Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉብሔራዊ ምክክሩን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አኳያ ብንመረምረውስ?

ብሔራዊ ምክክሩን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አኳያ ብንመረምረውስ?

ቀን:

በዓባይነህ ግርማ

አገራዊ የምክክር ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ በፖለቲካው ዓምድ ከአገር ህልውናና ሉዓላዊነት መጠበቅና መከበር አንስቶ እስከ ሕግ መከበር፣ እስከ ዴሞክራሲያዊ ፈሊጦች ግንዛቤና ትግባራ፣ እንዲሁም እስከ ሰብዓዊ መብት መከበር በማስመልከት ሊሆን ይችላል፡፡ በኢኮኖሚው ዓምድ ከዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ እስከ ድህነት መወገድ፣ እስከ ኢኮኖሚ ዕድገትና የሀብት ክፍፍልና አገራዊ ብልፅግናን በሚመለከት ሊሆን ይችላል፡፡ በማኅበራዊ ረገድም ከጤና አጠባባቅ ተደራሽነት፣ ከትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣ ትውልድን ከማብቃት እስከ ማኅበራዊ ሥነ ልቦና ተሃድሶ አስመልክቶ ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህም ላቅ ሲል የአገርንና የሕዝብን ታሪክ አረዳድና ትርክት ወይም የወደፊት ዕጣ ፈንታን በሚመለከት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡  ታዲያ በእጅጉ ሊያሳስበንና ምክክር ልናደርግበት የሚገባ ጉዳይ የቱ ነው? ታሪካዊው ትርክት ወይስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ? ከፍ ብሎ የተመለከቱት ጉዳዮች ሁሉ አንገብጋቢና አሳሳቢ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከታሪክና ከወደፊት ዕጣ ፈንታ አኳያ የሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በምን አስተሳሰብና ሥነ ልቦና ልንረዳቸው፣ በምን ምግባርና ተግባር ልናስተናግዳቸው ይገባል የሚለው ትልቁ የአገር የምክክር ጉዳይ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡

ከታሪክ አኳያ የሚደረጉ ዲስኩሮች ጫፍና ጫፍ የሚረግጡ ሆነው ይታያሉ፡፡ አንዱ ጫፍ ያለፈውን መልካምም ሆነ መጥፎ ታሪክ ሸፍኖ ማለፍ ሲል፣ የዚህ ሌላው ጫፍ ማጋለጥ የሚል ይሆናል፡፡ አንዱ ጫፍ አርበኝነትን ሲያወድስ የዚህ ሌላው ጫፍ ባንዳነትን በምክንያትነት ይከራከራል፡፡ አሁንም አንዱ ወገን/ጎራ የነበረውን ማስቀጠል/መጠበቅ በሚል ሲከራከር፣ ሌላው ወገን/ጎራ ለውጥን በመሻት ይከራከራል፡፡ በአጠቃላይ በአንድ በኩል ያለፈውን መልካምና የመልካም ምግባርና ተግባር መገለጫ የማድረግ ዝንባሌ፣ በሌላ በኩል በተቃራኒው ያለፈውን ሁሉ የመጥፎ ምግባርና ተግባር መግለጫ የማድረግ ዝንባሌ እንዳለ ሆኖ፣ የአገራችንና ሕዝቦቿ ታሪክ የመልካምና ጥሩ ትሩፋት መገለጫዎችን  የማጉላትና ውድቀትንና መጥፎ ድርጊቶችን የመካድ ዝንባሌ ያሳያል ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ ጫፍ ከረገጡ አመለካከቶችና ክርክሮች በመለስ የሚታሰብ አመለካከትና እውነታ ሊኖር አይችልምን? የሁለቱም ጫፍ ረገጥ ምግባርና ተግባር መገለጫ መሆን ይቻላልን? እንደ አገርና ሕዝብ ፃድቅና ኃጥያተኛ ሁለቱንም መሆን ይቻላልን?

