Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትትችት ያልተለየው የዓለም ዋንጫውና የኳታር ‹‹ጆሮ ዳባ…›› ማለት

ትችት ያልተለየው የዓለም ዋንጫውና የኳታር ‹‹ጆሮ ዳባ…›› ማለት

ቀን:

አራተኛ ቀኑን የያዘው የኳታር ዓለም ዋንጫ ከመክፈቻው ቀን በኋላ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ቀድሞም በትችትና በውዝግብ ታጅቦ የነበረው ውድድሩ አሁንም ውርጅብኝ ሳይለየው ቀጥሏል፡፡

በተለይ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ዕንከን እየፈለጉ፣ አዘጋጇን አገር እያብጠለጠሉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የእንግሊዙ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱን በቀጥታ ሳያስተላልፍ ቀርቷል፡፡

የኳታርን ዓለም ዋንጫ እንደማያስተላለፉ ካሳወቁ አገሮች መካከል አንዷ ፈረንሣይ ናት፡፡  

በተለይ የእንግሊዙ ቢቢሲ፣ ዴይሊ  ሜይል፣ ዘ ጋርዲያን፣ የአሜሪካ ኤቢሲ ዜና እንዲሁም ሲኤንኤን ሌት ተቀን ዕንከኖችን ፈልገው አዘጋጇን ማጣጣላቸውን ተያይዘውታል፡፡

የውዝግቡ መነሻ ሦስት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እነሱም በሙስና መጠርጠር፣ የኳታር የሰብዓዊ መብት አያያዝና የአየር ንብረት ጉዳዮች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ ምንም እንኳን የዓለም ዋንጫ መሰናዶ ጋር ተያይዞ ክርክር ባይታጣም፣ የኳታር ያህል ውዝግብ የፈጠረ አለመኖሩን የበርካቶችን ቀልብ ገዝቷል፡፡  

ሁለት ኦሊምፒኮችን ያዘጋጀችው ቻይና እንኳን ትልቅ የሰብዓዊ መብት ሥጋት እያለባት ማስተናገድ ችላለች፡፡ በ1936 ኦሊምፒክ በናዚ ጀርመን መስተናገዱ ቢታወስም፣ የኳታርን ያህል ግን ክርክር አለማስተናገዱ ይነሳል፡፡

ኳታር ከፍተኛ ውግዘት ማስተናገዷን ተከትሎ፣ ባለሥልጣኖቿ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ፍትሐዊና ለማንኛውም ተመልካች ክፍት እንደሚሆን በመግለጽ የተሰነዘረውን ብዙ ትችት ውድቅ አድርገዋል። በተለይ ኳታር ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ስሟ በተደጋጋሚ ቢነሳም፣ አዘጋጆቹ እንዳሉት በአገሪቱ ውስጥ በስደተኛ ሠራተኞች መብት ላይ ከፍተኛ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸው፣ የሚወጡ ዘገባዎችን በተመለከተ ፀረ ዓረብ ወገንተኝነትን መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

 በአንፃሩ ኳታር እንደ ሌሎች ቀደምት አስተናጋጆች በስታዲየምና በሥልጠና ተቋማት ረገድ አነስተኛ የእግር ኳስ መሠረተ ልማት ያላት ናት፡፡ የዓለም ዋንጫን ባልተለመደ ወቅት ላይ መደረጉ ለአብዛኛውን ተካፋይ አገር ሥጋት ላይ ሊጥላቸው አስችሎ ነበር፡፡ ሥጋቱን ተከትሎም አገሪቱ በዚህ አየር ንብረት ውድድሩን ማስተናገድ እንደማትችልና ይህም ሊሳካላት የቻለው በሙስና ብቻ ነው የሚል መከራከሪያ ዋነኛው ነበር፡፡

ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2014 የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ባወጣው ሪፖርት፣ ጉቦ መቀበል ክስ ቢመሠርትም ምንም ዓይነት ጥፋት አለመኖሩን አረጋግጧል። ሪፖርቱ ከሦስት ዓመት በኋላ ለሕዝብ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ‹‹በተወዳዳሪ አገሮችም ሆነ በእግር ኳስ ኃላፊዎች ምንም ዓይነት ያልተገባ ድርጊት ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ማስረጃ አልተገኘም፤›› ከመባሉም በላይ በዚህ ምክንያት ‹‹ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንደማይወስድ›› ይፋ አድርጓል፡፡

የ32 አገሮችን ውድድር ለማስተናገድ ኃላፊነት ከተረከበች በኋላ፣ በርካታ ግዙፍ የግንባታ ፕሮጀክት ጀመረች። 95 በመቶ የሚሆነው የኳታር የሠራተኛ ኃይል በስደተኞች የተዋቀረ ሲሆን፣ በተለይ በዓለም ዋንጫ ላይ የሚሠሩትን ጨምሮ ከስደተኛ ሠራተኞች ጋር በተያያዘ ሰፊ እንግልት ፈጽማለች የሚል ክስ ይቀርብባታል፡፡

