Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ለረጅም ጊዜ ካዳበርኩዋቸው ልማዶች አንዱ በሥራ ቀን ማልዶ መነሳት ነው፡፡ በመጠኑ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ቀኑን መጀመር የእኔ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ቅዳሜ ማለዳ በደንብ እተኛለሁ፡፡ እሑድ ደግሞ ማልጄ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ከልጅነቴ ጀምሮ ያዳበርከት ልማዴ ነው፡፡ ቀኑ ቅዳሜ ሲሆን ግን ከእንቅልፌ የምነሳው አርፍጄ ነው፡፡ ለነገሩ ቅዳሜ አርፍጄ የምነሳው ቀኑ የዕረፍት ቀን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ዓርብ ሥራ ስለማመሽ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግን ሁሌም ከምነቃበት ሰዓት በፊት ያነቃኝ አንድ ስልክ ነበር፡፡

ስልኩን የደወለልኝ የጓደኛዬ ወንድም ሲሆን፣ በአፋጣኝ ወደ ቤታቸው እንድመጣ ይነግረኛል፡፡ እኔም ትንሽ ግራ ተጋብቼ ለምን እንደፈለገኝ ብጠይቀውም፣ ምንም ሳይነግረኝ ብቻ በአፋጣኝ ቤታቸው እንድመጣ ያሳስበኛል፡፡ እኔም በነገሩ ተደናግጬ ከአልጋዬ ተስፈንጥሬ ቶሎ ወደ ጓደኛዬ ቤት ማምራት ጀመርኩ፡፡ ምን ቢገጥመው ነው አጣድፎ የጠራኝ የሚለው ከንክኖኛል፡፡

ወደ ጓደኛዬ ቤት ለመሄድ የግድ ታክሲ መጠበቅ ስለነበረብኝ አሰልቺ የሆነውን የታክሲ ሠልፍ ተቀላቀልኩ፡፡ በስልክ የተነገረኝ በአፋጣኝ ቶሎ ድረስ የሚለው መልዕክት በህሊናዬ ቢያቃጭልም፣ የታክሲ ሠልፉ ግን ሊገፋልኝ አልቻለም፡፡ ለክፋቱ ደግሞ ያለወትሮ ታክሲዎች የመስቀል ወፍ ሆነው በየአሥር ደቂቃው ብቻ ነው ብቅ የሚሉት፡፡ የማይደርስ ነገር የለምና ተራዬ ደርሶ ተሳፈርኩ፡፡

መሳፈር ብቻ ግን ምን ያደርጋል? ጉዟችንን ከጀመርን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የታክሲው ጐማ ይፈነዳና መንገድ ላይ ሁላችንም ተራገፍን፡፡ እኔም ሌላ ታክሲ መጠበቁን ትቼ በኮንትራት ታክሲ ተሳፍሬ ወደ ጓደኛዬ ቤት ነጐድኩ፡፡ በመንገዴ ሁሉ ግን ምን ገጥሟቸው ይሆን የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይመላለስብኛል፡፡ ዘንድሮ እንደሆነ አስደንጋጩ ነገር በዝቷል፡፡

ጓደኛዬ ቤት አካባቢ ስደርስ ግን ሰዎች ገባ ወጣ ሲሉ ተመለከትኩ፡፡ ልቤ መደንገጥ ጀመረ፡፡ ወደ ቤታቸው ስገባ የለቅሶ ድምፅ መስማት ጀመርኩ፡፡ የጓደኛዬ አባት ሽማግሌ በመሆናቸው እሳቸው አርፈው ይሆናል ብዬ እኔም ማልቀሴን ቀጠልኩ፡፡ እሳቸው 80 ዓመት ቢያልፋቸውም ደግ ሰው ስለነበሩ ነው የማልቀሴ ምክንያት፡፡