እኔ የታሪክም ሆነ የሃይማኖት ተማሪ አይደለሁም፡፡ ስለፖለቲካዊ ታሪክም ሆነ ስለክርስትና ሃይማኖት ታሪክ ያለኝ ዕውቀት ከንባብና ከልምድ፣ በምግባርና ተግባር ከሚገለጥ ማንነት የተገኘ ነው፡፡ ታሪክን በክርስትና ሃይማኖት መነጽር ሲባል ስለታሪክ ትርክት ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን መማር ይቻላል? የሚለውን ሐሳብ የሚያስገንዘብ ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ሰነድ በሆነው በመጻሕፍ ቅዱስ ከተገለጡ ታሪኮች (Biblical History) የምንማራቸው ምሳሌዎች መኖራቸውን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች ለአገራዊና ብሔራዊ ምክክር የሚያበረክቱት አስምህሮት ይኖራል፡፡

እስከ 20ኛው አጋማሽ ምዕት ዓመት ካቶሊካውያን ብቻ መልካምነት ፕሮቴስታንቶች ግን በተቃራኒው የሚፈረጁበት ጊዜ እንደነበር፣ በሌላ በኩል በሁለቱም በኩል በተመሳሳይ መጥፎ ምግባርና ተግባር የሚታወቁ እንደነበሩ ለሁለቱም ወገኖች ታሪክ እንደ ፕሮፓንዳ ይቆጠር እንደነበር ይነገራል፡፡ ከዚህ ሌላ በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ (Biblical History) በአመዛኙ ከአይሁዳውያን ቀደምት የምግባርና ተግባር ታሪኮች ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ እነዚህም ሁለቱንም ባህሪያት ይዘው እንደነበርም ተተርኳል፡፡

ለምሳሌ እነ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ዳዊትና ሰሎሞን በመጽሐፍ ቅዱስ ይወደሱ የነበረው ውድቀታቸውን በመጨመር እንደነበር፣ ይኸውም ከእግዚአብሔር መንገድ የወጡና ከኃጥያተኝነት የሚያስፈረጃቸው እንደነበር፣ የአይሁድ አዋቂዎች የድሆችን ችግር ችላ በማለት ጦርነት ያደርጉ እንደነበር፣ ሕዝቡም አማኝ እንዳልነበርና ጣኦት አምላኪ እንደነበር ተጽፏል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት ጎልያድን ድል ያደረገ ታላቅ ጦረኛ እንደነበር፣ ንጉሥ ሰሎሞን መቅደስ (ቴምፕል) የሠራ ታላቅ ጥበበኛ እንደነበር የተወደሱ ቢሆኑም፣ አይሁዳውያን ንጉሥ እንዳይኖራቸው ማስጠንቀቂያ ተጽፏል፡፡ ለዚህም የንጉሥ ሳኦል፣ የዳግማዊ ንጉሥ ዳዊት መጥፎ ምግባርና ተግባራት የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመጥፎ ምግባርና ተግባር የዳዊት ተወላጆችም የባሱ እንደነበሩ ራሳቸውና ወዳጆቻቸው የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ ሕዝቡን ይበዘብዙና የማያሸንፏቸውን ጦርነቶች እያካሄዱ እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ያስረዳል፡፡

በአንፃሩም በመሀላቸው ለተራቡ፣ ለታረዙ፣ ለባለዕዳው ደሃ የወገኑና አራጣ አበዳሪዎችን፣ መሬት ነጣቂዎችን፣ ንጉሦችንና ሀብታሞችን በመገዳደር ለኅብረተሰብ ተሃድሶ ስለቆሙ ሰዎችም የምንማርበት ነው፡፡ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች የሚያስተምሩን የአገርና ሕዝብ ታሪክ ስኬቶችን ኅብረተሰብና ተቋማቱ ሁልጊዜ ሊሳሳቱና ለውድቀት ሊዳረጉ የሚችሉ መሆናቸውን፣ አይሁዳውያን ስለራሳቸው ጥሩ እንዲሰማቸው ለማድረግ ሳይሆን የቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው የሰመረ እንዲሆን ማስገንዘብን ወይም መገንዘብን ነው፡፡

እነዚያ ንጉሦች እንኳን በኃጥያተኝነት የተፈረጁበትን ታሪክ ስናስታውስ ለምንድነው የአገራችን የቀድሞ መሪዎች ውድቀት እንደነበረባቸው ሲታሰብ የሚያስገርመን ወይም የምንገረመው? የአይሁድ መሪዎች የሞኝነትና ያልተገባ ጦርነት በማካሄዳቸው የተወገዙ ከሆነ፣ ዛሬ በዓለማችን ዙሪያ የተካሄዱትንና የሚካሄዱትን ጦርነቶች ጥያቄ ውስጥ የማናስገባበት ምክንያት ሊኖር አይችልም? የተዋጋ ወታደር ጀግንነት ሲወደስ፣ የመሪዎች ብቃት ሊወደስ ስህተት ሊነቀፍ አይገባምን? የመሪዎችስ አሻራ ሊታወስ የሚገባው በማወደስ ወይስ በማዋደቅ? ሊሆን የሚገባው እነሱንም ሆነ እኛን ማወደስ ወይም ማዋደቅ ሳይሆን፣ ሙሉ ዙሪያ ገብና አስቸጋሪ ሰዋዊ ፍጡር (Full, Rounded and Difficult Human Beings) መሆናችንን ነው፡፡

