የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በፀጥታ ምክንያት ለአራት ዓመታት ኦዲት አልተደረገም
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በሚያደርገው የኦዲት ሥራ፣ መከላከያን ጨምሮ ሌሎች በአዋጅ ያልተካተቱ ተቋማት ኦዲት እንዲደረጉ የሚረዳ አዋጅ እንዲያዘጋጅ በፓርለማው ተጠየቀ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑና ተግባሩን በአዋጅ የመገደብ በሚመስል መንገድ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት ኦዲት እንደማይደረጉ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ተናግረዋል፡፡
ኦዲት ከማይደረጉ ተቋማት መካከል የአገር መከላከያ ሚኒስቴር መሆኑንና በዚህ ሁኔታ የኦዲት ተቋሙ ነፃ እንዲሆን እንሠራለን ተብሎ እንደሚገለጽ፣ ነገር ግን ቢያንስ ከተጣለበት አገራዊ ኃላፊት አኳያ የሚመጥን የአዋጅ ማሻሻያ እንዲደረግ ራሱ ተቋሙ መነሻ የሚሆን ሕግ ለቋሚ ኮሚቴው አዘጋጅቶ ማቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ዋና ኦዲተር መሥሪ ቤት ነፃና ገለልተኛ እንዴት ሊሆን ይችላል ሲሉ አቶ ክርስቲያን ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፣ የአገር መከላከያ ተቋምን በተመለከተ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመነሳት መልስ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም አንዳንድ አገሮች ለመሰል ተቋማት ለብቻ ኦዲተር ተሰይሞላቸው ወይም በሌላ ዓይነት የኦዲት አሠራር ኦዲት እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያለው አሠራር ከአገር ደኅንነት አንፃር ታስቦ እንደሚከናወን፣ ሕዝባዊ ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅትም የአገር ሚስጥር አሳልፎ ላለመስጠት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የአገርን ሚስጥር ለመጠበቅ ሲባል በአንድ አዋጅ እንዲጠቃለል ከማድረግ ይልቅ፣ የአገር መከላከያን ኦዲት የሚያደርግ የራሱ የሆኑና የተጠናከሩ ኦዲተሮች ወይም ከዋና ኦዲተር መከላከያን ብቻ ኦዲት የሚያደርጉ አካላትን መሰየም እንደሚቻል ወ/ሮ መሠረት አስረድተዋል፡፡
ለአብነት በደቡብ አፍሪካ የአገር መከላከያ ኦዲት የሚደረገው ሁሉ ነገራቸው በተጠና ኦዲተሮች ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ መሆኑን፣ ተቋሙ ኦዲት ከተደረገ በኋላ የኦዲት ሪፖርት ለሚመለከተው አካል እንደሚሰጥ፣ በኢትዮጵያ ያለው አሠራርም የአገር ሚስጥር መጠበቅ ስላለበትና በአዋጅ መገደብ ተገቢ ባለመሆኑ፣ ጉዳዩን አሳልፎ ከመስጠት ሚስጥሩን በመጠበቅ ኦዲት ተደርጎ ማወቅ የሚገባው አካል ማወቅ አለበት ብለዋል፡፡
በመሆኑም ከጅምሩ የኦዲት አዋጁ ሲወጣ ይህ ተቋም እንዲካተት ያልተደረገው ሚስጥር እንዳይባክን በሚል ዕሳቤ በመሆኑ፣ ወደፊት ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን የፌዴራል መንግሥት የበጀተውን በጀት የመቆጣጠር ሥልጣን ለምክር ቤቱ መስጠቱን፣ ይህንን በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በዋና ኦዲተር በኩል የሚያረጋግጥ ቢሆንም፣ ለክልሎች የሚሰጥ የድጎማ በጀት በዋና ኦዲተር ኦዲት እየተደረገ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተነሳ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የሥልጣን እርከን ላይ ግልጽነት የጎደላቸውና ለአሠራር የማያመቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው፣ በዘላቂነት መሰል የድጎማ በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉ የሚረጋገጥበት አሠራር እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የመንግሥት ፕሮጀክትና የልማት ድርጅቶችን በተለየ ሁኔታ ትኩረት በማድረግ ኦዲት እንዲደረጉ አቶ ክርስቲያን አሳስበዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት በበኩላቸው፣ ቋሚ ኮሚቴው ኦዲት ይደረጉ የሚላቸውን ፕሮጀክቶች፣ ‹‹አደራጅቶ ከሰጠን እናደርጋለን፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ኦዲት ልናደርግ ገብተን ተጠያቂ የሚደረግ አካል አናገኝም፤›› ብለዋል፡፡
የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በፀጥታ ምክንያት ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲን ለአራት ዓመታት ኦዲት ማድረግ አለመቻሉን የገለጹት ወ/ሮ መሠረት፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ የወሎና የመቅደላ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ዓ.ም. ኦዲት እንዳልተደረጉ አስታውቀዋል፡፡