በእስጢፋኖስ ስሜ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች በኩል ለኢትየጵያ ሕዝብ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን የተሰጡትን ማብራሪያ፣ እንደ አንድ ንቁ ዜጋ ለመከታተል ሞክሬያለሁ፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያና መልስ እንደ መስጠታቸው አንዱን ዓብይ ጉዳይ ብቻ አንስቼ እንዲህ ለማለት ወደድኩኝ፡፡
በአገሪቱ እንደ ተንሰራፋው ሌብነት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሌብነቱ መዋቅራዊ እስኪመስል ሥር እንደ መስደዱ፣ ዜጎች ያለ እጅ መንሻ ምንም ዓይነት ጉዳይ (አገልግሎት) ማግኘት ብርቅ በሆነባቸውና እጅግ በተማረሩበት ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቂና አጥጋቢ መልስ ወይም ማብራሪያ አልሰጡም ባይ ነኝ፡፡
እንደ ወትሮው የመንግሥት ዓይን ያወጣ ችግሮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሲጠየቁ እንደሚያደርጉት የችግሩን ዙሪያ በብዙ ምክርና ተግሳፅ ከማከክ ውጪ፣ ቁርጠኛ የሆነውን የመንግሥታቸውን አቋም እንደማያንፀባርቁ ሁሉ የሌብነትን መጥፎነት፣ አስፀያፊነት፣ የተበላሸ ሥነ ምግባር መሆኑን፣ እንዲሁም በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት በተለይ አነስተኛ ገቢ ባለቸው የኅብረተሰብ ክፎሎች ላይ ስለሚያደርሰው ጫና ከደሃ ወደ የደሃ ደሃ እንደሚያወርዳቸው እየጠቀሱ፣ በአጠቃላይ የሌብነትን አሉታዊ ተፅዕኖ ማብራራት በችግሩ ዙሪያ መዞር እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡
ይህ ማብራሪያ ኅብረተሰቡ አያስፈልገውም፡፡ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር በየዕለቱ እያየውና እየኖረው ስለሆነ፡፡ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑና በግል ተቀማት ባለ ሌብነት ከዚህ አልፎ በሃይማኖት ተቋማት ባለ ማጭበርበርና ሌብነት፣ ኅብረተሰቡ በቂና የዳበረ ሰለባ የመሆን ልምድና ተሞክሮ አለው፡፡ የቸገረው ማብራረያ አይደለም፡፡ ለማብራራት ለማብራራትማ ሌቦቹ እንኳን ስለአሉታዊው ተፅዕኖ በየመድረኩ አፍ የሚያስከፍት ዲስኩር ማሰማት የሚያቅታቸው አይመስለኝም፡፡ የሚያቅታቸው አለመስረቅ እንጂ፡፡
ሌላው በንግግራቸው በዚህ በሌብነት ጉዳይ ላይ መንግሥትን ተሸናፊ እንደሆነ አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ ይህንንም በጠቀሷቸው ምሳሌዎች አሳብቀዋል፡፡
እንደ መንግሥት ሌብነትን ቀይ መስመር እንደሆነ አስቀምጦ ሳለ ሌቦቹ ግን ቀይ መስመሩ እንደ ቀይ ምንጣፍ ሆኖላቸው እንዳሻቸው ከፈነጩ፣ መንግሥትን የማይፈሩ ወይም የመንግሥትን የአሠራር ሥርዓትን የገለበጡ ከመንግሥት ቁጥጥር በላይ የሆኑ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሌቦች እንደ አገር አፍርተናል እንደ ማለት ነው፡፡ ቀይ መስመር ከመጣስ አልፎ ቀይ ምንጣፍ ከሆነና ፋይል በእጁ እንጂ በእግሩ እንደማይሄድ በግልጽ የሚናገሩ የመንግሥት አግልግሎት ሰጪዎች መኖራቸው ከታወቀ ከተሸናፊነት ውጪ ምን ሊባል ይችላል?
በእርግጥ ምሳሌዎቹን ሲናገሩ የችግሩን ጥልቀት ለማስረዳት ነው፡፡ ተው፣ ነገር አትጠምዝዝ የሚል አይጠፋም፡፡ ነገሩ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ እኔን ያሳሰበኝ የችግሩ ጥልቀት ከመንግሥት መጥለቁ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ስለኑሮ ውድነት ሲጠየቁ የኑሮ ውድነት የለም የማለት ያህል፣ ‹‹ሰው በየሥጋ ቤቱ እየተተራመሰ እንደሆነ›› በመናገራቸው፣ በኑሮ ውድነት ናላው የዞረበትን የበለጠ አዙረውበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእፍኝ ከባህሩ ጨልፎ ስለባህሩ አጠቃላይ ሁኔታ እንደ መናገር ያህል ነበር፡፡
ኅብረተሰቡ እጅግ የተማረረባቸውንና የሚያለቅስባቸውን ነገሮች እንዲህ ዳር ዳሩንና እያለባበሱ መሄድ ለድርጊቱ ፈጻሚዎች ከአቅማችን በላይ ናችሁ እንዲሁም ኅብረተሰቡን ተሰፋ ቁረጡ የሚል አንድምታን ይፈጥራል፡፡
መንግሥት ሌቦችን ከልቡ እንዳይቀጣቸው የተቸገረበት ጉዳይ ምን ይሆን?