ዕለታዊው የእንግሊዝ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን አድርጌያለው ባለው ጥናት መሠረት፣ ከ2012 ጀምሮ ከህንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከስሪላንካ፣ ከኔፓልና ከባንግላዴሽ የመጡ ከ6,500 በላይ ስደተኞች በኳታር መሞታቸውን ዘግቧል። ከእነዚህ ሞት ውስጥ 37ቱ ከዓለም ዋንጫ ስታዲየም ግንባታ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው ሲል ያስቀምጣል፡፡

ዓለም አቀፉየ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ በበኩሉ፣ ዓለም አቀፋዊ ትችት ቢገጥመውም ኳታርን ከትችቱ ተከላክሏል፡፡ የወቅቱ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አስተያየት ከሆነ፣ ስደተኞች ቢሞቱም በኳታር መሠረተ ልማት ላይ በመሥራት ‹‹ክብርና ኩራት›› ያገኛሉ ሲል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ኳታር የመጀመሪያውን ሙሉ በሙሉ ከካርቦን ልቀት ንጹህ የሆነ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ውድድር ለማሰናዳት ቃል መግባቷን ተከትሎ፣ ውድድሩ በአጠቃላይ 3.6 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ እንደሚለቀቅ ፊፋ ቢገመትም 95 በመቶ የሚሆነው የልቀት መጠን ከአየር ጉዞ እንደሚመጣ ይተነብያል፡፡

 በዚህም ጫና የበዛበት ፊፋ በፕሬዚዳንቱ በኢንፋንቲኖና በዋና ጸሐፊዋ ፋጡማ ሳሞራ አስተያየት መሠረት ‹‹ለጊዜው በእግር ኳስ ላይ እናተኩር›› የሚል ምላሽን ሰጥተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል ኳታር ለስደተኛ ሠራተኞች የማካካሻ ፈንድ መክፈል እንደሚገባት በተደጋጋሚ ተናግሯል።  

እንደ እንግሊዝና አውስትራሊያ ያሉ የበርካታ ቡድኖች አመራሮች በአወዛጋቢው የዓለም ዋንጫ ላይ ስላሉ ጉዳዮች ከመናገር ወደኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ውድድሩ የተከናወነበት ወቅት በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ላይ ትልቅ መስተጓጎል እንዳስከተለ የሚያነሱ አሉ፡፡ በተለይም በአውሮፓ አብዛኛው የሊግ መርሐ ግብሮች ከክረምት መጨረሻ ጀምሮ እስከ ሚቀጥለው የመፀው ወቅት ድረስ እንዲቆይ ያስገድደዋል ይላሉ፡፡ እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የጀርመኑ ቡንደስሊጋና የስፔን ላሊጋ ያሉ ታላላቅ ፕሮፌሽናል ሊጎች የዓለም ዋንጫን ተከትሎ የሁለት ወራት ዕረፍትን አስታውቀዋል።

ከ65 ሺሕ በላይ ተጫዋቾችን የሚወክለው ዩኒየን ‹‹FIFPRO›› ባወጣው አዲስ ዘገባ፣ የዓለም ዋንጫው በዚህ ወቅት ላይ መከናወኑ በተጫዋቾች ላይ ጫና እንዲፈጠር አድርጓል ሲል ያስቀምጣል፡፡ በተለመደው የክረምት የዓለም ዋንጫ የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች በታሪክ በአማካይ 31 ቀናት ለመዘጋጀትና ለማገገም 37 ቀናት እንደነበራቸው ዘገባው አመልክቷል። በዚህ ዓመት የዝግጅትና የማገገሚያ ጊዜ ወደ ሰባትና ስምንት ቀናት ዝቅ ብሏል ይላል ማኅበሩ።

የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ የዝግጅት ሒደት ላይ አልኮል መጠጣትን እንደሚፈቅድ፣ አልኮል የሚገዛበትም ልዩ የደጋፊ ዞኖች እንደሚቋቋም ተገልጾ ነበር፡፡

ሆኖም ውድድሩ ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኳታር በስምንቱ ስታዲየሞች ውስጥ የአልኮል መጠጦችን እንዳይሸጥ በይፋ አግዳለች። በዚህም ውሳኔ የመጠጥ አምራች ድርጅቶችና የተሳታፊ ክለቦች ደጋፊዎችን በእጅጉ አስቆጥቷል፡፡

ምንም እንኳን የምዕራባዊያን ትችት ውድድሩ እየተካሄደም ቢቀጥልም፣ ኳታር ግን እንግዶቿን ተቀብላ እያስተናገደች፣ ለትችቱ ‹‹ጆሮ ዳባ…›› ብላ ውድድሯን ቀጥላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...