Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች ለውድድር ብቁ ለመሆን ዝግ ያደረጉትን የአክሲዮን ሽያጭ እንደገና እንዲጀምሩ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ነባር ባንኮች በፋይናንስ ዘርፉ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቆየት፣ ዝግ ያደረጉትን የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ እንደገና በመጀመር ራሳቸውን በካፒታል የሚያጠናከሩበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ‹‹ባንኮቻችን ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር እንዴት መወዳደር ይችላሉ? በተለይም በማንነት ተኮር ላይ የተመሠረቱ ባንኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን የሚስችላቸው ራዕይ አላቸው ወይ?›› በሚል ርዕስ ላይ፣ በኢትዮ በጅሮንድ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን በስካይላይት ሆቴል የምክክር መድረክ በተዘጋጅበት ወቅት ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ያቀረቡት የዋይኤችኤም ኮንሰልቲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ ባንኮች ከዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ባንኮች ጋር ሲነፃፀሩ ያላቸው ካፒታል ዝቅተኛ የሚባል ሲሆን፣ ለዚህም የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ መዳከም አንዱ ሰበብ ሆኖ የሚነሳ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ወቅት 30 ባንኮች እንዲፈጠሩ ካስገደዱ ምክንያቶች ውስጥ ነባር ባንኮች አክሲዮን መሸጥ ባለመፈለጋቸው መሆኑን በማስታወስ፣ ባንኮችን መጀመሪያ ያቋቋሙ ሰዎች ድርሻቸውን ይዘው መቀመጣቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 16 የነበረውን የባንክ ቁጥር እንዲሻቅብና አዳዲስ ባንኮች እንዲቋቋሙ ማድረጉን አቶ ያሬድ አስረድተዋል፡፡

የአክሲዮን ሽያጭ ዝግ አድርገው የቆዩ ባንኮች ፈጥነው ከፍተው ራሳቸውን በካፒታል ማጠናከር እንደሚገባቸው በውይይት መድረኩ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ መሆኑም በአገሪቱ ለዋጋ ግሽበት መንስዔ የሆነውን ብር ከመቆጣጠር በተጨማሪ፣ በቅርቡ ለሚከፈተው የፋይናንስ ዘርፍን ከፍት የማድረግ ምኅዳር የአገር ውስጥ ባንኮች ተፎካካሪ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያግዝ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ 30 ባንክ ሳይሆን አንድ ነው ያለው፣ እሱም ብሔራዊ ባንክ፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ ሌሎች እንደ ቅርንጫፍ የሚቆጠሩ እንጂ፣ ‹‹አንዱ ከሌላው ጋር የሚወዳደርበት መድረክ አልተከፈተለትም፤›› የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ባንኮቻችን ነው ዶላር የሚገዙበት፣ የሚሸጡበት፣ ኤልሲ የሚከፍቱበትና ብድራቸው ተመሳሳይ ነው፡፡›› በቀጣይ የሚመሠረቱ ባንኮች ዝግ በሆነ ገበያ ነው የሚመሩት ከተባለ የሚሠሩበት መንገድ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

ሌላው በመድረኩ ላይ ገለጻ ያደረጉት የቢዝነስ አማካሪው አቶ ከፈለኝ ኃይሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች ማንነት ላይ ተመሥርተው ተቋቁመዋል የሚባለው በየትኞቹ መሥፈርቶች እንደሆነ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ አንድ ባንክ በብሔር ነው የተደራጀው ተብሎ ሲገለጽ መገለጫ ከሆኑት አንዱ፣ መሥራቾቹ ወይም አደራጆቹ ሃምሳና ከሃምሳ ከመቶ በላይ ከአንድ ብሔር ሲሆኑ፣ በማኔጅንመንት ደረጃም በተመሳሳይ፣ በባለቤትነት ደረጃ (ሼር) አብዛኞቹ ከአንድ ብሔር የወጡ ናቸው የሚለው ሲመሳከር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማንነትን መሠረት አድርጎ ባንኮችን ማቋቋም ጥቅምም ሆነ ጉዳት ያለው መሆኑ በጥናቱ የቀረበ ሲሆን፣ በተለይም ከፋይናንስ ሥርዓት መገለል ደርሶበታል ተብለ የሚታሰብን ኅብረተሰብ ለማገልገል ከተቋቋመ፣ ይህ አሠራር የፋይናንስ አካታችነት የሚጨምርና ማኅበራዊ ፍትሕ በማምጣት ረገድም የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ደንበኞች በሚናገሩበት ቋንቋና ባህል ለመስተናገድ የተሻለ ዕድል መፍጠሩ ሌላው በጎ ጎኑ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ባንኮች ብሔርን መሠረት አድርገው መቋቋማቸው በሌላኛው ጎን የተገለለ ማኅበረሰብ እንዲኖር፣ ተገልጋዮች እኩል ብድር የማግኘት ዕድል እንዳይኖራቸው ከማድረጉ ውጭ ለሙስና ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አሉታዊ ጎኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ማንነትን መሠረት ያደረገ ባንክ ማቋቋም፣ በአገር ውስጥ፣ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስቸግራል ብለው፣ ባንኮች ብሔርን መሠረት አድርገው ከመመሥረት ይልቅ የበለጠ ትርፋማና ተገቢውን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት፣ የባንክ አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ መሆኑን ማወቅ ሲገባቸው ነው ብለዋል፡፡ ‹‹በሐሳብም ደረጃ ከአገራችን ድንበር ጥሰን መውጣት አልቻልንም፤›› ያሉት አቶ ከፈለኝ፣ አፍሪካ ውስጥ በተመሠረተው ነፃ ገበያ ተዘዋውሮ ለመሥራት በሐሳብ ደረጃ ድንበር አለመሻገር የሚያዋጣ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፋይናንስ በባህሪው ድንበር ተሻጋሪ ስለሆነ ባንኮች ሲመሠረቱ ይህንን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባቸው በመድረኩ ምክረ ሐሳብ ሆኖ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች