Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን ካፒታሉን ለማሳደግና ለውጭ ኩባንያዎች ድርሻ ለመሸጥ ወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስድስት የአገር ውስጥ ባንኮች ዋነኛ ባለድርሻ የሆኑበት ፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን አክሲዮን ማኅበር (ፒኤስኤስ) ካፒታሉን በ232 ሚሊዮን ብር ለማሳደግና ለውጭ ኩባንያዎችም የአክሲዮን ድርሻ ለመሸጥ መወሰኑን አስታወቀ። 

ኩባንያው አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋትና የዲጂታል የፋይናንስ ተጠቃሚነቱ ለማስፋት የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የካፒታል መጠኑን ለማሳደግ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው እስካሁን የተከፈለ የካፒታል መጠን 165 ሚሊዮን ብር ሲሆን አሁን ግን ይህ የካፒታል መጠን በ232 ሚሊዮን ብር ጨምሮ ወደ 396 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ መወሰኑን የፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሴፍ ክብረት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን ዋነኛ ባለአክስዮኖች የሆነበት የአገር ውስጥ ባንኮች አዋሽ፣ ኅብረት፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ፣ አዲስ ኢንተርናሽናል፣ ንብና ብርሃን ባንኮች ሲሆኑ፣ የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ የሚወጡ አክሲዮኖች በቅድሚያ ለስድስቱ መሥራች ባንኮች የሚሸጡ መሆኑን አመልክተዋል። ከእነርሱ የተረፈውን አክሲዮን ደግሞ የውጭ ኩባንያዎች ጭምር እንዲገዙ ለማድረግ ውሳኔ መተላለፉ ገልጸዋል፡፡ 

የኩባንያው ካፒታል ማሳደግ አስፈላጊ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ኩባንያው ባለፉት አሥር ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን መሠረተ ልማትና ሶፍትዌሮችን ደረጃ ማሳደግና ማበልፀግ አንዱ ሲሆን፣ አዳዲስ የቢዝነስ አገልግሎቶችን መጀመርና ለኩባንያው ተጨማሪ ገቢ ማስገኘትም ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ዮሴፍ ገልጸዋል።

ኩባንያው በአሥር ዓመት የአገልግሎት ዘመኑ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 24.18 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ኩባንያው በ2013 የሒሳብ ዓመት ካገኘው ትርፍ ጋር ሲነፃጸር በ696 በመቶ ብልጫ እንዳለው ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ኩባንያው በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶ የነበረው የትርፍ መጠን 3.03 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ኩባንያው የትርፍ ምጣኔውን እያሳደገ መምጣቱን ያመላክታል ተብሏል፡፡ 

ፕሪሚየር ስዊች ሶሉዊሽን በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ ለኩባንያው ባለአክሲዮኖች ከፍተኛ የሚባል የትርፍ ድርሻ ያበረከተ ነው። የኩባንያው ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመለክተው በ2013 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው አጠቃላይ ትርፍ ባለአክሲዮኖች ያገኙት የትርፍ ድርሻ ክፍያ በአንድ አክሲዮን 6.34 ብር ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ግን የአንድ አክሲዮን ትርፍ ድርሻ በብዙ እጥፍ ጨምሮ 169.7 ብር አስገኝቷል፡፡ 

