በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ መቃኘት ሲኖርበት፣ አስፈጻሚ አካል እንደመሆኑ መጠን በሕግ አውጭው ፓርላማ ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡ የፓርላማ አባላትም ሥራቸውን የሚያከናውኑት ለሕገ መንግሥቱ፣ ለመረጣቸው ሕዝብና ለህሊናቸው ተገዥ በመሆን ስለሆነ፣ ያለ ምንም ይሉኝታ ወይም ፍራቻ አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል መሞገት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፓርላማው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ካልቻለ ግን ከማኅተም መርገጫነት (Rubber Stamp) የዘለለ ሚና ስለማይኖረው፣ እያንዳንዱ ውሳኔውም ሆነ የሚያፀድቀው ሕግ የአገርንና የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ማድረግ አይችልም፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ጡንቻው እየፈረጠመ ፓርላማውን የሚገዳደር ሲሆን፣ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ስለአገር ህልውና መግባባት አይቻልም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በሕግ የተገደበ ሆኖ ሹማምንቱም ከሕግ በታች መሆን ካልቻሉ፣ ከዴሞክራሲ ይልቅ አምባገነንነት ይንሰራፋል፡፡ ተጠያቂነት እየጠፋ ማናለብኝነት ይነግሣል፡፡
በኢትዮጵያ የመንግሥታት ታሪክ ለአገር የሚያስቡና የሚለፉ ዜጎች በታሪክ የሚታወሱትን ያህል፣ በአስመሳይነትና በአድርባይነት መንግሥትን ከጥፋት ወደ ጥፋት ሲነዱ የኖሩም አይዘነጉም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዘመነ ኢሕአዴግም ሆነ በዘመነ ብልፅግና የእስስት ባህሪ ተላብሰው፣ መንግሥት የቅን ዜጎችን ምክረ ሐሳብ እንዳይቀበል ሸፍጥ የሚፈጽሙ በብዛት ይታወቃሉ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጭፍን ድጋፍ ቀልባቸውን ስተው ሒሳዊ ተቃውሞ እንዳያዳምጡ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ከአንዱ ወደ ሌላው ጥፋት እየዘለሉ ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ለማመን የሚከብዱ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፡፡ እነዚህ ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በስተቀር ለአገር ደንታ ስለሌላቸው፣ ሕዝብና መንግሥት ከሚቀራረቡ ይልቅ እሳትና ጭድ ሆነው እንዲቀጥሉ ነው ፍላጎታቸው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡ ሰዎች ግን ከትናንት ስህተቶች ተምረው አገርን በተባበረ ጥረት ከፍ ካለው ማማ ማድረስ ሲገባቸው፣ የእንዲህ ዓይነቶቹ እስስቶች ሰለባ ሆነው ለቅን ዜጎች ምክረ ሐሳቦች ጀርባቸውን መስጠታቸው ያስቆጫል፡፡ ከጊዜያዊ የውሸት ከበሮ ደላቂዎችና አስመሳዮች ይልቅ፣ ጠንካራ ሐሳብ ያላቸውን ሀቀኞች ማዳመጥ ለአገር ይጠቅም ነበር፡፡
በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን ባገኙት የመገናኛ ዘዴ ለአገራቸው የሚበጀውን ሲያመላክቱ፣ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትም በአማካሪዎቹ አማካይነት አዋጭ ምክረ ሐሳቦችን በጥሞና የማዳመጥና ምላሽ የመስጠት ባህል ማዳበር ይጠበቅበታል፡፡ እርግጥ ነው ሁሉንም ነገር ማዳመጥ ወይም መከታተል ተገቢ ባይሆንም፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚጠቅሙና የወትሮ ሥራን በተሻለ መንገድ ለማቀላጠፍ ለሚያግዙ ምክረ ሐሳቦች ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በግንባታ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በከተማ ፕላንና አስተዳደር፣ በውኃ ሀብትና አጠቃቀም፣ በመሬት፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት አከባበር፣ በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮችና በሌሎች በርካታ መስኮች ከበቂ በላይ ዕውቀት የሰነቁ ወገኖች የተሻለ ሐሳብ ሲያቀርቡ ማዳመጥና አብሮ ለመሥራት ዕድል መስጠት ተገቢ ነው፡፡ በአጋጣሚ የተገኘን ሥልጣን የአዋቂነት ማሳያ ለማድረግ አጉል መውተርተር ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ መንግሥት ሊያዳምጠን ይገባዋል የሚሉ ዕውቀትና ክህሎት የሰነቁ ወገኖችን ችላ ብሎ፣ በተለመደው ጎዳና መንጎድ ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ የአገር ጉዳይ ሁሌም ምክክርና ትብብር ነው የሚያስፈልገው፡፡
