Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ያቀደው ድርዜማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ባሉ የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የተቋቋሙ ኩባንያዎች እምብዛም ውጤት እየተገኘባቸው እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ አብዛኛዎቹ የተቋቋሙለትን ዓላማ ሳያሳኩ ከገበያ ውጪ የሆኑ በእርሻ፣ በሪል ስቴት፣ በትራንስፖርትና መሰል የቢዝነስ ዘርፎች ለመሳተፍ የተቋቋሙ የአክሲዮን ኩባንያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከውጥናቸው ተደነቃቅፈዋል፡፡

አሁንም ጥቂት በአክሲዮን በኩባንያ ደረጃ ተቋቁመው በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቢኖሩም፣ በተመሳሳይ መንገድ ከተመሠረቱት የፋይናንስ ተቋማት ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ እንዲህ ያለው ጅማሮ ከግብ ያለመድረስ ችግር በአክሲዮን ኩባንያዎች ላይ እምነት እንዳይፈጠር ማድረጉ ይታመናል፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ በዚህ ምልከታ ይስማማሉ፡፡ ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ያሉ የአክሲዮን ኩባንያዎች በአብዛኛው ተሰነካክለው የሚቀሩት እነዚህን አክሲዮን ኩባንያዎች የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ አካል ባለመኖሩ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን በሚቆጣጠርበት መንገድ ሌሎች አክሲዮን ኩባንያዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ተቋማዊ አሠራር ባለመዘርጋቱ ብዙዎቹ ውጤት ሳይገኝባቸው ተፈናቅፈው ቀርተዋል፡፡  

ከዚህ ቀደም በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ አክሲዮን በመሸጥ ካፒታል በማሰባሰብ በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ ለመሰማራት የሞከሩ ኩባንያዎች ሊሳካላቸው ያልቻለበት ምክንያት ይዘው የተነሱትን ዓላማ ማስቀጠል ባለመቻላቸው ነው፡፡ ቢዝነሶቹ አዋጭ ሳይሆኑ ቀርተው ሳይሆን፣ በአብዛኛው ከአስተዳደር ጋር በተያያዘ፣ በግለሰቦች ብክነት ኩባንያዎቹን ዳር ማድረስ አልቻሉም ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል መሆኑንም የሕግ ባለሙያው ያብራራሉ፡፡ በተለይ ተቆጣጣሪ የሌላቸው መሆኑ አንዱና ትልቁ ችግር መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት አሁንም ባልተቀረፈበት ወቅት ግን፣ በግል ዘርፉ ብዙም በማይሞከረው የግብርና ኢንቨስትመንት ውስጥ አክሲዮን ኩባንያ በማቋቋም ወደ ሥራ እንደሚገባ ያስታወቀው ድርዜማ አክሲዮን ማኅበር አንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ለመሸጥ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡ ከሌሎች የአክሲዮን ኩባንያዎች በተለየ በግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በመስጠት ሥራ እንደሚጀምርም ገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩትን ችግሮች በመቅረፍ ወደ ሥራ እንደሚገባ የአክሲዮን ኩባንያው አደራጆች ባለፈው ቅዳሜ ኩባንያቸውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ከተጋበዙ የግብርና ባለሙያዎች መካከል የቀድሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ በላይ ደምሴ (ዶ/ር)፣ ድርዜማ ይዞት የመጣው ሐሳብ ብዙ ሲጮህለት የነበረ ሐሳብ መሆኑን ገልጸው፣ የኤክስቴንሸን አገልግሎቱ የመንግሥት ሞኖፖሊ ከሚሆን የግል ዘርፉ እየገባ ማገዝ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ከዚህ መውጣት እንዳለበት የሚያምኑት በላይ (ዶ./ር)፣ ድርዜማ ይዞት የተነሳው ይህ ዓላማ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተሞከሩ ሥራዎች የነበሩ ቢሆንም ሳይሳካ መቅረቱንም አስታውሰዋል፡፡

