Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትዥንጉርጉርነታችን የተንጨፈጨፈበት ኢትዮጵያዊነት

ዥንጉርጉርነታችን የተንጨፈጨፈበት ኢትዮጵያዊነት

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ሀ) ኢትዮጵያን ለብተና እንቅስቃሴ ያጋለጣት ታሪካዊ የጎረቤት ጠላትነት አይደለም፡፡ በግብፅ ላይ ሮጦ ማላከክ አያስፈልገንም፡፡ ወይም ከውስጣችን ተነስቶ የነበረውን የብተና እንቅስቃሴ የምዕራብ ኃያላን ማገዛቸውን በነጮች የበላይነት ላይ የዓድዋ ድል ያደረሰውን ሽንፈት ከመበቀል ጋር ማያያዝም አይጠቅመንም፡፡ ቁምነገሬን በውል ማስጨበጤን ስለተጠራጠርኩ ዘወር አድርጌ ልድገመው፡፡ ጉዟችንን የሚያወላክፉ የቅርብና የሩቅ ኃይሎችን ከእነ ፍላጎቶቻቸው ማወቅና ነቅቶ መጠበቅ ግዴታችን ነው፡፡ ከእኛ ፖለቲካዊ የብስለትና የውስጥ ግብብነት ድክመት ይልቅ፣ ለዚህ ሁሉ ያደረሰን የውጭ ኃይሎች መሰሪ ፍላጎት ነው የሚል መንጠላጠያ ማበጀት፣ ወይም የእነሱን ፍላጎት ነጋ ጠባ ማውራት መፍትሔ አይሆነንም፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ፍላጎትና እንቅስቃሴ በእኛ ቁጥጥር ያለ አይደለም፡፡ ለእኛ የሚበጀን በእጃችን ውስጥ ባሉ ተግባሮችና ግዴታዎች ላይ ማተኮር ማለትም ለልዩ ልዩ የውጭ ጥቃት የሚያጋልጡንን የውስጥ ገመናዎች ለይተን እነሱን በመቀየር ላይ መጠመድ ነው፡፡

ከዚህ አተያይ አኳያ ለአገራችን ህልውና ጠላት በሆናት የእኛው ጉደኛነት ነው፣ የፖለቲካ ሰላማችንን በአግባቡ ለማደራጀት ሳንችል ለረዥም ጊዜ መቆየታችን፡፡ ከ1966 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ድረስ ድፍን 50 ዓመት ሊሞላ ነው፡፡ ለግማሽ ምዕት ዓመት ንጠት አልተለየንም፡፡ በተለይ የሕወሓት ወደ ሥልጣን መምጣት የወለደው ቻርተርና ሕገ መንግሥት ከእነ አወቃቀሩ የኢትዮጵያን ማኅበረሰቦች ግንኙነትና ተዛምዶ ሜካኒካዊ (ቀፏዊ) አስመስሎት ቆይቷል፡፡ ‹‹የትም ሠርቶ ብሔርን/ጎጥን መጥቀም… የብሔር ማንነት ተፈጥሯዊ፣ ኢትዮጵያዊነት በፍላጎት የሚያዝና የሚተው የዜግነት ጉዳይ›› የሚለው ሕወሓትና ቅጣዮቹ የሰዎችን አዕምሮ ያሟሹበት አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን አንድ ላይ መኖር ሜካኒካዊ ያስመለሰ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የኦነግና የሕወሓት ግልቦች ካባዙት ‹‹ኢትዮጵያ አገር-አከል ብሔሮችንና ነባር መንግሥታትን ደፍጥጣ የያዘች ኢምፓየር›› ከሚል ሐሰተኛ ‹‹የታሪክ›› ሥዕል ጋር ተጋግዞ፣ አሜሪካ በምትመራው ምዕራባዊ ዓለም አካባቢ ኢትዮጵያ ከፌዴራል አገርነት ይልቅ ብዙ አገር ሆና መከፋፈሏ፣ ‹‹ለዘላቂ ሰላም ሳይሻል አይቀርም›› የሚል የማመካኛ ግንዛቤ ሳይፈጥር አልቀረም፡፡

በተመድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ‹‹የምርመራ›› ሪፖርት (A/HRC/51/4 Report of the International Commission of Human Rights Experts on Ethiopia; 19TH Sept 2022) ኢትዮጵያን ለመወንጀል ያለመ ዘገባ ከማዘሉ ባሻገር፣ ‹‹ዳራ›› የሚል ርዕስ ያለው የኢትዮጵያን መበተን ተገቢ የሚያደርግ ውስጠ-ወይራ ያለው ታሪክ ተብዬ ቢጋር በአባሪነት መያያዙ፣ ከዚሁ የተሳሳተ ግንዛቤ መስፋፋት ጋር የተገናኘ አይሆን ይሆን? ተንኮለኛው ቢጋር ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥር ያላት መሆኗን ባይክድም፣ የአሁኗን ኢትዮጵያ ከ1855 እስከ 1898 ዓ.ም. ባለ ጊዜ (የደቡብ ሕዝቦችና መንግሥታት የአማራ/የትግሬ ‹‹ኤምፐረሮች›› በተፈራረቁበት የሰሜን መንግሥት ሥር ወድቀው) የተቋቋመች አገር አድርጎ ከመሳል አልፎ፣ በጊዜው አፍሪካን ከተቀራመቱ ቅኝ ገዥዎች ጋር በቅርምት ተሿሚነት ያመሳስላታል፡፡ ይህንን መሳይ ቢጋር የጎለቱት ሰዎች ተዘጋጅቶ የተሰጣቸውን ከማስቀመጥ ያለፈ ጥናት አድርገው ቢሆን ኖሮ፣ በጥንታዊው የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ታሪክ ውስጥ የድሮ ኦሮሞ የነበረውን ሚና ባይደርሱበት እንኳ፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ ምሥራቅ እስላማዊ ገዥዎችና በሰሜናዊዎቹ መሀል የነበሩትን የጠቅላይነት ውጊያዎችንና የተፈራረቁ መሸናነፎችን፣ የእነሱን በጦርነት መዛል ተመርኩዘውም የኦሮሞ ጎሳዎች በሰፊ አድማስ እስከ ሰሜን ምዕራብና ምሥራቅ ድረስ እየተሠራጩ (እየወጉ፣ እየማረኩ፣ እያሸነፉ ያሸነፉትን በሞጋሳ ኦሮሞ እያደረጉ፣ በአፀፋ ተፅዕኖ እነሱም ከእነሱ ውጪ ከነበረ ባህል ጋር እየተወራረሱ) በረዥም ጊዜ የፈጠሩትን የሰፊ አገር ማኅበራዊ ንጣፍን ሊስቱት አይችሉም ነበር፡፡ የዚሁ የረዥም ጊዜ መወራረስ ውጤት የሆነውን ከቴዎድሮስ በፊት በጎንደር ቤተ መንግሥት ውስጥ ገብቶ 70 ምናምን ዓመታት አካባቢ ጊዜ ያህል አፄያዊ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ የነበረውን የኦሮሞ መሳፍንታት የትውልድ ሐረግ ሊዘሉት አይችሉም ነበር፡፡ እነዚህን ታሪኮች ተቆናጠው ቢሆን ኖሮም ከ1855 እስከ 1898 ዓ.ም. የአሁኗ ኢትዮጵያ ‹‹የተቋቋመች›› (ኢስታብሊሽ) የተደረገች ሳትሆን፣ በረዥም ሒደት በብዙ ሰበዞች ቅንብር የተገነባች መሆኗን ባዩ ነበር፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ውስጥ የተካሄዱት ዘመቻዎች የረዥም ዘመን ሒደት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ‹‹ማጠናቀቂያ›› ገጾች መሆናቸውን የመረዳት ዕድል ባገኙ ነበር፡፡ በ19ኛ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ውስጥ የነበሩት ዘመቻዎች፣ የአማራና የትግሬ ብቻ ሳይሆኑ አገው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌውና ሌሎች ውጥንቅጦች ሁሉ የተሳተፉበት መሆኑና በዚሁ ጊዜ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1896 በተካሄደው በዓድዋ ዘመቻ፣ ሁሉም ሕዝብ ከሁሉም አካባቢ ተነቃንቆ መትመሙ፣ ብቻውን የኢትዮጵያ የ19ኛው ክፍለ ዘመን አገራዊ አሰፋፍ ከቅኝ ገዥዎች ቅኝ አስገቢ መስፋፋት ጋር የባህርይ መመሳሰል እንደ ሌለው በደንብ ያስረዳቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ከመረዳት ይልቅ ጉዳያቸው ሌላ ነበር፡፡ ለመሆኑ በትግራይ ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ‹‹ከመመርመር›› ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌለውንና ለዚያ የሥራ ተልዕኮም አንዳችም አስተዋጽኦ የማያዋጣውን አንጋዳ ቢጋር መለጠፍ ለምን አስፈለገ? በበኩሌ ቅኝ ገዥዎች ተስፋፍተው የያዙትን ከመልቀቅ እንዳላመለጡ ሁሉ፣ ‹‹የሰሜን ‹ኢምፐረሮች› በመስፋፋት ያቋቋሟት›› ኢትዮጵያም መፍረሷ አግባብ ነው የሚል መርዘኛ መልዕክት ከመርጨት የተሻለ መልስ አላገኘሁለትም፡፡ በነገራችን ላይ በ‹‹ኤክስፐርቶቹ›› ቡድን ውስጥ የተሳተፈችው አፍሪካዊት የጥቁሮችና የአፍሪካውያን መኩሪያ የሆነውን የዓድዋ ጦርነትና ድልን እንደረጋገጠችው (ጦርነቱን የጥቁር ቅኝ ያዥና የነጭ ቅኝ ያዥ ጦርነት፣ ድሉንም ከጥቁሮች የነፃነት ድል ይልቅ የጥቁር አቅኝ ድል እንዲመስል አስተዋጽኦ እንዳደረገች) ይታወቃት ይሆን?

በኢትዮጵያ ላይ የሚሠሩና የሚነዙ የሸፍጥና የሐሰት ሥራዎችን ከጊዜ ጊዜ እያሳደዱ መተቸት ውስን ፋይዳ ቢኖረውም፣ የሸፍጥ ሥራዎችን አምክኖ የኢትዮጵያን ህልውና የሚያስከብረው፣ በተቀዳሚነት የኢትዮጵያ አንድነት ቀፏዊ (ሜካኒካዊ) አለመሆኑን የሚያሳዩ የዘመናት ትስስሮችንና ውርርሶችን የእኔ ባለ አተያይ እየተንከባከቡ ይበልጥ እንዲለሙና እንዲንጨፈጨፉ (የሁሉም ዜጎች ወዘናና ገጽታ ሆነው እንዲወጡ) ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ይህንን ማድረግ ማለት የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ማለት ነው፣

  • በብሔር ተበድዬ ነበር ከሚል ሮሮ፣ ጥላቻና በቀል ነፃ መውጣት፣
  • የብሔር ማንነትን ‹‹ጎዶሎ›› እና ‹‹ሙሉ›› ከሚልና ጥራትን ልስፈር ከሚል አስተሳሰብ ነፃ መውጣት፣
  • በራስ ጎጥና ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ገመናና ጥፋትን ሸፋፍኖ የሌላውን ከማጋነንና ከማጦዝ ነፃ መውጣት፣
  • በማኅበረሰባዊ ማንነት መኩራትንና ብሔርተኛ/ጎጠኛ ጥበትን ከማሳከር መገላገል፣
  • ‹‹ሀ›› ብሔረሰብን በማንነቱ መናቅና መጥላት ነፃነት ሳይሆን የጭቆና ምርኮኛ መሆን መሆኑን ማወቅና ይህንን ማራገፍ፣
  • እነ ሕወሓት/ሸኔ፣ ወዘተ. ለብሔረሰባቸው እንዳልበጁ ከኢትዮጵያ ልምድ ተምሮ ‹ለ‹‹ሀ›› ብሔረሰብ ለማሰብ ከሁሉ በፊት የዚያ ብሔረሰብ አባል መሆን ያሻል› ከሚል አልባሌ አስተሳሰብ መላቀቅና ሰፊ የወገን ፍቅርና ተቆርቋሪነት ውስጥ መግባት፣
  • የማንኛውንም ሰውና ማኅበረሰብ ጥቃት አለመቃወም፣ ለማንኛውም ሰው መብት አለመቆም፣ የገዛ ራስ መብት እንዲጠቃ መፍቀድ መሆኑን የሰርክ ኑሮ ንቃት ማድረግ፣
  • የፖለቲካ ቡድንንና ሕዝብን ‹‹አንድና ሊነጣጠሉ የማይችሉ›› የሚል ውስወሳዊ ሥዕል እግር ከብረት መሆኑን አውቆ ተረት ማድረግ፣ ፌዴራላዊና አካባቢያዊ የሙያ አውታራትን አግባባዊ በሆነ ዥንጉርጉነትና ለሙያ በመታመን እስትንፋስ መገንባት፣
  • ብሔርተኛ/ጎጠኛ መሆን ለሙያና ለመላ የአገር ልጅ ከመታመን ጋር ይጋጫል፡፡ ጠባብ ወገናዊነት ሠፈርተኛዬ ለሚለው ማድላትን፣ በሥልጣን ዙሪያ ሠፈርተኛን ማሰባሰብንና ወደ ሠፈር ጥቅም ማሸሽን ልክ አድርጎ ያምናል፡፡ ኅብራዊ ማንነትን (አገርነትን) እስከ መካድ ሊወስድ ይችላል፡፡ እናም በኢትዮጵያዊ ሰፊ እኔነት፣ መብትና ግዴታ መበልፀግ የሚሳካው ጠባብ ግቢን ሰብሮ በመውጣት መሆኑን አውቆ ወደዚያ መሻገር፡፡
  • በአጠቃላይ ‹‹ብሔረሰባዊ ማንነቴ ተፈጥሯዊና ተቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በፈቃደኝነት የምይዘው የዜግነት ጉዳይ ነው›› ከሚል ግልብ አስተሳሰብ መውጣት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዥንጉርጉርነት ጀርባ መስጠትን ወይም ዥንጉርጉርነትን መሸፋፈንን ወይም ዥንጉርጉርነትን ሁለተኛ ደረጃ ጉዳይ አድርጎ ማየትን የብርቱ ኢትዮጵያዊነት መለያ አድርጎ ከሚቆጥር ደንቆር ‹‹ንቃት›› መውጣት፣ እናም ሁለቱንም ጠባብ አተያዮች ተሻግሮ የኢትዮጵያን ማኅበረሰቦች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ሁሉ የእኔ ባለና አዲሱን ትውልድ በዥንጉርጉርነት በሚቀርፅ የኢትዮጵያዊነት ርዕዮተ ዓለም ውስጥ መግባት ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሁሉን ነገር በብሔርተኛ ቀጭን ማስመሪያም ሆነ በኢትዮጵያዊነት ቀጭን ማስመሪያ ከመለካት ወጥተን፣ ዥንጉርጉርነታችንን የኢትዮጵያዊነት ማንነታችን እናድርገው ማለታችን ነው፡፡ የዜግነት ንቃተ ህሊናችን እንዲህ ሀብታም በሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነትና በሠለጠነ ሰብዕና የታነፀ ይሁን ማለታችን ነው፡፡ ይህ ሁሉ አስተናነፅ በአገራዊ ምክክራችን ውስጥና ሕገ መንግሥት በማሻሻል ሥራችን ውስጥ የጋራ መግባቢያችን ሆኖ መፍካትን ይሻል፡፡

ለ) ይህ ጉዳይ ከአገራዊ ምክክርና ከሕገ መንግሥት ማሻሻል አልፎ፣ የዜጎች መታነጫ መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ በታደሰ ሥርዓተ ትምህርት መጓዝ እየጀመሩ ያሉት ትምህርት ቤቶቻችን ትልቅ ሚና እንዳላቸው ዕውቅ ነው፡፡ እነሱ በትምህርት ዕድሜ ውስጥ የሚያካሂዱት ኃላፊነቶችንና መብቶችን ባዋደዱ የዜግነት እሴቶች ትውልድን የማነፅ ሥራ፣ ከሥር ከቤተሰብ ካልጀመረ ግልብ ይሆናል፡፡ ትምህርት ቤት የተማሩት ነገር ሠፈር ለሠፈር ከሚቀስሙት ጋር ከተጋጨ፣ ከታላላቅ ወንድሞቻቸው/እህቶቻቸውና ከወላጆቻቸው ከሚቀስሙት ጋር ከተጋጨ፣ መደበኛ ኑሯቸውን የሚመራ ንቃት ወደ መሆን አይሸጋገርም፡፡ በወሬ ጊዜ ብቻ የሚተረተር አፋዊ ንቃት ከመሆን አያልፍም፡፡

በየሠፈሩ የሚታየውና የሚሠራው ነገር ሁሉ ልጆችን የመቅረፅ ሚና አለው፡፡ ከአዎንታዊው ይበልጥ አላሻቂው ዓይን ሊወጋ እየደረሰም ነው፡፡ በዘልማድ ውስጥ መከተር፣ አድርጉ የተባለን ሳይንሳዊ ነገር ንቆ ማለፍ፣ የተለመደ አኗኗርን ለማረም አለመጨነቅ አዋቂነት መስሏል፡፡ ተከተቡ ሲባል ሰምቶ ማለፍ፣ ቆሻሻ በተለይም ፕላስቲክ ማቃጠል ጠንቀኛ ነው ሲባል ሰምቶ ማለፍ፣ ከቤት/ከግቢ ቆሻሻ አውጥቶ መሀል መንገድ ላይ ወይም ሌላ ሰው አጥር ሥር መጣል፣ ሽንት በፕላስቲክ ኮዳ ሞልቶ የትም መጣል ወዘተ፣ ወዘተ. መብትና መሠልጠን መስሏል፡፡ በመረንነትና በጨዋነት መካከል ልዩነቱ ጠፍቷል፡፡ በየመንገዱ የሚታየው ልሽቀት ኃላፊነትንና የሰውን መብት ማክበርን ከማስተማር ይልቅ ሰውን መናቅንና መዳፈረን የሚያስተምር ነው፡፡ አጭበርብሮ መሸጥ (ከደህነኛ ጋር ብስባሽ/ባዕድ/አይረቤ ቀላቅሎ፣ ይዘት አቅጥኖ/ቀንሶና ሚዛን ሸፍጦ መሸጥ)፣ በመንገደኛ ላይ አቧራ መጥረግ/የልዩ ልዩ ሥራ አቧራ ማቡነን/ ቀለም መንፋት፣ ዕቃ በመደርደር የእግረኛ መንገድ መዝጋት፣ በየታክሲ ውስጥ ተሳፋሪ (ከተሳፋሪም በዕድሜ የጎለመሱ) ማንጓጠጥና እየተሳደቡ ሰው መጠቅጠቅ፣ እነዚህን የመሳሰሉ ነውሮች ከብልግና ውጪ የሆኑ ተገቢ የኑሮ ዘዬ መስለዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታየው አገራዊ ኃላፊነትን እስከመሳት የተራመደ ስድነት ሁሉ የዚህ ነፀብራቅና ብቃይ ነው፡፡ ይህንን ታቅፎ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለውን ብቃይ ነጥዬ ላስተካክልህ ቢሉት፣ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ካለ ልሽቀት ጋር ብቻ ልተናነቅ ቢሉት ችግሮች ብዙም አይገፉም፡፡

በቤት ውስጥ ወዳለ ‹‹ዘመናይ›› አስተዳደግ ስንመጣ፣ ከመንታሎች ቤት እስከ ትምህርት ቀመሶች ቤት የምናገኘው የልጅ አስተዳደግ በአያሌው ቀውስ ውስጥ ገብቷል ሊባል የሚችል ነው፡፡ ድሮ በእኛ ልጅነት ጊዜ አያቶች ልጅ አባጣጭ ተደርገው ይታዩ ነበር፡፡ ለአጭር ጊዜ አያት የልጅ ልጃቸውን ሲያሰነብቱ፣ ‹‹አቅብጠሽ ልጄን እንዳታበላሺ›› ሊባሉ ይችሉ ነበር፡፡ ዛሬ የተገላቢጦሽ አያቶች ጨቋኝ ተደርገው የሚታዩ ወላጆች ደግሞ አሞላፋጭ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ራመድ ተብሎ፣ የዛሬ ብዙ ወላጆች ኮትኩቶ የማሳደግ ሥራን አቁመዋል ቢባልም ማጋነን አይመስለኝም፡፡ አለንጋም ቁጣም ባለበት ‹‹ሥነ ሥርዓት›› ያደጉ፣ ከእኛ ዓይነት ትውልድ የተወለዱ፣ ወጣትነት የዘለላቸው ባለትዳሮች በእነሱ አስተዳደግ ውስጥ የነበረውን በጎና ክፉ ሳያበጥሩ በደፈናው እነሱ ያለፉበትን አስተዳደግ ጨቋኝ አድርገው ጥለው፣ ልጆቻቸውን ‹‹ከነፃነት›› በቀር ኃላፊነትን፣ ክልከላን፣ ገደብንና ቁጣን የማያውቁ አድርገው ሲያሞላፍጡ ዓይቻለሁ፡፡

ለእኔ የወንድም ያህል የሆነ ጓደኛዬ ልጅ በቅንነት፣ በሩኅሩኅነትና በትኅትና የተሞላ ባህርዩዋ የሚደንቅ ነው፡፡ ተምራና ሥራ ይዛ፣ አግብታ ስትወልድ የተከተለችው የልጅ አስተዳደግ እሷ ካደገችበት እጅግ ተቃራኒ ነው፡፡ ልቅ የመስደዷ ብዛት ‹‹በደል በእኔ ይብቃ›› የሚል ግንዛቤ በሆዷ ያለ የሚያስመስልም ነው፡፡ የአምስት ዓመቷ ሕፃን የምትከለከለው ነገር የለም፡፡ ወላጆቿ ዕቃ ካሳሳቸው ሳታይ መደበቅ ብቻ ነው፡፡ ዓይታ ከጠየቀች ይሰጣታል፡፡ ከእሷ ዓይን ዕንባ ከሚወጣ ዕቃው ቢበላሽ ይሻላል፡፡ ቴሌቪዥናቸው ሥዕል ከማሳየት በቀር አይናገርም፡፡ እሷ ስለምትነካካው ማሠራትም አላስፈለጋቸውም፡፡ ስልክ ይገዛሉ ታበላሻለች፣ ሌላ ይገዛሉ፡፡ እሷ ፊት ለተደወለ ስልክ መልስ አይሰጡም፡፡ እንግዳ/ዘመድ ሲመጣ ትንሿ ልጅ ስልክ ፍለጋ የሰው ኪስ ልትገባ ትችላላች፡፡ ‹‹ልጅቷ እኮ የእሷ ነፃነት የት ድረስ እንደሆነ፣ የእሷ ያልሆነና የሚከለከል የሚባል ነገር አታውቅም፡፡ ይህንን ካላሳወቅሻት ምን አሳደግሁ ትያለሽ!›› ብዬ ብላትም፣ ሰበባ ሰበብ ከመደርደር በቀር እናቲት ነገሬ አልዘለቃትም፡፡ ጭራሽ ልጇን ይዛ ለጥየቃ ወደ እኔ ቤት ለመምጣት ስታቅድ ‹‹እንግዲህ የሚሚን ዕቃ አተራማሽነት ትችለዋለህ›› አለችኝ፡፡

