Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአጣዬ የውኃ ችግርን ያቃልላል የተባለው ፕሮጀክት

በአጣዬ የውኃ ችግርን ያቃልላል የተባለው ፕሮጀክት

ቀን:

በርካታ የውኃ ጀሪካኖች ተደርድረዋል፡፡ አላፊ አግዳሚዎቹም ጀሪካን ይዘው ውኃ ለመቅዳት ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ ዕድል የቀናቸው ደግሞ የቀዱትን ውኃ በጀርባቸው አዝለው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ይጓዛሉ፡፡ ውኃ ይዘው መታየታቸው በአካባቢው ያለውን የውኃ አቅርቦት ችግር በተወሰነ መልኩ ሊቀረፍ እንደቻለ ማሳያ ነው፡፡

ይኼ ሁሉ ተግዳሮት ከገጠማቸው መካከል በአጣዬ ከተማ ቀበሌ 03  ኑሮዋን ያደረገችው ወጣት ኸውለት ሁሴን ትገኝበታለች፡፡ ወጣት ኸውለት በሰላማ አካባቢ ተወልዳ ካደገችበት ጊዜ ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ የውኃ ችግር ገፈት ቀማሽ ሆኖ መቆየቱን ትናገራለች፡፡

ከዚህ በፊት የአንድ ሰዓት መንገድ ከጓደኞቿ ጋር በመጓዝ ውኃ እንደምትቀዳ የምትናገረው ወጣቷ፣ በወቅቱ እየቀዱ የሚጠቀሙት ውኃ ንፅህናው ያልተረጋገጠ እንደነበር ታስረዳለች፡፡ ከዚህ በፊት ለምግብና ለመጠጥ የሚሆን ውኃ ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከሞላ ጎደል ንፅህናው የተጠበቀ ውኃ ለማግኘት የቻሉት ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት ባስገነባው የውኃ መስመር ነው፡፡ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕፎይታ ማግኘታቸውንም ተናግራለች፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ወድማ እንደነበር፣ በወቅቱም ውኃም ሆነ የሚላስ የሚቀመስ ማጣታቸውን መብራት፣ ውኃ፣ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን ያስታወሰችው ወጣቷ፣ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች በኋላ ከተማዋን ወደነበረችበት ለመመለስ ሰፊ ጊዜ ይፈጃል ትላለች፡፡ በተለይም ለምግብነት የሚውሉ ግብዓቶችን ለማኅበረሰቡ በትክክለኛው መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ጊዜ እንደሚፈጅ ታስረዳለች፡፡

በጦርነቱ ወቅት ለምግብነትና ለመጠጥ የሚሆን ውኃ ከምንጭ ሄደው በመቅዳት ይጠቀሙ እንደነበር፣ በዚህም የተነሳ አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የጤና ችግር ገጥሟቸው እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ እንደሚቀዳና አንዳንድ ጊዜ ውኃ ለመቅዳት የሚሠለፉ ሰዎች ቁጥርና በአካባቢው ላይ ያለው የውኃ ምጣኔ አለመጣጣም ችግር እየሆነባቸው መምጣቱን ታስረዳለች፡፡

ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ተግባራዊ ባደረገው ፕሮጀክትም ከ500 በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል የምትለው ወጣቷ፣ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች አንድ ጀሪካን በሃምሳ ሳንቲም እየቀዱ እንደሚጠቀሙ ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡

ከፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ከድጃ ይማም እንደሚሉት፣ ከዚህ በፊት አብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ ረዥም ርቀትን በመጓዝ ውኃ ይቀዳ ነበር፡፡ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቤተሰቦች የሚጠቀሙት ውኃ ብዙ በመሆኑ ችግር ውስጥ ሲወድቁ ነበር፡፡ እሳቸውም የዚህ ችግር ተካፋይ ነበሩ፡፡

‹‹በተለይም ልጅ ያለበት ቤተሰብ ውስጥ ውኃ ከሌለ ከባድ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ከድጃ፣ በአሁኑ ወቅት ለአካባቢው ቅርብ የሆነ የውኃ ቦኖ መዘርጋቱ ለበርካታ ዜጎች ዕፎይታን ቢፈጥርም፣ አሁንም ቢሆን በአካባቢው ላይ ተጨማሪ የውኃ መስመር ዝርጋታ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሰላማና አርቤሳ ሜዳ አካባቢ ሄደው እንደሚቀዱ፣ እዚያም ሄደው በሚቀዱበት ወቅት ከብቶች የሚጠጡት ውኃ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ለመጠጥነት እንደማይጠቀሙት ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ የተዘረጋው የውኃ ቦኖ በርካታ ሰዎች ተጠቃሚ ስለሚሆኑበት አንዳንድ ጊዜ ጭልጭል የምትል ውኃ እንኳን እንደማያገኙ፣ ይህንንም ችግር ተረድቶ መንግሥት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የዋሽ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን አድማሱ እንደገለጹት፣ በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ውስጥ ለመጠጥነት የሚውል የንፁህ ውኃ ፕሮጀክት በመቅረፅ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በዚህም ከ167 ሺሕ በላይ ወገኖች መጠቀማቸውን፣ በአጣዬ አካባቢም ተግባራዊ የሆኑት የውኃ ዝርጋታ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ ሰፊ ሥራ መሥራቱንና ማኅበረሰቡም ከንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለመከላከል ፕሮጀክቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡  

በአጣዬ ከተማ ሦስት ቀበሌዎች የሚሸፍንና 55 ሺሕ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 12 ኪሎ ሜትር የውኃ የመስመር ዝርጋታ መከናወኑን ያብራሩት አቶ ወንደወሰን፣ በቀጣይ በስምንት ወረዳዎች ውስጥ ተጨማሪ በጀት በመመደብ፣ የንፁህ ውኃ አገልግሎቶችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...