ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በተለያዩ ዞንና ወረዳዎች ላይ በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ተደራሽ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ድርጅቱም በመጠነኛ ውሃና ሳኒቴሽን በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ ሲሆን፣ በቅርቡም ደግሞ በሰሜን ሸዋና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውሃ፣የንፅህና አገልግሎት ተቋማት ግንባታና የንፅህና አጠባበቅ አገልግሎት እንዲያገኙ 70 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ተደራሽ ለማድረግ ችሏል፡፡
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከዩኒሴፍ በኩል ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራቶች ውስጥ 16 የሚሆኑ የውኃ መስመር ዝርጋታዎችን ማስፋፋት፣ በመጠለያ ጣቢያዎችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ወደ 14 የመፀዳጃ ቤት ግንባታ ማከናውን ተጠቃሽ ሲሆን፣ ደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኝ የመጠለያ ማዕከል ላይ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች ከ10 በላይ የሚሆኑ የሻወር ቤት ብሎኮችን ገንብቶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በጦርነቱ ምክንያትም ለተጎዱ ወገኖች ተደራሽ እንዲሆኑ የተዘረጉ የውኃ መስመር ዝርጋታዎች ላይ ብልሽት እንዳይከሰት ተጠቃሚ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው ስምንት ወረዳዎች ላይ ለሚገኙ የውኃ ተቋማቶች ላይ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ከክልሉ የውኃ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
የንፁህ ውኃ መጠጥ ዝርጋታ በተከናወነባቸው ወረዳዎች ላይ ለሚገኙ ተቋማት፣ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የውኃ ጥራት መለኪያ መሣሪያ በመግዛት ተደራሽ ሊያደርግ ችሏል፡፡
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በተለይም በማኅበረሰቡ ቸልተኝነት የተነሳ ከመጠጥና ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከልና በቀላሉ ለማስቆም የአይጂን ሳይንቴሽን ፕሮሞሽን ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ደብረ ብርሃን አካባቢ በሚገኝ የመጠለያ ካምፕ ውስጥ ተፋፍገው ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይኼው አገልግሎት ተደራሽ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተላላፊ በሽታዎች መታደግ ችሏል፡፡
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በአጣዬ ከተማ ሦስት ቀበሌዎችን የሚሸፍንና 55 ሺሕ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 12 ኪሎ ሜትር የውኃ የመስመር ዝርጋታ አከናውኗል፡፡
ፕሮጅክቱም ተግባራዊ በተደረገባቸው ስምንት ወረዳዎች ከ167 ሺሕ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በመዘዋወር የተለያዩ ፕሮጀክቶች ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ በቀጣይ ተጨማሪ 35 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ በስምንት ወረዳዎች ላይ የፍሲሊቱ አገልግሎቶች ዕውን ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የሚገኙ በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ንብረታቸውን ላጡ ወገኖች የተለያዩ አገልግሎቶችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከአጣዬ ከተማ ካራቆሬና አርሶ አምባ የገጠር ቀበሌዎች በነዳጅና በኤሌክትሪክ እጥረት ሳቢያ አገልግሎት ተቋርጦ የነበሩ አራት ውኃ ተቋማትን መልሶ ሥራ እንዲጀምሩ ያደረገ ሲሆን፣ በቀጣይም አቅም ግንባታ ሥራዎችን ለተለያዩ ክልሎች ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፕላን ኢንተርናሽናል ከጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበሩ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ፣ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ሰፊ ሥራ ይሠራል፡፡
ድርቅ የተከሰተባቸው ቦረና፣ ጉጂና ደቡብ አሞ ዞኖች እየሠራ ይገኛል፡፡