የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባዋቀረው የኢንቨስትመንት ቡድን ሥር የሚገኙ ስድስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በ2014 ዓ.ም. ሁለት ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘታቸው ተገለጸ፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ 34 ድርጅቶችን በሥሩ የያዘው የኢንቨስትመንት ቡድኑ ከአጠቃላይ 48 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ በ31 ቢሊዮን ብር በተከፈለ ካፒታል በዚህ ሳምንት ሥራ መጀመሩን፣ የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቢሮ ኃላፊ አደሬ አሰፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ያልተከፈለው ቀሪ 18 ቢሊዮን ብር እንደ ድርጅቶቹ የምሥረታ ወቅት በተለያየ ጊዜ የሚከፈል መሆኑን አደሬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ስድስቱ ድርጅቶቹ የተቋቋሙበት አጠቃላይ 48 ቢሊዮን ብር ካፒታል ራሳቸውን ችለው የተቀላቀሉትን ሲንቄ ባንክና የኦሮሚያ ካፒታል ጉድስ አክሲዮን ማኅበርን የማያካትት መሆኑን የገለጹት አደሬ (ዶ/ር)፣ ሁለቱን የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ስለሆነ ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ የቡድኑ አካል ናቸው ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ስድስት የኢንቨስትመንት ቡድኖችና ሁለት ራሳቸውን የቻሉ ድርጅቶች፣ በአጠቃላይ ስምንት ድርጅቶች የያዘ ቡድን መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡
በቡድኑ ውስጥ ያሉት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ሥር ካሉ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ድርጅቶቹ የተቋቋሙበት ደንብ በካቢኔ በማፅደቅ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ቡድኑ ምን እንደሚሠራ፣ ድርጅቶቹ ምን እንደሚሠሩ፣ የሚዋቀረው ቦርድ ተግባርና ኃላፊነትን የሚገልጽ፣ እንዲሁም የኃላፊዎችን የሥራ ድርሻ የሚያብራራ ደንብ ነው የፀደቀው ብለዋል፡፡
በዚህ ሳምንት የተቋቋመው የኢንቨስትመንት ቡድን የወደፊት ዕቅዱን እንደሚያወጣ የገለጹት አደሬ (ዶ/ር)፣ በቅድሚያ የቡድኑ የሦስት ወራት ተግባር ምን መሆን እንደሚገባው ዕቅድ በማውጣት ሥራ ይጀምራል ብለዋል፡፡
ሁሉም ድርጅቶች የኦሮሚያ ክልል የልማት ድርጅቶች ይሁኑ እንጂ፣ የሚያከናውኑ ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የልማት ድርጅቶች ኢንቨስትመንት ቡድን በግብርና፣ በግንባታ ሥራዎች፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድንና በቱሪዝም ገበያን ለማረጋጋት ያለመ ሲሆን ኢንተርፕራይዞቹ የዋጋ ንረት ለመቀነስ ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ቡድኑ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ የግሉ ተሳትፎ በብዛት በሌለባቸው፣ ጣልቃ ገብነታቸው አነስተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ጣልቃ እንዲገቡ ለማድረግ ነው። በተጨማሪም የገበያ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የክልሉን ኢኪኖሚ ለማዳበር የተቋቋመ ነው፤›› ሲሉ አደሬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በ34 የውጭ ድርጅቶች እስካሁን ድረስ ከስምንት ሺሕ በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ የብቃት ማነስን፣ ውጤታማ አለመሆንን፣ ምርታማ አለመሆንን፣ የአመራር ተግዳሮቶችን፣ የሥራ ሥነ ምግባር ጉድለት ችግሮችን የሚፈታ ቡድን ነው ሲሉ አደሬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ቡድኖቹ ‹‹ኦ ፕሮዱስ፣ ኦሮ አሴምብሊ፣ ኦሮሚያ አግሮ ግሩፕ፣ ቱምሳ ዴቬሎፕመንት ግሩፕ፣ ኦሮ ኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም ኦ ማይኒንግ›› የተባሉ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ ቱምሳ ዴቨሎፕመንት ግሩፕ በሥሩ 14 ድርጅቶችን በመያዝ ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