Thursday, September 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለሦስትና አራት እግር ተሽከርካሪዎች የሚመሩበት የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ የአሠራር መመርያ ሳይዘጋጅላቸው በኅብረት ሥራ በመደራጀት ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩትን የባለሦስትና አራት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች የሚመሩበት የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ተደራጅተው በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የክትትልም ሆነ ቁጥጥር ሥራ እንደማያደርግባቸው ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ እፀገነት አበበ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የባለሦስትና አራት እግር የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከዚህ ቀደም ተጠሪነታቸው ለትራንስፖርት ቢሮ ባለመሆኑ  በርካታ ችግሮች ያጋጥሙ ነበር፡፡

በተለይ የትራፊክ ፍሰት መስተጓጎል፣ ከጭነት አቅም በላይ ማሳፈር፣ እንዲሁም ወጥ የትራንስፖርት ታሪፍ ባለመኖሩ ተገልጋዮች በከፍተኛ ምሬት ጥያቄዎችን ያነሱ እንደነበር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ቢሮው የአሠራር መመርያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ በከተማዋ ትራንስፖርት ፖሊሲ ላይ የሠፈረው ከተማዋን የሚመጥን ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርት የማስፋት ዕቅድ ሳይዘነጋ፣ በዚህ ወቅት ያለውን የትራንስፖርት ፍላጎት መነሻ በማድረግ፣ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ቢሮው በሚያስቀምጠው መመርያና የሥራ አቅጣጫ ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቢሮው የሚዘጋጀው መመርያ የባለሦስትና አራት እግር የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ታፔላ ወጥቶላቸው፣ የትራፊክ መጨናነቅ በማይኖርባቸው ቦታዎች፣ የትራንስፖርት ቢሮው በሚመርጠው የጉዞ መስመሮችና የታሪፍ ተመን ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚሉትን ዓበይት ጉዳዮች ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡

የአሠራር መመርያው ከመጽደቁና ከመተግበሩ አስቀድሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ የትራንስፖርት ቢሮው ካለፈው ሳምንት አንስቶ ከከተማዋ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ እንዲሁም ከባጃጅ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጋር ውይይቶች ማድረግ መጀመሩ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የባለ ሦስትና አራት እግር ተሽከርካሪ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎችን ማወያየት  በተያዘው ሳምንትም እንደቀጠለ ወ/ሮ እፀገነት አስረድተዋል፡፡

መመርያው በሥራ ላይ የሚውልበትን ትክክለኛ ቀን በዚህ ወቅት መናገር ባይቻልም፣ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የትራንስፖርት ቢሮው እስካሁን ስምንት ሺሕ ተሽከርካሪዎችን መመዝገቡ የታወቀ ሲሆን፣ ከተመዘገቡት ውጪ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የባለ ሦስትና አራት እግር ተሽከርካሪዎች እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡

በጎፋ ኮንዶሚንየም፣ በላፍቶና በጀሞ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ በተለምዶ ባጃጅ በሚባሉ ተሽከርካሪዎች የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ተስፋፍተዋል፡፡ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቱን ሥርዓት ለማስያዝ ይረዳል ተብሎ እየተዘጋጀ የሚገኘው የአሠራር መመርያ በመዘግየቱ፣ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በባለሦስትና አራት እግር ተሽከርካሪ ማኅበራት ተወካዮች የተነሱ ችግሮች ትክክለኛ መሆናቸውን፣ ከአደረጃጀትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የትራንስፖርት ቢሮው ተፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በሚያወጣው የአሠራር መመርያ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ወ/ሮ እፀገነት አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች