Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ተሳትፎና ለፍፃሜ ያለመድረስ አባዜ

በዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ተሳትፎና ለፍፃሜ ያለመድረስ አባዜ

ቀን:

በዓለም ዋንጫ ጨዋታ ለመካፈል አገሮች በየአኅጉራቸው በሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታ ተለይተው ዕድል ያገኛሉ፡፡ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ፣ በሥሩ ለሚተዳደሩ ፌዴሬሽኖች የአገራቸውን የእግር ኳስ ዕድገት ተመልክቶ በዓለም ዋንጫ ላይ መካፈል የሚችሉትን ቁጥር መጠን እያሳደገ ይሄዳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1930 ላይ በጀመረው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ተሳታፊ የተለዩት አኅጉራት በፊፋ ጋባዥነት ነበር፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ በማጣሪያ ያለፉ አገሮች ተሳትፎ ማድረግ ጀመሩ፡፡

ከዚያ ጊዜ አንስቶ በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ ለመካፈል ፊፋ ለአባል አገሮች የሚሰጠው ኮታ መሠረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ለአባል አኅጉራት የሚሰጠው የኮታ መጠን በዓለም ዋንጫው ላይ መካፈል የሚችሉትን ብሔራዊ ቡድኖች ከግምት የከተተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከ1934 እስከ 1978 ላይ 16 የነበሩትን ብሔራዊ ቡድኖች፣ ከ1982 እስከ 1994 ወቅት ቁጥሩ 24 ሲደርስ ከ1998 እስካሁን ደግሞ 32 ብሔራዊ ቡድኖች እንዲካፈሉ ተደርጓል፡፡

በፊፋ ውስጥ የአፍሪካ 54 አገሮች በአባልነት የሚገኙ ሲሆን፣ ከ1998 ዓለም ዋንጫ በኋላ አምስት ብሔራዊ ቡድኖች በማጣሪያ አልፈው እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም አፍሪካ በፊፋ ላይ 54 ድምፅ የያዘች አኅጉር በመሆኗ፣ በዓለም ዋንጫ ለመካፈል የተሰጣት ኮታ አነስተኛ ነው የሚል ክርክር ሲነሳ ከርሟል፡፡ በዚህም መሠረት በ2026 በአሜሪካ፣ በካናዳና በሚክሲኮ በሚስተናገደው የዓለም ዋንጫ አፍሪካ በዘጠኝ ብሔራዊ ቡድኖች እንደምትከፈል ተቀምጧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አፍሪካ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ

ግብፅ በ1934ቱ የዓለም ዋንጫ የተሳተፈች የመጀመሪያ አፍሪካ አገር ነች፡፡ በወቅቱም አብዱራሃማን ፈዋዚ ግብፅ ከሐንጋሪ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተጫዋች ነው፡፡ በ1978 ዓለም ዋንጫ ቱኒዚያ ሚክሲኮን 3 ለ 1 ያሸነፈች የመጀሪያዋ አፍሪካ አገር ያደርጋታል፡፡ በሒደት የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ አልጄሪያ በ1982 በስፔን እንዲሁም በ1986 በሜክሲኮ ዓለም ዋንጫዎች ላይ መካፈል የቻለች አገር መሆን ችላለች፡፡

 በ1998 ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት የአፍሪካ አገሮች የመካፈል ዕድል አገኙ፡፡ በጊዜውም ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሮንና ናይጄሪያ በዓለም ዋንጫው መድረክ መካፈል የቻሉ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡

በሒደት የአፍሪካ አገሮች ዓለም ዋንጫን ከመካፈል በዘለለ ከምድባቸው እያለፉና በእግር ኳሱ ገናና ስም ያላቸው ብሔራዊ ቡድኖች መርታት የቻሉበት ጊዜም ነበር፡፡ በ1990 ዓለም ዋንጫ ካሜሮን አርጀንቲናን 1 ለ 0 መርታት የቻለች የመጀመሪያው አፍሪካዊት አገር ሆናለች፡፡ በዚያው ዓለም ዋንጫ ካሜሮን ሩብ ፍፃሜ በመድረስ ለአፍሪካ ሌላ ታሪክ ማጻፍ ችላለች፡፡

የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ የቀጠለው ካሜሮን፣ በ1994 የአሜሪካ ዓለም ዋንጫ ላይ ተጫዋቿ ሮጀር ሚላ በ42 ዓመቱ ግብ ማስቆጠር የቻለ ተጫዋች በመሆን በታሪክ ስሙ የሠፈረ ሲሆን፣ በዘንድሮ የኳታር ዓለም ዋንጫ ላይ ካሜሮን ከስዊዘርላንድ ባደረገችው የምድብ ጨዋታ አስቀድሞ በፊፋ ሽልማት ሊበረከትለት ችሏል፡፡

አፍሪካ በዓለም ዋንጫ መድረክ መካፈል ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ናይጄሪያ (1994፣ 1998፣ 2002፣ 2010፣ 2014 እና 2018)፣ ቱኒዝያ 1978፣ 1998፣ 2002፣ 2006፣ 2018 እና 2022) ስድስት ጊዜ መካፈል ሲችሉ፣ ጋና (2006፣ 2010፣ 2014 እና 2022) እንዲሁም አልጄሪያ (1982፣ 1986፣ 2010 እና 2014) በመካፈል ቀዳሚ የአፍሪካ አገሮች መሆን ችለዋል፡፡

የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ ስኬታማ ጉዞ

የ2010 የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ሲደረግ ደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅ ሆናለች። ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ አይቮሪኮስት፣ ካሜሮንና ጋና ከአፍሪካ ማለፍ የቻሉ ብሔራዊ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ሆኖም ከጋና ውጪ ከምድብ ጨዋታዎች ማለፍ አልቻሉም ነበር፡፡

በአንፃሩ ጋና ለሁለተኛ ጊዜ ከፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ ድልድል አልፋ 16ቱ ውስጥ ከገባች በኋላ፣ በተጨማሪ ሰዓት አሜሪካን 2 – 1 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለች ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር መሆን ችላለች፡፡

በጨዋታው ከጋና ተጫዋቾች የተመታው ኳስ በዑራጋዊው ተጫዋች ሉዊስ ሱዋሬዝ በእጅ በመመለሱ ‹‹ኳሷ ከመስመር አልፋለች? አላለፈችም?›› የሚል ክርክር ቢነሳም፣ የፍፁም ቅጣት ምት ብቻ ተሰጥቶ ታለፈ፡፡ ተከታዩን የቅጣት ምት የጋናው ተጫዋች አሳሞአ ጂያን ወደ ግብ ቢለጋውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ጋና የሩብ ፍፃሜዋን ብታሸንፍ ኖሮ ለዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በማለፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር ትሆን ነበር። በ2010 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከተሳተፉት 32 አገሮች መካከል ፊፋ ጋናን ሰባተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧት ነበር፡፡

በሌላ በኩል በ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ  ግብፅ፣ ሞሮኮና ቱኒዝያ  በመጀመሪያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል። ናይጄሪያም ከክሮሺያ ጋር ባደረገችው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ 2-1 ተሸንፋለች።

ሌላዋ የአፍሪካ ተወካይ ሴኔጋል ከፖላንድ ጋር ባደረገችው የመክፈቻ ጨዋታ 2-1 አሸንፋ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከጃፓን ጋር አቻ ስትጨርስ፣ ከኮሎምቢያ ጋር ባደረገችው የመጨረሻ ግጥሚያ አቻ መውጣት ይታወሳል።

አፍሪካ በኳታር ዓለም ዋንጫ

በኳታር ዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ ካሜሮን፣ ቱኒዝያ፣ ጋና፣ ሞሮኮና ሴኔጋል እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በራሳቸው አሠልጣኞች እየተመሩ ይገኛሉ፡፡ ሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ሞሮኮና ቱኒዝያ ግን ነጥብ ተጋርተዋል። ምንም እንኳ ገና ቀሪ የምድብ ጨዋታዎች ቢቀሩም ቀድሞ አግኝተው ከነበረው ግምት አንፃር በእንቅስቃሴ ረገድ ተስፋ የተጣለባቸው ጥቂት ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡ አስደናቂውን ክስተቶች እያስመለከተ የሚገኘው የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ አርጀንቲናን በመርታት እንዲሁም ጃፓን ጀርመንን በማሸነፍ፣ በውድድሩ ከወዲሁ ትኩረትን ስበዋል፡፡

በእግር ኳስ ክስተት የሚሆኑ ቡድኖች ባይታጡም፣ በርካታ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች በተለያዩ አውሮፓ አገር በሚገኙ ክለቦች ውስጥ እያደረጉት ካለው  እንቅስቃሴ አኳያ፣ በዘንድሮ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች በውድድሩ ላይ አንዳች ነገር ያሳያሉ የሚል ግምት አግኝተው ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር በርካታ የአፍሪካ ተወላጆች በስደት ምክንያት ኑሯቸውን በቀለሱበት የተለያዩ ዓለም አገሮችን ወክለው መጫወት እየተለመደ በመሆኑ፣ አፍሪካ በእግር ኳሱ ያላትን አቅም ማረጋገጫ ሆኗል፡፡

ሆኖም የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከምድባቸው ማለፍ ሲሳናቸው የሚስተዋል ሲሆን፣ በተለይ በጨዋታ ላይ በሚሠሩት ጥቃቅን ስህተቶች ከውድድር ወጪ መሆኑ የተለመደ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ ትችቶችን ሲያስተናግዱ ይስተዋላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ መላምቶች በባለሙያዎች ቢቀመጥም፣ በአፍሪካ እግር ኳስ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ማደግ አለመቻሉ ይጠቀሳል፡፡

ለሌሎች ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸው ተጫዋቾች በትውልድ አገራቸው ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ወደ ተለያዩ የዓለም አገሮች ተሰደው፣ አሊያም የተሻለ ሕይወት ለመመሥረት ብለው፣ ኑሯቸውን በተለያዩ ዓለም አገሮች ያደረጉ በርካታ የዘር ግንዳቸው አፍሪካ የሆኑ ተጫዋቾች ይገኛሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ የአውሮፓና ሌሎች አኅጉሮች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የአፍሪካ የዘር ግንድ ያላቸውን ተጫዋቾች መመልከት እየተለመደ ነው፡፡

በተለይ የ2018 የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ባነሳቸው ፈረንሣይ ውስጥ ቁልፍ  የሆኑ ተጫዋች ተካተው ነበር፡፡ በጊዜው ፈረንሣይ ሳትሆን የአፍሪካ ቡድን ነው ዋንጫውን ያነሳው የሚል አስተያየት ሲሰነዘር ነበር፡፡ በአውሮፓ በተለያዩ ሊጎች ላይ ስማቸው የገነነ፣ የዘር ግንዳቸው የአፍሪካ የሆኑ ተጫዋቾች አሁንም ይገኛሉ፡፡

በዘንድሮ የኳታር ዓለም ዋንጫ እንኳን ከ130 በላይ ተጫዋቾች የትውልድ አገራቸውን ትተው ሌሎች አገሮችን ወክለው በውድድሩ ላይ መቅረባቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጥቂቶቹ የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ አስቀድሞ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ተጠቅሷል፡፡

በዚህም መሠረት በኳታር እየተካፈሉ ከሚገኙት ውስጥ፣ 14 ብሔራዊ ቡድኖች የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪካ የሆኑ ተጫዋቾችን በስብስባቸው ውስጥ ማካተታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ የትውልድ አገራቸውንም መርጠው የሚጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አፍሪካ በእግር ኳስ ያላትን ዕምቅ አቅም ባለመጠቀምና የእግር ኳስ ዕድገቷ እየተሻሻለ አለመሄዱ ለተጫዋቾቹ ወደ ሌላ አገር መፍለስ ምክንያት መሆኑ በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡

በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫው የሚያደርጉት ጉዞ በጊዜው እንዲቀጭ መንስዔ ተደርጎ ይነሳል፡፡ በኳታር ዓለም ዋንጫ አጀማመራቸው እምብዛም ያልሆኑት የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች፣ ‹‹በቀጣይ የምድብ ጨዋታዎች ምን ያሳያሉ?›› የሚለውና ‹‹በዘንድሮ ዓለም ዋንጫ እስከ የት ይጓዛሉ?›› የሚለው ጥያቄ አብዛኞቹ በጉጉት የሚጠብቁት ጥያቄ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...