ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው የፔይሊንክ ፔይመንት ፕሮሰሲንግ አክሲዮን ማህበር ከብሔራዊ ባንክ በፔይመንት ጌት ዌይ ኦፕሬተርነት እውቅና አግኝቶ ምሥረታውን አካሄደ።
ፔይሊንክ ፔይመንት ፕሮሰሲንግ የከፍያ ስርዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሞያዊ ድጋፍና ማበረታቻ ተደርጎለትና የኩባንያውን ምስረታ እንዲያካሂድ ከባንኩ እውቅና አግኝቶ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ህዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በማካሄድ የኩባንያውን ምሥረታ መፈጸሙን የአክኪዮን ማሕበሩ ዋና አደራጅ አቶ ዳዊት ኪሮስ በላይ ገልጸዋል።
ፔይሊንክ ፔይመንት ፕሮሰሲንግ አክሲዮን ማህበር በ10 መስራች አባላት የተቋቋመ ሲሆን ፣ እያንዳንዳቸው 1000 ብር መጠን ያላቸው 3000 አክሲዮኖችን በመሸጥ በ ሦስት ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል እንደተመሠረተም ገልጸዋል።
ፔይሊንክ ኩባንያ የዲጂታል የክፍያ ስርዓትን በማበልጸግ ከባንኮችና ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በመተሳሰር ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ ዘመናዊ የክፍያ ስርዓትን ለመፍጠር አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ዋና አደራጁ ገልጸዋል።
“በቀጣይ የኩባንያውን ተሞክሮ የበለጠ በማጎልበት ፣ ከውጪ ሃገር እና ከሃገር በቀል የዘርፉ አንቀሳቃሶች ጋር በመሥራት፣ አሁን በሀገራችን ያለውን የክፍያና የግብይት ሥርዓት በማዘመን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅድን ለማሳካት የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማኖር በሙሉ ዝግጅት ላይ እንገኛለን” ሲሉ ዋና አደራጁ ገልጸዋል።