እኔም እያለቀስኩ ጓደኛዬን ባፈላልገውም ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ወዲያው ግን አባቱን ሳያቸው በነገሩ ግራ ተጋብቼ የጓደኛዬን ወንድም ከሩቅ ተመለከትኩት፡፡ እሱም ወደ እኔ መጥቶ ጓደኛዬ ማረፉን አረጋገጠልኝ፡፡ እኔም በቈሜ ላብ አጠመቀኝ፡፡ በውኔ ሳይሆን በህልሜ እስኪመስለኝ ድረስ ግራ ተጋባሁ፡፡ በድንጋጤ ከንፈሮቼ ደረቁ፡፡

ጓደኛዬ ገና በሰላሳዎቹ ውስጥ የነበረና ፍጹም ጤነኛ ስለነበር በጣም ግራ ተጋባሁ፡፡ በተፈጠረው ነገር እጅግ ባዝንም ጉዳዩን ከማጣራት አልተቆጠብኩም፡፡ እንደ ነገርኳችሁ ጓደኛዬ ወጣት ከመሆኑም ባሻገር ስፖርተኛና ጤነኛ ነው፡፡ ሰሞኑን በርካታ ሰው ምንነቱ ባልታወቁ በሽታ በተኛበት እየቀረ ስለሆነ፣ ጓደኛዬ ምን እንደ ገጠመው ማጣራቱን ቀጠልኩ፡፡

ወንድሙ እንደነገረኝ ከሆነ ጓደኛዬ ሁሌም እንደሚያደርገው ዓርብ በጊዜ ገብቶ ግቢያቸውን ሲያፀዳዳ ቆይቶ፣ ምሽት ላይ ቴሌቪዥን ተመልክቶ ወደ መኝታው ያመራል፡፡ እሱም ማታ አግኝቶት በጠዋት ስፖርት ለመሥራት ስለሚነሳ እንዲቀሰቅሰው ነግሮት እንደነበር አጫወተኝ፡፡ ጠዋት ሊቀሰቅሰው ሲሄድ ግን ወንድሙን እንዳላገኘው ነገረኝ፡፡

ጓደኛዬ የሞተበት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ወንድሙን ስጠይቀው፣ ፖሊስ ገና የምርመራ ውጤቱን ባያሳውቅም ከምግብ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ነገረኝ፡፡ ወንድሙ እንዳብራራልኝ ጓደኛዬ አዘውትሮ ሆቴሎች ስለሚመገብ የሚበላው የምግብ ዘይት የሞቱ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል አጫወተኝ፡፡

የጓደኛዬ ወንድም ምንም እንኳን ጥርጣሬውን ቢነግረኝም፣ እኔም በየሆቴሉ ስለምንመገበው የፓልም ዘይት ብዙ ጥያቄ አለኝ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ የምግብ ዘይት በአገራችን ከተስፋፋ በኋላ በርካታ የጓደኛዬ ዓይነት ገጠመኞች በርክተዋል፡፡ ብዙዎች ከተኙበት ሳይነሱ ቀርተዋል፡፡ በርካቶቹ ደግሞ ጤነኞች የሚባሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ይህን ገጠመኝ ያጫወትኳችሁ፣ የሁልጊዜም ጥያቄን በዚያው ለማንሳት ፈልጌ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ የእኔና የመሰሎቼ ሥጋት ምክንያታዊ ቢሆንም፣ እንደ ወጡ መቅረት ወይም በተኙበት ለዘለዓለሙ ማሸለብ የዘመናችን አደገኛ ክስተት እየሆነ ነው፡፡ ከምንመገበው በተጨማሪ የጤና ምርመራ አድርገን ራሳችንን አለማወቃችን ለድንገተኛ ሕልፈታችን ምክንያት ስለሆነ፣ በተቻለን መጠን ቢቻል በዓመት ሁለቴ ጤናችንን ብንፈትሽ መልካም ነው፡፡ እባካችሁ እንመርመር በማለት ማሳሰብ የፈለግኩት ድንገተኛ ሞት ስለበዛ ነው፡፡ ለማንኛውም ቸር እንሰንብት!

(ቴዎድሮስ ተዘራ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...