Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኦነግ ሸኔ ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ማገቱና ማቃጠሉ ተነገ

ኦነግ ሸኔ ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ማገቱና ማቃጠሉ ተነገ

ቀን:

  • ከሳዑዲ ዓረቢያ ከተመለሱ 72 ሺሕ ዜጎች ሦስት ሺሕ በካምፕ ይገኛሉ ተብሏል

ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞንና በቤንሻንጉል ክልል ከማሺ ዞን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለማድረስ የተላኩ ተሽከርካሪዎች ለሦስት ወራት ማገቱን፣ መዝረፉንና የተወሰኑትን ማቃጠሉን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ይህ የተነገረው የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የ2015 ዓ.ም. ዕቅድና የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኅዳር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያቀርቡ ነው፡፡

ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለ ማርያም (አምባሳደር) በሪፖርታቸው፣ በኦነግ ሸኔ ሳቢያ እየደረሰ ባለው የፀጥታ ችግር የዕርዳታ አቅርቦት ለሚፈልጉ አካላት በወቅቱ ለማድረስ በከፍተኛ ሁኔታ መሰናክል መፍጠሩን የዕርዳታ እህል ለሚፈልጉ ተረጂዎች በወቅቱ ማድረስ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር አይዳሩስ ሐሰን በበኩላቸው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን የተላኩ አሥር የጭነት ተሽከርካሪዎች ለሦስት ወራት ቆመው እንደሚገኙ፣ እንዲሁም ወደ ኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የዕርዳታ እህል ይዘው የተላኩ ተሽከርካሪዎች ደግሞ በእሳት መቃጠላቸውንና መዘረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህም የተቃጠሉት ተሽከርካሪዎች ባለቤት ክስ መሥርቶ ክርክር ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 21.2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ፣ ከእነዚህ ውስጥ 16 ሚሊዮን በድርቅ የተጎዱ፣ እንዲሁም 4.6 ሚሊዮን የተፈናቀሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ መንግሥት ለ9.4 ሚሊዮን ዜጎች ዕርዳታ እያቀረበ መሆኑን፣ ለ11 ሚሊዮን ወገኖች ደግሞ በለጋሽ ድርጅቶች እንደሚሸፈን ዋና ኮሚሽነር ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

በመጪዎቹ ሁለት ወራት በመንግሥት በኩል ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 8.8 ሚሊዮን ዜጎች መንግሥት ስድስት ቢሊዮን ብር ያለው ቢሆንም፣ ሙሉ ለሙል ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ 13 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው አክለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ወኪሎች በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ካደረጉ በኋላ፣ 263 ከባድ የጭነት መኪኖች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ዕርዳታ ጭነው መጓዛቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ድጋፍ ከሚያደርግላቸው ዜጎች መካከል ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሽ ዜጎች የሚገኙበት መሆኑን፣ ይመለሳሉ ተብለው ከሚጠበቁት 102 ሺሕ ሰዎች መካከል 71 ሺሕ የሚሆኑት ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን የገለጹት ሽፈራው (አምባሳደር)፣ ከሰኞ ኅዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ 31 ሺሕ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የማስመለስ ሥራ እንደሚከናወን  ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመልሰው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄድ የነበረባቸው ከ3,000 በላይ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች መሄድ ባለመቻላቸው፣ አሁንም በመጠለያ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የድጋፍ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚቀርቡ የዕርዳታ ጥያቄዎች መጨመርና ዕርዳታ መሰጠት ለማይገባው አካል ዕርዳታ መቅረቡ የድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር እንዳበራከተው ተናግረዋል፡፡

ከመንግሥት የሚመደበው ሀብት ከዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር ጋር የማይጣጣም በመሆኑና ከውጭ የሚመጣውን ዕርዳታ ጠባቂ ላለመሆን፣ በተለየ ሁኔታ ከሕዝብ ሀብት የሚሰባሰብበት አሠራር ለመፍጠር ኮሚሽኑ አንድ አጥኝ ቡድን አዋቅሮ ሀብት ማሰባሰብ ስለሚቻልበት ሁኔታ ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ለቀጣይ ሥራዎች ይረዳኛል ያላቸው ስትራቴጂዎች የተካተቱበት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዳቀረበ፣  በቶሎ ፀድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ፓርላማው ዕገዛ እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ ዕርዳታ ከማመላለስ ወጥቶ፣ ዕርዳታ ፈላጊ ዜጎች ስለሚቋቋሙበት መንገድ የተሻለ ስትራቴጂ እንዲቀይስ አሳስበዋል፡፡

በመሆኑም ዕርዳታ ማድረስ ጊዜያዊ ሥራ እንጂ ቋሚ ተግባሩ ሊሆን እንደማይገባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ የውጭ የዕርዳታ ድርጅቶች የምዕራባውያን የፖለቲካ ማስፈጸሚያ በመሆናቸው፣ በተቻለ መጠን የእነዚህን ተፅዕኖ ለመቀነስ ጥገኝነትን መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...