ኩባንያው ከቀደሙ ዓመታት እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለውን ትርፍ ለማስመዝገብ የቻለባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን ኩባንያው በርካታ የክፍያ ካርዶችን በ2014 የሒሳብ ዓመት እንዲሠራጩ ማደረጉና በእነዚህ ካርዶች የተካሄደው የገንዘብ ልውውጥ መጠንም በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ እንደሆነ የፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሴፍ ክብረት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹትም፣ ኩባንያው በ2014 የሒሳብ ዓመት 1.3 ሚሊዮን የክፍያ ካርዶችን በማተም ለአባል ባንኮች ማሠራጨቱን ጠቁመዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተሠራጩት የክፍያ ካርዶች መጠን ኩባንያው ሥራ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ለገበያ ካቀረባቸው የክፍያ ካርዶች 30 በመቶ እንደሚሆን በመጥቀስ በአንድ ዓመት የተሠራጨው የክፍያ ካርድ መጠን እጅግ ግዙፍ የሚባል መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በገበያ ውስጥ የተሠራጨው አጠቃላይ የኩባንያው የክፍያ ካርዶች ብዛትም 4.40 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2014 የሒሳብ ዓመት ፒኤስኤስ በአጠቃላይ የገንዘብ መጠናቸው ከ18.5 ቢሊዮን በላይ የሆኑ 18.8 ሚሊዮን የገንዘብ ማውጣት (ATM Withdrawal) ሒደቶችን የተካሄደ ሲሆን፣ ይህ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ በ25 በመቶ የላቀ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑት የገንዘብ ማውጣት ክንዋኔዎች የፒኤስኤስ መለያ የያዙ ካርዶችን በመጠቀም የአንዱ ባንክ ደንኛ በሌሎች የፒኤስኤስ አባል ኤቲኤም ማሽኖች ላይ ያካሄዷቸው ናቸው ተብሏል፡፡ ፒኤስኤስ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት ውስጥ በጥቅሉ ከ78 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ማውጣት ሒደቶችን በኤቲኤም አማካይነት እንዳስተናገደም አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የፒኤስኤስን መለያ የያዙ ካርዶችን በመያዝ በኢትስዊች መረብ በኩል የሌሎች ባንኮች ኤቲኤሞች ላይ የተፈጸሙ ትራንዛክሽኖች ብዛት በቁጥር 7.2 ሚሊዮን እንዲሁም በገንዘብ መጠን ደግሞ 5.7 ቢሊዮን ብር እንደነበረም የቦርድ ሊቀመንበሩ ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአባል ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖች ላይ ከፒኤስኤስ ውጪ በሆኑ የአገር ውስጥ ካርዶች የተፈጸሙ ትራንዛክሽኖች በቁጥር 5.1 ሚሊዮን፣ በገንዘብ ደግሞ ከ6.2 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ማውጣት ሒደቶች ተፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪም አባል ባንኮች ደንበኞቻቸውን በራሳቸው የኤቲኤም ማሽኖች ያስተላለፏቸው ትራንዛክሽኖች መጠን በአጠቃላይ በቁጥር 4.7 ሚሊዮን በላይ ሲሆን በገንዘብ መጠን ደግሞ 4.9 ሚሊዮን ብር መድረሱም ተጠቅሷል፡፡ 

በ2014 የሒሳብ ዓመት የክፍያ መቀበያ (POS) ማሽንን በመጠቀም በአባል ባንኮችና በዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶች አማካይነት 195 ሚሊዮን ብር ያወጡ ብዛታቸው 91,894 የግዥ ግብይቶችን ፒኤስኤስ ማስተላለፉንና ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 65 በመቶ ዕድገት የታየበት ሆኖ እንደሆነ ኩባንያው አስታውቋል፡፡ 

በተያያዘ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ዓለም አቀፍ ካርዶችን በመጠቀም 106 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ በቁጥር 25,979 የገንዘብ ማውጣት ሒደቶችን በፖስ ማሽን አማካይነት ማስተላለፍ መቻሉን እንዲሁም በተያያዘም የክፍያ መቀበያ ማሽንን በመጠቀም 353 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያወጡ ብዛታቸው 152,236 የሆኑ የገንዘብ ማውጣት በሒሳብ ዓመቱ ማከናወን ተችሏል፡፡ 

በሌላ በኩል የክፍያ መቡን ከማስፋት አኳያ በሒሳብ ዓመቱ 122 ተጨማሪ ኤቲኤም ማሽኖች እንዲሁም 1,188 የክፍያ መቀበያ ፖዝ ማሽኖች ከፒኤስኤስ ሲስተም ጋር ተገናኝተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ይህም በአጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥርን 1,198 እንዲሁም ከፍ ያደረገ ሲሆን በንግድ ተቋማቶች የሚገኙ የክፍያ መቀበያ ማሽኖች ቁጥር 3,868 ሊደርስ ችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች