በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ሲፈተኑ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ኖሯቸው መኖሪያ ቤት ለመሥራት የሚቸገሩ ባለሀብቶችን ማየትም እየተለመደ መጥቷል፡፡ እነዚህን ባለሀብቶችም ሆነ ዳያስፖራዎችን ለመታደግ የተለያዩ ተቋሞች አፓርታማ ገንብተው በማስረከብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት መካከል ሆሴዕ ትሬዲንግ ሐውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ ማኅበሩም የተለያዩ አፓርታማዎችን ገንብቶ ከማስረከብ በተጨማሪ፣ ሰሊጥና ቡና ኤክስፖርት በማድረግ ይታወቃል፡፡ አቶ ሰይፈ ፈቃደ የሆሴዕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ የድርጅቱን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሆሴዕ ትሬዲንግ ሐውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንዴት ተመሠረተ?
አቶ ሰይፈ፡- ሆሴዕ ትሬዲንግ ሐውስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከተመሠረተ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ ገና እንደተመሠረተ ሰሊጥና ቡና ኤክስፖርት በማድረግ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብረት፣ ጣውላና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን በማስመጣት እየሠራ ሲሆን፣ አሁን ላይ ተጨማሪ ሥራዎችን በማካተት የሪል ስቴት ዘርፉ ላይ ተሰማርቷል፡፡ በአምስት ዓመታት ጉዞው ፈተናዎችን ቢያይም፣ ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ የመጀመርያ የሪል ስቴት ፕሮጀክቱንም ጂ+8 አፓርትመንትን መሀል ከተማ ላይ ሠርቶ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡ በሌላ በኩል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አያት 49 በሚባል አካባቢ ከ300 በላይ ቤቶችን የያዘ የረር ሆምስ የመኖሪያ መንደር ኅዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቤት ባለቤቶች ሊያስተላለፍ ችሏል፡፡ የግንባታ ሥራው በሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የመኖሪያ መንደሩም በ23 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ናቸው፡፡ ይህም 280 ባለ አንድ፣ ባለሁለት እንዲሁም ባለሦስት መኝታ ቤት የመኖሪያ ቤቶችንና አሥር ሱቆችን የያዙ ባለአራት ወለል ያሉት ሲሆን፣ 14 አፓርታማ ሕንፃዎችን እንዲሁም እያንዳንዳቸው 250 ካሬ ሜትር ግቢ ያላቸው 20 ቪላዎችን ያካተተ ነው፡፡ ቤቶቹም የተጠናቀቁና ጥራታቸውን ጠብቀው የተሠሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቢሮዎችን የያዘ ሲሆን፣ በሥራም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከቤታቸው ርቀው ለሚቆዩ ነዋሪዎች የግል መኪናቸውን የሚያቆሙበት ፓርኪንግ መኖሩ ትልቁ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ቤት የተናጠል የመብራትና ውኃ ቆጣሪዎች የተገጠመላቸው ሲሆን፣ ኮሪደር መብራቶች፣ እንዲሁም ለውኃ ፓምፕ አገልግሎት የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጄኔሬተር ተገጥሟል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በሥራችሁ ላይ ያጋጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ?
አቶ ሰይፈ፡- በሥራችን ላይ ትልቅ ተግዳሮት የሆነብንና ፈተና ውስጥ እንድንገባ ያደረገን ለኮንስትራክሽን ግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች መወደድ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበራችን እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች በመወጣት አፓርታማዎቹን በመሥራት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች የተላለፉ አፓርትመንቶችን ሲሠሩ የነበሩ ተቋራጮችን ማኔጅ በማድረግ፣ ማኅበሩ ጉልህ ሚና ሊጫወት ችሏል፡፡ ማኅበሩ ከተቋራጮች ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር የነበሩ ተግዳሮቶችን መፍታት ተችሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ጥራቱን የጠበቀና ምቹ የሆኑ የመኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ሊያደርግ ችሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዱን የኮንስትራክሽን የሚቆጣጠር ማኅበር መቋቋሙ በዘርፉ ላይ ችግር እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡ በተለይም ማኅበሩ የተለያዩ አፓርታማዎችን ሲሠራ የይድረስ ይድረስ ሳይሆን ጥራቱን ባማከለ መልኩ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ጊዜ ደረጃቸውን የጠበቁና ምቹ የሆኑ አፓርታማዎችን ከመገንባት አኳያ ክፍተቶች እንዳሉ ይነሳል፡፡ የእናንተ ማኅበር ይህንን ለመቅረፍ ምን ይሠራል?
አቶ ሰይፈ፡- ቅድም እንዳልኩህ ማኅበራችን የተለያዩ አፓርታማዎች ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ሲያደርግ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጥራት ያለው ሥራን መሥራት ነው፡፡ ይህንን ያልኩት ዋነኛ ምክንያት ከደንበኞች ጋር ግልጽ የሆነ ውይይት በማድረግ የተሠሩ ሥራዎች አስቀድመው እንዲያዩ ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቱ የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ረገድ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ሆሴዕ ሪል ስቴት ከቤት አሠሪና ገዥ ደንበኞቹ ጋር በገባው ውል ከተቀመጡ የውል ግዴታና ሁኔታዎች በዘለለ፣ ቤቶቹን በማጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የድርጅቱን ምርትና አገልግሎት ጥራት በመጠበቅ፣ እንዲሁም ታማኝነትን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ሌሎች አፓርታማዎችን ለመገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህም ፕሮጀክት በቅርብ የሚጀመር ሲሆን፣ የደንበኞችን ዕርካታ ባማከለ መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከቤት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ምን አስቧል?
አቶ ሰይፋ፡- ሆሴዕ ሪል ስቴት በቀጣይ በከተማዋ የሚታዩ የቤት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በጋራ ሕንፃና መንደር መተዳደሪያ ሕግ መሠረት የቤት ባለቤቶች ወይም ነዋሪዎች ማኅበር ከወዲሁ እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡ ይህም ማኅበር የቤት ባለቤቶችን አፓርታማዎችን እንዲያገኙ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከተለያዩ አጋር ተቋሞች ጋር በቅንጅት በመሥራት የቤት ችግርን ለመታደግ ይጥራል፡፡ በተለይም አብዛኛዎቹን ተጠቃሚዎች ዳያስፖራና የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች በመሆናቸው ቤት ለመሥራት ጊዜ ሲያጥራቸው ይታያል፡፡ ለእነዚህም ሰዎች ድርጅቱ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
አቶ ሰይፋ፡- ሆሴዕ ሪል ስቴት በቀጣይ የተለያዩ አፓርታማዎችን ገንብቶ ለደንበኞች ለማስረከብ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እነዚህንም አፓርታማዎች በሚገነቡበት ወቅት የደንበኞችን ዕርካታ በጠበቀ መልኩ ይሆናል፡፡ ግንባታውንም ከተባለበት ጊዜ አስቀድሞ ለማስረከብና በተሻለ መንገድ ለማስፈጸም ጥረቶችን የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የቤት ባለቤቶች በባለ ንብረትነታቸው መብት ተጠብቆ የፈለጉትን አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ጥረቶችን ያደርጋል፡፡