Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተማሪዎች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ለተማሪዎች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ለተማሪዎች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና መስጠት የሚያስችለው የዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኅዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ሆነ።

ሁዋዌ ኢትዮጵያ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሁና ከአይኮግ ኮድ ጋር ይፋ ያደረገው ‹‹ዲጂ ትራክ››፣ ተንቀሳቃሽ ዲጂታል መማርያ ክፍል ሲሆን፣ ከገጠር አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎች የቴክኖሎጂው ሥልጠና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

ዲጂ ትራክ የላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን፣ ሮቦቲክ መሣሪያዎችንና ማይክሮ ኤሌክትሮኒክስን ጨምሮ የተማሪዎችን የመማር ማስተማር ሒደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚያደርሱ መሣሪያዎች የተገጠመለት ኮንቴይነር ነው።

ሥልጠናውም በመጀመርያው ዙር በተመረጡ ከተሞች የሚሰጥ ሲሆን፣ በእሱም ተማሪዎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምሕንድስና፣ አርትና ሒሳብ (STEAM) ትምህርት ፋይዳ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ይሠራል።

ዲጂ ትራክ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቃሽና ለአጠቃቀም ምቹ ከመሆኑም ባሻገር፣ በፀሐይ ብርሃን ብቻ የሚሠራ መሆኑ በቀጣዮቹ ዓመታት በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተነግሯል።

እ.ኤ.አ. በ2025 የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገትን ለማሳለጥና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ኢትዮጵያ ላስቀመጠችው ዕቅድ፣ ዲጂ ትራክን የመሳሰሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች አስፈላጊ ናቸው ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ሦስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፣ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና አለውም ብለዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የጀመረው ዲጂ ትራክ የነገ ፕሮግራመሮችንና ሶፍትዌር ኢንጂነሮችን ለመፍጠር አልሞ፣ ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 18 ዓመት ያሉ ተማሪዎች ቴክኖሎጂን ተላምድው እንዲያድጉ የሚሠራ መሆኑን፣ የዲጂ ትራክ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤተልሔም ደሴ ተናግረዋል።

 ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በመጀመሪያ ዓመት ትግበራው፣ በዘጠኝ የክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ 3,500 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት በሚኖረው ትግበራ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

 ትምህርቱን ወስደው ያደጉ ተማሪዎች ለቴክኖሎጂው ቅርብ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂን ለመፍጠር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማዳበር፣ ብሎም ለማኅበረሰቡ ችግር ፈቺ ይሆናሉ ሲሉ ወ/ሮ ቤቴልሔም ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የቴክኖሎጂ ትምህርቱን ከሕፃናት ጀምሮ መስጠት አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ፣ የትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲና የዲጂታል ዘርፍ ኃላፊ ዘለዓለም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው።

ምንም እንኳን ካለው የተማሪዎች ቁጥር አንፃር ሲታይ ተደራሽነቱ አነስተኛ ቢሆንም፣ እንደ ዲጂ ትራክ መሰል የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን በማሳደግ በስፋት እንሠራለን ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በተለይም ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚገኙ ተማሪዎች ከቴክኖሎጂው ጋር ለመተዋወቅ በር ከፋች ነው ተብሏል። ለዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ተግባራዊነት በዋናነት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ለሥራው ስኬታማነት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም ለአይሲቲ ባለሙያዎች ሥልጠናውን በመስጠት በአቅራቢያቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ትምህርቱ እንዲሰጡ እናደርጋለን ሲሉም ኃላፊው አክለው ተናግረዋል።

ከዲጂ ትራክ ጋራ ለመሥራት የተስማማው ሁዋዌ ቴክኖሎጂ፣ በተለያዩ አገሮች በመዘዋወር የሰዎችን የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለማጎልበት ሲሠራ እንደቆየና አሁንም በኢትዮጵያ በተለይም በትምህርት፣ በኤሌክትሪሲቲና በሌሎችም ዘርፎች የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን እየሠራ ነው ያሉት በደቡብ አፍሪካ የሁዋዌ ቴክኖሎጂ ኃላፊ ሊዮ ሊዮ (ዶ/ር) ናቸው።

በኢትዮጵያ ሁሉም ሰው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከዲጂ ትራክና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠሩ ኃላፊው ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...