Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉይድረስ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳሪዎች - አሁን ላሉትም ወደፊት ለሚመረጡትም (ከአዲስ...

ይድረስ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳሪዎች – አሁን ላሉትም ወደፊት ለሚመረጡትም (ከአዲስ አበባ ዕድገትና ልማት ጋር ሊታሰቡ የሚገባቸው ጥቂት ጉዳዮች)

ቀን:

በወንዴ ገብረ ሥላሴ

አዲስ አበባን ለማስዋብ እየተደረገ ያለው ጥረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ወዲህ እየተጠናከረ መሄዱ እውነት ነው፡፡ ይህ በብዙ መልኩ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የአገራችን መዲና እንደመሆኗ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ በተጨማሪም አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መዲና በመሆኗ አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና እህቶታችን ሁሉ እንደሚያስደስታቸው አያጠያይቅም፡፡

የከተማዎች ዕድገትና ልማት ሲታሰብ በርካታ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የአገልግሎት ተቋማት፣ የኢኮኖሚ፣ የልማት መዋቅሮች/የምሕንድስና፣ የፀጥታ፣ ወዘተ. ጉዳዮች ታሳቢ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ከተሞች ብዙ ሰዎች ተሰባስበው የሚኖሩባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው በርካታ ጉዳዮችን አርቆ ማሰብ፣ በጥንቃቄ ፕላን ማድረግ፣ ችግሮችን በጥንቃቄ መመርመርና መፍትሔ መስጠት ጥቂቶቹ ታሳቢዎች ናቸው፡፡ በዚህች አጭር ማስታወሻ ውስጥ ላነሳቸው የፈለግኳቸው ጉዳዮች መታየትና በየጊዜው ተገቢ መፍትሔ ማግኘት ከሚገባቸው ነጥቦች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ጉዳዮቹ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶአቸው ሊታሰብባቸውና መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

የመንገድ ላይ አደባባዮችና ሹፍርና

የመንገድ ላይ አደባባዮችን በተመለከተ ከዓመታት በፊት ኒውስ ዊክ የተባለው መጽሔት የአውሮፓንና የአሜሪካንን መንገዶች፣ አደባባዮችና የትራፊክ ፍሰት ችግሮችን በተመለከተ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር፡፡ እንደማስታውሰው ጽሑፉ ሲያጠቃልል የአውሮፓ መንገዶች ጥሩ ጥሩ አደባባዮች ስላሏቸው ሾፌሮች አደባባይ ላይ ሲደርሱ ፍጥነታቸውን ስለሚቀንሱ፣ የትራፊክ አደጋ ከአሜሪካው ጋር ሲወዳደር በአውሮፓ አነስተኛ ነው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱም የተሻለ ነው የሚል ነበር፡፡

ከአደጋው ማነስና ከትራፊክ ፍሰት በተጨማሪ፣ በአውሮፓ አደባባዮች ላይ የተተከሉ ሐውልቶችና መታሰቢያዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው የታሪክ መታሰቢያዎች ከመሆናቸው አልፎ፣ ለከተሞቹ ውበትና ሞገስ በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለው አደባባዮችን የማንሳትና በትራፊክ መብራት የመቀየር ሥራ ግን ከእነዚህ መልካም ከሚባሉ ልምዶች ጋር የሚጣጣም አይመስልም፡፡ ወይም በየአገሩ የሚገኘውን መልካም ልምድ አወዳድሮና መዝኖ ከግንዛቤ መውሰዱ ያጠራጥራል፡፡

የእኛ አገር የትራፊክ ችግር በአብዛኛው የመንገዶች ወይም የአደባባዮች ችግር ነው ብዬ አላስብም፡፡ ችግራችን የሾፌርነት ችግር ነው፡፡ በእርግጥ ለትራፊክ አደጋና ለትራፊክ መጨናነቅ በርካታ ታሳቢዎች ቢኖሩም፣ ዋነኛው ግን የመኪና አነዳድ ችሎታ፣ ሥርዓት፣ ዲሲፕሊን፣ ትዕግሥት ማጣት፣ ከመጠን ያለፈ አጉል ራስ ወዳድነትና የትራፊክ ሕግ ያለ ማክበር ነው፡፡ የእኛን አገር ሾፌሮች እንዳለ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ወስደን እንዲነዱ ብናደርግ (በመንገዶች፣ በትራፊክ መብራቶች፣ በአደባባዮቹ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግ) የአደጋው ቁጥር እዚህ አዲስ አበባ በምናየው ልክ አሜሪካ ወይም አውሮፓ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ እንዲያውም መንገዶቹ ከዚህ በጣም የተሻሉ በመሆናቸው ምናልባትም አደጋው ከዚህ የከፋ ሊሆን ይችላል።

ከአንድ ሁለት ዓመት በፊት በፎርቹን ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ ከአዲስ አበባ የመንገድ ባለሥልጣን ጋር የሚሠሩ ስዊድናዊ የመንገድ ባለሙያ መንገዶች ሲታቀዱ መታቀድ ያለባቸው፣ ሰዎች ስህተት መሥራታቸውን ታሳቢ በማድረግ መሆን አለበት ያሉትን ተመልክቻለሁ፡፡ ትክክለኛ አባባል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ የእኛ አገር፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሾፌሮች ዋናው ችግራቸው ስህተት መሥራታቸው ሳይሆን፣ የስህተት መጠናቸውን መቶ ጊዜ የሚያባዛው ስለመኪና መንዳት ያላቸው አስተሳሰብ፣ ከላይ እንደገለጽኩትም ሥርዓት፣ ዲሲፕሊን፣ ችሎታ፣ ትዕግሥት ማጣት፣ አጉል ራስ ወዳድነትና የትራፊክ ሕግ አለማክበር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እስካልተሻሻለ ድረስ መንገዶች ያላግባብ መጨናነቃቸው፣ መዘጋታቸው፣ አደጋ መድረሱ፣ እንዲሁም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አላስፈላጊ ጉዳት መድረሱ ይቀጥላል፡፡

ዋናው ሥራ መሠራት ያለበት (ሰዎች ስህተት ሊሠሩ መቻላቸው ታሳቢ ተደርጎ፣ መንገዶች የትራፊክ አደጋን እንዳያባዙ መደረግ ያለበት የንድፍና ሌሎችም ጥንቃቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው) በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ቀጣይና ያልተቋረጠ ሥራ መሥራት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ ያለፈበት አስተሳሰብ ነው የሚለውን ማጠቃለያ መቀበል ያስቸግረኛል። አዚህ ላይ ለውጥ ማምጣት ካልቻልን የፈለገውን ያህል አደባባዮችን ብናነሳ፣ መንገዶችን ብናሰፋ፣ የመንገድ መጨናነቅን፣ መዘጋጋትንና የትራፊክ አደጋን ልንቀንስ አንችልም፡፡ ስንት ሾፌሮች ናቸው ሥርዓት ጠብቀው፣ መንገዳቸውን ይዘው፣ የራሳቸውንም ሆነ የሌሎች መንገድ ተጠቃሚዎችን መብት አክብረው፣ ሾፌርነት የሚጠይቀውን ዲሲፕሊንና የመንገድ ሕግና ሥርዓት አክብረው የሚነዱት? ትልቁ ጥያቄ ይህ ይመስለኛል፡፡ የትራፊክ ሥርዓት አስከባሪዎችስ አልፎ አልፎ የሚታዩ የትራፊክ ሥርዓትና ሕግ ጥሰትን (በዋናነት፣ የዓመታዊ የመንገድ ብቃት ምርመራ (ቦሎ) ስለመደረጉ፣ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ክፍያ ስለመፈጸሙ ማጣራት) ካልሆነ በስተቀር፣ ምን ያህሉን ሥርዓት ያጣ አነዳድ ተቆጣጥረው ዕርምጃ ይወስዳሉ? በአዲስ አበባ ከተማ ከሃያ አምስት ዓመት በላይ መኪና በመንዳት ልምዴ ከታዘብኩት፣ እስከማውቀው ድረስ ቁጥጥር የሚደረገውና ዕርምጃ የሚወሰደው በጣም በተወሰኑት የትራፊክ ደንብና ሥርዓት ጥሰቶች ላይ ብቻ ነው። መሬት ላይ የተደረጉ የትራፊክ ምልክቶችንማ አብዛኛው ሾፌርም ሆነ የትራፊክ ደንብ አስከባሪዎች ከእነ መኖራቸውም የሚያውቋቸው አይመስልም።

አደጋ ከሚያስከትሉ ጥሰቶች ውስጥ ፍጥነት፣ ሞገደኛ/አዋኪ/ተጋፊ/አተራማሽ አነዳድ (Agresssive Driving)፣ መሽሎክሎክ፣ የትራፊክ መስመር ጠብቆ አለመንዳት ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህን ጥሰቶች የሥርዓት አስከባሪዎች እንደ ጥሰትም አይቆጥሯቸውም። እኔ እስከማውቀውም፣ በእነዚህ ጥሰቶች ዕርምጃ ሲወሰድ ያየሁበት ጊዜ የለም። በሌሎች አገሮች ‹‹ለሞገደኛ/አዋኪ/ተጋፊ/አተራማሽ አነዳድ ትዕግሥት የለንም፡፡›› (No Tolerance for Aggressive Driving) የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች በየመንገዱ በተለያዩ ዘዴዎች እንዲታዩ ተደርገው ይለጠፋሉ።

በሥውርም በግልጽም የሚሠሩ የትራፊክ ፖሊሶችም ይከታተላሉ፣ ዕርምጃ ይወስዳሉ። በእኛ አገር ግን ሞገደኛ/አዋኪ/ተጋፊ/አተራማሽ አነዳድ “ትልቅ ችሎታ” ነው። በርካታ ሾፌሮች እንዲህ ያለውን አነዳድ እንደ ትልቅ ችሎታ ይቆጥሩታል፣ የመንገድ ሥርዓት አስከባሪዎችና ተቆጣጣሪዎችም እንደ ጥፋት አይወስዱትም። ከዚህ ችግር አብሮ መታየት ያለበት፡- ለመሆኑ ስንቶቹ የትራፊክ ሥርዓት አስከባሪዎች (የትራፊክ ፖሊሶች) መኪና መንዳት ይችላሉ? መንዳት ካልቻሉ ደግሞ ምን ያህሉ ከመንዳት ጋር የተያያዙ ችግሮችን፣ ሥርዓቶችን፣ ዲሲፕሊኖችን፣ ቅድሚያ አሰጣጦችን ወዘተ. በትክክል ይረዳሉ? በትክክልስ ዕርምጃ ይወስዳሉ? መልካም ያልሆኑ አነዳዶችንስ ምን ያህል ይቆጣጠራሉ፣ ዕርምጃስ ይወስዳሉ? ቁጥጥር የሚደረገውና ዕርምጃ የሚወሰደው ከላይ እንደ ጠቆምኩት፣ በጣም በጥቂት የትራፊክ ደንብና ሥርዓት ጥሰቶች ላይ ብቻ ነው። ያውም አንድ ቀን ያዝ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለቀቅ በሚል፣ ጭራሽ ወጥነት በሌለው ሁኔታ ነው። አንድ ሰሞን ጠጥቶ መንዳትንና ከተፈቀደው በላይ ፍጥነትን ለመቆጣጠር ሥራ ተጀምሮ ነበር። አሁን ስለመኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም።

በዚህም ምክንያት አደጋን ለመቀነስ፣ አደባባዮችን ማፍረስና በመብራት መቀየር የሚያመጣው መፍትሔ በጣም የተወሰነ ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ አደባባዮች የማይሆን ቦታ ላይ ተሠርተው ይሆናል፣ ከመንገዱ መጠን ጋር ያልተጣጣሙ ሆነውም ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ መታረምና መሻሻል እንዳለባቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህን ማለት ግን አደባባዮችን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድ በሚመስል መልክ የከተማ መንገድ ፖሊሲን መቀየስ ግን የትራፊክ ፍሰትን አያሻሽልም፣ አደጋን አይቀንስም፣ የከተማ ውበትን አያሻሽልም፣ በአንፃሩም የታሪክ ቅርሳችንን እንዳናስፋፋና እንዳናሳድግ ይገታናል፡፡ 

ሰዎች ስህተት ስለሚሠሩ መንገዶች የሰውን ስህተት ሊቀንሱ በሚችሉበት ሁኔታ መንደፍ፣ መቀየስና መሥራት እስከ ተወሰነ ድረስ የሚያስኬድ ቢሆንም፣ በዋናነት ግን የተሟላ መፍትሔ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የመንዳትን ስህተት ለመቀነስ የሰዎችን ባህሪ መግራትም አንዱና ዋነኛው ሥራ መሆን አለበት፡፡ ሰዎች ችሎታ፣ ትዕግሥት፣ ዲሲፕሊን ከሌላቸውና ሕግና ሥርዓት ካላከበሩ መንገዶች የትኛውንም ያህል የሰዎችን ስህተት ሊቀንሱ በሚችሉበት መንገድ ቢሠሩም፣ ሙሉ በሙሉ ችግሮቹን ሊያስወግዱ አይችሉም፡፡ በእግረኛ መንገድ ላይ ለመንዳት የማናፍር ሰዎች እኮ ነን!! ሾፌሮች ኃላፊነታቸውን በዋናነት መወጣት አለባቸው፡፡ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ችሎታና ክህሎት፣ የፍሰቱ ቁጥጥርና ዕርምጃም እንዲሁ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል ያለበት ችግር ነው። በዋናነት በመንገዶች ዲዛይን ለውጥ የመኪና አደጋን እንቀንሳለን ብለን ካሰብን፣ የመጨረሻውና አማራጭ የሌለው መፍትሔ፣ ሰዎች በእግራቸው ብቻ እንዲሄዱ ማድረግ ነው፡፡ ያም ሆኖ እግረኞችም ቢሆኑ ሥርዓት አክብረውና ተሳስበው ካልተጓዙ እርስ በራስ መጋጨታቸው የማይቀር ነው፡፡

ስለዚህ የትራፊክ ችግሮችንና አደጋን ለመቀነስ ለመንገድ ተጠቃሚዎች በሙሉ፣ በዋናነት ሾፌሮች ተገቢ ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ፣ የሾፌሮችን አመለካከትና ባህሪ ማሻሻል፣ ችሎታ ያላቸው በግልጽም በሥውርም የሚሠሩ የመንገድ ሥርዓት አስከባሪዎች እንዲኖሩ ማድረግ፣ ጥብቅ የመንገድ አጠቃቀም ሕጎችን፣ ሥነ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል፣ ማስፈጸም፣ ተደጋጋሚ አጥፊዎችን መኪና እንዳይነዱ በተግባር ማድረግና ሌሎቸም ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን መውሰድ፣ አንዲሁም መንገዶችን ማሻሻል አስፈላጊ ነው። በሹፍርናችን ጉድለት፣ በመንገድ አጠቃቀም ቁጥጥርና ዕርምጃ ጉድለት ምክንያት ለሚደርስ ችግር አደባባዮችን ማፍረስና በመብራት መቀየር ሐኪሞች እንደሚሉት በሽታውን ማከም ሳይሆን የበሽታውን ምልክት ማከም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ካለንበት ችግር አያወጣንም። ሰለዚህ አደባባዮችን ለመቀነስ የምንወስደው ዕርምጃ በጣም በጥልቀት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና አጥሮች

የአዲስ አበባ አንዱ ችግር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በበቂ ያለ መኖር ነው፡፡ አሁን አሁን የሚታዩት የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ሥራ፣ የከተማው አስተዳደር ችግሩን እንደ ተረዳው ያሳያል፡፡ መልካም ነው፡፡ ይበል! ይቀጥል! ያሰኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት በርካታ ትልልቅ መንገዶች ተሠርተዋል፡፡ እነዚህን ዋና ዋና መንገዶች የሚያገናኙ፣ ወይም ደግሞ በዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚቀንሱ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በበቂ መጠን የሉም፡፡ የከተማው አስተዳደር በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ማትኮር መጀመሩ በእጅጉ የሚበረታታ ነው፡፡ እነዚህ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ፣ የትራፊክ ፍሰትን ለማሻሻል፣ የመንገዶችን መዘጋጋት ለመቀነስ፣ ተጠቃሚዎች አጭር አማራጮችን እንዲጠቀሙ ዕድል ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በመዝጋት በመንገድ የመጠቀም መብትን የሚቀንሱ፣ የከተማውንም የመንገድ ችግር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያባብሱ እንቅፋቶችን መመልከቱና መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

በአንድ ወቅት መንገዶችን በማጠር በበራቸው በኩል ማናቸውም ትራፊክ እንዳይተላለፍ የሚያደርጉ መሥሪያ ቤቶች እንደ ነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ለምሳሌ ያህል ከጋንዲ ሆስፒታል አጠገብ ያለውን ወደ ብሔራዊ ቴዓትር የሚወስደውን መንገድ ዘግቶ የነበረ ድርጅት ነበረ፡፡ ሌሎችም በየአካባቢው መንገዶችን ያጠሩ መሥሪያ ቤቶችም፣ ነዋሪዎቸም ነበሩ፡፡ በኋላ ላይ የከተማው አስተዳደር በተለይም ደግሞ በጊዜው የነበሩት የከተማው የመንገድ ባለሥልጣን ኃላፊ በወሰዱት መልካም ዕርምጃ፣ ብዙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተከፍተው ለሕዝብ አገልግሎታቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ሥራ ነው፣ መበረታታት ያለበትም ይህ ነው፡፡

አሁን ደግሞ አልፎ አልፎ የሚታየው የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የማጠር፣ የመዝጋት ተግባር በአንዳንድ የመኖሪያ ሠፈሮች አካባቢ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገርጂ፣ ወሰን ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንደ ፋሽን በሕዝብ መንገዶች ላይ በርና አጥር መሥራት ተይዟል፡፡ የመኖሪያ ቤቶች ባለቤቶች ቤታቸውን የመጠበቅ፣ ቤተሰባቸው ችግር እንዳይደርስበት የመከላከል መብት እንዳላቸው ጥያቄ የለውም፡፡ ይህም ቢሆን መንገድ እስከ መዝጋት ሊያደርስ አይገባውም፡፡  ዋና መንገድ ሆነ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ማንም ሰው በማናቸውም መንገድ ላይ በማናቸውም ጊዜ የመጠቀም የማለፍ መብት አለው፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ መሠረት የሰዓት ዕላፊ ካልተጣለ በቀር፣ ማንም ሰው በማናቸውም ሰዓት በማናቸው መንገድ የመጠቀም መብት አለው፡፡ መንገድ የሕዝብ ሀብት (Public Good) ነው፡፡ ማንም ቢሆን ማንንም በመንገድ ላይ እንዳያልፍ ሊከለክል አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ጎዳናዎች፣ መንገዶችና የመሳሰሉት ነገሮች የመንግሥት ወይም የአስተዳደር ክፍል ድርጅት ንብረቶች የሆኑት የሕዝብ አገልግሎት ንብረቶች ናቸው ይላቸዋል፡፡ በአጭሩ የሕዝብ አገልግሎት ንብረቶች ናቸው፡፡

የአንዳንድ አካባቢ ነዋሪዎች በውስጥ ለውስጥ መንገድ ላይ አጥር ሠርተው ከተወሰነ ሰዓት በኋላ በተለይም ሌሊት ይዘጉታል፡፡ ዓላማው ፀጥታ የሚያውኩ፣ የስርቆት ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ለመከላከል የሚል ነው፡፡ ችግሩ የለም ማለት አይቻልም። ሆኖም እንዲህ ያሉ ሰዎች ምናልባትም ከመቶ ወይም ከሺሕ መንገድ ተጠቃሚ አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ቢሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ከመቶ ወይም ከሺሕ አንድ ወይም ሁለት የሆኑ ሰዎችን ለመገደብ ሲባል፣ ሌሎች ዘጠና ዘጠኝ ወይም ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሰዎች መብታቸው ሊገደብ ይገባል ወይ ነው ጥያቄው፡፡ እንደ እኔ፣ እንደ እኔ መልሱ አይገባም የሚል ነው፡፡ ይህ መንገዶችን የማጠር ተግባር፣ በሕግም ቢሆን የማያስኬድ አሠራር ነው፡፡

ሌሎቹ ዘጠና ዘጠኝ ሰዎች በማናቸውም ሰዓት ለሥራ፣ ለአስቸኳይ ጉዳይ፣ የእሳት አደጋ በመከሰቱ፣ ድንገት የታመመ ሰው በመኖሩ፣ ማናቸውንም የሚያስኬድ የእግርም ሆነ የመኪና መንገድ ተጠቅመው የፈለጉበት ቦታ የመድረስ መብት አላቸው፡፡ ይህንን መብት ማንም ሰው ሊገድብ አይችልም፡፡ በእርግጥ በተወሰነ ደረጃ በፈቃድ መንገዶችን መዝጋት ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ግን በጣም በጠባቡ የሚተረጎምና ለጊዜያዊ ችግር ብቻ የሚፈቀድ ሊሆን ይችል እንደሆነ ነው እንጂ፣ የሕዝብ ሀብት የሆኑ መንገዶችን አጥር ወይ በር ሠርቶ መዝጋት ትክክልም፣ ሕጋዊም አይደለም፡፡ መንግሥት የአካባቢ ሰላምን የመጠበቅ ግዴታ አለበት ሰዎችም በተጨማሪ የራሳቸውን ሰላምና ፀጥታ ይጠብቃሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ማናቸውም ነዋሪ፣ በሕግ በባለቤትነት ማረጋገጫ (ካርታ) ከተሰጣቸው ይዞታቸው ውጪ አልፈው የሚገኝን መንገድ በግልም ሆነ በቡድን ሊዘጉና በማናቸውም ሰዓት ተጠቃሚ እንዳያልፍበት ሊከለክሉ ግን አይችሉም፡፡

እነዚህ መንገዶች ላይ የተሠሩ አጥሮችና በሮች ቀንም ቢሆን፣ እንኳን የራሳቸው የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እኔንም ጨምሮ የታጠረ መንገድ አቋርጠው ሲሄዱ፣ ወደ የማይፈለጉበት የሰው ሠፈር እንደገቡ እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ማንም ሰው በነፃነት ሊሄድበት በሚገባ የሕዝብ መንገድ ላይ እንዲህ ያለ ስሜት እንዲፈጠር ለምን ይደረጋል? ይህ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ይህ ልምድ ሌላም መጥፎ ታሪክ አለው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከዘር መድልኦና ከሀብት ጋር በተያያዘ በግቢ የታጠሩ መንደሮችን ሠርቶ፣ ሌላው ዝቅተኛ ተብሎ የሚታሰብ ወገን በዚያ አካባቢ እንዳይኖርና እንዳያልፍ የሚያደርግ ልማድ አለ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ መንገድ የሚያጥሩ ወገኖች ይህንን ልምድ አውቀው ነው ያደረጉት የሚል ግምት በፍፁም የለኝም፡፡ ግን አጥር የሚሠሩ ሰዎች እንደዚያ እንዳይመስልባቸውም መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ከሌሎች አገሮች የምንወስደውንም ልምድ ከሥር ከመሠረቱ ሳናጣራ እንዳለ መውሰዱም ቢሆን የራሱ ችግር እንዳለው ማወቅ ይገባል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ይህንን ተረድቶ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዳይታጠሩ እንዳይዘጉ መከላከል አለበት፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን ሰዎች ሰላምና ፀጥታቸው እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት።  ከላይ እንደ ጠቀስኩት ይህንን ማስታወሻ ከጻፍኩ ወዲህ በመንገዶች ላይ አጥር መሥራት ተገቢ እንዳልሆነ ውይይት መጀመሩን አድምጫለሁ። ውይይቱ መቀጠል፣ የተሠሩ አጥሮችም መነሳት፣ ወደፊትም እንዲህ ያሉ አጥሮችን የመሥራቱ ልማድ መቆም አለበት። 

በጋራዎች ላይ የሚሠሩ ቤቶች

በአዲስ አበባ ዙሪያ ለከተማዋ ከፍተኛ ውበት የሚሰጡ ጋራዎች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ እኒህ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ጋራዎች በዛፎች የተሸፈኑ በመሆናቸው እንደ ከተማዋ ሳንባ የሚታዩም ናቸው፡፡ በተለይ የእንጦጦና የየካ ሰንሰለታማ ጋራዎች በዚህ የታወቁ ናቸው፡፡ በጋራዎቹ ላይ የሚገኙት ደኖች ለአዲስ አበባ ዕድገትና እንደ ከተማ መቆየትም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበራቸው አንዳንድ የታሪክ ማስረጃዎችም ይገልጻሉ፡፡ በቀድሞው ዘመን ከተማ ይቆረቆርና ማገዶ ሲያልቅና አካባቢው ሲቆሽሽ፣ ቦታውን ለቆ መሄድ የተለመደ እንደነበረ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባ ግን ጋራዎቿን ከሸፈኑት ደኖች ማገዶ ማግኘት በመቻሏ፣ ቀስ በቀስ እያደገችና እየተስፋፋች ዛሬ የምናውቃት አዲስ አበባ ሆነች ይሉናል የታሪክ አዋቂዎች፡፡ ታዲያ ወደ ጋራ ሰንሰለቶች እየወጡ ያሉ መኖሪያ አካባቢዎች እንደ ቀድሞው ጊዜ የከተማዋን ማገዶ ባይሻሙ እንኳን፣ የከተማዋን ሳንባ እያጠበቡት መሄዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ውበቷንም ቀስ በቀስ እየቀነሱት ይሄዳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የአየር ብክለት እየጨመረ ለመሄዱም ብዙ መረጃዎች አሉ። ከአምስት ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ይኖርባታል ተብሎ ለሚገመተው አዲስ አበባ ይህ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ነው፡፡ 

ከዚህ ጋርም ተያይዞ በጋራው ላይ ለሚሠሩ ቤቶች የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራትና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማቅረብም ከመሬቱ አቀማመጥ የተነሳ አስቸጋሪና እጅግ በጣም ውድ እንደሚያደርገው መገመት ብዙም ዕውቀት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ብዙ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት አዲስ አበባ በታላቁ የስምጥ ሸለቆ ጠርዝ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡ ይህም ማለት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የመሬት መንቀጥቀጥ ሥጋት ያለባት ከተማ ነች፡፡ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ደግሞ ጋራ ላይ በተሠሩ መኖሪያዎች ላይ የሚያደርሰው ችግር ከፍ ያለ ነው፡፡ በተጨማሪም የመሬት መንሸራተት አንዱና ሌላው እንደዚህ ባሉ ዳገታማ አካባቢዎች ላይ በተሠሩ መኖሪያዎችና የግንባታ ሥራዎች ላይ ተደጋግሞ ሊደርስ የሚችል ችግር መሆኑን ከብዙ አገሮች ልምድ የምናየው ነው፡፡

ጋራዎች ላይ ሥርዓት ሳይጠብቁና ተገቢው ፕላን ሳይኖራቸው ከተሠሩ የከተማ ክፍሎች በብራዚሏ ሪዮ ዲጃኔሮ፣ ፋቤላ በተባለው ጋራ ላይ የተሠራችው ሳንታ ማርታ የተባለችው ሠፈር ጥሩ ምሳሌ ነች። ሳንታ ማርታን በቴሌቪዥን መስኮት ብዙዎቻችን ሳናያት የቀረን አይመስለኝም። ሳንታ ማርታ በብራዚል ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የማኅበራዊ አገልግሎት፣ የሰላም፣ የፀጥታ፣ የድህነትና የተያያዙ በርካታ ችግሮች ካለባቸው መንደሮች ቀዳሚነቱን የያዘች መንደር ነች። ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት (መንደሯ ከተሠራች ከሰማንያ አምስት ዓመት በኋላ) የሪዮ ዲጃኔሮ ከተማ አስተዳደርና የብራዚል መንግሥት የሳንታ ማርታን መንደር ችግሮች ለማቃለል ከፍተኛ ድካም በማድረግ ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ችግሮቹን ለማስወገድ እንዲህ ቀላል አልሆነም። እኛም እንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ አለብን። ብልህ ከሰው ስህተት ይማራል ሞኝ ግን በራሱ ከሚደርሱ ችግሮች ብቻ ነው የሚማረው ይባላል፡፡ ታዲያ እኛ በዚህ ረገድ ከየትኞቹ ነን?

ከመኖሪያ አካባቢ ጋር የማይሄዱ ሥራዎች

መኖሪያ ቤቶች የቤተሰብ መሠረቶች ናቸው፡፡ ቤተሰቦች ደግሞ የአገር መሠረቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ መኖሪያ ቤት መሠረታዊ ከሚባሉት ጉዳዮቹ አንዱ ነው፡፡ መልካም መኖሪያ ቤትና የመኖሪያ አካባቢ ደግሞ ጥሩ ቤተሰብና አዲስ ትውልድ የሚበቅልባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ መኖሪያ አካባቢዎች ችግር ያለባቸው ከሆኑ ሰዎች መልካም ኑሮ አይኖራቸውም፡፡ እንደዚያ ባሉ አካባቢዎች የሚያድጉ ልጆችም በአብዛኛው ጥሩ ዜጋ የመሆናቸው ዕድል ይጠባል፡፡ ለዚህም በተለያዩ አገሮች በሚገኙ ጌቶዎች፣ ፌቤላዎች፣ ስኳተር ካምፕ፣ ወዘተ. በሚባሉ ውጥንቅጣቸው በወጣ መኖሪያዎች ውስጥ የሚኖሩ የአብዛኞቹን ዜጎችና እንደዚያ ባሉ አካባቢዎች የሚያድጉ ወጣቶችን ሁኔታ ማጠያየቅና መገንዘብ ጥሩ መረጃ ይሰጣል፡፡

በእርግጥ በመኖሪያ አካባቢዎች አቅራቢያ መሠረታዊና ከመኖሪያ አካባቢዎች ጋር በመልካም ሁኔታ ሊደጋገፉ የሚችሉ እንደ መለስተኛ ክሊኒኮች፣ መድኃኒት ቤቶች፣ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች የሚሸጡ ሱቆች እንዲሠሩ ቢፈቀድ ክፋት የለውም፡፡ በአገራችን በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ አካባቢ የሚታየው ልምድ ግን ከዚህ በጣም የራቀ ነው፡፡ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት ክበቦች፣ ጫት መቃሚያዎች፣ ሺሻ ቤቶች፣ ከፍተኛ ድምፅ ያላቸው ተቋማትና የመሳሰሉት ፈቃድ እየተሰጣቸው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ተቋማት ከመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሊካሄዱ የማይገባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ ለምን ይደረጋል ብዬ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተነጋግሬአለሁኝ፡፡ ብዙውን ጊዜ የማገኘው መልስ ‹‹ባለቤቱ በቤቱ የመጠቀም መብት” አለው የሚል ነው፡፡

“ባለቤቱ በቤቱ የመጠቀም መብት›› አለው የሚለው አባባል ስለመብትና በመብት ስለመጠቀም የተሳሳተ/የተወላገደ አመለካከትን ያሳያል፡፡ ሰዎች ብዙ መብቶች አሏቸው፡፡ የመኖር መብት ያለው ሰው ሌላውን የመግደል መብት አለው ማለት አይደለም፡፡ የሌላውን ሰው የመኖር መብት ማክበር አለበት፡፡ ሐሳብ የመግለጽ መብት ያለው ሰው ሐሳቡን መግለጽ የሚችለው የሌላውን መብት ሳይነካ ነው፡፡ የመኪና ባለቤት የመሆንና የመንዳት መብት ያለው ሰው፣ ሌላውን ሰው በመንገድ እንዳይጠቀም መከልከል ወይም መንገደኛን መግጨት ይችላል ማለት አይደለም፡፡  በንብረቱ የመጠቀም መብት ያለው ሰው ሌላው ሰው፣ ተመሳሳይ የሆነ ንብረቱን የመጠቀም መብቱን ማሳጣት ይችላል ማለትም አይደለም፡፡ እኔ በቤቴ የመጠቀም መብት አለኝ ብዬ ጎረቤቴን በጩኸት ጆሮውን ማደንቆር፣ ወይም እንቅልፍ የመንፈግ መብት የለኝም፡፡ መኖሪያ አካባቢዎች ሊኖራቸው የሚገባውን ፀጥታና ሰላም ማወክ የሚያስችል መብት  ሊኖረኝ አይችልም፡፡

በቤቴ ውስጥ የሞራል ብክለትን በአካባቢው የሚያስፋፋ ሥራ መሥራት የለብኝም።

እንዲህ ያሉ ሥራዎችን መሥራት ‹‹የባለቤቱ በቤቱ የመጠቀም መብት›› ነው የሚሉ የሥራ ኃላፊዎች መብት ምን ማለት እንደሆነ ያልገባቸው፣ መብት ሲኖር አብሮትም ግዴታ እንዳለ፣ ሌላው ቢቀር የአንድ ሰው መብት የሌሎች ሰዎችን መብት መንካትን እንደማያስከትል ማወቅ የተሳናቸው ይመስለኛል፡፡ በዚህ የተሳሳተ የመብት ትርጉም ላይ ተመሥርቶ የከተማ ልማት ፖሊሲ ይወጣል ወይም ወጥቷል ብሎ መገመት በጣም ይከብዳል፡፡ ግን በተግባር የሚታየው ይህ ነው፡፡ አንድ ሰው መኖሪያ ቤቱን ከፈለገ (በሌሎች መኖሪያ ቤቶች መካከል) መጠጥ ቤት ይከፍትበታል፣ ቢፈልግ የምሽት ክበብ ያደርገዋል፣ ቢፈልግ ጫት ቤት ያደርገዋል፣ ቢፈልግ ፔንሲዮን ያደርገዋል፣ ቢፈልግ “ማሳጅ” ቤት ይከፍትበታል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከላይ ለማሳየት እንደ ሞከርኩት አንድ ሰው በራሱ ንብረት የመጠቀም መብቱን ተጠቅሞ፣ የሌሎችን በመኖሪያ ቤታቸው የመጠቀም መብታቸውን መንፈግ ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ በጣም ትክክል ያልሆነ “የመብት” ወይም “የነፃነት” አስተሳሰብ በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ በስፋት ይታያል፡፡ በጣም ከፍተኛ ችግር ያለበት ምናልባትም ጥራዝ ነጠቅ የሆነ “የመብት” ወይም “የነፃነት” አስተሳሰብ በመሆኑ ሊታረምና ሊስተካከል ይገባዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

በበርካታ አገሮች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ የከተማ ክፍሎች በተለያየ ዞኖች ይከፋፍላሉ። በተለይ መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ መኖሪያ ቤቶች የመልካም ቤተሰብ፣ የመልካም አዲስ ትውልድ መብቀያ ሥፍራዎችና የአገርም መሠረት በመሆናቸው፡፡ የከተማ አስተዳደሮች የመኖሪያ ዞኖችን ከሌሎች ዞኖች መለየት አለባቸው (ዞን መወሰን፣ አጥር ማጠር እንዳልሆነ ግን ልብ ይሏል)፡፡ ምናልባት ሌሎች ሥራዎችም አብረው እንዲቀላቀሉ ማድረግ ካስፈለገ ሊቀላቀሉ የሚገባቸውን ሥራዎች መለየት፣ ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በጉዳዩ ላይ በግልጽ መክረው ሊወስኑበት ይገባል፡፡ በቤቱ የመጠቀም መብት ያለው ሰው የሌሎች ሰዎችን በቤታቸው የመጠቀም መብት ሊያሳጣቸው አይገባም፣ አይችልምም። ይህ በጥልቀት ሊታሰብበትና መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

የውኃ ጉዳይ

ለመጠጥና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ንፁህ ውኃ በበቂ መጠን ለከተማ ማቅረብ በጣም ከፍተኛ ተግዳሮት ነው። ይህ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ላይ ላሉ ከተሞች ሁሉ ራሱን የቻለ ትልቅ ፈተና ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ለመፍታት በጣም ከባድ እንደሚሆን መገመት ነብይነት አይጠይቅም። አሁን ባሉት ግድቦችም ሆነ የከርሰ ምድር ውኃ ልማት ሁሌ እያደገ በመሄድ ላይ ያለውን የአዲስ አበባ ከተማን የውኃ ፍላጎት ማሟላት፣ ሁልጊዜም መቋጫ የሌለው ትግል ነው። ለዚህ አንዱም ችግር አዲስ አበባ በትልቅ የገጸ ምድር ውኃ አካል ወይም ትልቅ ወንዝ/ዥረት ዳር የተመሠረተች ከተማ ባለመሆኗ፣ ለችግሩ የተሻለ መፍትሔ ለማግኘት እንዳይቻል ያደረገ ይመስለኛል።

አብዛኛው የአዲስ አበባ ክፍል ሳምንቱን ሙሉ ወኃ አያገኝም። አንዳንድ አካባቢዎች ውኃ የሚያገኙት በሳምንት አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ቢሆን ነው። እኔ የምኖርበት አካባቢ በሳምንት አንዴ እጅግ ቢበዛ ሁለቴ ውኃ ከሚያገኙት አካባቢዎች አንዱ ነው። ያም ቢሆን በጣም በተቆራረጠ ኃይልና መጠን ነው። ሰለዚህ እያንዳንዱ ቤተሰብ በተገኘው የውኃ ማጠራቀሚያ ተጠቅሞ ለሁለትና ለሦስት ቀናት፣ ለሳምንትም ውኃ መያዝ የግድ ነው። ለዚህም እንደ አዲስ አበባ ከተማ በየቤቱ የውኃ ማጠራቀሚያ ያለው ወይም የሰቀለ ከተማ በዓለም ላይ ብዙ የሚገኝ አይመስለኝም።

