Saturday, December 2, 2023

የሰላም ስምምነቱና የተጋረጡ እንቅፋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተግባር እንዲተረጎም ያስችላል የተባለለት የናይሮቢው ስምምነት፣ ከአምስት ቀናት ንግግር በኋላ ተፈርሟል፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመ በማግሥቱ፣ የሁለቱ ወገኖች የጦር መሪዎች ግንኙነት እንዲመሠርቱ ይጠበቅ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከአምስት ቀናት በኋላ ደግሞ የመንግሥትና የሕወሓት የጦር መሪዎች በአካል ተገናኝተው፣ የትጥቅ መፍታት ጉዳዮችን እንደሚነጋገሩና ዝርዝር ሒደቶችን እንደሚያስቀምጡ ይጠበቅ ነበር፡፡ በናይሮቢ ለአምስት ቀናት የተደረገው ንግግርና የተፈረመው ስምምነትም ለዚህ  ተብሎ የተካሄደ ነበር፡፡

የመንግሥትና የሕወሓት የጦር መሪዎች በናይሮቢ የፈረሙት ስድስት አንቀጾች ያሉት የአምስት ገጽ የስምምነት ሰነድ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡  ግጭት በዘላቂነት ከሚወገድበት ሁኔታ ጀምሮ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ስለሚፈቱበት ሁኔታ፣ ለሲቪሎች ስለሚደረግ ጥበቃ፣ ስለሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት፣ እንዲሁም ኃላፊነት ስለተሞላው የሚዲያ አጠቃቀም ዝርዝር ነጥቦች ሰፍረዋል፡፡ የስምምነቱን አተገባበር ስለሚቆጣጠሩ አካላትም ከስምምነት መደረሱ ይፋ ተደርጓል፡፡

ይህ የሁለቱ የጦር መሪዎች ስምምነትም የፕሪቶሪያውን ስምምነት የተከተለ ዝርዝር አፈጻጸም መሆኑ ተነግሯል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የስምምነት ሰነድ የያዛቸውን ጥቅል የስምምነት አንቀጾች ወደ ሥራ ለማውረድ የሚያስችል መሆኑ ሲነገር ነው የከረመው፡፡

የናይሮቢ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግን፣ ስምምነቱንም ሆነ የሰላም ሒደቱን ወደኋላ የሚመልሱ ይመስላሉ እየተባለ ነው፡፡

የሰላም ስምምነቱ ከሕወሓት ጋር እንጂ ከትግራይ መንግሥት ጋር አይደለም የሚለው ሙግት ደግሞ፣ ከወዲሁ ውዝግብ እያስነሱ ካሉ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል፡፡

በተለይ የናይሮቢው ስምምነት በተፈረመ ማግሥት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሰጠው የተባለው መግለጫ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በዜሮ የሚያባዛ ነው የሚል ግምት እያሰጠ ነው፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 9 እና 10 መሠረት የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያለው ሥልጣን እንዲመለስ ተደንግጓል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በማይቀበለው ምርጫ ሕወሓት መሠረትኩት ያለው ክልላዊ መንግሥት ፈርሶ በትግራይ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ፣ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም በእነዚህ አንቀጾች ከእነ ዝርዝር ሒደቱ ተደንግጓል፡፡

ሕወሓትን ለሁለት ዓመታት ከመንግሥት ጋር ወደ ውጊያ የከተተው ዋና ጉዳይ ይኸው ያለ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ በትግራይ ክልል የተደረገው ምርጫ ጉዳይ ሲሆን፣ ምርጫው በተካሄደበት ወቅትም የፌዴራል መንግሥቱ ሒደቱን በማውገዝ ውጤቱንም እንደማይቀበለው አስታውቆ ነበር፡፡

በሰላም ንግግሩ ሒደትም ይኸው ጉዳይ ተነስቶ በፕሪቶሪያው ስምምነት ችግሩ የሚፈታበት ሒደት በአንቀጽ 9 እና 10 ላይ በግልጽ መቀመጡ ተመላክቷል፡፡   ስምምነቱ በተደረገ ማግሥት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን  (አምባሳደር) በአዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ኮሙዩኒቲ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ ስለዚሁ ሒደት በዝርዝር አብራርተው ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን በትግራይ ክልል ከተመለሰ በኋላ በሚመሠረተው ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር ውስጥ ሕወሓት ቦታ እንደሚኖረው የጠቀሱት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሁሉንም አካታች ሆኖ ይመሠረታል ብለው ነበር፡፡ ሕወሓት ትጥቁን ፈቶ እንደ ማንኛውም ፓርቲ ይንቀሳቀሳል ያሉት አምባሳደሩ፣ ምርጫ ሲካሄድም በሰላማዊ መንገድ መፎካከር እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡

ይህ ሁሉ ማብራረያ አልፎ የናይሮቢው የሰላም ንግግር ተደርጎ ሌላ ዙር ስምምነት ተፈረመ፡፡ ከዚህ ስምምነት በኋላ ግን የትግራይ ክልል መንግሥት አወጣው በተባለ መግለጫ፣ ‹‹ስምምነቱ ሕወሓትን እንጂ የትግራይ ክልል መንግሥትን አይወክልም፤›› የሚል አቋም ሲንፀባረቅ ነው የታየው፡፡ ይህ ደግሞ የሰላም ስምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን፣ ገና ያልጠናውን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰላምና ፀጥታ መልሶ እንዳያደፈርሰው እየተሠጋ ነው፡፡

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በስምምነት ማግሥት ቀውስ መፈጠሩ የተለመደ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የባድመ ጦርነት ካከተመ በኋላ ሕወሓት ተፍረከረከ፡፡ እሱን ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ምስቅልቅል ተፈጥሯል፤›› ሲሉ መለስ ብለው የታሪክ አጋጣሚን ያስታወሱት አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከአሁኑ ድርድርና ስምምነት በኋላም ተመሳሳይ የፖለቲካ ክፍፍልና ቀውስ ሊኖር ይችላል በማለት ቀደም ብለው ለሪፖርተር ግምታቸውን ተናግረው ነበር፡፡

አሁን ስምምነቱን የፈረመው ሕወሓት ለስምምነቱ መተግበር ያለው ቁርጠኝነት ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በትግራይ መንግሥት ስም የወጣው መግለጫ የፈጠረው ሥጋት ብቻ ሳይሆን፣ ከአንዳንድ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን የሚንፀባረቀውም ቢሆን ስምምነቱ ፈርሷል እንዲባል የሚጋብዝ ነበር፡፡

ወደ ፕሪቶሪያም ሆነ ወደ ናይሮቢ በመሄድ ስምምነቱን የተፈራረመው የሕወሓት ተደራዳሪ ቡድን መሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ከስምምነቶቹ በኋላ ግን ሕወሓት እንጂ የትግራይ መንግሥት አይደለም የሚሉ ክርክሮች ጎልተው እየተነሱ ነው፡፡

መንግሥት ከድርድሩ ቀደም ብሎ በወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ በኩል፣ ‹‹የትግራይ መንግሥት፣ የትግራይ የውጭ ግንኙነት›› የሚሉ አገላለጾች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደሚፃረሩ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ሕወሓትን በዋና ተደራዳሪነት ወክለው የፕሪቶሪያውን ስምምነት የፈረሙት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን ሰሞኑን በቢቢሲ በወጣ ቃለ መጠይቃቸው፣ ስምምነቱን የትግራይ መንግሥት እንጂ ሕወሓት አይደለም የተፈራረመው በማለት ተከራክረዋል፡፡

የናይሮቢው ስምምነት በተፈረመ ማግሥት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹በትግራይ ያለውን ጦርነት በሰላማዊ መንግሥት ለመፍታት ያደረግነውን ረዥም ሒደት ጨርሰናል፡፡ ከፊታችን ያለውና ሒደቱን አያያዛችን ግን እስካሁን ከተጓዝንበት የበለጠ ፋይዳ ይኖረዋል፤›› ብለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ጌታቸውና አጋሮቻቸው መቀሌ ከረገጡ በኋላ ሐሳብ ካልቀየሩ በስተቀር፣ ስምምነቱን  የፈረመው የትግራይ መንግሥት እንጂ ሕወሓት አይደለም ብለው እንዴት ይከራከራሉ? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡

የናይሮቢውን ስምምነት ተፈራርመው አዲስ አበባ ሲገቡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ‹‹እኛ ከመጀመርያውኑ የሰላም ፍላጎት ይዘን ቆይተናል፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹አሁንም ቢሆን ሰላም እንፈልጋለን፡፡ የተፈራረምነውን ስምምነት ለመፈጸምም ዝግጁ ነን፡፡ ሰላም የማይፈልግን ኃይል ግን እንታገለዋለን፤›› ሲሉ ፊልድ ማርሻሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በመንግሥት ወገን ለስምምነት ተገዥነት የማሳየት ስሜት ተደጋግሞ እየተንፀባረቀ ነው፡፡  

በትግራይ ክልል በመንግሥት ስም መግለጫ መውጣቱን ተከትሎ ጠንከር ያለ ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ሁሉም ወገን ለስምምነቱ ተገዥ እንዲሆን ጠይቀው ነበር፡፡

‹‹መንፈራገጥ ይቻላል፡፡ እየተደረገ እንዳለው የተዛቡ መረጃዎችን ማሠራጨት እንዲሁ ይቻላል፡፡ ይህን ተቀብለናል፣ ይህን አልተቀበልንም፣ እነዚህ አንቀጾች እንዲቀየሩ እንታገላለን ሊባልም ይችል ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁሉ መሬት ላይ ያለውን እውነታና ስምምነቶቹን መቀየር አይችሉም፡፡ ያለው ብቸኛ አማራጭ የስምምነቱን መርሆዎች ማክበርና መራርም ቢሆን እውነታውን ተቀብሎ መተግበር ነው፡፡ ይህ ለዘላቂ ሰላም ሲባል የሚከፈል ዋጋ ነው፣ በሌላ በኩል ጀግንነትም ነው፤›› በማለት ሚኒስትሩ ለገሰ (ዶ/ር) በፌስቡክ ገጻቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የሕወሓት ተደራዳሪዎችና አንዳንድ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነቱ የተደረገው አንድ ጊዜ ከትግራይ መንግሥት ጋር ነው ይላሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ከሕወሓት እንጂ ከትግራይ ጋር አይደለም ይላሉ፡፡ ለውዝግብ መነሻ የሆኑ ጉዳዮች እየተነገሩ ባሉበት በዚህ ወቅት ደግሞ ጉዳዩ ከፕሪቶሪያ በፊት ወደነበረው ሁኔታ ተመልሶ ግጭቱ ዳግም እንዳያገረሽ ብዙዎች እየሠጉ ነው፡፡

በዚህ መሀል ትናንት ማክሰኞ በፓርላማ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ይኸው ሥጋት ተነስቶላቸው የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡

የማያልቅ ጦርነት ‹‹የወንፊት ውኃ›› መሆኑንና ‹‹የሰላም መጥፎ›› እንደሌለ የጠቀሱት ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ ህልውና ሲል የሰላም ስምምነቱን መፈረሙንና ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹በመተማመን ዕጦትና የተገባን ቃል ባለመፈጸም በዓለማችን 154 ድርድሮች ፈርሰዋል፤›› ሲሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያውያን የሰላም ስምምነትም እንዳይፈርስ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲቀጥሉም፣ ‹‹ሕወሓት ነው የተደራደረው እኛ አይደለንም ብለው የተቃወሙ አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት አንድ አይደሉም ስንል አንድ ነን የሚል ተቃውሞ ገጥሞን ነበር፡፡ አሁን የተደራደረው ሕወሓት እንጂ የትግራይ መንግሥት አይደለም መባሉ ጥሩ ነው፡፡ አንድ ሕዝብ ሁሌም በአንድ የፖለቲካ ኃይል እንደማይወከል በስተመጨረሻ አረጋግጠናል፤›› ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡

የሰላም ስምምነቱን እየገጠመው ስላለው ተቃውሞና እንቅፋት ሲያወሱም፣ ስምምነቱን የማይደግፉ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎችም በጦርነት የሚያተርፉትና ውስጣዊ ሰላም የሌላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹በጦርነት ለማትረፍ የሚፈልጉ ኃይሎች የሰላም ስምምነቱን ከእነ ጭራሹ አይፈልጉትም፣ ይቃወሙታል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የሌላቸው ወገኖች ደግሞ አቋማቸው ግራ የተጋባ ይሆናል፡፡ ጦርነት ፈላጊ ወገኖች ቢኖሩም፣ ነገር ግን ለሰላም ሁሌም መትጋት ያስፈልጋል፤›› በማለት ነው ዓብይ (ዶ/ር) ያስረዱት፡፡ በመንግሥት በኩልም የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር ፍፁም ዝግጁነት መኖሩን ነው ለፓርላማው ያረጋገጡት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -