Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥና ተግዳሮት (ክፍል አንድ)

የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥና ተግዳሮት (ክፍል አንድ)

ቀን:

በላቀው በላይ

ሰው፣ ግብረ ገብና ሥነ ምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ (ጠና ደዎ) ‹‹አንድ ሰው የሚጽፈው የመጻፍ ችሎታ ስላለው ብቻ አይደለም፣ ስለሚጽፈው ነገር በቂ ዕውቀት ስላለው ላይሆንም ይችላል፣ ምናልባትም የመጻፍ ፍላጎትና ተነሳሽነት ስላለውም ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ ዕረፍት የሚነሳ ችግር ሲኖር፣ መልስ የሚሻ ጥያቄ ሲፈጠር ወይም ለእነዚህ ችግሮችና ጥያቄዎች ተገቢ ትኩረት ሲታጣ ለመጻፍ ይነሳሳ ይሆናል፡፡ ችግሮችና ጥያቄዎች የተኛ አዕምሮን መቀስቀስ፣ የዘነጋ ህሊናን ማስታወስና ያንቀላፋ ዜጋን ማንቃት አለባቸው፤›› በማለት ያሰፈሩት ሐሳብ ለዚህ ጽሑፍ መጻፍ በቂ ምላሽ የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡

የአገራችን የዳኝነት አገልግሎት ፍፁም ዕረፍት የሚነሳ ነው፡፡ በአንድ በኩል የዳኛነት ሥርዓቱ ፍፁም በሙስናና ብልሹ ሥነ ምግባር የተበከለ ነው እየተባለ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር በተደጋጋሚ ይከሰሳል፡፡ ሕዝቡም ፍርድ ቤት ትክክለኛ ፍርድ አይሰጥም እያለ ከፍተኛ ቅሬታ እያሰማ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል በመንግሥት በኩል በዳኝነት አካሉ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ይደረግበታል እየተባለ የሚነገርና የሚጠበቅ ቢሆንም፣ እስካሁን የተጀመረ ሥራ የለም፡፡ ሁላችንም ያለንበት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተስፋ መቁረጥ የዳኝነት አካሉን የማፅዳት ሥራ የሚጀመርም የሚጨረስም አያስመስለውም፡፡ የአንድ ሰው የጤና ሁኔታና የአንድ አገር የዳኝነት ሥርዓት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ አንድ የተፈጥሮ ሰው ጤናው ተበክሎና ዋና ዋና አካላቱ ተቃውሶ ስለሥራው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለአገሩና ስለሙያው ስለዕውቀቱ ሊያስብ አይችልም፡፡ ይህ ሰው ከሁሉም በፊት የጤናውን ሁኔታ ለማስተካከል የሞት የሽረት ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ አገርና ሕዝብ የተበላሽ የዳኝነት ሥርዓት ይዞ ስለሰብዓዊ መብት፣ ስለዴሞክራሲያዊ መብት፣ ስለንብረት መብት፣ ስለሰው ልጆች ነፃነትና ክብር፣ ስለሰላም፣ ወጥቶ ስለመግባት፣ ተኝቶ ስለመነሳት፣ ስለመጪው ትውልድ ከቶውንም ሊያስብ አይችልም፡፡ ስለእነዚህ ነገሮች ከማሰቡ በፊት ለሰው ልጆች የተረጋጋ ሕይወት ዋስትና የሚሰጥ የፍትሕ ሥርዓት ማዋቀር፣ በየጊዜው ማለምለም፣ ሲያረጅ ማደስና ሲበላሽ ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ደራሲ በማናቸውም ደረጃ የሚጻፍ ጽሑፍ የችግር መፍቻ አንድ መንገድ ሆኖ ያገኙት ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው የችግር መፍቻ መንገዱ ብዙ ነው፡፡ የችግር መፍቻ መንገዱ ፈጣሪን ከመለመን፣ ፈጣሪን ከማማረር፣ ከማልቀስ ጀምሮ በትጥቅና በሰው ኃይል ተደራጅቶ እስከ መፋለምና የሕይወት ዋጋ እስከ መክፈል ይደርሳል፡፡ የሰው ልጅ ችግርን አቅፎና ችግርን አንግሦ ለመኖር ያልተፈጠረ ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ችግርን ሲታገል ኖሯል፣ አሁንም በመታገል ላይ መሆኑ በዓይን የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ለችግር እጅ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ያልቻለውን ችግር እንኳን በማልቀስ ይታገለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሞትን የሰው ልጅ የማይፈልገው ጉዳይ ቢሆንም የማያስቀረው በመሆኑ ሞት በመጣ ጊዜ የሰው ልጅ ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል፡፡ ይህ አንድ የትግል ሥልት መሆኑ ነው፡፡ ለቅሶው ሞት ብትመጣም አልተቀበልኩህምና አልወደድኩህም የሚል ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት በተለይም በዳኝነት አካሉ ውስጥ የሚታየው ብልሹ አሠራር በለቅሶ የሚራራ አይደለም፡፡ ስለዳኝነት አካሉ ጉድለት የሚጻፈውን የሚያነብበት ዓይን፣ ስለሚቀርብበት ትችትም የሚሰማበት ጀሮ የለውም፡፡ እንዲያውም ‹‹ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ›› እንደሚባለው፣ ‹‹የሕዝብን አመኔታ ያተረፈ ፍርድ ቤት›› የሚል ሎጎ (Logo or Brand) አስቀርፆ በሚዲያ ተከስቷል፡፡ አንደኛው የመንግሥት አካል ስለሙስና ሲባል ዳኞች በቴሌግራም ተደራጅተዋል ብሎ ክስ ሲያቀርብ፣ ሌላኛው የመንግሥት አካል የሆነው የዳኝነት ክፍል ደግሞ ‹‹በሕዝብ የታመነ ፍርድ ቤት ሆኛለሁ›› እያለ ከሳሹን (አስፈጻሚውን) እያስፈራራ ይገኛል፡፡

