Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበግንባታ ቦታዎች የሚከሰት ሞትና የአካል ጉዳት አሳሳቢ መሆኑ ተነገረ

በግንባታ ቦታዎች የሚከሰት ሞትና የአካል ጉዳት አሳሳቢ መሆኑ ተነገረ

ቀን:

ሰው ሳይሞት የሚጠናቀቅ የግንባታ ፕሮጀክት እየጠፋ መሆኑ ተገልጿል

የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በግንባታ ቦታዎች በሠራተኞች ላይ የሚደርስ ሞትና የአካል ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው የ2015 ዓ.ም. የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሸኞ ኅዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያቀርብ ነው፡፡

ፓርላማ የተገኙት የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች እንደተናገሩት በግንባታ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሞትና የአካል ጉዳት እንደሚደርስ ቢታወቅም እስካሁን ድረስ ተጠያቂ የሆነ አካል የለም፡፡

በቅድመ ኮንትራት ስታንዳርድ ሰነድ ውስጥ ከአልባሳት እስከ ደኅንነት መቆጣጠሪያና የጥንቃቄ ምልክቶች እንዲሟሉ የሠፈረ ቢሆንም፣ በተግባር የሚታየው አሠራር ግን በተቃራኒው እንደሆነ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲሱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የግንባታ ቦታዎች ሞትና የአካል መጉደል መኖሩን፣ በአንዳንዶቹ ሥፍራዎች ደግሞ የሚደርስ ጉዳትን በትክክል ሪፖርት እንደማይደረግ፣ ይልቁንም ጉዳት ሲደርስ የግንባታ ሥፍራውን ዝግ በማድረግ ምን እንደተከሰተ ሳይታወቅ እየታለፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የሠራተኞች ደኅንነት በጣም አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት፣ ስለጉዳዩ ያለውን ሁኔታ ለማወቅና በቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች ለመለየት ከዓለም ባንክ ጋር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የዜጎችን ደኅንነትና ጤንነት መጠበቅ አለበት ቢባልም ወደ ታች ሲወርድ በግንባታ ቦታዎች በሚከሰት አደጋ ምክንያት የዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን አሁን ሰው ሳይሞት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አኳያ ትልቅ ትኩረት መደረግ አለበት፤›› የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ኮንትራክተሩ፣ የግንባታው ባለቤትና የመንግሥት መዋቅር በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡

አክለውም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ቁጥር ሲጨምር አደጋው እየጨመረ መምጣቱን፣ እንዲሁም ኮንስትራክሽን ሲቀንስ ደግሞ አደጋው እንደሚቀንስ ገልጸው፣ የሚከሰተው አደጋ እምብዛም ሪፖርት እንደማይደረግ አስረድተዋል፡፡

ማንኛውም ሕንፃ ከአምስት ወለል በላይ ከሆነ መወጣጫዎቹ በብረት እንጂ በእንጨት እንዲሆኑ የማይፈቀድ መሆኑን፣ በተግባራት የሚታየው ግን ተቃራኒ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

በኮንስትራክሽን አካባቢዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰቱ አደጋዎች በግዴለሽነት እንደሚደርሱ፣ የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎች ባለመቅረባቸውና ሠራተኞችም የደኅንነት መሣሪያዎችን ባለመጠቀማቸው አደጋው የሚከሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበርካታ የግንባታ አካባቢዎች ሠራተኞችን ከመሐንዲሶች፣ እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦችን ከግንባታ ሠራተኞች መለየት እንደሚከብድና የተለየ ዓይነት አለባበስና ጥንቃቄ የተሞላበት አሠራር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በኮንስትራክሽን ቦታዎች የሚከሰቱ ሞትና የአካል ጉዳት አደጋዎች ከሕንፃ ላይ በመውደቅ፣ በሚስማር መፈናጠርና በመሰል በጥንቃቄ ጉድለት የሚመጡ በመሆናቸው የኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ የግንባታ ባለቤቶችም ሆኑ አማካሪዎች ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹የግንባታ ቦታዎች የጦር ሜዳ እየመሰሉ ነው፣ በሚገባ ሪፖርት ስለማይደረጉ እንጂ በርካታ አደጋዎች እየተከሰቱ ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኮንስትራክሽን ሳይቶች አደጋዎች ሲከሰቱ ኮንትራክተሮች ጉዳዩ እንዳይሰማ በመፈለግ በራሳቸው ትራንስፖርት የተጎዳውን ሰው አፋፍሰው ይወስዳሉ፡፡

በኮንስትራክሽን አካባቢ የሚታየው አደጋ በርካታ ከመሆኑም በላይ ሪፖርት እንደማይደረግ ገልጸው፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ሰዎች አፈር ውስጥ ሲቀበሩ ወይም የከፋ ዕገዛ የሚያስፈልገው አደጋ ሲያጋጥም ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ንጋቱ እንዳሉት በ2014 ዓ.ም. በኮንስትራክሽን የሥራ ላይ አደጋ የ14 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ በ21 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን ሪፖርት ተደርጓል፡፡

 አደጋዎቹ እየደረሱ ያሉት የኮንትራት ሥራ በሚሰጣቸው የቀን ሠራተኞች ላይ መሆኑን፣ ሠራተኞቹም ሥራውን ፈጥነው ለማጠናቀቅ ሲንቀሳቀሱ አደጋ እየደረሰባቸው መሆኑን አቶ ንጋቱ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከአደጋዎቹ መካከል በቁፋሮ ጊዜ ከመሬት ያወጡት አፈር በላያቸው ላይ እየተደረመሰ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ፣ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች አብዛኞቹ የመወጣጫ ደረጃ እንጨት በመሆኑ ዝናብና ፀሐይ ሲፈራረቅበት የቆየው መወጣጫ እየተደረመሰ እንደሚሞቱ ወይም ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ አስረድተዋል፡፡

አደጋ እየደረሰባቸው ያሉት ሠራተኞች አብዛኞቹ ከገጠር የሚመጡና  የኮንስትራክሽን ሥራ ላይ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ምንም ዓይነት ሥልጠና ሳይወስዱ ቀጥታ ወደ ሥራ ስለሚሰማሩ፣ በዚህ ምክንያትም ሥራ በጀመሩበት ዕለት ሕይወታቸው ያለፉ ሠራተኞች እንዳጋጠሟቸው አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡

 ይህ ሁሉ እየተከሰተ ያለው በኮንትራክተሮች፣ በባለቤቶችና በተቆጣጣሪዎች ቸልተኝነትና ሠራተኞች እንዴት ራሳቸውን ከአደጋ መከላከል እንዳለባቸው በቂ ሥልጠና ባለመሰጠቱ፣ ለተጠያቂነት ሥፍራ ባለመሰጠቱና በአደጋ ለሚደርስ ጉዳት የሚከፈለው ካሳ ወይም ተጠያቂነት አለመኖር ችግሩን እንዳባባሰው አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ አባል አምሐ ስሜ (ኢንጂነር) ስለሁኔታው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኮንስትራክሽን የሥራ ላይ ደኅንነት በየትኛውም አገር ተግባራዊ የሚደረግና  ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

የሥራ ላይ ደኅንነት ሲሟላ ኮንትራክተሩም ሆነ ዘርፉ ተጠቃሚ እንደሚሆን የሚናገሩት አምሐ (ኢንጂነር)፣ በኮንስትራክሽን ላይ ስለሚረደጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች ማስተማርና ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በሌላው አገር ከምንም በላይ ደኅንነት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሠራ ጠቁመው፣ በዚህም የተነሳ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎቹን ከ50 በመቶ በላይ ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡

በሌሎች አገሮች የኮንስትራክሽን አካባቢዎች ሠራተኞች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የሥራ ላይ ቅድመ ጥንቃቄዎች የግንዛቤ ገለጻ እንደሚደረግ፣ በደኅንነት መሣሪያዎችም ላይ የቅድመ ጥንቃቄ ማረጋገጫ ተደርጎ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የአንድ ሕንፃ ግንባታ የጨረታ ማስታወቂያ ሲወጣና ግዥ ሲፈጸም አንዱ መለኪያና ተወዳዳሪው ሊለካበት የሚገባው፣ በግንባታ ሒደት ለደኅንነት የሚያደርገው ጥንቃቄ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

አምሐ (ኢንጂነር) እንደሚሉት፣ በአሁኑ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ በኮንስትራክሽን ሳይቶች የሚደርሱ አደጋዎችን በተደራጀ መንገድ ማግኘት አይቻልም፡፡ ተቆጣጣሪ ተቋሙ የሚወጡ ሕጎችን በሚገባ መተግበርና መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ ችግሩን እንዳባበሰው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አንድ ኮንትራክተር አንድን ሕንፃ በውሉ መሠረት ለመገንባት ስምምነት ላይ ሲደርስ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ተገምግመው ፈቃዱ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...