Wednesday, November 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ያከትማል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ቢፈጠርም፣ ከናይሮቢው የወታደራዊ ኃላፊዎች ስምምነት በኋላ የሚሰሙ ተቃራኒ ነገሮች ከወዲሁ ሥጋት እየፈጠሩ ነው፡፡ ከትግራይ ክልል እየወጡ ያሉ መረጃዎች የሰላም ስምምነቱን ሊያስቀለብሱ በሚችሉ ድምፀቶች መታጀባቸው፣ በፌዴራል መንግሥት በኩል ደግሞ ሁሉም ነገሮች በሚገባ እየተከናወኑ መሆናቸውን በደምሳሳው የሚያስተጋቡ መልዕክቶች መተላለፋቸው አሁንም ያልጠሩ ጉዳዮች እንዳሉ እያሳበቁ ነው፡፡ በሰላም ስምምነቱ መሠረት መከናወን ያለባቸው ሥራዎች በቅደም ተከተል እንዲካሄዱ ሲጠበቅ፣ ለስምምነቱ መፍረስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ፕሮፓጋንዳዎች መብዛታቸው ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡ አንደኛው ከሌላኛው ወገን ለማጣላት ወይም ለማካሰስ የሚያግዙ ፕሮፓጋንዳዎች ከስምምነቱ መርህ ጋር የሚጋጩ በመሆናቸው፣ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ ሕወሓት ጥርት ያለ አቋማቸውን በግልጽ ማስታወቅ አለባቸው፡፡ ፕሮፓጋንዳው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰላም ሒደቱን እየጎዳው እንደሆነ ይታወቅ፡፡

በናይሮቢው ስምምነት ላይ የተጠቀሰው ‹‹የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ለቀው እንዲወጡ›› የሚለው ሐረግ ላይ በመመሥረት፣ የኤርትራ ጦር ወደ ድንበሩ እንዲመለስ እየተጠየቀ ነው፡፡ ከዚህ ጥያቄ ጋርም ጦሩ ግድያና ዘረፋ እየፈጸመ ነው እየተባለም ነው፡፡ በኤርትራ ወገን በኩል የትግራይ ክልል ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች የሰለቸና ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መሆኑ በስፋት እየተስተጋባ ነው፡፡ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተመለከተ ከግራም ሆነ ከቀኝ የሚሰማ አስተማማኝ መረጃ ባለመኖሩ፣ ሌላ ዙር ጦርነት ሊያስቀሰቅስ የሚችል ፕሮፓጋንዳ ግን አየሩን ሞልቶታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ለውጭ ጣልቃ ገቦች የሚመች መደላድል በቀላሉ ስለሚገኝ፣ የሰላም ሒደቱ ይታወክና የበለጠ ጥፋት ሊደርስ ይችላል፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተቀሰቀሱ ጦርነቶች አብዛኞቹ፣ በተዛቡ የሚዲያ ዘገባዎች ወይም በፕሮፓጋንዲስቶች እንደሆነ ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ጥናት አመልክቷል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተለይ በፕሮፓጋንዳው መስክ ምን ዓይነት ተዋንያንን አሠልፎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የምዕራቡ ዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች እንዴት ሲዘግቡ እንደነበርም አይረሳም፡፡

አሁንም ደግመን ደጋግመን ማሳሰብ የምንፈልገው ከኢትዮጵያ ምድር ጦርነት በፍጥነት እንዲቆም ነው፡፡ ከጦር መሣሪያ ይልቅ በሐሳብ መሟገት፣ ልዩነትን ከጉልበት ይልቅ በውይይት ወይም በክርክር ማስተናገድ፣ በሕዝብ ስም እየማሉ ከማጭበርበር ይልቅ የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅና ጠመንጃን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስከብራል፡፡ ‹‹ውኃ ቀጠነ›› እያሉ በረባ ባልረባው እርስ በርስ ለመፋጀት ማድባት አስነዋሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጽ የሚያስቸግር የመረረ ድህነት ውስጥ ሆኖ፣ የጥቂቶችን ፍላጎት ለማርካት ሲባል አገርን ሲኦል ለማድረግ እንቅልፍ ማጣት አስነዋሪ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ፀባቸውንና ፍቅራቸውን በልክ ቢያደርጉት የኢትዮጵያ ሕዝብ አይጎዳም ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይ ሕዝቡን በብሔር፣ በእምነት፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰሉት በመከፋፈል አገር መበጥበጥ በመለመዱ ከተራ ግጭት ታልፎ አገር አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ተገብቷል፡፡ አሁንም በሕዝብ ስም የምትምሉና የምትቆምሩ ወደ ቀልባችሁ ተመልሳችሁ ሰላም እንዲሰፍን ሥሩ፡፡ ማንኛውም ዓይነት ጦርነት ከዕልቂትና ከውድመት በስተቀር ለሕዝብ የሚበጅ መፍትሔ የለውም፡፡ የሰላም ስምምነቱ እንዲሰናከል የምትጥሩ በሙሉ ከድርጊታችሁ ታቀቡ፡፡

በቅርቡ የተፈረመው ግጭት የማስቆም የሰላም ስምምነት ውጤት ሊያመጣ የሚችለው፣ በስምምነቱ መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት በቅደም ተከተል መፈጸም ሲጀምሩ ነው፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት 70 በመቶ የሚሆነውን የትግራይ መሬት ተቆጣጥሮ ስምምነቱ ሲፈረም፣ ብዙዎች የሰላሙ ሒደት በመልካም ሁኔታ ይከናወናል የሚል ተስፋ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ከስምምነቱ በተቃራኒ የሚሰሙ ሰላምን የሚገዳደሩ ድምፆች ሲበዙና ከዚህ ቀደም በፕሮፓጋንዳው መስክ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው የውጭ ሰዎች አንገታቸውን ቀና ሲያደርጉ፣ አንፃራዊው ሰላማችን በቀላሉ መደፍረስ የለበትም የሚሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ደምፃቸው ከፍ ብሎ መሰማት ይኖርበታል፡፡ ቀደም ሲል በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የደረሱ ዕልቂቶች፣ መፈናቀሎችና ሰቆቃዎች እንደገና እንዲያገረሹ ዕድል መሰጠት የለበትም፡፡ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም እንዲደፈርስ የሚያግዙ ፕሮፓጋንዳዎች ሲበዙ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ መዘናጋት የወገኖቻችንን መከራ ከማብዛት ውጪ የሚፈይደው የለም፡፡ አንፃራዊው ሰላም ደፍርሶ ሌላ ዙር ጦርነት እንዲካሄድ ከየአቅጣጫው የሚነዛውን ፕሮፓጋንዳ ተባብሮ ማክሸፍ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ነጋዴዎች ሰለባ እንዳትሆን ጥንቃቄ ይደረግ፡፡

ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በምትገባበት ጊዜ ሊታደጓት ከየጎራው የሚጠራሩ ልጆቿ፣ ጦርነቱን በጨዋነት አጠናቃ ወደ ሰላማዊ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሽግግር ስክነትና ብስለት ይፈልጋል፡፡ ከቂምና በቀል በመፅዳት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በማሳየት፣ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር አውዳሚው ጦርነት እንዳይከሰት ክፍተቶችን መድፈን ተገቢ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት የማይመራ ጦርነት ንፁኃንን በመግደል፣ በማፈናቀል፣ በመዝረፍ፣ በመድፈርና ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙበት ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚገባ ታይቷል፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጀምሮ በዘር ማጥፋት የሚያስጠይቁ አደገኛ ድርጊቶች ተስተውለዋል፡፡ እነዚህ ለሕግና ለታሪክ ሰነድነት ከመጥቀም አልፈው፣ ለማስተማሪያ ጭምር የሚውሉ እንደሚሆኑ መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ጭካኔዎች በአገራቸው ውስጥ ዳግም እንዳይከሰቱ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ነገ በሕግም ሆነ በታሪክ ከሚያስጠይቁ ወንጀሎች ራሳቸውን ከወዲሁ መግታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥትም ባለበት ኃላፊነት መሠረት የጦርነቱን ፍፃሜ ያሳምር፡፡ ኢትዮጵያ የሚጠቅማት ዘለቄታዊ ሰላምና ዕድገት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያንን እንደገና ወደ ጦርነት ሊከቱ የሚችሉ አጉል ባህርያት መገራት አለባቸው፡፡ ጦርነት የጥጋበኞችና የእብሪተኞች መሣሪያ እንጂ ማንንም ከማንም ነፃ የሚያወጣ፣ ወይም የተቀደሰ ዓላማ ለማስፈጸም የሚያገለግል አስፈላጊ ነገር እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሰላም ስምምነቱ ያልጠሩ ጉዳዮች ካሉ ችግሮችን በመነጋገር መፍታት እየተቻለ፣ ምክንያት እየፈለጉ ሴራ መጎንጎንም ሆነ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ መዘፈቅ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰለቸው በጦርነት ውስጥ መኖርና በመረረ ድህነት ውስጥ ኖሮ ማለፍ ነው፡፡ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ እንቆረቆራለን የምትሉ የመጀመሪያ ሥራችሁ ግጭት በማስቆም ሰላም ማስፈን ይሁን፡፡ የአንድ ወገን የበላይነትን ለማስፈን ስትሉ ብቻ የነገር ድር እያደራችሁ አገር አትበጥብጡ፣ ሕዝብ አታሰቃዩ፡፡ በእናንተ ምክንያት ሕፃናት ያለ አሳዳጊ ቀርተዋል፡፡ ወላጆች ጧሪና ቀባሪ አጥተዋል፡፡ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ተፈናቅለው ተስፋ ቢስ ሆነዋል፡፡ አርሰውና ነግደው ኑሮአቸውን የሚገፉ ወገኖች ከጎጇቸው ተፈናቅለው ለልመና ተዳርገዋል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የምታስቡ ከሆነ ለሰላም መስፈን ሥሩ፡፡ የሰላም ስምምነቱም ተግባራዊ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...