አገልግሎት አሰጣጥና ዳኝነት ወደሚለው ጉዳይ ስንመለስ የዳኝነት ሥራ አገልግሎት የመስጠት ሥራ ነው ወይስ? አይደለም? የዳኝነት ሥራ በአገልግሎት አሰጣጥ መርሆዎች ይመራል? ወይስ አይመራም? የዳኝነት ሥራን ከሌሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥራዎች ምን የተለየ ያደርገዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንገደዳለን፡፡ በጤናማና ትክክለኛ ትርጉሙ አገልግሎት (Service) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መስጠትና መውሰድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አገልግሎት (መስጠትና መውሰድ) በዘፈቀደ (Arbitrarily) የሚከናወን አይደለም፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ መግባባት፣ መከባበርና መተማመን ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ መከባበር በሌለበት አገልግሎት መስጠትና አገልግሎት መቀበል አይኖርም፡፡ መከባበር በሌለበት ሊኖር የሚችለው መነጣጠቅና ሁከት ብቻ ነው፡፡ መተማመንም በአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አገልግሎት ተቀባዩ በአገልግሎት ሰጪው መታመን ላይ ጥርጣሬ እንኳን ሊኖረው አይገባም፡፡ አገልግሎት ሰጪውም አገልግሎት ተቀባዩ ስላገኘው አገልግሎት መወጣት የሚገባውን ግዴታ የማይወጣ በመሆኑ ላይ መጠራጠር የለበትም፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ መከባበርንና መታመንን የሚያጠናክሩ መሣሪያዎች የግድ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ የአገልግሎቱ መግለጫ፣ የጥራት ማረጋገጫ፣ የብዛትና የክብደት መለኪያዎች (ሚዛኖች) በእጅጉ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በስኳር ሻጭና ገዥ መካከል መተማመኑና መከባበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክብደቱ መለኪያ ሚዛኑ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሚዛኑ ሻጩም ዕላፊ ያልሄደበት ገዥውም ጎሎ ያልቀረበት ስለመሆኑ መተማመኛቸው ነው፡፡

የዳኝነት ሥራ በቀጥታ መስጠትና መውሰድ ባይሆንም በውስጡ የሰዎች መስተጋብር (ግንኙነት) አለበት፡፡ በሰዎች መካከል በሚደረግ ግንኙነት ሁሉ መከባበርና መተማመን የግድ በመሆኑ በዳኝነት ሥራ ውስጥ መከባበርና መተማመን ምንጊዜም መኖር አለባቸው፡፡ የዳኝነት ሥራው ከመከባበርና መተማመን በተጨማሪ ሌሎች የሥነ ምግባር ግዴታዎች አሉበት፡፡ እነሱም ነፃነት (Independence) እና ገለልተኝነት (Impartiality) ሲሆኑ ዳኛው በግል ኑሮውም ሆነ በዳኝነት ሥራው ፍፁም ነፃና ገለልተኛ ሆኖና መስሎ መታየት ይጠበቅበታል፡፡ ዳኛው በሥራው ላይ እያለ እንከን የለሽ (Integrity and propriety) ሆኖ እና መስሎ መታየት አለበት፡፡ ዳኛው እሱ ስለሚያደርገው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች ስለእሱ ጉድለቶች ሊናገሩ የሚችሉበትን ቀዳዳ ሁሉ የመዝጋት ግዴታ አለበት፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ከመልካም ሥነ ምግባር ላፈነገጠ ዓላማ ዳኞች በሶሻል ሚዲያ ጭምር ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ነው፤›› የሚል ጥርጣሬም ሆነ ትችት እንዳይቀርብበት ዳኛው ምንጊዜም ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

በኢትዮጵያ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ትልቁ ስብራት የመከባበር ዕጦት ነው፡፡ ጸሐፊው እንዳየውና ራሱም እንደሚያደርገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፍርድ ቤትና ለዳኛው ከፍተኛ አክብሮት አለው፡፡ በአፀፋው ዳኛው በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ ለሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ክብር ሲሰጥ አይታይም፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች ራሳቸው ብቻ የተከበሩ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቱ ተገልጋዮችን እንደ ሰው ለመቁጠር ስለሚቸገሩ ከሰው የሚጠበቀው ‹‹እንደምን አደራችሁ፣ እንደምን ዋላችሁ›› የሚለው ተግባቦት እንኳን የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዳኞች የሰጠው ክብር ዳኞችን በእጅጉ አሳስቷቸዋል፡፡ እንደ ዳኞች አረዳድ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከበረው ብቸኛ ሰው ዳኛ ብቻ ነው፡፡ እንደ ጸሐፊው አረዳድ ደግሞ ሁሉም ሰው እኩል የተከበረ ነው፡፡ ዳኝነት የተለየ ክብር መጎናፀፊያ ሳይሆን የሥራ ድርሻ ነው፡፡ ተራ የሥራ ድርሻ ነው፡፡ የዳኝነት ሥራ ልክ እንደ አስተማሪው፣ እንደ ሐኪሙ፣ እንደ አናፂውና እንደ ግንበኛው የሥራ ድርሻ ነው፡፡ ጸሐፊው ኢትዮጵያውያን ዜጎችን የሚሰድብና የሚያዋርድ አስተማሪ፣ ሐኪም፣ ግንበኛ ወይም አናፂ አጋጥሞት አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች በየትኛውም የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ይሰድባሉ፣ ያዋርዳሉ፡፡ በወንጀል ሕግ ቁጥር 122 እንደተደነገገው በወንጀል ጥፋተኛ የተባለውን ሰው በልኩ ከማስጠንቀቅ፣ ከመውቀስ፣ ከመገሰጥ፣ አስፈላጊም ሲሆን ይቅርታ እንዲጠይቅ ከማድረግ ባለፈ ነፃውን ዜጋ መስደብና ማዋረድ ቀርቶ ባልተገባ ዕይታ የማየት ሥልጣን እንኳን አልተሰጣቸውም፡፡ የፍርድ ቤቱን ክብር በማይቀንስ መልኩ በችሎት አውቆ አጥፊዎችን እንዲስተካከሉ የማድረግ ሥልጣን ዳኞች ያላቸው ሲሆን፣ ለምን ውኃ ቀጠነ እያሉ በፍርድ ቤቱ ተገልጋዮች ላይ የመጮህ፣ ዜጋውን የማዋረድና የማሳቀቅ ሥልጣን የላቸውም፡፡ ሁሉም ሰው ክብር ይገባኛል ብሎ ያምናል፡፡ ደግሞ ሁሉም ሰው ክብር ይገባዋል፣ በሕገ መንግሥቱም ታውቆለታል፡፡ በሕግ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው የማንንም ክብር የመግፈፍ ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ለነገሩ የሰዎችን ክብር የማያውቅ ወይም ሰዎችን የማያከብር ሰው ፍርድ ቤት ግቢ እንዲገባ ለምን እንደተፈቀደለት የጸሐፊው የዘወትር ግርምት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት ውስጥ ትልቁ ካንሰር ዳኞች ሚናቸውን የተረዱበት መንገድ ነው፡፡ የእኛ ዳኞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀጣሪዎች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገልግሎት ሰጪዎች መሆናቸውን የተረዱ አይደሉም፡፡ ዳኞች በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያው ሕይወት ውስጥ የምናበረክተው ተቋማዊ አስተዋጽኦ አለን ብለው የሚረዱ ሰዎች መሆን ይገባቸው ነበር፡፡ ዳኞች የዳኝነት ሥራው ቢጓደል በሕዝቡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የሚጎድል ነገር አለ ብለው የሚረዱ ሰዎች ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች ስለሕጉና ስለእውነቱ ‹‹አንገቴ ይቆረጥ›› የሚሉ ሰዎች ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች ‹‹መብት›› ስለሚባለው ቁልፍ እሴት መቼም ዘብ ሊቆሙ ይገባ ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ የኢትዮጵያ ዳኞች መብቱን የሚጠይቅ ሁሉ በእጅጉ የሚያናድዳቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች በሥራቸው ላይ ሆነው ለአንድ አገራዊ ተልዕኮ፣ ለአንድ ማኅበራዊ ተልዕኮ የተሰማሩ መልካም ዜጋ መስለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች የሚሠሩት በልመና ብዛት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዳኞች ለሚለምናቸው የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልገው የጥብቅና ሥራ ወደ ልመና ሥራ ተቀይሯል፡፡ ጠበቃው የጥብቅና ፈቃዱን ይዞ ፍርድ ቤት የሚገኘው ዳኛውን ለመለምን እንጂ ስለደንበኛው መብት ለመጠየቅና ለመከራከር አይደለም፡፡ ጠበቃው ይህንን የሚያደርገው ስለደንበኛው መብት ለመሟገት ብቃት ጎድሎት አይደለም፡፡ ሲለመን ከሚሰጥ፣ ሲፈልግ ከሚሰጥ የዳኝነት ሥርዓት ከሙግት የሚከበር መብት የሌለ በመሆኑ እንጂ፡፡

የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ከሌላው አገልግሎት አሰጣጥ ለየት የሚያደርግ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ዳኛው እንደ ሰው አገልግሎት ሰጪ፣ እንደ መሣሪያ ደግሞ ሕግና ፍሬ ነገር የሚመዝን ሚዛን መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል በስኳር ሻጩና በስኳር ገዥው መካከል ባለው ግንኙነት የልኬቱን ሥራ የሚሠራው ሚዛኑ ነው፡፡ ሚዛኑ ሕይወት አልባ በመሆኑ ከገዥውም ሆነ ከሻጩ የተለየ የስኳር ፍላጎት የለውም፡፡ ሚዛኑ በሻጭም ሆነ በገዥ እንዲሁም በራሱ ፍላጎት ተፅዕኖ ውስጥ ሳይወድቅ በገለልተኝነትና በትክክል የመለካት ሥራውን የሚያከናውን በመሆኑ፣ በገዥውም ሆነ በሻጩ ከፍተኛ መታመን አለው፡፡ ሚዛን በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የተጫወተው መልካም ሚና ይህን ያክል የጎላ ነው፡፡ አንድ ዳኛ ሕይወት ከሌለው ሚዛን የላቀ አገልግሎት የመስጠት፣ ሕይወት ከሌለው ሚዛን የላቀ መታመን ይጠበቅበታል፡፡ ዳኛው በከሳሹና በተከሳሹ መካከል ላለው ክርክር ሕጉንም ሆነ ፍሬ ነገሩን ሳያፈስ፣ ልክ እንደ ሚዛኑ ከከሳሹ ጥቅምም ሆነ ከተከሳሹ ጥቅም ቀንሶ ወደ ራሱ ወደ ዳኛው ሳይወስድ የምዘናውን ሥራ በትክክል መሥራት አለበት፡፡ አሁን በፍርድ ቤቶቻችን የታጣው ሁለቱም ነው፡፡ ዳኞች ጥሩ አገልግሎት ሰጪ አይደሉም፣ አገልግሎት ሰጪዎች ነን ብለውም አያምኑም፡፡ በዋናነት ተገልጋዮች ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ዳኞች የሚያምኑት ስንለመን የምንሰጥ፣ ስንጠየቅ የምንከለክል ሰጪና ነሺ ነን ብለው ነው፡፡ አሁን ያሉን ዳኞች ጥሩ ሚዛኖችም አይደሉም፡፡ አሁን በሕዝቡ ዘንድ ቅሬታ እየተነሳ ያለው ዳኛው ልክ እንደ ስኳሩ ሚዛን ሚዛንነቱን ተጠቅሞ ለከሳሹ ወይም ለተከሳሹ መፍረድ ሲገባው፣ ከከሳሹ ወይም ከተከሳሹ ጋር ተመሳጥሮ ከፊሉን ለራሱ ከፊሉን ደግሞ ለተመሳጠረው ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ይሰጣል የሚል ነው፡፡ አንድ ስኳር ነጋዴ የስኳሩን ክብደት እንዲለካለት የገዛው ሚዛን ስኳሩን እያሾለከ ለራሱ ለሚዛኑ የሚወስድ ከሆነ፣ ወይም ደግሞ በሆነ ቀዳዳ ስኳሩን አሾልኮ ለገዥው እየሰጠ ከገዥው ላይ ሚዛኑ ለራሱ ገንዘብ የሚቀበል ከሆነ የሚዛኑ ባለቤት መቼም ሁሌ በሚዛኑ እየተሰረቀ አይኖርም፡፡ ሚዛኑን ያድሳል ወይም ያስወግዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአንድ የሚዛን ባለቤት ያነሰ መብት የለውም፡፡ ሚዛኑ በትክክል ካልሠራ ሥልጣኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የዳኝነት ሥራ በግልጽ አደባባይ የሚከናውን አገልግሎት ሰጪነትም መሣሪያነትም (ሚዛንነት) ነው ከተባለ፣ የዳኝነት አገልግሎት ከሚዲያ ትችት የተከለለ (Immune) ነው ወይስ አይደለም የሚለውን መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የፍርድ ቤቱ የሩብ ዓመት ክንውንና የቀጣይ ጊዜ ዕቅዶች በሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተገመገመበት ጊዜ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፍርድ ቤቱ በማናቸውም ዜጋ (ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ማለታቸው እንደሆነ ይገመታል) በሚዲያ እንዳይተች የተወካዮች ምክር ቤት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው፣ ወይም ሕግ እንዲያወጣላቸው የቋሚ ከሚቴውን ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱን ሲለማመጡ ታይተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በተለይም የዳኝነት የሥራ ክፍሉ ከሚዲያ ትችት የተከለለ ነውን? ፍርድ ቤት ከሚዲያ ትችት ከለላ ሊሰጠውስ ይገባልን? የሚሉ ጥያቄዎች ገጥመውኛል፡፡