ከሌላ ጓደኛዬ ጋር ቤቱ ተቀምጠን በምናወጋበት ጊዜ ወፍራም ክፍያ ያለበት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ የልጁ ልጆች በተደጋጋሚ አጋጥመውኛል፡፡ ልጆቹ ቤት እንደገቡ የሚያደርጉት ነገር ታጥቦ እንጎቻ መብላት ሳይሆን፣ ምንም ፈቃድ ሳይጠይቁና ሳይሳቀቁ ቴሌቪዥን ላይ ይታይ የነበረውን ፕሮግራም ወደ እነሱ ፍላጎት ማዞር ነው፡፡ የሚናገራቸው እንኳ የለም፡፡ አያታቸው አስተዳደጋቸውን ቢነቅፍም እጅ ሰጥቷል፡፡

የዞረበት አስተዳደግ ውስጥ የገቡ ልጆች ቤትህ መጡ ማለት ወረራ ገጠመህ ማለት እንደሆነ በራሴ ዘመዶችም ዓይቻለሁ፡፡ ስለሚድሁና ስለሚውተረተሩ ሕፃናት አይደለም የማወራው፣ ጥርስ ስለነቀሉ ነው የማወራው፡፡ ‹‹ይህን ልጫወትበት?›› የሚል ፈቃድ ሳይጠይቁ ያንንም ያንንም አፈፍ ማድረግ ነፃነት ሆኖ፣ ‹‹ተው፣ እሱ አይነካም!›› እያልኩ ሳግድና ‹‹በዚህ በዚህ መጫወት ትችላላችሁ፣ ከዚህ ውጪ እኔ ያልፈቀድኩትን ወይም የእኔን ፈቃድ ሳታገኙ አንድ ነገር ብትነኩ!!›› ብዬ ሳስጠነቅቅ፣ እኔ እንደ አምባገነን/‹‹እንደሚያካብድ›› ነው የምቆጠረው፡፡ ጥፍጥ ያለች ነገር ልጆች አግኝተው ፈንታቸውን ላስ እያደረጉ፣ ‹‹አሁንም…›› ሲሉና የአዋቂ ፈንታ እየተነሳ ሲከመርላቸው በተቃወምኩና ‹‹ሌላ ሰው ፈንታ ሊኖረው እንደሚገባ አውቀው ፍላጎታቸውን መቆጠብ ካልተማሩ፣ ለሌላ ሰው ማሰብን እንዴት ይለማመዳሉ?›› ባልኩ ጊዜ የገጠመኝ ጠንከር ያለ ቅያሜ ነበር፡፡

የዚህ ዓይነቱ ችግር እናቶች ላይ ያይላል፡፡ ከዚሁ ከእናቶች ችግር ጋር ተያይዞ ይመስለኛል የትምህርት ቤት ምገባ ከመጣ ወዲህ አዲስ ልማድም እያየሁ ነው፡፡ ለምናልባቱ ብለው ልጆቻቸውን ለመጥቀም የፈለጉ እናቶች ጀምረውት መሰለኝ፣ የትምህርት ቤት ምገባን የሚጠቀሙ ልጆች ከቤት ምግብ ይዘው ይመጣሉ፡፡ አንዱ የአንዱን መያዝ እያወራ ፉክክሩም እየተዛመተ ይመስላል፡፡ እናም በ9፡30 ሰዓት ግድም ተማሪዎች ሲለቀቁ፣ ደፍና ጥላ በተገኘበት የመንደር መንገድ ዳርቻ ላይ ተሰባስቦ ባልፀዳ እጅ መብላትና የየሰውን አጥር የፍርፋሪ ስጥ ማስመሰል ሲደጋገም አስተውያለሁ፡፡ ቤት ሲደርሱ ደግሞ እናቶች ጠገብኩ ቢሏቸው እንኳ እንደማያስችላቸው ይገመታል፡፡ ‹‹ሆድ እንዳሳዩት ነው›› የሚል ነባር አባባላችን ጥንቃቄን ይጠቁማል፡፡ ያ ጥንቃቄ በቅጡ ስለመጤኑ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ጉስጎሳ ቀረሽ የሆነ የእህል ምገባ ሻል ያለ ኑሮ ባለበት ብዙ ቤት ውስጥ ልጅን ከመንከባከብ ጋር ሳይምታታም የቀረ አይመስለኝም፡፡

ይህንን የመሳሰሉት የልጅ አስተዳደግ ችግሮች አዕምሮ በማታወዛ ‹‹ፍርንጅና›› ቀመስ ‹‹ዕውቀት››፣ የልጅ አስተዳደጋችን ውዥንብር ውስጥ እንደወደቀ ይጠቁማሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ዞሮ ዞሮ የደደረ የኑሮ አመራር ክህሎት ድንቁርና በኅብረተሰባችን ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ ባለ መኃይምነት ላይ መኗኗሪያ ለመሆን የሚበቃ የዜግነት ንቃተ ህሊና በዜጎቻችን ውስጥ ለማስረፅ መሞከር ውጤታማ አያደርግም፡፡ በመልካም እሴቶች የበለፀገ የዜግነት ንቃተ ህሊና፣ ተዋህዶን የምንኖርበት የተግባር ሀብት የሚሆነን፣ ከላይ ወደታች ከማስረፅ ይበልጥ ከሥር እየተኮተኮትንበት በማደግ ጉዞ ወደ ሰብዕናችን ሲሰርፅ ነው፡፡ የጨዋነት፣ የማስፈቀድ፣ ፈንታ የማክበር፣ ለሌላው የመራራት የራስ ነፃነትን ድንበር የማወቅ፣ ወዘተ. እሴቶች ሁሉ ለኩትኳቶ መዋል ያለባቸው ከሥር ነው፡፡

‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› (ሊያሳስበን የሚገባው የምንሻው ውጤት መገኘት እንጂ የተገኘበት መንገድ አይደለም) በሚል አስተሳሰብ ‹‹ውጤትን›› ብቻ እያዩ መሮጥ አያዋጣም፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የትምህርት ጥራትን ገደል እንደ ሰደደ ሁሉ ለሌላም መፍትሔ አይሆንም፡፡ በየሠፈሩና በየመንገዱ አገር እያበላሸ ያለ ልሽቀትን/ስድነትን ታቅፎ ከተማ አፅዱ ባይነት ውጤት አያመጣም፡፡ ቆሻሻ በየሰው አጥርና መንገድ ላይ የመጣልን ስድነት የማረቅ ነገር ደግሞ የየመንደር ሕይወትን በዴሞክራሲያዊ መተሳሰብ የተሞላ፣ የነዋሪዎችን ፍላጎትና መነሳሳት የተቆናጠጠ፣ የልጆችን መንደራዊ አኗኗር ከነፃትና ከኃላፊነት ጋር እንዲስማማ ያደረገ የኑሮ ለውጥን ያመላክታል፡፡ በአጭሩ ችግሮቻችን ሰፊ ምንጭ እንዳላቸው ሁሉ፣ መፍትሔያቸውም የብዙ ፈርጆችን ተቀናብሮ መምጣት ይፈልጋል፡፡ ፈርጀ ብዙ መፍትሔዎችን አቀናብረን ችግሮቻችንን ወደ ማቃለል ስንገባ፣ በአጭር ቃል የ50 ዓመታት የንጠት ታሪካችንን ዘግተን፣ ሰላምንና ግስጋሴን ሙጥኝ ያለና የሚያፋፋ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈታችን ነው፡፡

ሐ) በዚህ ሁሉ ረገድ፣ ነጋችን ብሩህ እንደሆነ ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ወዲህ እየታየ ያለው ለልማት መቅበጥበጥ፣ ከሰላም ጋር ሲገናኝ ብዙ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ አገራዊ ህልውናችንን በማትረፍ ትግላችን ውስጥ፣ በተለይም ወደኋላ ላይ ማስተዋል የቻልነው፣ ብስለትና ሳይዝረጠረጡ ውስብስብ ፈተናን ተቋቁሞ የመጓዝ ጥንካሬ ለነገ የሚሆን አይበገሬነትንም እየሰነቅን ስለመሆናችን ፍንጭ የሰጠ ነበር፡፡ ጦርነት እያካሄዱ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለሰላማዊ መፍትሔ ዝግጁ መሆን፣ እየተዋጉ በሌሎች ሥፍራዎች ሁለገብ ልማትን ማካሄድ፣ ለሰላም ውይይት ቀጠሮ ይዞና ወደ ደቡብ አፍሪካ ልዑክ እየላኩ የትግራይን ሕዝብ ከስቀዛ ነፃ የማውጣቱን ሥራ ማፍጠን፣ ነፃ የማውጣቱን ሥራም ከተሞች በማይወድሙበትና ብዙ ታጣቂዎች እጅ በመስጠት በሚተርፉበት ሥልት መምራት፣ እንዲሁም ነፃ በወጡ አካባቢዎች ዕርዳታ ማድረስንና የአውታራትን መልሶ መቋቋም፣ ማስከተል በተቀናበሩበት ብልኃተኝነት ከምዕራባዊ የጫናዎች አጣብቂኝ ለመውጣት መሥራት፣ በመርፌ ቀዳዳ ለማለፍ ከመቻል የሚቆጠር ነው፡፡