በጤናማ አገርና ኅብረተሰብ ውስጥ በፖለቲካ መሪዎች፣ በልሂቃንና በተቺዎች መካከል ሚዛን የጠበቀ መስተጋብር ይኖራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ አለበለዚያ የፖለቲከኞች ኃይል ባለበት አምባገንነት ይሰፍናል፡፡ ሁሉን እናውቃለን ባይ ልሂቃን ባየሉበት ንፅረተ ዓለማዊና ጭልታዊ አስተሳሰብ (Elitism) ይገናል፡፡ እናውቃለን ባይ ተችዎች በበዙበት የበሬ ወለድ ውዥንብር (Fakeness Chaos) ይፈጠራል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያስገነዝበን ዴሞክራሲ የማይሠራበትን ነው (How democracy should not/does not work)፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው እግዚአብሔር አይሁዳውያንን በንስሐ እንዲመለሱና  በእርሱ መንገድ እንዲመሩ ጥሪ እንዳደረገላቸው፣ ነገር ግን እነሱ ትክክል ሊሆኑ እንዳልቻሉ፣ በሌላ በኩል ግን እግዚአብሔር ጨርሶ እንዳልጣላቸው፣ እያንዳንዱ ትውልድ ግን ጥረቱን እንዲያደርግ ያስተምራል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ትክክል ልንሆን እንዳልቻልንና ትውልድ ሁሉ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ነው ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ልንማር የሚገባን፡፡

ስለታሪክ ማውሳት አላስፈላጊ ክርክርን መቀስቀስ ተደርጎ የሚወሰድበት አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የወደፊት ዕጣ ፈንታን ማሰብ ይልቃል ቢባልም፣ የወደፊቱን ከምን ተነስቶ ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም የአሁኑም ሆነ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በታሪክ መልካምም ሆነ መጥፎ ክስተቶችን ያዘለ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆንም አገራዊ ብሔራዊ ምክክር ታሪካችንም የወደፊት ዕጣ ፈንታችንም በእኩል ሊጤኑ የሚገቡ ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት ታሪካዊ ተምሳሌቶች የሚያስተምሩን ታሪክን እንዴት መረዳት እንዳለብን ነው፡፡ 

ታሪክ አገርና ሕዝብ ያሳኳቸውን ታላላቅ ክንዋኔዎችን የሚያስተምር ሲሆን በአንፃሩ የነገሥታትን፣ የመሪዎችን፣ የአስተዳዳሪዎችን፣ የፍትሕ አካላትን፣ የደኅንነት አካላትን አምባገነንነት፣ ሙሰኝነት፣ ግዴለሽነትና ደንታ ቢስነት (Arrogance, Corruption, Blindness to Social Issues)፣ እንዲሁም ሕዝብን ወደ ተሳሳተ መንገድ የሚመሩና ለጥፋት የሚዳርጉ ትንቢቶችንና ተግባራትንና ያልተሳኩላቸውን ውድቀቶች ባለመሸፈን ሲሆን ነው፡፡ ያልተሳኩ ውድቀቶችን ማስገንዘብ ለተመሳሳይ ውድቀት የሚዳርጉ ምግባርና ተግባር እንዳንፈጽምና ከስህተት አለመማር ክስረት እንዳይሆንብን ለመገንዘብ ነው፡፡ በምንም ምክንያት ግን የአገርና የሕዝብ ታሪክ በብሔርተኝነት ትርክትና ፖለቲካ መበላሸት የለበትም፡፡

