Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገቢዎች ሚኒስቴር በአራት ወራት 139 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከተጀመረ አራት ወራት ባስቆጠረው የ2015 በጀት ዓመት 139 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከአገር ውስጥ ገቢ 106 ቢሊዮን ብር አቅዶ 105 ቢሊዮን ብር፣ ከጉምሩክ ገቢዎች 59 ቢሊዮን ብር አቅዶ 57 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ ዓርብ ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ኮሚቴ አቅርቧል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ53 ሺሕ በላይ የተመዘገቡ ግብር ከፋዮች እንዳሉ፣ ተቋሙ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ግብር ከፋይ ኪሳራ፣ ተመላሽ ባዶና፣ ጭራሽ ግብር የማያሳውቁ መኖራቸው ተገልጿል፡፡

በአራት ወራት ውስጥ ከተሰበሰበው 139 ቢሊዮን ብር ውስጥ 11 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ማስተላለፉን፣ የሚኒስቴሩ የበላይ ኃላፊዎች የተቋማቸውን የ2015 ዓ.ም. በጀት ዕቅድና የ2015 ሩብ ዓመት አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ሲያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

የኮንትሮባንድ የወጪ ንግድ መጨመሩን የገለጹት የሚኒስቴሩ ስትራቴጂክ ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ታደሰ፣ በዚህም የወጪ ንግድ ኮንትሮባንድ ባሳደረው ጫና የተነሳ በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የተላኩ የጫትና የቁም እንስሳት ገቢ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

 የገቢዎች ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. 450 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ዕቅድ የያዘ ቢሆንም፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መሠረት በ2015 ዓ.ም. አጠቃላይ ገቢ መታቀድ የነበረበት 497 ቢሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ የገቢዎች ሚኒስቴር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ የገቢ ዕቅዱ ከአሥር ዓመቱ ዕቅድ ጋር አብሮ እንዳይሄድ ሊያደርገው የቻለው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት የተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በትግራይ ክልል ገቢ የማይሰበሰብ በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አራት ወራት 351 ኮንትሮባንዲስቶች መያዛቸውን፣ ከኮንትሮባንድ የተሰበሰበው ገንዘብ ደግሞ ሁለት ቢሊዮን ብር መሆኑ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

ጠንካራ የሆነ የምክር ቤት ዕገዛ ያስፈልገኛል ያለው የገቢዎች ሚኒስቴር ሕገወጥ ንግድና የታክስ ማጭበርበር በተለያየ መንገድ በሚገለጹ በሐሰተኛ ደረሰኝ፣ የግብይት ደረሰኝ ባለመቁረጥ፣ በሐሰተኛ የግብይት ደረሰኝ መሸጥና መሰል ችግሮች በገቢ አሰባሰቡ ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት በገቢ ንግድ ኮንትሮባንድና በወጪ ንግድ ኮንትሮባንድ ከተያዙ ሸቀጦች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው አደንዛዥ ዕፅ መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች