Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  ቀን:

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው፣ ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚፈቅድ ድንጋጌ የተካተተበት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

  ማክሰኞ ኅዳር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከአንድ ሳምንት በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት በተመራለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ምክክር አካሂዷል፡፡

  በረቂቁ እንደተመላከተው ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ለሁለት ዓመታት በሠራዊቱ ብሔራዊ ግልጋሎት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትን፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ተቀብሎ ግልጋሎት እንዲሰጡ ሊያደርግ እንደሚችል በረቂቁ ተብራርቷል፡፡

  ሠልጣኞቹ ግልጋሎታቸውን ሲጨርሱ የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል አባል ለመሆን የሚፈልጉ ከሆነ፣ ተቋሙ በሚያወጣው መመርያ መሠረት ተያያዥ መብቶችና ጥቅሞች እንዲጠበቁላቸውና ይህንን የተመለከተ ዝርዝር አፈጻጸም በመመርያ እንደሚወጣ በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል፡፡

  ወታደራዊ ሥልጠና ከወሰዱት መካከል ፈቃደኛ የሆኑትን ለወታደራዊ ተልዕኮ አስፈላጊ ናቸው ተብለው በሚለዩ ሙያዎች፣ በመመልመል በብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይልነት ሊይዝ እንደሚችልም በረቂቁ ተገልጿል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በነበራቸው ቆይታ ብሔራዊ አገልግሎት ሊጀምር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡ በወቅቱ እንደተናገሩትም፣ አንድ ወጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከጨረሰ በኋላ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ለጥቂት ወራት የብሔራዊ አገልግሎት ዓይነት ሥምሪት እንደሚጀመር፣ ይህ አገልግሎትም ወጣቶች አገራቸውን ለማወቅ ይጠቅማቸዋል፡፡

  ‹‹… ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ከዚህ በፊት አንደነበረው አስገዳጅ አይሆንም፣ በግድ ካልዘመትክ አንልም፣ በግድ አገርህን ካላወቅህ አንልም፣ ነገር ግን አገሩን የማያውቅ ሰው ሥራ አንቀጥርም፣ ሥራ የምንቀጥረው ከፍተኛ ትምህርት ጨርሶ ሦስትና አራት ወር ወጣ ብሎ አገር ለማየትና ለመሥራት የሞከረን ሰው ነው፣ አንዱ መመዘኛችንም እሱ ይሆናል…›› ብለው ነበር፡፡

  በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ግንባታ ሥራዎች አስተባባሪ የነበሩት ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከዚህ በፊት ከሩሲያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ብሔራዊ ውትድርና የሚለውን ብሔራዊ አገልግሎት በሚል ለማስጀመር መታሰቡን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

  ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዋጅም ለመስጠት የታቀደው ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት በፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን በግልጽ ያመለክታል፡፡

  በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ሌሎች ድንጋጌዎች መካከል ለሠራዊት አባላት ስለሚደረግ ማበረታቻ በሚያብራራው አንቀጽ ይገኝበታል፡፡ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወታደራዊ አገልግሎታቸውን በላቀ ሞራል እንዲያከናውኑ ለማበረታታት ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉና በቀላሉ የማይተካ ልዩ ክህሎት ያላቸው የሠራዊት አባላት፣ ሃያ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ ኮሎኔሎችና ጄኔራሌ መኮንኖች አንድ የቤት መኪና ከቀረጥ ነፃ መግዛት እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ሰላሳ ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ ሁሉም የሠራዊቱ አባላት አንድ የቤት መኪና ከቀረጥና ግብር ነፃ መግዛት እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡

  በረቂቅ አዋጁ ማንኛውም በክብር የተሰናበተ የሠራዊት አባል የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥም አደጋውን ለመመከት፣ መንግሥት ወይም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዳግም ጥሪ ሲያደርግ ለጥሪው ምላሽ የመስጠትና አገራዊ ግዴታውን የመወጣት ኃላፊነት እንደሚኖርበት ተብራርቷል፡፡

  በዚህም በዳግም ጥሪው መሠረት ወደ ሠራዊቱ የተቀላቀለ የሠራዊት አባል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው፣ በቀጣይነት እንዲያገለግል በነበረበት የማዕረግ ደረጃ መልሶ ሊቀጥረው እንደሚችልም በረቂቁ ተደንግጓል፡፡

  በሌላ በኩል በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ያልተካተተውን የፊልድ ማርሻል ማዕረግ በረቂቅ አዋጁ ተካቶ ቀርቧል፡፡

  የፊልድ ማርሻል ማዕረግ ማለት፣ ‹‹አገርን ከከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ለማውጣት ለሚፈጸም ከፍተኛ የውትድርና አመራር ብቃት በልዩ ሁኔታ በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የሚሰጥ ከፍተኛ የውትድርና ማዕረግ ነው፤›› የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...