በመጀመርያ ደረጃ በ2014 ዓ.ም. ራሳቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ስለፍርድ ቤቱ መልካም አፈጻጸም የኢትዮጵያን ሕዝብ ገንዘብ በመጠቀም፣ ከፍተኛ የሚዲያ ቅስቀሳ (Propaganda) ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ ስለፍርድ ቤቱ መታመን ከፈረንጅ ተለምኖ ተገኘ በተባለ ገንዘብ ጥናት አሠራሁ በማለት ‹‹የመልካም ስም ምስክር ወረቀት›› ያገኙ ስለመሆኑም ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ ስለፍርድ ቤቱ መልካም አፈጻጸምና ስለፍርድ ቤቱ ዳኞች መልካም ሥነ ምግባር በሚዲያ ቅስቀሳ ለማድረግ የሚፈቅድ ሕግ ወይም አሠራር ካለ፣ ስለፍርድ ቤቱ ድክመት ወይም ስለዳኛው ጉድለት በሚድያ ትችት ለማድረግ የሚከለክል ሕግም ሆነ አሠራር የለም ማለት ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ ላይ የሚቀርብን ትችት የሚከለክል ሕግ ይውጣ ከተባለም፣ ፍርድ ቤቱ ስለራሱ ስኬት ስለሚያሠራጨው ፕሮፓጋንዳም መከልከል አለበት፡፡ በዜጎች ላይ በደል የፈጸመ ፍርድ ቤት በሚዲያ በደሉን እያፀዳ በደል የደረሰባቸው ዜጎች በደላቸውንና ቅሬታቸውን ለሕዝብና ለሚመለከተው አካል በሚዲያ እንዳያሳውቁ የሚከለክል ሕግ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም፡፡ 

በቀጣይ ፍርድ ቤት የመንግሥት ተቋም ሲሆን፣ ሥራውንም በግልጽ ማከናወን የሚገባው/የሚገደድ ስለመሆኑ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 ሥር ተደንግጓል፡፡ በግልጽ የሚደረጉ ተግባራት በሙሉ ከሕዝብና ከሚዲያ ትችት የተከለሉ አይደሉም፡፡ ፍርድ ቤት ዓለማዊ ወይም ምድራዊ ተቋም ነው፡፡ ዓለማዊ ነገሮች ሁሉ ፍፁምና የተቀደሱ አይደሉም፡፡ ሰው እንደ ዓለማዊ ፍጡርነቱ ስህተቶች ይሠራል፣ ሲሠራም ኖሯል፡፡ ፍርድ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ዳኞችና የፍርድ ቤት አመራሮች ከሌላ ዓለም የመጡ ቅዱሳን አይደሉም፡፡ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የሚሠሩ ዳኞችና አመራሮች በቀን በቀን ህልቆ መሳፍርት የሌለው (Infinite) ስህተት እንደሚሠሩ የምናየው፣ የምናውቀው፣ የምናምንበት ጉዳይ ነው፡፡ በፍርድ ቤት የሚሠሩ ዳኞችንና የፍርድ ቤቱን አመራሮች የበቁና የፀዱ ናቸው ብለን የፍፁምነት ካባ የምንደርብላቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ የፍርድ ቤቱ አመራሮችና ዳኞች የፍርድ ቤቱን ክብር አይመጥኑም የሚለው በመላው ሕዝብ የታመነበት ጉዳይ ነው፡፡ በየጊዜው ከፓርላማው ውሉ የምንሰማው ምሬት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የነውሩን መኖር ሳንጠላ ስለነውሩ መናገርን ልንጠላ አንችልም፡፡ የነውሩ መኖር ባልተካደበት ሁኔታ ስለነውሩ አትናገሩ ልንባል አንችልም፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለፍርድ ቤቱ ከለላ የሚያደርገው በፍርድ ቤቱ ነፃነት (Independence) እና ገለልተኛነት (Impartiality)፣ እንዲሁም ተቋማዊነት ላይ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. ራሳቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ያጋጋሉትን የሚዲያ ቅስቀሳ ተከትሎ በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው ፍርድ ቤት ይፍረስ፣ ወይም በአስፈጻሚው ሥር ይካተት ወይም ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው ብሔር መሣሪያ ይሁን የሚል ትችት አልቀረበም፡፡ የፍርድ ቤቱን ተቋማዊነት፣ ገለልተኝነትና ነፃነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ ካሰበው በላይ ስለሚፈልገው በፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊነትና ተቋማዊነት ላይ ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም፣ አላነሳምም፡፡ በሌላ በኩል ከላላ የተሰጠው ለዳኞች ብቻ ነው፡፡ ከለላውም ዳኞች የመከሰስ መብታቸው በሚመለከተው አካል ሳይነሳ በፖሊስ አይያዙም፣ በፍርድ ቤት አይከሰሱም የሚል እንጂ በተቋም ደረጃ ስህተት የሚፈጽም ፍርድ ቤት፣ ወይም በግሉ ስህተት የሚሠራ ዳኛ በሚዲያ እንዳይተች ከለላ የሚሰጥ ሕግ አይደለም፡፡ በሌለ ሕግ ፓርላማው ፍርድ ቤቱን ከትችት የሚከላከልበት መሠረት የለውም፡፡ ፍርድ ቤቱን ከትችት የሚከለክል ሕግ ካለ ራሱን ከትችት መከላከል ያለበት ራሱ ፍርድ ቤቱ እንጂ፣ ፓርላማው የፍርድ ቤቱ ሞግዚትም አይደለም፡፡