መንግሥት ያሰመረውን የማይጣስ ቀይ መስመርን እንዳሻው ሲጣስ አልፎ ተርፎ ቀይ መስመሩ ወደ ምቹ ቀይ ምንጣፍነት ተቀይሮ ሌቦች ጀብዱ እንደሠራና ግዳጅ እንዲጣል እስኪንጎማለሉበት ድረስ የተደረሰው፣ መንግሥት ምን ቸግሮት ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
የእኔ መላምት
የማስቀምጠውን መላምት መሞገት ወይም በጥናት ውድቅ ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ መላምቴን እንዲህ አሰቀምጣለሁ፡፡ አገሪቱን እየመራ ያለው የብልፅግና መንግሥት ነው፡፡ ማለቴ በምርጫ አሸንፎ መንግሥት የሆነው የብልፅግና ፓርቲ ነው፡፡
እንደ እኔ መረዳት የመንግሥት (የብልፅግና ፓርቲ) ከፍተኛው መዋቅር በሌብነት ጉዳይ ላይ የአቋም ችግር ያለበት አይመስለኝም፡፡ ወይም ሌብነትን ከልቡ የመታገል፣ ከተቻለ የማጥፋት ካልሆነ በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስና በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚወገዝ ሥነ ምግባር የማድረግ ፅኑ ፍላጎት አለው ብዬም አምናለሁ፡፡
ነግር ግን የመንግሥት መካከለኛውና የታችኛው መዋቅር በአብዛኛው ከዚህ ዕሳቤ ያፈነገጠና ሌብነትን እሴቱ ያደረገ፣ ብልፅግና ፓርቲን ተገን አድርገው ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ፀጉራቸው ድረስ በተነከሩ አመራሮችና አባሎች የተሞላ ይመስለኛል፡፡
ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውን ክፉ ብሂል የሕይወት መርህ ባደረጉ፣ ሕግን በማይፈሩና ሰውንም በማያፍሩ ስብሰቦች ሁለት የመንግሥት መዋቅሮች እንደወደቁ ግልጽ ይመስላል፡፡ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ካላልን በስተቀር፡፡
እንደሚታወቀው የአንድ መንግሥት (ገዥ ፓርቲ) ጠንካራ መሠረቱ ያለው ደግሞ፣ በታችኛውና በመካከለኛው መዋቅር ላይ ነው፡፡ የእነዚህ መዋቅር መነካት የአጠቃላዩ የመንግሥት ሥርዓት መነካት ጉዳይ ይሆናል፡፡
ታዲያ የመንግሥት (የብልፅግና) የበላይ አመራሮች በሌብነት ጉዳይ ላይ ከልብ እንዳያለቅሱ እያደረጋቸው ያለው ምክንያት፣ በእኔ መላምት መሠረት ይህ ጉዳይ ነው ባይ ነኝ፡፡
አሁን ሌብነት ላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ መውሰድ ማለት ብልፅግናን ፓርቲን እንደማፍረስ ያህል ይሆናል፡፡ በወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ላይ ይህ እንዲሆን የበላይ የመንግሥት አመራሮች አይፈልጉም፡፡ ሌብነትን ለማጥፋት አገርን ማፍረስ ምርጫ ሊያደርጉ ስለማይችሉ፡፡
ጥያቄው ኅብረተሰቡ እስከ መቼ ድረስ የራሱን ኢኮኖሚ እያከሳ ለሌቦች እየገበረ ይቀጥላል? መንግሥትስ በችግሩ ዙሪያ መዞሩን ትቶ እነዚህን ሌቦችን ከመዋቅሩ ጨክኖ ቆርጦ ይጥላል? የሚለው ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር ብዬ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ‹‹ከኑግ የተገኝ ሰሊጥ…›› እንዳይሆን፣ በታማኝነት ኅብረተሰቡን እያገለገሉ ያሉ በየትኛው የመንግሥት የመዋቅር ዕርከን ውስጥ ያሉትን አገልጋዮች ስላላቸው የሞራል ልዕልና ምሥጋና ይደረሳቸው፡፡
ሐሳቤን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ተነስቼ እንደ ጀመርኩት እሳቸው ባነሱት አንድ ንግግር እቋጫለሁ፡፡
‹‹ሌቦቹን ቤት (ቤቶች) ያሏቸው ነግር ግን አገር የሌላቸው፤›› ብለው ጠቅሰዋቸዋል፡፡ እኔን ደግሞ አገር እያለው ቤት የሌለው የበለጠ ግራ ያጋባኛል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው estifanos.sime@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