Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ተቀላቀለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት 48 ዓመታት በጣና ኃይቅ ዙሪያ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየው የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አንድ ቅርንጫፍ ሆኖ ወደ ተቋቋመው ‹‹ኢትዮ ፌሪስ›› ድርጅት ተጠቃለለ፡፡

‹‹ኢትዮ ፌሪስ ጣና›› ከዚህ በኋላ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ስያሜን ተክቶ የሚቀጥል ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርትና አገልግሎት ድርጅት በሚመድብለት ካፒታል፣ ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የቆየውን አገልግሎት አዘምኖና ሌሎች የውኃ ትንስፖርት አገልግሎቶችን ጨምሮ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅቱ የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅትን ‹‹በኢትዮ ፌሪስ ጣና›› ድርጅት አማካይነት ከዚህ በኋላ ሙሉ በሙሉ የሚያስተዳድረው ይሆናል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከአማራ ክልላዊ መንግሥት፣ የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ የተቋቋመው ድርጅት ከሚያገኘው የትርፍ ድርሻ ላይ በማኅበራዊ ኃላፊነት ከሚደረግ የድጋፍ ማዕቀፍ የተወሰነውን በየዓመቱ በጀት እየመደበ ለክልሉ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አቶ ሮባ ተናግረዋል፡፡

ጣና ሐይቅ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በመንግሥት ድጎማ የሚተዳደርና ኪሳራ ላይ የነበረ ድርጅት በመሆኑ፣ ባህርና ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ደረጃ በሚያቋቁመው አዲስ ድርጅት አማካይነት፣ ጣናን ከኪሳራ አውጥቶ ትርፋማ በማድረግ ዘርፉን ማሳደግ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር ዋናው ድርጅቱን የማዋሃድ ግብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጣናን ወደ አዲስ አገልግሎት ለማምጣት ከመወሰኑ አስቀድሞ፣ በርካታ የቢዝነስ ፕላንና የአዋጭነት ጥናቶችን ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ሮባ፣ ውህደቱ ጣናን ከመጠቅለል ባለፈ ‹‹ኢትዮ ፌሪስ ጣና›› የሚባል ተቋም አቋቁሞ፣ አንዱ የድርጅቱ አካል በማድረግ ከጣና ባለፈ በሌሎች ሐይቆች ላይ የውኃ ላይ ትራንስፖርት ማስፋፋትን ታሳቢ ያደረገ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ሐይቅን ጨምሮ በሌሎች መንግሥት ያስተዋወቃቸው የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች፣ የውኃ ዙሪያን መሠረት አድርገው እንደመሠራታቸው፣ ‹‹ኢትዮ ፌሪስ ጣና›› በተባሉት አካባቢዎች የጀልባ ትራንስፖርት አገልግሎትን ከአማራጭነ ትራንስፖርት ባለፈ የቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

‹‹በቅርቡ የትራንስፖርት ጀልባዎች እንገዛለን፣ ሰውም ጭነት የሚያጓጉዙ፣›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከዚህ ባሻገር የሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅቱ ቢሮዎች ጨምሮ የሚያስተዳድራቸው ትንንሽ ወደቦች ማደስ የቅድሚያ ተግባራቸው እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

እስከ 200 ሰው ማጓጓዝ የሚችሉ ሁለት ጀልባዎች፣ አንድ ልዩ (ቪአይፒ) ጀልባ በመግዛት በጣና ሐይቅ ማሰማራት የቅድሚያ ሥራዎች ተብለው ከተለዩት ውስጥ ተጠቃሹ መሆኑን ያስታወቀው የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅቱ፣ ከውኃ ትንስፖርት በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጥበት ቅርንጫፍ እንደሚከፍት ተገልጿል፡፡

‹‹ጎርጎራ ላይ ወርክ ሾፕ ይኖረናል፣ ወርክ ሾፑ ጀልባ መገጣጠሚያ፣ የመርከብ ማንሸራተቻ ክሬን ይኖረዋል›› በማለት ያስረዱት አቶ ሮባ፣ ከውጭ አገር የሚመጣውን የጀልባ መገጣጠም ቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ በቀጣይ ድርጅቱ የሚሠራቸው ሥራዎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውኃ ትራንስፖርት ማስፋፋት በተለይም በውኃ ዙሪያ ላይ የጀልባ የመዝናኛ፣ የቱሪስት አገልግሎቶች ከገቢ አንፃር አዋጭነታቸውን የሚገልጸው ድርጅቱ፣ ከዚህ ባሻገር በቀጣይ ለመጀመር የወጠነው የጀልባ ማምረትና መገጣጠም ሥራ እንዲሁ ለድርጅቱ ትልቅ ገቢ እንደሚኖረው አስታውቋል፡፡

አቶ ሮባ እንደተናገሩት፣ ከጣና ሐይቅ መጀመር አንጋፋ የሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ከመሆኑ አንፃር ጥቅሙ ብዙ እንደሆነና በቀጣይ ሐዋሳ፣ ዓባያ፣ ባሮና በሌሎቹም ለመጀመር የታሰበውን ውጥን የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡

በተያያዘም የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በተያዘው ሩብ ዓመት ከፋይናንስ ግኝት አንፃር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከታክስ በፊት ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የጭነት መጠን መቀነሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሌሎች አገሮች የሚሰጠው የመርከብ አገልግሎት የድርጅቱ ገቢ በተጠቀሰው ጊዜ ትልቅ እንዲሆን እንዳስቻለው አቶ ሮባ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች