Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በግል ተቋማት የሚደርሱ በደሎችን እንዲመረምር ሥልጣን የሚሰጥ ረቂቅ...

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በግል ተቋማት የሚደርሱ በደሎችን እንዲመረምር ሥልጣን የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ‹‹በትልልቅ›› የግል ተቋማት ውስጥ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን እንዲመረመር ሥልጣን የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

ፓርላማው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የተቋሙን ሥልጣንና ተግባር የሚያሰፋውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ማክሰኞ ኅዳር 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ላካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ ከአራት ዓመት በፊት የወጣውን የተቋሙን አዋጅ ቁጥር 1142/2011 የሚሽር ነው፡፡

- Advertisement -

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከያዛቸው ዋነኛ ለውጦች ውስጥ አንዱ የሆነው የተቋሙን ሥልጣን የማስፋት ጉዳይ፣ ‹‹በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን መቀበልና ምርመራ በማካሄድ መፍትሔ ሐሳብ መስጠት›› በሚል የተቋሙ ሥልጣንና ተግባር ሆኖ በረቂቅ ላይ የተቀመጠ ነው፡፡

የተቋሙ የዕንባ ጠባቂነት ኃላፊነት ‹‹ለዜጎች በሙሉ›› መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ ‹‹በደሎች ግን እየደረሱ ያሉት በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ብቻ አይደለም፤›› ሲሉ የተቋሙ ኃላፊነት መገደብ የተወሰኑ በደሎችን ብቻ እንዲመለከተ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአብዛኛው ‹‹በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ›› እየሆነ በመሄዱ፣ የግል ተቋማት ‹‹ከመንግሥት ባልተናነሰ›› ሠራተኞች እየቀጠሩና እያስተዳደሩ በመሆናቸው የተቋሙ ሥልጣን እንዲሰፋ የተፈለገበትን አንድ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ዕንባ ጠባቂው ገለጻ፣ ወደ ተቋሙ ከሚመጡ አቤቱታዎች ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑት ‹‹በተቋሙ ሥልጣን ሥር የማይወድቁ›› ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ‹‹ከትልልቅ የግል ተቋማት›› የሚመጡ አቤቱታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ተቋሙ ከግል ተቋማት የሚመጡ አቤቱታዎች የሚመረምር ክፍል አቋቁሞ ‹‹ሊመረምር ይገባል›› የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳደረሱ እንዳለ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ላይ ተቋሙ አንድ ዋና ዕንባ ጠባቂ፣ አንድ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ፣ እንዲሁም አንድ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ አካል ጉዳኞችና አረጋውያን ዕንባ ጠባቂ እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በአንፃሩ ‹‹የልዩ ልዩ ዘርፎች ዕንባ ጠባቂዎች›› እንደሚኖሩ አስቀምጧል፡፡

የልዩ ልዩ ዘርፎች ዕንባ ጠባቂዎች በሚል ‹‹በጥቅሉ›› በረቂቁ ላይ የተቀመጠው ተቋሙ ‹‹ለወደፊት›› አቤቱታ ለሚበዛባቸው ዘርፎች ራሳቸውን የቻሉ ዕንባ ጠባቂዎችን ለመመደብ ዕቅድ ስላለው እንደሆነ የገለጹት እንዳለ (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ለግል ዘርፉ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በግሉ ዘርፍ በሚሾም ዕንባ ጠባቂ ሥር ዘርፉ ላይ የሚያተኩር የምርመራ ክፍል እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡

የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ ተቋሙ የሚመረምረው ‹‹በትልልቅ›› የግል ተቋማት ውስጥ የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን ነው፡፡ ‹‹ትልልቅ›› የሚባሉት የግል ተቋማት ከአዋጁ መፅደቅ በኋላ በሚወጣ መመርያ የሚወሰኑ መሆናቸውን የሚገልጹት እንዳለ (ዶ/ር) የግል ባንኮች፣ ማሽኖችን የሚጠቀሙ ትልልቅ ፋብሪካዎችና የአበባ እርሻዎች በብዛት የአስተዳደራዊ በደል ከሚቀርብባቸው የግል ዘርፍ አካላት ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ከግል ተቋማት የመጡ አቤቱታዎች ምዘና፣ እንዲሁም በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ብዛት ተቋሙ ምርመራ የሚያደርግባቸውን የግል ተቋማት ለመለየት እንደ መነሻ ሊጠቀም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ተቋሙ ያለው የሰው ኃይል ብዛትም ከግምት ውስጥ እንደሚገባ ዋና ዕንባ ጠባቂው አክለዋል፡፡

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተካተቱ ዋነኛ ጉዳዮች ውስጥ ሌላኛው የተቋሙ ዕንባ ጠባቂዎችና መርማሪዎች ያለመከሰስ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ የተቋሙ ዕንባ ጠባቂ ከምክር ቤቱ ዕውቅና ውጪ የምርመራ ሥራ የሚያከናውን ዳይሬክተር ጄኔራል፣ ዳይሬክተር ወይም መርማሪ ከሆነ ደግሞ ዋና ዕንባ ጠባቂው ሳይፈቅድ ወይም ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እንጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር እንደማይያዝ፣ እንደማይከሰስና እንደማይታሰር ደንግጓል፡፡

ይህ አሠራር በ2011 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ በተተካው በቀድሞ አዋጅ ላይ እንደነበር የሚናገሩት እንዳለ (ዶ/ር)፣ መብቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ረቂቅ ሲቀርብ ‹‹በስህተት›› እንዲሻር የተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው ምክር ቤት አባላት ለዳኞችና ለምክር ቤት አባላት በሕገ መንግሥት ከተሰጠው ያለመከሰስ መብት ጋር ግርታን ስለፈጠረ እንዲሻር ያደረጉት›› ሲሉ፣ አሁን ባለው አዋጅ ላይ ያለ መከሰስ መብት የሌለበትም ምክንያት አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ዕንባ ጠባቂው ገለጻ ለተቋሙ ዕንባ ጠባቂዎች የሚታሰሩት በምክር ቤቱ መብታቸው ሲነሳ እንደሆነ ተብሎ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጠው የሚመለከተው አፈ ጉባዔውን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም ዕንባ ጠባቂዎች የሚታሰሩት ወይም የሚከሰሱት ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ ሲወስን ሳይሆን፣ አፈ ጉባዔው አውቆ ምላሽ ሲሰጥበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ47 አንቀጾች የተዋቀረው ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራ ሲሆን፣ በቀጣይ ሕዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱበት ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...