በኢሚግሬሸንና ዜግነት አገልግሎት አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማንሳት፣ ክፍያ የፈጸሙ ተገልጋዮች ሁሉ በአስቸኳይ እንዲያገኙ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ቅድመ ሁኔታዎቹ ሲነሱ በአሁኑ ጊዜ ተገልጋዮች በአስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው የሕክምና ደብዳቤ፣ ነፃ የትምህርት ዕድል ማስረጃና የመሳሰሉትን ማቅረብ አይጠበቅባቸውም፡፡ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው የአገልግሎት ክፍያ ተመን ላይ ፓስፖርት በአንድና በአምስት ቀናት ውስጥ በአስቸኳይ ለማግኘት የተቀመጠውን ክፍያ ‹‹መክፈል የቻለ ሁሉ››፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆን የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ግንበቶ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎችን ለማንሳት ዝግጅት እየተደረገ ያለው፣ የአስቸኳይ ፓስፖርት አሰጣጡ ‹‹ከሙስናና ከብልሹ አሠራር ጋር የተያያዘ›› በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹አስቸኳይ ፓስፖርት ከውስጥ ሠራተኞች ተነጋግረን እናስጨርሳለን የሚሉ ደላሎች አሉ፤›› ያሉት አቶ ታምሩ፣ ከብልሹ አሠራሮች ጋር በተያያዘ፣ ‹‹በዓመት ግፋ ቢል ከ50 ሰዎች በላይ እያባረርን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ተቋሙ ከአስቸኳይ ፓስፖርት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ‹‹ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት›› ያስችለኛል ብሎ ያሰበው መፍትሔ፣ አገልግሎቱን ለማግኘት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማንሳት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው አሠራር ፓስፖርት በአስቸኳይ ለማግኘት ከሚያስችሉ ማስረጃዎች መካከል ወደ ውጭ ሄደው መታከም እንዳለባቸው የሚገልጽ የሕክምና ደብዳቤ፣ ለሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ የሆነ የትምህርት ዕድል ማግኘትን የሚገልጽ ደብዳቤና የዲቪ ሎተሪ ዕድል ማግኘትን የሚያሳይ ማስረጃ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አገልግሎቱ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች አንስቶ ሥራ ሲያስጀምር፣ ደንበኞች የሚስተናገዱት በአዲሱ የክፍያ ተመን እንደሚሆን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው አሠራር መሠረት ባለ 32 ገጽ ፓስፖርት በአምስት ቀናት ውስጥ በአስቸኳይ ለማግኘት 2,186 ብር የሚከፈል ሲሆን፣ ይኼንኑ ፓስፖርት በሁለት ቀናት ውስጥ ለማግኘት 3,279 ብር ክፍያ ይፈጸማል፡፡ በቅርቡ በሥራ ላይ መዋል ይጀምራል የተባለው የአገልግሎት ክፍያ ተመን በአምስት ቀናት ውስጥ ባለ 32 ገጽ ፓስፖርት ለማግኘት የሚጠየቀውን ገንዘብ ወደ 5000 ብር አሳድጎታል፡፡ ፓስፖርቱን በአንድ ቀን ለማግኘት ደግሞ 6,500 ብር ክፍያ መፈጸም እንዳለበት ደንቡ ያስረዳል፡፡
ባለ 64 ገጽ ፓስፖርት በአምስት ቀናት ውስጥ ለማግኘት 6,500 ብር የሚከፈል ሲሆን፣ በአንድ ቀን ለማግኘት የሚከለፈለው ክፍያ 8000 ብር ደርሷል፡፡
ተቋሙ ቅድመ ሁኔታዎችን አንስቶ አገልግሎቱን ለመጀመር ጥናት ማስጠናቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ታምሩ፣ አገልግሎቱን ለማስጀመር የፓስፖርት ወረቀት፣ ላምኔት፣ የማተሚያ ቀለምና የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ መለዋወጫዎችን የመሳሰሉ ግብዓቶች መሟላት እንዳለባቸው ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የአስቸኳይ ፓስፖርት የሚሰጥባቸው መስኮቶች ሁለት መሆናቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት የአገልግሎቱ የኦንላይን ፓስፖርት ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል የሻነው፣ የአስቸኳይ ፓስፖርት አገልግሎትን ያለገደብ ለማስጀመር ቢያንስ ስድስት መስኮቶች መኖር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ ታምሩ አገልገሎቱን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸው፣ ‹‹ምን ያህል ብር እንደሚጠይቅም አዘጋጅተን ለሚመለከተው ክፍል አቅርበናል፤›› በማለት፣ አገልግሎቱን ለማስጀመር ተጨማሪ በጀት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ይኼ በጀት የሚፈቀድልን ከሆነ በቅርብ ወራት ውስጥ ይኼንን አስጀምረን አገልግሎት አሰጣጡን [እናሻሽላለን]፤›› ብለዋል፡፡