ይህ ማለትም ያልነበረውን የብሔር ጥላቻና ፍራቻ አለ ብሎ የሚሰነዘር ሐሳቦችን መከላከል ይገባል ማለት ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሌላው ታላቅ አስተምህሮ ታሪክን ወይም ታሪካችንን እንዳንፈራ ነው፡፡ አምባገነንና ትምክህተኛ ከመሆን ይልቅ፣ ያለፈን ስህተት እንዳንደግም ነው የሚያስተምረን ኢየሱሰ ክርስቶስ ሴትዮዋን ሂጂ ከኃጥያትሽ ድነሻል፣ ዳግመኛ ኃጥያት እንዳትሠሪ እንዳላት ሁሉ ማለት ነው፡፡ ካለፈው መማር ሲባል ትምህርቱ ከስኬት ከሆነ ያንኑ አጠንክሮ ለመቀጠል፣ ከጥፋትም ከሆነ ያንን መሰል ስህተት ላለመድግም፣ ከችግርም ከሆነ መፍትሔ ለመፈለግ፣ ከአሻራም ከሆነ የራስን መልካም አሻራ ትቶ ለማለፍ ነው፡፡ እኛ ለምን እንዲህ አናስብም? በየትኛውም አገር አንድ የመንግሥት ሥርዓት በሌላ ሲተካ ወይም የሥራ ኃላፈዎች በሌሎች ሲተኩ፣ ተተኪዎች ያለፉት ያሳኩትን፣ ያለሙት፣ የተውትን መልካም አሻራ ወይም በአንፃሩ ያልተሳካላቸውን፣ ያጠፉትን፣ ትተው ያለፉትን መጥፎ አሻራ ለይቶ የመማር ምግባርና ተግባር ሲያሳዩ አይታይም፡፡ ይልቁንም በመማር ፈንታ ብይን መስጠት፣ ማጣጣል፣ ማጠልሸትና ማፍረስ ይቀናቸዋል፡፡

ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ችግሮችን ብቻ ማውሳትና በመፍትሔዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ያለፈውን ምክንያት ማድረግ ይቀናቸዋል፣ ነግ በእኔን አያስቡም፡፡ ከስኬትና ከጥፋት አይማሩም፣ አያስተምሩም፡፡ በመሆኑም መልካም አጋጣሚዎችን ያከሽፋሉ፣ ከስኬትና ከጥፋት ባለመማርና ባለማስተር ጥፋቶች ይደገማሉ፣ ችግር ችግርን እንዲወልድ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያም እንዱ ከሌላው የመማር ፍላጎትና ዕድል ሲፈጠርበት አልታየም፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትና አስተዳደር ከአፄ ምኒልክ መንግሥትና አስተዳደር ሊማር የሚችልባቸው ጉዳዮች፣ ለምሳሌ በመንግሥትና ሕዝብ መካከል የነበረውን ግንኙነትና የግንኙነቱን ርቀትና ቅርበት በሚመለከት ሊሆን ይችል ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ ለሕዝብ ቅርብ የነበሩና እረኛ እንኳ ሳይቀር የሚለውን ለመስማትና ለማጤን ጥረት የሚያደርጉ ነበርና ነው፡፡ የደርግ/ኢሕድሪ መንግሥትና አስተዳደር ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትና አስተዳደር ሊማር ይችል የነበረው (የዘውድ አገዛዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠላ የመጣበት ወቅት የነበረ ቢሆንም)፣ የዘውዱን አገዛዝ ያህል ተከባሪነትና ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል መሆኑን በሆነ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትና አስተዳደር ደግሞ ከደርግ/ኢሕድሪ መንግሥትና አስተዳደር ሊማር በተገባው ነበር፡፡ ከሚያስኙ በርካታ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው በወቅቱ ስለነበረው የፀና የአንድ አገርና ሕዝብ የአንድነት፣ እምነትና ሥነ ልቦና በሆነ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ስላሳካናቸውም ሆነ ስላጠፋናቸው ድርጊቶች አልተማርንም፣ አላስተማርንም፡፡ ስለዚህ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ምን ልንማርና ልናስተምር ይገባል የሚለውን ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሥልጣን ላይ ያለው የሽግግርና የለውጥ መንግሥትና አስተዳደርም ሊማር የሚገባው ጉዳይ፣ የኢሕአዴግ መንግሥትና አስተዳደር የሄደባቸውን የጥፋትና ውድቀት መንገዶችን በመገንዘብ በሌላ መልክ ወይም በነበረው መልክ እንዳይቀጥሉ ማድረግን፣ መልካም አሳቢዎች የሚሏቸውን ሥጋቶች በማስወገድና ነግ በእኔ ባይነትን በማሰብ፣ ወደ ሥልጣን መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም እንዳለ በማጤን አገራዊና ሕዝባዊ እውነታን አጥብቆ መያዝን ይሆናል፡፡

ያለፈ ታሪክን ማወቅና መረዳት በአጉል ትርክት ሳይሆን ለተሻለ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲያበቃን መሆን አለበት እንጂ፣ የቂም ብይንን ለማወራረድ መሆን የለበትም፡፡ የአገራዊና ብሔራዊ ምክክሩ ታሪክን ከተጠቃቀሱት ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ አስተምህሮዎች አኳያ በማሰብ ጭምር መሆን አለበት እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው abgirma323@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...