ብዙ ተግባራትን ባቀናበረው ከአጣብቂኝ የመውጣት ጉዞ ውስጥ በበኩሌ የሚረሳ ነገር ይኖር ይሆን የሚል ሥጋት አልነበረኝም፡፡ የትግራይን ሕዝብ ለመቀስቀስ መሯሯጥም አስፈላጊዬ ሆኖ አልታየኝም ነበር፡፡ ምክንያቱም ግፍ ዋይነት ሕዝብን መከራ እያስቆጠረ ቅስቀሳውን ጨርሶ ሠርቶት ነበርና፡፡ የትግራይ ሕዝብ የአፈናው መዋቅር ውልቅልቁ እየወጣለት መሆኑን ማየት ብቻ ለመነቃነቅ በቂው ነው የሚል እምነት አድሮብኝ ነበር፡፡ እናም ትርዒቱን በግርምት እየተከታተልኩ ለማድነቅ ነበር የምሰናዳው፡፡ የሰላም ውይይቱ ተጀመረ አልተጀመረ፣ ስለምን ጉዳዮች መነጋገር ያዙ ብሎ መከታተል ጭንቄ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የመደራደሪያ ነጥቦች ፊት ለፊቴ የተጻፉ ያህል ዓይኔ ላይ ይመላለሱ ነበር፡፡ ‹‹ጦርነቱን ማለቂያ በሌለውና በከፋ መልክ እናራዝመዋለን…፣ ትግራይ የገባውን ሠራዊት እዚሁ እንቀብረዋለን›› የሚል የአንዳንድ ጦረኞች የጨበጣ ማስፈራሪያም በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሕዝብ ነፃ የማውጣት ሥራን አጥርቶ ለመሥራት በሽፋንነት ሲጠቅም ነበር የሚታየኝ፡፡ በአጭሩ ትኩረቴ ሁሉ ይንቆራጠጥ የነበረው በትግራይ ውስጥ እየሆነ በነበረው ፈርጀ-ብዙ ክንዋኔ ላይ ነበር፡፡ ወደፊትም ጦረኞችን በተገላገለች ሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በተለይም ትግራይ ውስጥ፣ የሚከተለው የዕፎይታና የነፃነት ትንፋሽ፣ ከፈካ ልማት ጋር ተጋግዞ፣ የትኛውንም መሰናክል ሲጠራርግ ይታየኝ ነበር፡፡ ትኩረቴ መሬት ላይ በነበረው ፈርጀ ብዙ ክንዋኔ ላይ ተሰክቶ የቆየውም የሰላም ውይይቱን ዋጋ በማሳነስ ሳይሆን፣ ውይይቱ ፈጠነም ተጎተተ፣ ወይም ተጓጎለ ምድር ላይ እየሆነ የነበረው ግስጋሴ የኋሊት የማይቀለበስ፣ ሰላምን የሚጠቅምና የሚያቀርብ አስተዋጽኦ እንደነበረው በማመን ነበር፡፡ ከውይይቱ የተገኘው ውጤት ከግምቴ እጅግ የዘለለ ቢሆንም፣ መላ ኅብረተሰባችን የተቀዳጀውን ድልና በድል አጀብ ውስጥ የተጀማመረውን ፍዳ የማቅለል ዘርፈ ብዙ ሥራ ያፀደቀና የሚያፋጥን ነው፡፡ ከትጥቅ መፍታት ጋር የአንድ ቡድን የአፈና መዋቅር ተጠራርጎ ከፖለቲካ ቡድን ታማኝነት የፀዳ፣ ለትግራይ ሕዝብ ነፃ ትንፋሽና ለሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች ደኅንነትና ነፃነት ዋስትና የሆነ የመንግሥታዊ አውታራት ግንባታም እንደሚጀመር እንጠብቃለን፡፡ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የሚያስቡ የዴሞክራሲ ቡድኖች በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ምን ያህል የሕዝብ ትርታ የመሆን ስንቅ እንደሰነቁ ለማየትም እንናፍቃለን፡፡ የምንናፍቀውም ለወግ ሳይሆን፣ የሰላሳ ዓመታትን መራር ልምዶች ተመርኩዘው ብሔርተኛነትንና ጎጠኝነትን ሰብሮ የወጣ ሰፊ ዕይታ፣ ‹‹ክልል›› በሚባል በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የብዙኃን ንቃት እንዲሆን፣ ይህም ንቃት የተደራጀ ሥር እንዲያበጅ የማድረግ ትልቅ ሥራ ከፊታቸው ስለሚጠብቃቸው (ይህንን መደላድል ሳያዘጋጁ የሕገ መንግሥት መሻሻልን በአግባቡ ስለማያሳኩት) ነው፡፡

ብዙ ኃይሎች ከተሳተፉበት የጦርነት አጣብቂኝ ኢትዮጵያ በብልኃት ያለፈችበት ይህ የአሁኑ ልምድ ሌሎች የእኛ ቢጤ አገሮች ሊማሩበት የሚችሉበት ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲከኞችም ከዚህ ልምድ ትልቅ ትምህርት ቀስመው፣ ከዚህ በኋላ ባለ እንቅስቃሴያቸው ከወጠጤ ቡትለካ ምራቅ ወደ ዋጠና የነገሮችን አመጣጥና አካሄድ አስቀድሞ ወደ የሚያስተውል የፖለቲካ ጉልምስና ውስጥ መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከእንግዲህ በገዛ ጥፋትና ዝርክርክነት እገጭ እገው ያለበት ፈተና ውስጥ ላለመውደቅ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን አውቆ ቁርጠኛ ትግል ማድረግ የሁላችንም አገር ወዳዶች ተግባር ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግሥት አመራርና የሕዝብ ተያይዞ ጉዞ ከሆነ ይሁን የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እየተጠናከረ እንዲሄድ ደግሞ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ የለውጥ ፖለቲከኞችና ከሥልጣን ውጪ ያሉ ተፎካካሪ የለውጥ ኃይሎች አንድ ላይ መሳመራቸው ወሳኝ ነው፡፡ መሳመር ስል አንድ ዓይነት ትንፋሽ መያዝ ለማለት አይደለም፡፡ የሐሳብ ልውውጣቸው፣ አድናቆትና ሂሳቸው፣ በአጠቃላይ የሚተነፍሱትና የሚሠሩት ነገር ሁሉ ሰላምን፣ ለውጥንና ልማትን የሚያራምድ፣ ሁለገብ ግስጋሴያችንን የሚቀናቀኑ የውስጥና የውጭ ንፋሶችንና ትንኮሳዎችን የሚያልፈሰፍስ መሆኑን በየጊዜው መለካት ይጠበቅባቸዋል ለማለት ነው፡፡

ይህንን ማድረግ ከቻልን ህልውናችንና ግስጋሴያችን ዋስትና አለው፡፡ ይህ ግን ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ከአሁንም በኋላ የሚኖርብን የአርበኝነት ተጋድሎ ካለፈው ይበልጥ እንደ ቆቅ ንቁ መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡ ትንሽ ሳት ቢለን ወይም ብንንገላጀጅ የምንከፍለው ኪሳራ ውድ ሊሆን ይችላል፡፡ ልብ እንበል፣ ገንታራነት ያልለቀቃቸው የሸር ሊቀጳጳሶች እንኳን ኢትዮጵያን፣ አፍሪካ ቀንድን ለማመስ እንደማይተኙ እነሱን በአማካሪነት እስከመጠቀም ሊሄዱ የሚችሉ አገሮችም እንደማይታጡ መታወቅ አለበት፡፡ በመላ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ኦሮሚኛ ቋንቋ መጠቀምን ተጨባጭ እንዲሆን በመሥራት ፈንታ፣ አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያን ክልል መዝሙር ዘምሩ ምንትስ የሚል ውዝግብ የሚያነሳሳ ቀሽማዳ ነገር ውስጥ እየተትረከረኩ ስለጥንቁቅነትና ስለብስለት ማውራት አይቻልም፡፡ የአካባቢ ይዞታ ትስስባችን ሁሉ በጠባብ አካባቢያዊ ብልጣ ብልጥነት ውስጥ የሚልወሰወስ ከሆነ፣ ለሚባርቁ ብዙ ችግሮች መጋለጥን ለመሻገር እንቸገራለን፡፡ አማሮ ልዩ ወረዳ ምንትስ ከሚባሉ ሠፈሮች እስከ ትግራይ ድረስ የምንሠራው ሁሉ፣ ከሠፈር ይልቅ በአገር ደረጃ የምናተርፈውን የፖለቲካ ሰላምና የአንድነት ጥንካሬ ዋና መመዘኛ ካላደረገ ብስለትንና አርቆ አስተዋይነትን ስለመቆናጠጥ ልናወራ አንችልም፡፡ በፖለቲካችን ውስጥ የሰከነና አርቆ አስተዋይ ፖለቲካ አይሎ እንዲወጣ ከፈለግን፣ በጥራዝነጠቅነት፣ በጀብደኝነትና አፍ እንዳመጣ በመንደቅደቅ የተሞላ ቡትለካን እየበረበረ ወጣቶች ነገሮችን ወደ ማጣራትና አጣርተውም የምንተነፍሰው ምን ጠንቅ ይኖረው ይሆን በማለት ደጋግሞ ወደ ማሰብ እንዲሻገሩ የሚያግዝ የሐሳብ ልውውጥ ሥራ ይፈለግብናል፡፡

የፖለቲካ ብስለታችንና ጥንቃቄያችን ከአገራችን የውስጥ ጉዳዮች አልፎ እስከ ቀጣናችንና አኅጉራችን ድረስ መርዘምም ያለበት ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያንም ሆነ ቀጣናችንንና አፍሪካችንን በአደገኛ የፖለቲካ አስተሳሰብና የጥቅም ተጋፊነት ታላላቆቹ ጉልበተኞች ቢጠረጥሩና ቢጠምዱ ምን ሊያመጡ ብለን ቸል ልንል አንችልም፡፡ ጥንቃቄያችን በመጠመድ ውስጥ ላለመግባትና መጠመድን ለማራቅ የሚሠራም መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚሁ አኳያ ‹‹አፍሪካን መልሶ ቅኝ የማድረግ ፍላጎት አለ!…›› የሚል ሆይ ሆይታ ውስጥ ከመሽከርከር ይልቅ ከዕርዳታና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ አቅዶ እየሠሩ አፍሪካውያን ከየትኛውም ጎራ ገለልተኛ መሆንን መለያቸው አድርገው የዓለማችንን በሞት አፋፍ ላይ መድረስ እያስተጋቡ (ዓለምን የሚያመክን የጦር መሣሪያ የያዙ ጎራዎች የተያያዙትን መካረርና ጦርነት እያወገዙ) ፍትሐዊና የተሳለጠ አረንጓዴ የዓለም ሥርዓት እንዲመጣ መወትወት፣ ተመድና የፀጥታ ምክር ቤቱ የዓለማችንን ሰላምና ደኅንነት ማስከበር በማይችልበት አኳኋን ማንከሱን በማሳየት እንዲቃና መወትወት አጠቃላይ አቋማችን ቢሆን ይመረጣል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሰብዓዊ ርኅራኄ ዕርዳታ፣ ወዘተ. የሚባሉት ነገሮችና በእነሱ ስም የሚካሄድ ጣልቃ ገብነት የፖለቲካ ዓላማ መነገጃና የሰው ልጆችን ስቃይ ማባባሻ እየሆነ መምጣቱን፣ የዴሞክራሲ ነፃነቶችና የሰብዓዊ መብቶች ወገን ነን ሲሉ የኖሩት ምዕራባዊ ኃይሎች መዳፋቸው ውስጥ ያልገቡ አገሮችን ሰላም የሚያናውጥ ዕርምጃ መውሰድ እየለመደባቸው መምጣታቸውን፣ በተመድ ውስጥና ከተመድ ውጪ ያሉ ባለ ስም የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ባይ ተቋማትም፣ በገንዘብ የሚደግፏቸው አገሮች ያልፈለጉት መንግሥት እንዲወድቅ ወይም እንዲያጎነብስ ለአመል ጥፋትን ጋራ እያሳከሉ/የሌለ ጥፋትን እየደረደሩ፣ ያልተፈጸመ ጥፋት ወደፊት ስለመፈጸሙ እየጠነቆሉ፣ የሚያግዙ መሣሪያዎች እየሆኑ መምጣታቸውን በመመርኮዝ፣ ከአፍሪካዊ መፍትሔ ውጪ በየትኛውም ሰበብ የሚከጀሉ ወታደር የማስገባት ዕርምጃዎችን የሚቃወም አቋም በአኅጉር ደረጃ መያዝና የአፍሪካ ኅብረት የራሱን ፍሬያማ የመፍትሔ ዘዴዎችን እንዲያጎለብት መሥራት፣ የሁሉም አባል አገሮች ጥረት ሊሆን ይገባዋል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ‹‹ፓን አፍሪካኒዝም›› የትግል ዘይቤውን በዚህ መንገድ ቢመራ ሳይሻል አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...