በአማራ ክልል የሚገኙ ወረዳዎች በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ መሬቶች በክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሳያፀድቁ ለባለሀብቶች እንዳያስተላልፉ ዕገዳ ተጣለባቸው፡፡
ወረዳዎቹ ይህ ዕገዳ የተጣለባቸው በከተሞች ዙሪያ በሚሰጡት መሬት ላይ ‹‹ሕገወጥነት›› እና ‹‹መሬትን ሸንሽኖ የመያዝ›› አዝማሚያ በመታየቱ መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ አብዱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሰኞ ኅዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ለክልሉ ሁሉም የዞንና ሪጅኦ ፖሊታን አስተዳደሮች በጻፉት ደብዳቤ ትዕዛዙን ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ በከተማዎች ዙሪያ የሚገኙ ወረዳዎች ከተሞቻቸውን ከማልማት ይልቅ ለትላልቅ ከተሞች የቀረቡ መሬቶችን ‹‹ከፕላን ውጪ ተሽቀዳድሞ ወረራ›› በሚመስል መልኩ እየመሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የወረዳዎቹ የመሬት አሰጣጥ ‹‹ያለ ፕላንና ዘርፍን ባለየ መንገድ›› እየተካሄደ መሆኑን በደብዳቤው ላይ የጠቀሱት ይልቃል (ዶ/ር)፣ ‹‹በከተማ ዙሪያ ያለ መሬት [ላይ] የሕገወጥ ወረራ ማካሄድ ይስተዋላል፤›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡ አክለውም፣ ከተማና በከተማ ዙሪያ የሚገኙ መሬቶች በሥጦታ እየተላለፉ ‹‹ሕግ ለማይፈቅድላቸው›› አካላት ጭምር የመሬት ባለቤትነት ደብተር ‹‹እየታደለ›› መሆኑን በመጥቀስ የወረዳ አመራሮች ወቅሰዋል፡፡
የርዕሰ መስተዳደሩ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው የወረዳዎች የመሬት አሰጣጥ ‹‹የከተሞችን የወደፊት ዕድገት በሚገታና በሚያበላሽ›› መልኩ እየተካሄደ ሲሆን ከተማ ዙሪያ መሬት የሚወስዱ ባለሀብቶች የሚሰማሩባቸው ዘርፎች የገጠር መሬት መዋቅሮችን ‹‹የማይመለከት›› ነው፡፡ ‹‹ከከተማ ጋር የተያያዙ የአገልግሎት ዘርፎች እንደ ሆቴል ሎጅ፣ ሪል ስቴት ወዘተ ሳይቀር ከከተማው የዕድገት ፕላን ጋር ሳይገናዘብ የሚመለከተው የከተማ አመራር ሳይፈቅድ፤›› እየተሰጠ መሆኑን ይልቃል (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አቶ እንድሪስ፣ ‹‹ከተሞች ላይ መስተናገድ እየተቻለ ከከተማ ውጭ ባለ መሬት ላይ ባለሀብቱ ሪልስቴት፣ ሆቴልና ሎጅ ለመገንባት ይጠይቃል፤›› ሲሉ በርዕሰ መስተዳድሩ የተነሳውን ወቀሳ ተጋርተዋል፡፡ በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ መሬቶች ላይ የሚታየው የመሬት አሰጣጥ እንደ ባህር ዳር ያሉ ትላልቅ ከተሞች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያያዙትን የአሥር ዓመታት ትግበራ ‹‹ጥያቄ ውስጥ የከተተ›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ለምሳሌ ባህር ዳር ከተማ እያለ ከከተማ ውጪ ባለ ወረዳ ላይ የባህር ዳርን ዕድገት በሚገታ መልኩ [የወረዳ አመራሮች] ፕሮጀክቶችን ይመራሉ፡፡ ባህር ዳር ዙሪያ የሚመሩ ፕሮጀክቶች ከከተማው ጋር በሚናበብ መልኩ እንጂ ባህር ዳር ባለችበት እንድትቆም በሚያደርግ መልኩ መሆን የለባቸውም፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የመሬት አሰጣጡ ‹‹የተዘበራረቀ›› በመሆኑ የባለሀብቶቹን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና በሚፈለገው መልኩ መሠረተ ልማት ለማቅረብ ‹‹አስቸጋሪ›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ባለሀብቶችም የከተማውን ዙሪያ ይዘው መሬቱን ለታለመለት ዓለማ እንደማያውሉ ልምድ ዓይተናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ባለፈው ዓመት መጋቢት 2014 ዓ.ም. ባደረገው ዳሰሳ 937 ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የወሰዱትን መሬት ወደ ሥራ ሳያስገቡ አጥረው ማስቀመጣቸውን ገልጾ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ መሬቶች በዚሁ ሁኔታ ከአሥር እስከ 15 ዓመታት እንደቆዩም ተነግሮ ነበር፡፡
በዚያው ወር ስለጉዳዩ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት አድርገው የነበሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል (ዶ/ር)፣ ባሀብቶቹ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የማይገቡ ከሆነ መሬቱ እንዲነጠቅ በዞን፣ በወረዳና በከተማ ደረጃ ያሉ የኢንቨስትመንት ቢሮዎች ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር፡፡
በዚሁም መሠረት በተሰጠው የሁለት ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራ ያልጀመሩ 169 ፕሮጀክቶች መሬት እንደተነጠቁ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ላይ ተገልጾ ነበር፡፡
የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አቶ እድሪስ እንደሚያስረዱት ወረዳዎቹ ላይ ዕገዳ የተጣለው ቢሮው እያዋቀረው ያለው ኮሚቴ በየወረዳው ምን ዓይነት ኢንቨስትመንቶች መሬት ሊያገኙ እንደሚገባ ጥናት እስከሚያደርግ ድረስ ነው፡፡ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናቱን እናጠናቅቃለን›› ያሉት ኃላፊው ከጥናቱ በኋላ ወረዳዎቹ በሚለይላቸው ዘርፍ የኢንቨስትመንት መሬቶችን መምራት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