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ፍርድ ቤቱን ጨምሮ ማናቸውንም ተቋምና ጉዳይ መተቸት በሕግ የተፈቀደና የማያስጠይቅም ነው፡፡ አንድ ሰው ለሕዝብ ጥቅም በሚሆን ጉዳይ ላይ ሐሳቡን በመግለጽ ብቻ ከተወሰነ ምንም እንኳን ይህ አሳቡ በሕዝብ ድምፅ ሌላውን ሰው የሚያስወቅሰው ሆኖ ቢገኝ እንኳን ጥፋተኛ አያደርገውም፣ ተከሳሹ (ተችው) በከሳሹ (በተተችው) ላይ የገለጸው ሐሳብ ሐሰት መሆኑን በእርግጥ ያወቀው ካልሆነ በቀር፣ ስም እንዳጠፋ አያስቆጥረውም የሚለው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2046 ድንጋጌ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ፍርድ ቤቱን ያለምንም ተጠያቂነት መተቸት የሚቻል መሆኑን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርድ ቤቱን በፓርላማና በሚዲያ እየተቹ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የማይደርስባቸው ጠቅላይ ሚኒስቴር ስለሆኑ ብቻ፣ ትክክል ስለተናገሩ ብቻ አይደለም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ሕግ ጥበቃ ስለሚያደርግላቸው ጭምር ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ አለመታደሎችን የታደልን፣ በየታሪካችን ምዕራፍ መልካም የተቋማት አመራሮችን ያላገኘን በመሆናችን እንጂ፣ የሌሎች አገሮች የፍርድ ቤት አመራሮችና የፍርድ ቤት ዳኞች ሕዝቡ ፍርድ ቤቱንና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የመተቸት መብት እንዳለው ያበረታታሉ፡፡ አንድ ፍርድ ቤት አመራርና ዳኛ (ጀስቲስ ስቴቨን ሬርስ የተባሉ) ‹‹ጥራት ያለው ፍርድ ቤት ምንድነው? (What is a quality judiciary?)›› በሚል ባዘጋጁት ጽሑፍ ‹‹… an equally important, indeed vital, concomitant is the right of everyone to criticize judicial decisions and behavior. Whether the authority and position of an individual judge or the due administration of justice is concerned, no wrong is committed by any member of the public who exercises the ordinary right of criticizing, in good faith, in private or in public.›› የሚለውን አስፍረዋል፡፡ ፍርድ ቤትን መተቸት ራሱ ፍርድ ቤትን ያግዛል፣ የማናቸውም ሰው መብትም ነው የሚል መልዕክት ያለው ነው፡፡ ስለፍርድ ቤቱና ስለዳኛው ባህሪ የሚደረግ ትችት ፍርድ ቤትን የሚያግዝ በሆነበት ሁኔታ፣ የእኛ የፍርድ ቤት አመራሮች ፍርድ ቤቱና ዳኞች እንዳይተቹባቸው የሚያደርጉት ጥረት ራሱ ፍርድ ቤቱን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቱን ለማረምና ለማስተካከል ብሎም ለማሻሻል፣ በተለይም ከተሰጠው የሥልጣን ክልል ውጪ እንዳይወጣ ለማድረግ ከሚዲያ ትችት የተሻለ መሣሪያ የሌለ ስለመሆኑ በበርካታ ጸሐፍት የታመነበት ጉዳይ ነው፡፡

‹‹Ultimately, it is our customers that decide whether our service is ‘fit for purpose’ and it is their dissatisfaction that drive our need for improvement.›› የሚለው የእውነተኛ አገልግሎት ሰጪዎች መርህ የእርካታ ዕጦት ትችትን የሚያስከትልና ትችትም ለለውጥ መነሻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ትችትን የሚገድቡ ኃላፊዎች የተጨነቁና ለለውጥ መፈናፈኛ ቦታ የሌላቸው ናቸው፡፡ ትችትን ለመገደብ በተለይም ስለሕዝብ ጥቅም ተብሎ የሚደረግን ትችት ለመገደብ የሕግም ሆነ የምክንያት መሠረት የላቸውም፡፡ በቀጣዩ ክፍል (ክፍል ሁለት) የፍርድ ቤቶቻችን ተቋማዊ ሥነ ልቦና፣ የታዩ ችግሮችና መፍትሔዎች ይዳሰሳሉ፡፡

የጸሐፊው ማሳሰቢያ

ይህ ጽሑፍም ሆነ ተከታዩ ሥራቸውን በሙያው ሥነ ምግባር የሚያከናውኑ የፍርድ ቤት አመራሮችንም ሆነ ዳኞችን (ካሉ ወይም አለን ካሉ) አይመለከትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው wbdlakew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...