ታዲያ የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ሳስብ ሁልጊዜ የሚመጣብኝ የኢንጂነር ታደሰ ኃይለ ሥላሴ የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ለመፍታትና በምግብ ራስን ለመቻል ያቀረቡት የገጸ ምድር የውኃ ልማትና አጠቃቀም ሐሳብ ነው (ኢንጂነር ታደሰ ነፍሳቸውን ይማረውና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል)። ኢንጂነር ታደሰ ይህንን ሐሳብ ከማቅረባቸው በፊት በጣም ሰፊ የኢንጂነሪንግ፣ የውኃ ሀብትና የመልክዓ ምድር ጥናት አድርገዋል። አንዴ ወይ ሁለቴ የጥናታቸውን መግለጫ ባቀረቡባቸው ውይይቶች ላይ ተሳትፌአለሁ፡፡ ከሌሎች ሰዎችም ጋር ቢሯቸው ድረስ ሄጄ ውይይት አድርገናል። ጥናታቸውን ለማከናወን ከተጠቀሙባቸው ግብዓቶች አንዱ የገጸ ምድር ካርታዎች/ማፖች ናቸው። ኢንጂነሩ በከፍተኛ ወጪና ድካም ያሰባሰቧቸውን መካከለኛ አዳራሽ የሞሉ፣ በተለያየ መጠን የተሠሩ በርካታ የገጸ ምድር ካርታዎችን ተመልክቻለሁ። የኢንጂነር ታደሰን ጥናት ለማስተዋወቅና በሥራ ላይ እንዲውል ለመገፋፋትም አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበረ አስታውሳለሁ። የማስታውሰውን ያህል የኢንጂነር ታደሰ ሐሳብ ሦስት ዋና ዋና ዕቅዶችን የያዘ ነበር። አንደኛው የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ለዘለቄታው መፍታት ነው። ሁለተኛው ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ተጠቅማ በምግብ ራሷን እንድትችል የታለመ ነው።

የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ለማስወገድ የታለመው ዕቅድ አንደኛው፣ ከአዲስ አበባ ሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የሚገኙ ወንዞችን መጥለፍና በአዲስ አበባ መሀል የሚያልፍ ካናል መሥራትን የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪም በእንጦጦ ወደ ሰሜን ባለው አካባቢ ይመስለኛል ዥረቶችን ጠልፎ ትልቅ የውኃ ማከማቻ መሥራትና ጋራውን ሰርስሮ ቦይ (ተነል) በመሥራት ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለአዲስ አበባ ከተማ ማቅረብ መቻል ነው።  ሌሎቹ ሁለቱ ሐሳቦቻቸው ከአዲሰ አበባ የውኃ ፍላጎት ውጪ የሚገኙ የገጸ ምድር የውኃ ልማትና አጠቃቀምን የሚመለከቱ በመሆናቸው እዚህ ላይ ለጊዜው አላነሳቸውም። ሆኖም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጥናቱን አፈላልገው ቢያዩት መልካም ይመስለኛል። ኢንጂነር ታደሰ ለሥራው የሚያስፈልገውን የገንዘብ ግምት ሁሉ ሳይቀር አቅርበው ነበረ።

ከላይ እንደገለጽኩት ዕቅዳቸው የአዲስ አበባን የውኃ ችግር የሚያስወግድ ብቻ ሳይሆ፣ የአገራችን የውኃ አጠቃቀምና በምግብ ምርት ራስን የመቻል ዓላማን ለማሳካት ከፍተኛ ራዕይ የያዘ ነው። ካርል ሳንድበርግ የተባለ ጸሐፊ፣ ‹‹መጀመሪያ ሕልም ከሌለን ምንም ማምጣት አይቻልም” (Nothing Happens Unless We First Deam) እንዳለው፣ ራዕይ ሳይኖር ትልቅ ቁም ነገር መሥራት አይቻልም። ስለዚህ ይህንን ሐሳብ መለስ ብሎ ማየትና ተጨማሪ ጥናቶቸን ማድረግ፣ እንደ አስፈላጊነቱ አሻሽሎ ወይም ለውጦ በሥራ ላይ የሚውልበትን መንገድ መፈለግ አጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል። ሐሳባቸው በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል መንግሥት ደረጃም እንደገና መቃኘት ያለበት እጅግ አሸጋጋሪ (ትራንስፎርሜሽናል) ሐሳብ ነው የሚል እምነት አለኝ። ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ እንዳለ ሥራ ላይ ማዋል ባይቻል እንኳን፣ ሌላ ሐሳብ ለማጫር እንደሚረዳ እምነቴ የፀና ነው። ይህ ሐሳባቸው ኢንጂነር ታደሰን በኢትዮጵያ የገጸ ምድር ውኃ ልማትና አጠቃቀም ኢንጂነሪንግ ታሪክ (ሌላ ቢቀር ሐሳቡን በመፈንጠቅ) ከልጅ ልጅ ለሚዘልቅ ዘመን ስማቸውን ያስጠራዋል ብዬም አስባለሁ። የአዲስ አበባ የውኃ ችግር ደግሞ መሠረታዊና ዘላቂ መፍትሔ ይፈልጋል። መፍትሔውን ለማግኘት ደግሞ የማንፈነቅለው ድንጋይ የማናነሳው ሐሳብ መኖር የለበትም። ከቻልን የኢንጂነሩን ሐሳብም እንጠቀምበት። 

በሰላምና በጤና ያሰንብተን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው wgselassie@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...