መንግሥት ሥራውን በጥራትና በቅቡልነት ለማካሄድ ከሚያስችሉት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፣ ብቁ አመራሮችና የተመሰከረላቸው ባለሙያዎችን በተቋማቱ ውስጥ ማሰማራት ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የሙያ መስኮች ብቁ የሆኑ አማካሪዎችን መጠቀሙም እንዲሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ለመመደብ መልካም ጅምሮች ቢታዩም፣ ብዙዎቹ ተቋማት የሚመሩት ግን ብቃት በሚጎድላቸው ሰዎች እንደሆነ ማንም አይክድም፡፡ የፓርቲ አባልነትና የብሔር ተዋጽኦ ዋናው መሥፈርት በሆነበት አሠራር፣ ለብቃት የሚሰጠው ቦታ አናሳ በመሆኑ ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ በሕግ የተሰጠ ሥልጣንን ተጠቅሞ ተገቢውን አመራር ከመስጠት ይልቅ፣ ዘወትር የበላይ ኃላፊን ይሁንታ መጠበቅ ወይም በራስ መተማመን ማጣት ይስተዋላል፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት መዋቅሮችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጣቸው ሲፈተሽ፣ ከኦዲት ክዋኔ ዝርክርክነት እስከ መንግሥት ሀብት ብክነት ድረስ በርካታ ሪፖርቶች ይቀርብባቸዋል፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርትም ራሳቸውን ቀባብተው መቅረብ የሚፈልጉም ተስተውለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ የሚረዱ ሐሳቦች ሲቀርቡ ግን አዳማጭ የለም፡፡ መደማመጥ ከሌለ እንዴት አገር ማሳደግ እንደሚቻል ግራ ያጋባል፡፡
በመንግሥት ንብረት አያያዝ፣ ግዥ፣ ኮንትራት፣ ጨረታና መሰል ሥራዎች ውስጥ የሚስተዋለው መዝረክረክና ጥፋት በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በርካታ ሪፖርቶች መቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ በሪፖርቶቹ ድምዳሜ መሠረት ብዙዎቹ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ሕጉን ተከትለው መሥራት እንደማይፈልጉ ነው የሚነገረው፡፡ ይህ በቀላሉ የሚያሳየው ዝርፊያ ለማከናወን ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ነው፡፡ የግዥም ሆነ የንብረት አያያዝ ሕግ ይከበር ሲባል በየዓመቱ መሻሻል ካልታየ፣ ተቋማቱን የዝርፊያ ማዕድ ለማድረግ የተደራጀ ኃይል እንዳለ ነው የሚያመላክተው፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ተሿሚም ሆነ የሕዝብ ተመራጭ ሊታገለው የሚገባው እንዲህ ዓይነቱ ውንብድና በግላጭ ሲከናወን፣ ስለሕግ የበላይነት ለመነጋገር የሚያስችል አንድም ዓይነት ፈቃደኝነት እንደሌለ ነው የሚታሰበው፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ፍላጎት የሌላቸው ወይም ብቃት አልባዎች ደግሞ፣ የተገልጋዩን ሕዝብ ፍላጎት ያገናዘበ ደንብ ወይም መመርያ እንዲወጣ የበላይን ከማሳሰብ ይልቅ ሕጉ አይፈቅድም በማለት ሥራን መግደል ልማድ አድርገውታል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ መረን የለቀቀ ድርጊት መፍትሔ ይዘው የሚቀርቡ ወገኖች ግን አዳማጭ የላቸውም፡፡
ኢትዮጵያ ከቀውስ ወደ ቀውስ የምትንደረደረው አገራቸውን በነፃ ጭምር ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ወገኖች እየተገፉ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በነፃ ከማገልገል አልፈው ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ሌሎች ጠቃሚ ግብዓቶችን ጭምር ሰውተው እንርዳ ሲሉ ፈላጊ የላቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትና ትራፊክ ማኔጅመንት፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በውኃ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች አገራቸውን ለማገዝ በዚህ ጋዜጣ ጭምር ድምፃቸውን ያሰሙ የዕውቀትና የክህሎት ባለቤቶች ማንም አልፈለጋቸውም፡፡ ብዙዎቹ ገፍተው በየተቋማቱ በር እያንኳኩ ቢሄዱም የተሿሚዎችን ሥልጣን የሚጋፉ ይመስል ፊት ተነስተዋል፡፡ አሁንም በመደበኛውም ሆነ በዲጂታል ሚዲያ ለአገር የሚጠቅሙ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ወገኖች ፈላጊ ያላቸው አይመስሉም፡፡ በራሳቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሳይቀር ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ የሚመጥኑ ሙያዊ ሐሳቦች የሚሰነዝሩ ሰዎች ቢኖሩም፣ ለእነሱም ትኩረት መስጠት የተፈለገ አይመስልም፡፡ መንግሥት ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን ቢያዳምጥ ሕዝብና አገር ይጠቀማሉ!