Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየክልል መዋቅርነት ጥያቄ የተነሳበት ጉራጌ ዞን በኮማንድ ፖስት እንዲመራ ተደረገ

የክልል መዋቅርነት ጥያቄ የተነሳበት ጉራጌ ዞን በኮማንድ ፖስት እንዲመራ ተደረገ

ቀን:

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ በቤት የመቆየት አድማ የተደረገበት ጉራጌ ዞን በኮማንድ ፖስት እንዲመራ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የክልሉ መንግሥት ከሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ ዞኑ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ውሳኔ ያሳለፈው፣ በጉራጌ ዞን ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ‹‹የፀጥታ ችግር›› በመደበኛው አሠራር ‹‹ለማስተዳደር አስቸጋሪ›› እንደሆነ በመግለጽ ነው፡፡

ክልሉ በመገናኛ ብዙኃን ባስተላለፈው መግለጫ፣ ውሳኔውን ይፋ ያደረጉት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ፣ ዞኑን ለማስተዳደር በክልሉ የተደራጀው ኮማንድ ፖስት ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልሉ ልዩ ኃይልና ‹‹ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች›› ጋር በመቀናጀት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹የክልል ጥያቄ በሚል ሽፋን የተጀመረው ሕገወጥ እንቅስቃሴ አሁንም ቀጥሏል፤›› በማለት ኮማንድ ፖስት የተደራጀበትን ምክንያት ያስረዱ ሲሆን ‹‹ኢመደበኛ ቡድን እጅግ በርካታ አጥፊ ድርጊቶችን አቅዶ እየሠራ ነው ያለው፤›› ሲሉም ክስ አቅርበዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም፣ ይኸው ቡድን በጉራጌ ዞን ውስጥ ‹‹መደበኛ የመንግሥት አሠራር ቀጣይነት እንዳይኖረው›› ፍላጎት እንዳለው በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ‹‹ኢመደበኛ›› ያሏቸው ቡድኖች የክልልነት ጥያቄን አለመቀበል ‹‹የጉራጌን ክብር ማዋረድ ነው›› የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረው በዞኑ ውስጥ ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚተላለፉ መልዕክቶች ‹‹በማንነት ምክንያት ግጭተ እንዲፈጠር›› የሚያደርጉ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹ጉራጌ በክላስተር አይጠረነፍም፣ ጉራጌም ከሌላ ሕዝቦች ጋር ተደራጅቶ አይኖሩም የሚሉ በጣም አጥፊና ከሕዝቡ ጋር አብሮ የጉራጌ ሕዝብ እንዳይኖር የሚያደርጉ መልዕክቶች እየተጻፉ ታፔላዎች ላይ ይለጠፋሉ፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የመንግሥት አመራሮች በመደኛ ሥራቸው ላይ እንዳይገኙ ‹‹ተፅዕኖና ዕገታ›› እንደሚደረግ ‹‹አልፎ አልፎ›› የመንግሥት አመራሮች ላይ ‹‹ድብደባ›› እንደሚፈጸም ኃላፊው በመግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡ ‹‹መንገድ መዝጋት፣ ጎማ ማቃጠል፣ መደበኛ እንቅስቃሴ አንዳይደረግ የሚደረግ ዕገታ፣ ሕገወጥ ባንዲራ አዘጋጅቶ መስቀል፣ የሥራ አድማ ማወጅ፤›› በዞኑ ውስጥ ይፈጸማሉ ተብለው ከተጠቀሱ ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለጻ በዞኑ ውስጥ የፀጥታውን ሁኔታ የሚያስተዳድረው ኮማንድ ፖስት በዞኑ ውስጥ ተፈጥሯል በተባለው የፀጥታ ችግር የተሳተፉትንና በቀጣይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ሥር ያውላል፡፡ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉትን ‹‹የጥፋት ድርጊቶች›› ያቀዱ፣ የመሩና ያስተባበሩ አካላት ‹‹በተደራጀ መልኩ›› መለየታቸውንና የፀጥታ ኃይሉ አካላቱን ቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደትም ከ70 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክለዋል፡፡

ይሄ ኮማንድ ፖስት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በዞኑ መንግሥት ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጪ መንቀሳቀስና የመንግሥት ተቋማት ከሚያስተባብሩት ውጪ ስብሰባዎችን ማካሄድ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት የሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎችም ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በቅንጅት የሚመሩ እንደሚሆኑ ተናግረው፣ ከዚህ ውጪ በየትኛውም ቦታ ‹‹ያልተፈቀዱ ስብሰባዎችን›› ማድረግ ‹‹በፍፁም የማይፈቀድ›› እንደሆነ አንስተዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹በሕጋዊ በመንገድ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የመንግሥት አመራሮች ውጪ በየትኛውም መንገድ የትኛውንም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ ሁሉን ዓይነት የሕግ ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹ሕዝቡ አጋዥ መሆን አለበት፣ ጫካ መሆን የለበትም፤›› ሲሉ ሕዝቡ ለኮማንድ ፖስቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...