‹‹ነገር ግን ከዚህ በፊት ልክ እንደ እናንተ እየጀመሩ የከሰሙ አሉ፡፡ የግብርና ባለሙያዎች ጭምር ያሉበት አማድኮ የሚባል አክሲዮን ማኅበር የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ጠፍቷል፡፡ ከዚያ በኋላም የተቋቋመው እንደ ጃካራንዳ አ.ማ. ማኅበር ዓይነቶች ወድቀዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከፖሊሲ ጋር በተያያዘ ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ታች በሚያጋጥም ችግር ምክንያት እሳቸው ያሉበት አክሲዮን ኩባንያ ሳይቀር መክሰሙን አመላክተዋል፡፡ ስለዚህ የድርዜማ ሐሳብ ጥሩ ቢሆንም ከቀደሙት የአክሲዮን ኩባንያዎች መማር ካልቻለ ውጤት ላያመጣ ይችላል የሚል ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

የድርዜማ የግብርና አገልግሎት አቅራቢ አ.ማ. ምሥረታውን አስመልክቶ የአክሲዮን ኩባንያው ዋነኛ አደራጅና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘለዓለም እሸቱ ግን የድርዜማ አክሲዮን ማኅበር አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አደረጃጀት ኖሮት የሚሠራ በመሆኑ፣ የተባሉትን ችግሮች መቅረፍ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ኩባንያው ወደ እዚህ ሥራ ከመግባቱ በፊት ሰፊ ጥናት በማጥናት ወደ አክሲዮን ሽያጭ ለመግባት እንደወሰነ ያስረዱት አቶ ዘለዓለም፣ በግብርናው ዘርፍ ያለውን ሰፊ አቅም ትርፋማ መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ሥጋቶችን በሚቀርፍ መልኩ የሚደራጅ ስለሆነ ችግሩ ያጋጥመናል ብለው እንደማያምኑት የአቶ ዘለዓለም ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በመሸጥ ወደ ሥራ ለመግባት ያቀደው ድርዜማ፣ የመጀመርያ ሥራውን የሚጀምረውም በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ሁለት ቀበሌዎች ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ተግባር የግብርና ግብዓትና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በማቅረብ በዘመናዊ መንገድ እርሻ እንዲታረስ አገልግሎት በማቅረብ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ ቢያንስ በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያመርት ለማድረግና በአነስተኛ መሬት የተቀናጀ የእርሻ ሥራን በማላመድ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በጥናት በመረጋገጡ አዋጭነት ያለው የኢንቨስመንት ሥራ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡   

በአምስት ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ 3,800 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ሥራውን እንደሚጀምር የገለጸው አክሲዮን ማኅበሩ፣ በጋ ከክረምት ማምረት የሚቻልበትን አሠራር በመዘርጋት እንደሚሠራና አትራፊ መሆን እንደሚችል ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ ሥራውን በሚጀምርበት ምሥራቅ ጎጃም ወረዳ ባሻገር፣ ሊለሙ የሚችሉ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የሚገኙ ኩሬዎችን፣ ወንዞችን፣ ከርሰ ምድር የውኃ ምንጮችን በመጠቀም እስከ 400,000 ሔክታር መሬት ላይ አገልግሎቱን በማስፋት የሚቀጥል እንደሆነም አመልክቷል፡፡

እንደ አቶ ዘለዓለም ገለጻ፣ የዚህ አክሲዮን ማኅበር ዋነኛ ተግባር የአርሶ አደሩን የሰብል አመራረት ሳይንሳዊ እንዲሆን በማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን መጨመርን ግብ አድርጎ የሚሠራ መሆኑን ነው፡፡

ኩባንያው አብረውት ለሚሠሩ አርሶ አደሮች በዕቅዱ ልክ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ በየ20 ሔክታር መሬት አንድ የግብርና ባለሙያ በሙሉ ጊዜ የሚመደብ መሆኑን፣ አጠቃላይ ሒደቱን በማማከር ውጤታማነቱን የሚያረጋግጥበት አሠራር እንደሚዘረጋም አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም መንግሥት የአርሶ አደሩን ትርፋማነት ለመጨመር ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ድርዜማም አስፈላጊውን የእርሻ ግብዓት በማቅረብ ምርቱ እንዲመረት በማድረግ፣ ከአርሶ አደሩ ጋር የሚያገኘውን ጥቅም በመካፈል እንደሚሠራም ጠቁሟል፡፡

ይህ አሠራር በኢትዮጵያ ያልተለመደ ቢሆንም፣ ከአክሲዮን ኩባንያው ጋር የሚሠሩ አርሶ አደሮች ጋር ውል ገብተው አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ተገልጿል፡፡ የአገልግሎት ክፍያውን በተመለከተ ሲያብራሩም፣ አንድ ሔክታር ያለው አርሶ አደር በትራክተር ልረስ ቢል፣ በአማካይ 8,000 ብር ወጪ አለበት፡፡ ይህ አርሶ አደር በመሬቱ ላይ 45 ኩንታል ስንዴ አገኘ ቢባል ለማሳጨጃና ለመፈልፈያ ለኩንታል 150 ብር ያወጣል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ መረጃ በድምሩ 6,570 ብር ሲያወጣ፣ በአጠቃላይ 14,750 ብር የሚከፍል ይሆናል፡፡ ይህ ለእርሻና ለመሳሰሉት የሚያወጡት ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ፣ እንዲሁም የግብርና ባለሙያን አያጠቃልልም፡፡ በዳርዜማ አማካይነት ቢሠራ ግን የግብዓት፣ የባለሙያ አገልግሎት የእርሻ አገልግሎት፣ የአጨዳና የመውቂያ አገልግሎት ቀርቦለት በተመሳሳይ አንድ ሔክታር መሬት 18,000 ብር ብቻ ወጪ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ ሲመረት ከአንድ ሔክታር መሬት ላይ እስከ 90 ኩንታል ስንዴ ማስገኘት ያስችላል ተብሏል፡፡ ይህም በገንዘብ ሲተመን 316 ሺሕ ብር ማግኘት የሚያስችል በመሆኑ አርሶ አደሩም አክሲዮን ማኅበሩም የተሻለ ጥቅም ያገኙበታል ተብሏል፡፡ ይህ በአንድ ጊዜ ምርት ሲሆን፣ ዓመቱን ሙሉ እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ ምርት በማምረት ለአርሶ አደሩ የተሻለ ጥቅም ከመስጠት ባለፈ ለአክሲዮን ማኅበሩ ትርፋማነት የሚያስገኝ ይሆናል ተብሏል፡፡  

ዳርዜማን የተለየ ከሚያደርጉ ጉዳዮች ውስጥ በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና በግብርና ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ትኩረት ጋር ተዳምረው የምርት ብክነትን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑና አርሶ አደሩ በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሯዊ ምክንያቶች ኪሳራ ቢያጋጥመው ኪሳራውን ዳርዜማ የሚወስድ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በድርዜማ ውጥንና ተልዕኮ አንፃር ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት የድርዜማ የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ የቻለ አበበ፣ ‹‹ይህ ዕሳቤ ሥራውን በምናውቀው በግብርና ሥራ ላይ በነበርን ሰዎች ጭምር የሚመራ በመሆኑ ውጤታማ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ባለን አቅም ብዙ መሥራትን እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡ ሥራው የሚጀመርበት አካባቢም በግብርና ባለሙያ ሆነው ሲሠሩበት የነበረ አካባቢ በመሆኑ ሥራውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ምቹ ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡

በአክሲዮን ማኅበሩ ውጥን መሠረት አንድ መቶ ብር ዋጋ ያለውን አንድ አክሲዮን ለመግዛት የሚፈልግም መጀመርያ 30 በመቶውን፣ ቀሪውን ደግሞ 70 በመቶ ደግሞ በሚቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲከፍል የሚያስችል አሠራር እንደሚኖረውም ለማወቅ ተችሏል፡፡      

በዕለቱ የተገኙ የግብርና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የአክሲዮን ኩባንያውን ውጥን አድንቀው፣ አተገባበሩ ላይ በደንብ መሥራት እንደሚገባ የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው ጫንያለው ደምሴ (ዶ/ር)፣ በግል ደረጃ እንዲህ ባለ መልኩ ወደ ሥራ መግባቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ አገር ዘላቂ ልማት ሊመጣ የሚችለው በዜጎች በአገር ውስጥ ባለ ዕሳቤ ጥበብን ተሞክሮ ሲመራና በዘመናዊነት ሲታገዝ በመሆኑ የድርዜማ ተግባርም ይህንን ያሳያል ብለው፣ ኩባንያውን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የድርዜማ መሥራቾች ይዘው የመጡት ሐሳብ መልካም ቢሆንም፣ ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን ሊከብድ የሚችል መሆኑን ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ተቋቁመው የነበሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች ያጋጠሟቸው ችግሮችን ለማለፍ በምክክር መሥራት እንደሚያስፈልግ ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

የድርዜማን የመጀመርያ ማልሚያ ቦታ በተመለከተ በዕለቱ የነበሩ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች አቅርበው ነበር፡፡ በተለይ የተባለው ቦታ ላይ ያሉ አርሶ አደሮች ይሁንታ ተጠይቀዋል ወይ የሚለው አንዱ ነበር፡፡ የማልሚያ ቦታን በተመለከተ ድርዜማ የመጀመርያው የሥራ ቦታ አድርጎ የመረጠው ምዕራብ ጎጃም የሰሜን ሜጫ ወረዳ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አንተነህ ወልዱ ናቸው፡፡ በድርዜማ አ.ማ. የቀረበውን ሐሳብ ወረዳቸው የተቀበለና ይህንን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ድርዜማ በአርሶ አደሩ መሬት ላይ ሊሠራቸው ያቀዳቸው ልማቶች ውጤታማ እንዲሆኑ  ወረዳችን ያሉብንን ክፍተቶች የሚሞላ በመሆኑ በቅንጅት እንሠራለንም ብለዋል፡፡

‹‹ድርዜማ የሚሠራቸው ሥራዎች አርሶ አደሩን ጠቅላላ ሁኔታ የሚቀርፍና ጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመረጃቸውም አካባቢው በመስኖ ልማት የሚታወቅ ቢሆንም፣ አሁን ሊለማ የተመረጠው ቦታ በመስኖ ተጠቃሚ ያልሆኑ አርሶ አደሮች ያሉበት ስለሆነ የምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሳያገኙ የቆዩ በመሆናቸው ከድርዜማ ጋር ለመሥራት የሚያስችል ዕድል አለ ብለዋል፡፡

በሰሜን ሜጫ ወረዳ 40,500 ሔክታር መሬት ውስጥ እየለማ ያለው ጥቂት መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ በተለይ በመስኖ ከማልማት አኳያ ውስንነት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሥራው የሚጀምርባቸው ቀበሌዎች የዓባይ፣ የጅማና የቆላ ወንዞች የሚገኙበት ቦታ ስለሆነ በቂ ውኃ ያለ በመሆኑ የትኛውንም አማራጭ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በመስኖ በማልማት አክሲዮን ማኅበሩ ሰፊ ዕድል እንዳለው ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፤›› በማለትም ይለማል የተባለው ቦታ ዓመቱን ሙሉ ሊለማ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአክሲዮን ሽያጩ ላይም ተሳትፎ እንደሚደርግ አመልክተዋል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያው ከጅምሩ እንዳይሰናከል አሁን ያለው ሕግ ጥበቃ እንደሚሰጥ አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ በአክሲዮን የተሰባሰበ ገንዘብ ኦዲት ሳይደረግ በንግድ ሚኒስቴር ምዝገባ የማይደረግ መሆኑን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡

‹‹በአዲሱ የንግድ ሕግ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሲጠራ፣ በዚህ አጀንደ ላይ ውይይት ይደረግ ማለት የሚችሉ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ የድሮ ሕግ ይህንን አይፈቅድም ነበር፡፡ ቢያንስ አምስት በመቶ ድርሻ ያለው ባለአክሲዮን ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ አጀንዳ ይያዝልን ብለው አጀንዳ ማስያዝ የሚችሉ በመሆኑ፣ አክሲዮን ኩባንያዎች ችግር ውስጥ ሳይገቡ በውይይት ነገሮችን ሊያስተካክሉ የሚችሉበት ዕድል ይሰጣቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ድርዜማ መጀመርያ በሚያለማው ቦታ ላይ በዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት እሸጣለሁ ብሎ አቅዷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች