የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የቴሌቪዥን ባለቤትነት ፈቃድና ዓመታዊ ዕድሳት ክፍያ አለመክፈል በወንጀል እንዲያስጠይቅ የቀረበን ረቂቅ ሕግ አንቀጽ ውድቅ አደረገ፡፡
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)ን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በረቂቁ ውስጥ የቴሌቪዥን ባለቤትነት ክፍያን በተመለከተ መረጃ እንዲሰበስብ በኮርፖሬሽኑ ኃላፊነት ለተሰጠው አካል መረጃ የማይሰጥ ደንበኛ፣ ከአንድ እስከ ስድስት ወራት እስራት ወይም ከ500 እስከ 5,000 ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡
በረቂቁ ቅጣቱ ተግባራዊ መሆን የሚችለው የድርጊቱን መፈጸም በሚመለከት ኮርፖሬሽኑ ለፌዴራል ፖሊስ ወይም ለክልል ፖሊስ መምርያ በሚያቀርበው የከሳሽነት አቤቱታ መሠረት መሆኑ ተብራርቷል፡፡ እንዲሁም በየአምስት ዓመቱ የቴሌቪዥን የዕድሳት ክፍያ የማይከፍል ግለሰብ በዚሁ አንቀጽ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 20 ላይ የተቀመጠውን የቅጣት ዝርዝር አስመልክተው ሐሳብ የሰጡት የምክር ቤት አባል አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ፣ ድንጋጌው በግልጽ የሕግ ፍልስፍናን የሚለውጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ዘካሪያስ ‹‹የቴሌቪዥን ባቤትነት መክፈል አለብህ ከተባልኩ መክፈል አለብኝ፡፡ ነገር ግን ይህ ኃላፊነት የፍትሐ የብሔር ጉዳይ በመሆኑ ክፍያ ባለመፈጸሜ በየትኛው መለኪያ የወንጀል ቅጣት ሊያመጣብኝ አይገባም፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በመሆኑም ተቋሙ አልከፍልም ያለን አካል በመክሰስ ሊያስከፍል እንደሚገባ፣ ያ ካልሆነ ግን የሕግ ፍልስፍና ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አክለውም ‹‹ያልከፈለ ይቀጣ እንኳ ብለን መስማማት ከቻልን በደብዳቤ የጊዜ ገደብ ተሰጥቶኝ ካልከፈልኩ፣ ከወለድ ጋር ተደምሮ ይህን ያህል ክፈል ብሎ ይመጣል አንጂ በወንጀል ትቀጣለህ ሊለኝ አይችልም፤›› በማለት፣ ምክር ቤቱን አጥብቀው የተከራከሩት አቶ ዘካሪያስ ይህንን ይሁን ብሎ መፍቀድ የሰው መብትና ነፃነት ሊጋፋ የሚችል ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት የሕግ አሠራር የነበረው በድሮ ዘመን እንደነበር፣ በተለይም የፍትሐ ብሔር ሕግን በመተላለፍ ምክንያት የወንጀል ቅጣት ይከተል የነበረበት አሠራር አሁን ፈጽሞ የቀረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በረቂቁ ላይ ጠንካራ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ በረቂቅ አዋጁ የቀረበውን የወንጀል ቅጣት ድንጋጌ ላይ ድምፅ እንዲሰጥ ተደርጎ አንቀጹ በአብላጫ ድምፅ ከረቂቁ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. በፓርላማ ቀርቦ ውይይት ሲደረግበት የቆየው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ እንዲፀድቅ በምክር ቤቱ በቀረበበት ወቅት ከአባላቱ በርካታ ጥያቄ የተነሳበት ሲሆን፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ አባላት ተቋሙ ከተመሠረተበት ዕድሜ አንፃር እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ከሚጠበቅበት በታች መሆናቸውንና አገሪቱን ወካይ የሆኑ ፕሮግራሞች እንደማያቀርብ በመጥቀስ፣ የቴሌቪዥን ክፍያው ለኢቢሲ ከሚከፈል ለገንዘብ ሚኒስቴር ገቢ ይሁን የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በርካታ ውይይት ካካሄደ በኋላ በስብሰባው ከተገኙት 240 አባላት ውስጥ 44 አባላት ሲቃወሙት፣ በ24 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