- ለጋዜጠኞቹ መንግሥትን እንዲተቹ መረጃ የሚሰጧቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡
- እነሱ አይደሉም፡፡
- እና የትኞቹ ናቸው?
- እዚሁ ከተማችን የሚገኙ ምዕራባውያን ናቸው።
- እንዴት ነው መረጃውን የሚያቀብሏቸው?
- እራት እያበሉ ነው።
- ምን?
- አዎ፣ እራት ግብዣ ይጠሯቸውና መተቸት ያለባቸውን ጉዳይ ያስጨብጧቸዋል።
- ምን ዓይነት እራት ቢሆን ነው መንግሥትን ለመተቸት ያስደፈራቸው?
- እሱን ማወቅ አልቻልንም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምክንያቱ ይህ ጋዜጠኞቹን ለምን አታቀርቧቸውም?
- የተወሰኑትን አብልተናል።
- እራት?
- አይደለም።
- ምሣ ነው?
- አይደለም።
- እና ምንድነው?
- አሳራቸውን፡፡
- እንዴት እንደዛ ታደርጋላችሁ?
- መፍትሔ ያመጣል ብለን አስበን ነው ክቡር ሚኒስትር።
- ጋዜጠኞችን ማሰር መፍትሔ አይደለም ብየ ስንት ጊዜ ነው የተናገርኩት? ትክክል አልሠራችሁም፡፡
- ስህተት እንደሠራን ዘግይቶ ነው የገባን ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት?
- ጋዜጠኞቹ ቢታሰሩም ኤምባሲዎቹ ግን እራት መጋበዛቸውን አጠናክረው ነው የቀጠሉበት።
- ሌሎች ጋዜጠኞችን መጋበዝ ነው?
- አይደለም።
- እና ለማን ነው የእራት ግብዣው?
- ጋዜጠኞችን ስናስር የሚጋብዙት ዳኞችን ነው።
- ዳኞችን?
- አዎ።
- ዳኞችን መጋበዝ ለምን አስፈለጋቸው?
- ጋዜጠኞቹን በዋስ እንዲፈቱ፡፡
- ዳኞቹ?
- አዎ፡፡
- በእራት ግብዣ ሊያዳክሙን እየጣሩ ነው?
- በእራት ግብዣ የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ አይወድቅም ብለን እኛም ዕርምጃ ወስደናል፡፡
- የምን ዕርምጃ ማን ላይ?
- ጋዜጠኞቹን እንዳበላናቸው ዳኞቹንም…
- እንዳትጨርሰው እንዳትጨርሰው፡፡
- ለመቀጣጫ ብለን የተወሰኑትን አብልተናቸዋል።
- ዳኞቹን?
- አዎ። ግን እሱም ውግዘት አስከተለብን እንጂ አልሠራም።
- ማሰር መፍትሔ አይደለም ብዬ የምለፈልፈው ለዚህ እኮ ነው። እናንተ ግን አትሰሙም።
- ምን እናድርግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር? ዝም እንበል?
- መፍትሔው እሱ አይደለም፡፡
- ምንድነው ታዲያ?
- እራት የሚያበሉትን መከታተልና መሰለል ነው መፍትሔው።
- እነሱን መከታተል አስቸጋሪ ነው ክቡር ሚኒስትር። የሕግ ከለላ ስላላቸው ልናስራቸውም እንችልም!
- ማሰር መፍትሔ አይደለም እያልኩህ አስሬ ማሰር ማሰር አትበልብኝ፡፡
- እንዴት መከታተል እንችላለን ታዲያ?
- እሱን ሲደርስ ታያለህ፡፡
- ምን አስበው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እያንዳንዷን እንቅስቃሴያቸውን ከላይ ሆነን እንከታተላለን።
- እንዴት ብለን… ሳተላይት ሳይኖረን?
- እየገነባን ነው፡፡
- ሳተላይት?
- አዎ፡፡
- የት?
- እንጦጦ ላይ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሥራ ደክመው ውለው አመሻሹን ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን የፓርላማ ውሎ ተመስጠው ሲመለከቱ አገኟቸውና በድጋሚ አብረው መከታተል ጀመሩ]
- እንዴ? ምን ለማለት ፈልገው ነው?
- ምን አሉ?
- ስለ ብርጭቆ የሚሉትን አልሰማህም?
- ሰምቻለሁ።
- ታዲያ እንደዛ ማለት ነበረባቸው?
- እንዴት? ትክክል አይደለም የተናገሩት?
- ተመረመሩ የሚል ዜና ሰሞኑን ተነግሮ አልነበር እንዴ?
- ስለምንድን እያወራሽ ያለሽው አልገባኝም? ምን ያሉ መስሎሽ ነው?
- በእጃቸው ስለያዙት ብርጭቆ የተናገሩትን አትሰማም እንዴ አንተ ደግሞ?
- ይችን ብርጭቆ እዚያ ጋ ሆኖ ማየትና እዚህ ጋር ሆኖ ማየት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው ያሉትን አይደል የምትይው?
- አዎ፡፡
- ታዲያ ምንድነው ችግሩ?
- ከርቀት ቢያዩትም ብርጭቆ መሆኑን የሚስቱ አይመስለኝም ምክንያቱም…
- እ… ምክንያቱ?
- በቅርቡ ተመርምረዋል።
- ማን ነው የተመረመረው?
- አባላቱ፡፡
- ምናቸውን?
- ዓይናቸውን!