Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከገቢያቸው 15 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የወጣውን መመርያ መተግበር ጀመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከዓመታዊ ገቢያቸው 15 በመቶውን ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ እንዲሻሻል የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ የቦንድ ግዥውን ለመፈጸም መገደዳቸው ተገለጸ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርታቸውን ያጠናቀቁ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ይህንን መመርያ በአስቸኳይ ፈጽሙ በመባላቸው፣ ከ2014 የሒሳብ ዓመት የተጣራ ገቢያቸው 15 በመቶውን እያሠሉ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ታውቋል፡፡

መመርያው እያንዳንዱ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከተጣራ ገቢው 15 በመቶውን ለቦንድ ግዥ ማዋሉ ኩባንያዎቹን እንደሚጎዳና ቢያንስ መጠኑ እንዲቀንስ፣ በኢትዮጵያ መድን ሰጪ ኩባንያዎች ማኅበር በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቢያቀርቡም አዎንታዊ ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከሰሞኑ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን እያቀረቡ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ባንክ ‹‹መመርያውን በአስቸኳይ እንዲፈጽሙ›› በማለቱ የቦንድ ግዥውን ለመፈጸም እንደተገደዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

የቦንድ ግዥውን ስለመፈጸማቸው የሚያረጋግጥ መረጃና ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርታቸውንም አብረው አያይዘው እንዲያስገቡ ስለመደረጉም የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተጣራ ገቢያቸውን 15 በመቶ እያሠሉ ለቦንድ ግዥ የሚያውሉት በዘጠኝ በመቶ ወለድ ሲሆን፣ ይህንን የቦንድ ግዥ በየዓመቱ እንዲያካሂዱ ያስገድዳቸዋል፡፡ በየዓመቱ ለቦንድ ግዥው የሚውለው ገንዘብም ተመላሽ የሚሆንላቸው ከሦስት ዓመት በኋላ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በመመርያው መሠረት የ15 በመቶውን ግዥ የፈጸሙት ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርታቸውን ያጠናቀቁ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ ከዚህም በኋላ በተከታታይ የሒሳብ ሪፖርታቸውን ያጠናቀቁ ይህንን መመርያ ተፈጻሚ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያዎቹ የቦንድ ግዥ የሚፈጽሙበት ገንዘብ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በብድር እንዲሰጥ ለማድረግ መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው መመርያ ተግባራዊ መሆን ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ይጎዳል በሚል መመርያው እንዲስተካከል የቀረቡ ጥያቄዎች ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

በተለይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የቦንድ ግዥውን ሲፈጽሙ የሚታሰብላቸው የዘጠኝ በመቶ ወለድ አነስተኛ መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ ገንዘቡን በረዥም ጊዜ ለባንክ ተቀማጭ ቢያደርጉት እስከ 15 በመቶ የወለድ ጥቅም እንደሚያገኙበት ሲታሰብ፣ የኩባንያዎቹን ገቢ ይጎዳል የሚል ክርክርም እያስነሳ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች