ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለይም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከገለጹት ከመሬት ዝርፍያ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል በተባለ የወንጀል ድርጊት ላይ መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ፡፡
‹‹አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ፋይል በእግሩ አይሄድም’ የሚል ቋንቋ፣ የተለመደ ቋንቋ ነው። ፋይል በእጅ ብቻ ነው የሚሄደው፣ በእግሩ አይሄድም። ሌብነት ልምምድ ብቻ ሳይሆን እንደ መብት መወሰዱ፣ አደገኛ ነገር ነው›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሌብነት በጣም አታካች ነገር ሆኗል፣ መሬት የመንግሥትም፣ የሕዝብም አይደለም፣ የደላሎችና የሌባ ሹመቶች ነው፤›› ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከመሬት ዝርፍያ ጋር በተያያዘ ባደረገው ማጣራት፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከወረዳ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንስቶ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ በተለይም በመሬት ጉዳይ ይወስኑ የነበሩ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ደላሎችና ከኅብረተሰቡ ውስጥ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል ተብለው ከተለዩ 37 ተጠርጣሪዎች 12ቱን ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ አስታውቋል፡፡
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 12 ተጠርጣሪዎች ውጭ ቀሪዎቹን ግለሰቦችም ፖሊስ ክትትል እያደረገባቸው ይገኛል የተባለ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ተጨማሪ የማጥራት ሥራም እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል::
በአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደሩን ዘመናዊ ማድረግ አለመቻሉ፣ ሌብነትና የመሬት ወረራ መበራከቱን፣ ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት አለመኖር ሕዝቡን በዘርፉ የፀረ ሌብነት ትግል ላይ አለማሳተፍና ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ሥራ አለመሠራቱ በተለይም በከተማዋ ለሚስተዋለው የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ወንጀል መበራከት ተጠቃሹ ጉዳይ መሆኑ ይገለጻል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የከተማ አስተዳደሩ በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ጥናት ሲያካሄድ መቆየቱ የተሰማ ሲሆን፣ በቀጣይ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የድርጊቱ ተባባሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ጉዳይ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