Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም ሦስት ዘመናዊ የክፍያ መፈጸሚያ አመራጮችን አስተዋወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል መኒ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቴሌ ብር፣ በሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂስ ኩባንያ ሥር ካለው ሲኔት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር፣ ተገልጋዮች ግብይት ሲያከናውኑ ክፍያ የሚፈጽሙባቸው ሦስት አማራጮችን አስተዋወቀ፡፡

ይፋ የተደረጉት የክፍያ አማራጮች ተግባራዊ የሚሆኑት የሲኔት ሶፍትዌር ቴክኖሎጂን አገልግሎት ከሚጠቀሙ ሱፐር ማርኬቶች፣ ሆቴሎች፣ ፋርማሲዎች፣ ሲኒማዎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ነው፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት የተመሠረተውና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተጣመረው ሲኔት በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ከ4,200 በላይ ለሆኑ ተቋማት የክፍያ ቴክኖሎጂ ሥርዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ያስታወቀ ሲሆን፣ አሁን የሲኔት ደንበኛ ሆነው ከቴሌብር ጋር በመተሳሰር አዲሶቹን የክፍያ ሥርዓቶች እየተገበሩ ያሉት 31 ተቋማት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ሸዋ ሱፐር ማርኬት፣ ሴንቸሪ ሞል፣ በሽ ገበያ፣ አኮ ቡና፣ ክዊንስና አባድር ሱፐር ማርኬቶች አገልግሎቱን ከጀመሩ ተቋማት መካከል  ተጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ዓመት 2015 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት የክፍያ አማራጮቹን የሚጠቀሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ብዛት ከአንድ ሺሕ በላይ ለማድረስ እንደታቀደ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. አማራጮቹ ይፋ በተደረጉበት መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከሦስቱ አማራጮች ውስጥ አንደኛው በክፍያ ሪሲት ላይ የሚታተም ልዩ መለያ ኪው.አር ኮድ (QR code) ነው፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል መኒ ቢዝነስ ዲቪዥን ቺፍ ኦፊሰር አቶ ብሩክ አድሃና እንደሚያስረዱት፣ ሪሲት ላይ ኪው.አር ኮድ በማተም የሚፈጸም የክፍያ ዓይነት በአገሪቱ ሲተዋወቅ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ደንበኞች ከሪሲቱ ጋር የሚመጣላቸውን ኪው.አር ኮድ በስልካቸው ስካን ሲያደርጉ ክፍያው ይፈጸማል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ አግልግሎት ተጠቃሚው ደንበኛ ክፍያውን በቴሌ ብር እንደሚያከናውን በመግለጽ ገንዘብ ተቀባዩ አጭር የሚስጥር ቁጥር ወደ ስልኩ እንዲልክለት የሚያስደርግበት ነው፡፡ እንደ አቶ ብሩክ ገለጻ ወደ ደንበኛው የሚላከው የሚስጥር ቁጥር ለአንድ ጊዜ ክፍያ የሚያገለግል ሲሆን፣ ደንበኛው በስልኩ የደረሰውን አጭር ቁጥር ለገንዘብ ተቀባዩ ይሰጣል፡፡ ገንዘብ ተቀባዩ ቁጥሩን በሲኔት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ውስጥ ሲያስገባው ክፍያው ይፈጸማል፡፡

አጭር ቁጥር (USSD) በመጠቀም ክፍያ የሚፈጸምበት እንደሆነ አቶ ብሩክ ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛው አማራጭ ክፍያ ለመፈጸም ደንበኛው ለተቋሙ ክፍያ ተቀባይ የስልክ ቁጥሩን ሲሰጥ የክፍያ ተቀባዩ ቁጥሩን የሲኔት ሥርዓት ውስጥ በማስገባት፣ ደንበኛው በ127 አጭር ቁጥር የክፍያው ዝርዝር እንዲደርሰው ያደርጋል፡፡ ደንበኛውም የቴሌ ብር የይለፍ ቁጥር በመሙላት ክፍያውን ማጠናቀቅ ይችላል፡፡

አቶ ብሩክ እንደገለጹት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቀጣይ ጊዜያት የሲኔት ደንበኛ የሆኑትን 4237 ተቋማት በሙሉ በእነዚህ አማራጮች ክፍያ መፈጸም እንዲያስችሉ የማድረግ ዕቅድ ይዟል፡፡ ኩባንያው ከሥርዓቱ ጋር ሊያስተሳስራቸው ካቀዳቸው የተለያየ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የጅምላና የችርቻሮ ሻጮች እንዲሁም ሱፐር ማርኬቶች ናቸው፡፡ ለትስስር የታቀዱት የሽያጭ ማዕከላት ቁጥር 1415 ሲሆን የመዝናኛና የምግብ አገልግሎት ዘርፍ ላይ ያሉ ተቋማት ቁጥር 753 በመሆን ተከታይ ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እነዚህን የክፍያ አማራጮች የሚያሳልጥበት ቴሌ ብር የተጠቃሚ ብዛቱን 25.8 ሚሊዮን ብር ማድረሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በቴሌብር የ153 ቢሊዮን ብር ትራንዛክሽን እንደተፈጸመና በቴሌብር አማካይነት 1.46 ሚሊዮን ብር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ቴሌ ብር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ግንቦት 2013 ዓ.ም. ከ40 በላይ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች ክፍያ በቴሌ ብር እንዲፈጸም እንደተደረገና ከ200 በላይ የግል ተቋማት ቴሌ ብርን እንደሚጠቀሙ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች