም፣ መንግሥታዊ የልማት ዘርፍ የቡጥቦጣ ማሳው ነበር፡፡ ላይ ላዩን የግል አልሚነትና ሥራ ከፈታ አበረታች መስሎ፣ ውስጥ ውስጡን የሞቀ ሥራና የትርፍ ሲሳይ በታየበት የግል ኢንቨስትመት ውስጥ ‹‹የኔን/የፓርቲዬን ኩባንያ አሳትፉ አለዚያ…›› የሚል እንደነበርም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እንዲህ ባለ ስርሰራ የተራገፉ እንደነበሩም ዕውቅ ነው፡፡

በጥቅሉ የለውጥና የልማት ዕድሎች እየተልኮሰከሱ፣ እየታነቁና እየጨነገፉ ኖረው፣ ተስፋ ባለው አኳኃን የግስጋሴ ጎህ የቀደደው ከ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የረዥም ዘመን ሒደቶችንና ዘመኖችን በጣም በተቃለሉ ዓረፍተ ነገሮች ለመግለጽ የደፈርኩት፣ አስፍቶ ማሰስ የዚህ ጽሑፍ ፍላጎት ስላልሆነ ነው፡፡ በተቃለሉት የእኔ ድምዳሜዎች የማይስማሙ እንደሚኖሩም አውቃለሁ፣ ለምን ኖሩም አልልም፡፡ የእኔ ዋና ጉዳይ የትንታኔና የድምዳሜ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ ዕይታችን ዛሬም ይፈይደናል ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳት ነው፡፡

መልኮቹ፣ ሰበቦቹና ደረጃዎቹ ከጊዜ ጊዜ ይለያዩ እንጂ ዛሬ ለመልማት የምትፍጨረጨረዋ ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ዛሬም ከከበባና ከአነቃ ጋር እየታገለች ነው፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ የውጭ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ውስጥ የቡድን ሽርካ በጥቅም እየገዙ የመከፋፋል የማሸፈትና የማዋጋት ሥራ ይሠራሉ፡፡ የኢትዮጵያን መልማትና ሰላም ማግኘት የግብፅ መንግሥት ዛሬም ሥጋቱ አድርጎ፣ በየትኛውም ኢቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን ለማመስ እየሠራ ነው፡፡ የምዕራባዊ ኃያላን ጣልቃ ገብነት ከግብፅና ከአንዳንድ ወሰንተኛ ጎረቤቶች ጋር ተወሳስቦ ይገኛል፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያ ንግድ የስነጋ ትግል አለበት፡፡ ትናንትና ከፋሽስት ጣሊያን መሸነፍ በኋላ የኤርትራና የኢትዮጵያ አንድ ላይ መግጠም ሸፍጥ እንደገጠመውና እንደተፈራ ሁሉ፣ ዛሬም እንደዚያው ነው፡፡ ከጊዜ ጊዜ የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ የውጭ አጀንዳና የቤት ሥራ ተቀባይ የመሆን ሚናን ሲጫወቱ የቆዩ የቅርብ ጎረቤቶቻችን ራሳቸው የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ የሰላም ማጣትና የድቀት መጫወቻ ከመሆን አላመለጡም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ከኢትዮጵያ የባሰ የትርምስም ሆነ የቀውስ ማጥ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በጋራ ደኅንነት፣ በልማት ትስስርና በዲፕሎማሲ አባብላም ሆነ ኃይልን በኃይል መክታ ጥቃቷን ማድረቅ አልቻለችም፡፡ አንዱን ቀዳዳ ዘጋሁ ቋጠርኩ ስትል፣ አንዱ ጋ ያፈተልካል፡፡ የፍትልክልክ ሥጋቷ ከመንግሥት ለውጥ ጋር አብሮ ያምጣል፡፡ የመንግሥት ለውጥ በሌለበት እንኳ ዛሬ በሰለ የተባለ ግንኙነትና ወዳጅነት ለማግሥቴው ቃሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ የሚሙለጨለጭ ግንኙነት አንዳቸውም ድንበርተኛ ጎረቤቶቿ የመረጋጋትም ሆነ የልማትና የግስጋሴ ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ በውስጥ ቀውስ መታመሱ አለመረጋጋቱ ጥርጣሬው ተወራራሽ ነው፡፡ እናም የአፍሪካ ቀንድ የሕዝቦች ጉስቁልና የጋራ እውነታ ነው፡፡ ይህን አዙሪታም ኑሮ አልፈውት ሊሄዱ አለመቻላቸው፣ ሰላምን፣ ዕድገትንና ልማትን ለማግኘት በሚያደርጉት የየበኩል ሩጫ ውስጥ አንድ የጎደለ ነገር ወይም አዲስ ዕይታ የሚሻ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ የድቀት የቀውስና የጉስቁልናው ጣጣ ተወራራሽና አፀፋዊ መሆኑ ደግሞ የሚናገረው፣ ከዚህ አዙሪት የመውጣቱ ጉዳይ በተናጠል ከመሮጥና ከመቦጫጨር ወጥቶ በጋራ ማሰብንና መቆምን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም ህልውናን፣ ሰላምንና ዕድገትን በየተናጠል አገርነት ከማሰብ ወጥቶ ቀጣናዊ ዕድርን፣ ህልውናንና ልማታችን ብሎ ወደ ማሰብ መሸጋገርን የሚመለከት ነው፡፡ በማኅበራዊ ዕድር ደረጃ ከየትኛውም ልዕለ ኃያላዊ አሻንጉሊትነት ነፃ ገለልተኛ የመሆን የተሻለ አቅምና ዕድል ይገኛል፡፡

እንደ ማኅበረሰባዊ ዕድር ሰላምንና ልማትን ወደ መቀየስ ማለፍ ሉዓላዊነትን ወዶና ፈቅዶ የተናጠል ብቻ ሳይሆን፣ የጋራም አድርጎ መሸረብና (በአንድ ጊዜ የሉዓላዊ ማኅበረሰብ አካልም ሉዓላዊ አገርም መሆን) ማለት ነው፡፡ ጥንድ ሉዓላዊነት የመያዙ ፋይዳም ምርምር የሚጠይቅ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተቀዳሚ ዓላማ የትኞቹንም የዓባይ ውኃ ተቋዳሾች ሳይጎዳ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌትሪክ ብርሃን አዳርሶ፣ ሕዝብን ከኩራዝ ማውጣት እንደሆነ ሁሉ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች (ሕዝቦች) ተቀዳሚ ዓላማ የየትኛውም የኃያላን ጎራ ጉያ ውስጥ ሳይሸጎጡ፣ ወይም የኃይላዊ ጎራ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሳይሆኑ፣ ከኃያሎቹም ሆነ ከመሰሎቻቸው አገሮችና ቀጣናዎች ጋር መልካምና ወዳጃዊ ግንኙነት ውስጥ ሆነው፣ ሽብርተኝነትን፣ ትርምስን፣ የቢጤ ለቢጤ ጦርነትን፣ አንበጣን፣ ጎርፍን፣ ድርቅን፣ ረሃብንና ስደትን በማሸነፍ ለዜጎቻቸው የተከበረ ሕይወትን ማቀዳጃት ነው፡፡ ይህን ዓላማ ለአፍሪካ ቀንድ/ለምሥራቅ አፍሪካ የቀየስኩት እኔ አይደለሁም፡፡ እኔ ያደረግኩት ነገር ቢኖር የቀጣናውን እውነታ፣ ሰቆቃና ድምፅ ለማንበብ መሞከር ነው፡፡

ይህን አባባሌን ደጋግሜ በቃሌም በጽሑፍም ብዬዋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ያዳመጡኝ ሰዎች አባባሌን የኢትዮጵያዊ ትሁትነት ‹‹ብዙ ባውቅም›› እያሉ ራስን ዝቅ የማድረግ ዓይነት ወግ አድርገው ያቀሉታል፡፡ በአካል ከማያውቁኝ የጽሑፎቼ ወዳጆች ውስጥም፣ መረጃዎች ከመረጃዎች ጋር ያላቸውን ውስጠ ተዛምዶ ለመፈልቀቅ አዕምሮዬን አድክሜ የምጽፍ አድርገው የሚገምቱም ይኖሩ ይሆናል፡፡ የትምህርት ደረጃዬን አለማወላዳት የሚያውቅ ወዳጄ ራሱ ከአንዴም ሁለቴ ‹‹የዛሬው ጽሑፍህ መቼም…!›› የሚል አድናቆት ሰንዝሮልኛል፡፡ ነገር ግን ማንበብ ለተለማመደ አዕምሮ የዓለምም እውነታ፣ የኢትዮጵያም እውነታ ብዙ ነገሮችን አግዝፎ ያውላችሁ አንብቡና ተጠቀሙበት እያለ ያቀርባል፡፡ እርግጥ ነው እውነታ ቆዳና ሆድ ዕቃ አለው፡፡ ዲፕሎማሲም ቆዳና ሆድ ዕቃ አለው፣ ጽሑፍም እንደዚያው፡፡ ወለልን ብቻ የሚያስተውል ንባብ ግልብ ንባብ ነው፡፡ እንደ አገባቡ ‹‹እጅ ስልጡን›› ማለት ብዙ ሙያ የሚያውቅ ማለት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ ሌባም ለማለት ይውላል፡፡ ይህንን መሰል ልዩነቶችን ማጤን ያሻል፡፡ ‹‹አነበብኩ›› ስል ማንበብ ቀላል ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ጽሑፍን ላይ ላዩን ጋልቦ አነበብኩት እንደማይባል ሁሉ፣ የእውነታ ንባብም በደንብ ማስተዋልና ደጋግሞ መመልከትን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ እንዲህም ሆኖ እውነታ ለንባብ የምታቀርብልን መረጃ/መልዕክት ወሰብሰብ ሊል እንደሚችል ሁሉ ተነጥሮ ያበቃለት ሊሆንም ይችላል፡፡ በሁለት ምሳሌ ላስረዳ፡፡

የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ናንሲ ፔሎሲ በ2014 ዓ.ም. መገባደጃ ዓመት ያደረገችው፣ ከእሷም በኋላ ሌሎች እንደራሴዎች የለጠቁበት፣ የታይዋን ጉብኝት የአሜሪካንን ልዕለ ኃይላዊ አዲስ መጥ ተቀናቃኝ ቻይናን አጪሶ ታይዋንን አይዞሽ ባለ ዲፕሎማሲ፣ ሪፐብሊካኖችን በእንደራሴዎች ምርጫ የመብለጥ ሥራ አድርገን ብንወስደው የዓለም ፖለቲካ ንባባችን ግልብና ጠባብ ይሆናል፡፡ የእነ ፔሎሲ ጉብኝት ዓላማ ከአሜሪካ የውስጥ ምርጫ ያለፈ ግብ የነበረበት ነው፡፡ ሩሲያን ከዩክሬይን ጋር በጦርነት አላኩሶ ዩክሬይንን መደገፍ ሩሲያን የማድከሚያ ዘዴ ተብሎ እንደተገባበት ሁሉ፣ ለቻይናም ዘዴ እየተፈለገ ቢሆንስ? ታይዋንን አካሌ ባዩን የቻይና ፖሊሲ መተናኮል ቻይናን ክፉኛ እንደሚያስቆጣ ታውቆ፣ ትንኮሳው ‹‹በዴሞክራሲ›› ስም ከተጀማመረ ሰነባብቷል፡፡ ቻይና በታይዋን ከመጣሽብኝ ወታደራዊ ኃይል እስከ መጠቀም እሄዳለሁ ብላ በዛተች ጊዜ የእነ ናንሲ ፔሎሲ ጉብኝት ፈጥኖና ተከታትሎ መምጣት፣ ወታደራዊ የስልቀጣ ግጭቱን ለማስጀመር የቋመጠ ይመስላል፡፡ ቻይና ግን በቋመጠው ትንኮሳ ሳትጠመድ ቀረች፡፡ የአሜሪካ የ1.1 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሣሪያ ለታይዋን የመሸጥ ሐሳብም፣ ለታይዋን ከማሰብም ሆነ በሌሎች አገሮች ንቁሪያ የጦር መሣሪያ ከመሸጥ ብልጥነት በላይ ቻይና ሥጋት ገብቷት ታይዋንን እንድትወጋ መጎትጎት አይደል ይሆን?

ሩሲያ የተጠመደችበት የጦርነትና የማዕቀብ ወጥመድ ምዕራባዊ ኃያልነት በአድማው ያደባበትን ውጤት በአሁኑ ደረጃ አላቀዳጀም፡፡ ጭራሽ የሩሲያን፣ የቻይናን፣ የህንድን፣ የብራዚልንና የደቡብ አፍሪካ ሽርክና ወደ ሰፋ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጎራ የማደግ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ የማፋጠን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ወደ ቻይናና ሩሲያ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የህንድ ማዘንበል፣ ከሩሲያ አንስቶ መካከለኛ እስያን እየጠቀመ ወደ ቻይናና ህንድ የሚደርስ የየብስ ንግድ መቀየሱ፣ ምዕራባውያን ከሚያዳፉት ከእነ ዶላር ጋር ከተጣበቀ ግብይይት ተላቆ በሩብል/በሩፒ/ ዩዋን ለመገበያየት መስማማት መከሰቱ፣ ሦስቱ (ቻይና፣ ህንድና ሩሲያ) አገሮች ብቻቸውን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ማዕከል፣ የዓለም ሕዝብ ግዙፍ ሙዳ (ግዙፍ ገበያ)፣ ግዙፍ የንዋይ መንቀሳቀሻ መሆናቸው፣ ከዋናው ምድራቸው ውጪ በዓለም የተረጨ ብዙ ንቅል ዝርያ ያላቸው መሆናቸው ብቻ የአሜሪካ-ምዕራባዊያንን አፀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያኮስስ ነው፡፡ መቼ ይኼ ብቻ! አሁን ባለንበት ሁኔታ ቻይናና ህንድ ያላቸው የውጭ ፖሊሲ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትን ማዕዘኑ ያደረገ ነው፡፡ አሜሪካንን እነ ሶሪያና ኢራን ላይ ስትጋተር ያየናት ሩሲያ እንኳ ካልተተነኮሰች ወይም ሽርካዬ የምትለው አገረ-መንግሥት ካልተጠቃባት በቀር በአሁኑ ደረጃ ዘራፍ ስትል አትታይም፡፡ ከዚህ ፖሊሲ ጋር የአሜሪካ ፖሊሲ ሲነፃፀር የቡልዶዘር ፖሊሲ ሊባል የሚችል ነው፡፡ አፍሪካም ሆነ በአጠቃላይ ለማደግ የሚፍጨረጨሩ የምዕራባዊ ግልምጫና ጣልቃ ገብነት ቁስለኛ የሆኑ አገሮች፣ የየትኛውም ጎራ ጉዳይ ፈጻሚ አንሆንም በገለልተኛነት ከሁሉም ጋር ሉዓላዊነትን ያከበረ ግንኙነት እናራምዳለን የሚል አቋም ቢይዙ እንኳ፣ ይህ አቋም ‹ብሪክስ› እና ‹የሻንጋይ ትብብር ድርጅት› የሚሉ መልኮች ካሉት የሩሲያና የእስያ ግዙፎች ጎራ ጋር ያኗኑራቸዋል፡፡ ይህንን በመሰለው አንፃራዊ የፖሊሲ ስበት ብልጫ ብዙ የቅርብና የሩቅ ተከታይ ይዞ ወደ ሚዛን ብልጫ መራመድ የሚቻለው ግን፣ አሁን የተገባበትን ጦርነት በብልህ ስምምነት በቶሎ ማቆም ከተቻለ ነው፡፡ ከጦርነት ጋር ረዥም ጊዜ ከተቆየ የአቅም መዛልና የብዙ ነገሮች መበለሻሸት አደጋ አብሮ ማደጉ አይቀርም፡፡

አሜሪካ ጃፓንንና ደቡብ ኮሪያን ይዛ በክረምቱ 2014 ዓ.ም. ውስጥና ከዚያም በኋላ ያደረገችው የጦር ልምምድ፣ ሰሜን ኮሪያን በተመለከተ እነ ደቡብ ኮሪያ ያላቸውን ሥጋት ተመርኩዞ በደቡብ ሩቅ ምሥራቅም ‹‹አጋሮች አሉን›› የሚል ፕሮፓጋንዳዊ ተውኔት ነው፡፡ የደቡብ እስያ ፓስፊክ ላይ ቻይናን የጠመደ የኔቶ ሽርካ መፈጠርን አያሳይም፡፡ ሁለቱም አገሮች ከቻይና ጋር በንግድ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ከዚያም በላይ ጃፓን በፊትም ሆነ አሁን ያላት የውጭ ፖሊሲ ለ‹ብሪክስ› የቀረበ ነው፡፡ በቱኒዚያ በክረምቱ 2014 ዓ.ም. ሁለተኛ አጋማሽ ውስጥ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያደረገችው አንጓሎ ነከሳ የሌለበት ስብሰባም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ አሜሪካ ግን ያፈጀ የጉልቤ (የቡልዶዘር) ፖሊሲዋን የመቀየር ፍላጎት እስካሁን አልታየባትም፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ከመግባትም በላይ፣ አንድ ክፍለ አገር ውስጥ የተፈጠረ ቡድንን ደግፋ የመሬት ይዞታ ቆጣሪ እስከ መሆን ድረስ ስትፈተፍት ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያን የሚያንቅ ረቂቅ ሕግ ነድፋ ‹‹ኖ ሞር!›› የሚል ሰፊ አፍሪካ ቀመስ የቅዋሜ እንቅስቃሴ ተፈጥሮባት እንዳልነበረ ሁሉ፣ በቅርቡ በክረምቱ ውስጥ 2014 ዓ.ም. ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውስን የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በነበረው ጉብኝት፣ አሜሪካ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም ካለበት አስቂኝ ሽምጠጣ ያለፈ ነገር አላየንም፡፡ የሌሎችን አገሮች ሉዓላዊነት ማክበር የሚባለውን እንተወውና፣ የአሜሪካንን ጥቅምና ተሰሚነት በማስከበር ረገድ ነገሮችን ስንመዝን፣ ኢራቅን ወሮና ትርምስምሷን አውጥቶ ‹‹ዴሞክራሲ አቀዳጀሁ›› ያለው ጆርጅ ቡሽ—ትንሹ ካጋጠመው የጫማ ውርውርያ ቅሌት ብዙ የራቀ ሁኔታ ውስጥ አይደለም ዛሬ አሜሪካ ያለችው፡፡

አውሮፓን የሚመሩት ጀርመንና ፈረንሣይ አሁን ባለው የጎራዎች መፈላቀቅ ውስጥ የአሜሪካ አሮጌ የጉልቤ ፖሊሲ ሎሌ ሆነው ብዙ ይቆያሉ ተብሎም አይታመንም፡፡ የጉልቤ ፖሊሲ ሙሉ ለሙሉ የከሰረና ውጉዝ እየሆነ እንደ መምጣቱና የአውሮፓ ጥቅም ከሩሲያ ጋዝና ነዳጅ ባሻገር በብዙ ነገር ከቻይናና ከህንድ ጋር የሚፈላለግ እንደ መሆኑ፣ ምዕራብ አውሮፓዎች ጥቅማቸውን አስታርቀው ከመሄድ የበለጠ አዋጭ የሆነ ዕድል ብዙም የላቸውም፡፡ መካከለኛ እስያ፣ ኢራን፣ አዘርባጃን፣ እነ ካዛኪስታንና ፓኪስታን ሁሉ ከሩሲያ፣ ቻይና ህንድ ጋር የተያያዙ እንደ መሆናቸው የአውሮፓ የነዳጅ የጋዝ ፍላጎት ከሩሲያ የተሻለ አማራጭ የለውም፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከኳታር አካባቢ በቧንቧ ልሳብ ቢባልም አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና ራሱን የቻለ ፈተና ከመሆኑ ሌላ፣ ለቅርብ ጊዜው ችግር መፍትሔ የመሆኑ ነገር ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ቆስቁሰው ደጃቸው ያፈነዱትን ጦርነት እያገዙ እንቀጥላለን ቢሉ አገሮቻቸውን በኢኮኖሚ ቀውስ ከማስመታትም በላይ የአውሮፓ ኅብረትን ከመፍረክረክም ወደ መፈረካከስ እንዲያመራ ማገዝ ይሆንባቸዋል፡፡ ትልልቆቹ ጀርመንና ፈረንሣይ ከኑክሌር ኃይል በሚመነጭ ኤሌክትሪክ የጋዝ ዕጦትን እናጣጣለን የሚል (ራሳቸውን ብቻ ያሰበ) ሥሌት ይዘው እንገናተር ቢሉ እንኳ፣ ጋዝና ነዳጅ ብቻውን በሚፈጥረው የኢኮኖሚ መናጋት ልምድ የአውሮፓ አገሮች በአቋም መፍረክረካቸው የማይቀር ነው፡፡ በጣሊያን የመንግሥት አመራር ውስጥ ኅብረቱን የሚቀናቀን ዝንባሌ ያለው ቀኝ አክራሪ ፓርቲ ማሸነፍም የዚሁ ፍንጭ ይመስላል፡፡ እነ ጀርመን የዩክሬንን የኔቶ አባልነት ጉዳይ ጥለውና ጦርነት በሚያቆምበት አኳኋን ከእነ ሩሲያ ጋር በመግባባት ፈንታ፣ ለቡልዶዘር ፖሊሲ ታማኝ ሆነው አውሮፓዊ ኅብረታቸውን ማጣት ስንት የተለፋበትን ቤት አስፈርሶ ደጅ ከማደር አይተናነስም፡፡ ይህንን የሚያህል ውድ ኪሳራ መክፈልን ተገቢ የሚያደርግ ጥቅምም በጦርነቱ ውስጥ የለም፡፡

ይህንን ስለመሳሰለው ትርፍና ኪሳራ የምናወራው በኃይላኖቹ ጎራዊ ማዕቀፍ ውስጥ እያሰብን ነው፡፡ ከዚያ ማዕቀፍ ራሳችንን አውጥተን በሰው ልጅ ደኅንነት ዓውድ ውስጥ ስናስብ ግን የሚከነክኑን ነገሮች ይቀየራሉ፡፡ በዚህ ጦርነት ውስጥ ኮሜዲያኑ ዘለንስኪ የሚጫወተው ሚና ለገዛ አገሩ ጠላት ከመሆን ያነሰ ይሆን? ዕውን ዩክሬይንን በመሣሪያ እየደገፉ በጦርነት ውስጥ እንድትቆይ እየለፉ ያሉ አገሮችስ የወዳጅ ጠላት መባል ያንሳቸዋል? ለእነ ጀርመንም ቢሆን የኑክሌር ቦምብ ባለቤት የሆኑ አገሮች ጦርነት እንዲከፍቱ ሰበብ መስጠትና ጦርነትን ማሟሟቅ ከዕብደት አይሻልም፡፡ በዩክሬይን ቼርኖቤል የኑክሌር ማብለያ ላይ እ.ኤ.አ. በ1986 በደረሰ አደጋ ጊዜም ሆነ፣ በጃፓኑ (ፋኩሺማ) እ.ኤ.አ. የ2011 አደጋ ጊዜ ዓለም የተንጫጫው የዚያ ዓይነት አደጋ ሰፊ፣ ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ጠንቅ ስላለው ነው፡፡ የዚያን ጊዜ ዓይነቱ ጩኸት ባለኑክሌር ሁለት አገሮች መራር ጦርነት ውስጥ ሲገቡ የት ገባ? የሩሲያን ልዕለ ኃይላዊ አቅም ለመሰባበር ይበጀናል ብለው አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ በእጅ አዙር በጦርነቱ ተሳታፊ መሆናቸው፣ በተለይ አውሮፓ ደጇ ለፈነዳ ጦርነት አጫፋሪ መሆኗ፣ ራስን በራስ ከመስቀል ‹‹ብልጠት›› ምን ያህል ይርቃል? የእነ ሒትለር ብልጠት ራስን በራስ የማጥፋት ድግስ የጎረፈበትን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ወለደ፡፡ አሁን እየተካሄደ ባለው የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ውስጥ በክሬሚያ ባለ ግዙፍ የመተላለፊያ ድልድይ ላይ የደረሰ ጉዳት ቁጣን አንሮ፣ ውቧ ኪየቭ በሚሳይላዊ ቅዝምዝም የተመታችበትን ውጤት አስከተለ፡፡ ያ ደግሞ እነ አሜሪካንን አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የጦር መሣሪያ ወደ ማገዝ ውሳኔ ወሰደ፡፡ በዚህ አኳኋን የነገሮች እየተካረሩ መምጣት ሒትለራዊ ወፈፌነትን አይወልድ ይሆን? ባለኑክሌር ሚሳይል መተኮስ ቢመጣ ባለኑክሌር ሚሳይልን በሚሳይል በመምታት፣ መትረፍን ከርቀት ጋር አያይዞ ማሥላት የዘመናችን ቧልት ነው፡፡ ባለኑክሌር ሚሳይሉ ከተወሰነ መምዘግዘግ በኋላም ሆነ ገና ሲያሸቅብም ቢመታም፣ የቅርብና የብክለት ጠንቁ ለመካከለኛውም ለምዕራባዊው አውሮፓም ለሌላውም ይዳረሳል፡፡ የኑክሌር ፍንዳታ በሚረጫቸው ምናምንቴዎች ኦዞን ንጣፍ ላይ የሚያደርሰው ብርቀሳ፣ አየር ንብረት ላይ የሚያደርሰው ጥፋት፣ በተመረዙ ህያውና ግዑዝ ነገሮች አማካይነት (በአቧራና በውኃ እንቅስቃሴ፣ ወዘተ ሁሉ) የሚደርሰው የመርዝ መዛመት የሚያስከትለው የቅርብና የሩቅ ጠንቅ ስለመትረፍ ማሰብን ቀልድ ያደርገዋል፡፡ እናም ከማንም በላይ ጦርነቱ እንዲቆም ከመታገል ፈንታ የአውሮፓውያን የፀረ ሩሲያ አድማ ንቁ ተሳታፊና አጫፋሪ መሆን ከፍጅት አደጋ ጋር የመጨፈር ያህል ነው፡፡

በአጠቃላይ የሰው ልጅ ዛሬ ያለው የገደል አፋፍ ኑሮ ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ኑሮ ሁሉም ጥፋት ያዋጣ ቢሆንም ‹‹የሠለጠኑት›› አገሮች እያወቁ የሚያደርሱት ጥፋት ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዓለማችን የሥነ ምኅዳር መቃወስ አፍ አውጥቶ ‹‹ወዮላችሁ!!›› እያለ ነው፡፡ የዋልታዎች የበረዶ ክምር መሳሳት፣ የየብስ ስፋት መቀነስ፣ የምድረ በዳ መስፋት፣ የውቅያኖስ መበከልና የውኃ ሕይወት ጉዳት ማደግ፣ አንዱ ጋ ነጎድጓድና ጎርፍ የነበረውን እንዳልነበረ ሲያደርግ ሌላው ጋ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውኃ ውስጥ ሰጥሞ የነበር መርከብ ፈጦ እስኪታይ ድረስ የውኃ መጉደል መከሰት፣ ይህ ሁሉ የሥነ ምኅዳር መቃወስ አፍ ያወጣ ኡኡታ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ቀውስ ላይ የኑክሌር ፍንዳታዎች ሲታከሉ ደግሞ ለማንኛችንም አበሳው ‹‹ራስን በራስ በማጥፋት›› ቢገለጽ አያንሰውም፡፡ ለዚህ ነው ዓለም በሙሉ የባለኑክሌሮችን ጦርነት በመቃወም በአግባቡ አለመጮሁ ሞትን ከመናፈቅ የማይለየው፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን ያወሳሁት ከመጻሕፍት የወጣ ነገር ሳይሆን ዓለም ላይ ያለና ገና ያላለቀ የቅብጠት ሒደትንና አዝማሚያን ነው፡፡ አንድ ጽሑፍን በማንበብ ጊዜ በመስመሮች መሀል ያለውን መልዕክትና ፍላጎት ሁሉ በርብሮ ለመጨበጥ መጣር እንደሚገባ ሁሉ፣ የድርጊቶችን መልክና ፍላጎታዊ ይዘት ከዕውናዊ ትርፍና ኪሳራ ጋር ባላቸው መስተጋብር ለማስተዋል ከመጣር የተለየ አላደረግኩም፡፡

ይቀጥላል…

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...