Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየቀደምት ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት አምራች ፋብሪካዎችን አገራዊ ልምድና ተሞክሮ የመቅሰም ችግር

የቀደምት ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት አምራች ፋብሪካዎችን አገራዊ ልምድና ተሞክሮ የመቅሰም ችግር

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

በሪፖርተር የረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም በ‹‹ልናገር›› ዓምድ በእንየው ታደሰ (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት የዕውቀትና የሕግ ክፍተት ችግሮችና የመፍትሔ ዕጦት›› በሚል ርዕስ የተጻፈውን አነበብኩት፡፡ በጥሬ መረጃ፣ ማስረጃ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጭብጦችና መግለጫዎች ተደግፎ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፡፡ እንየው (ዶ/ር) በጻፈው ጽሑፍ በቅርብ ጊዜያት የውጭዎቹ በእነ ዩኒዶ፣ ኤፍኤኦ፣ አይኤልኦ በኩል ከአገር ውስጥ ከኢንዱስትሪና ግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በ2001 እና በ2007 ዓ.ም. የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪ ዘርፉን አስመልክቶ የተጠኑት ጥናቶች፣ እንዲሁም በስፔን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለሦስት ዓመታት (ከ2010 እስከ 2012) በምግብ ዘይት ፋብሪካ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ምርት ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ለማፈላለግ ተቀርፆ በተተገበረ ፕሮጀክት፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ በአነስተኛ (Small and Cottage Industries) የዘይት ጨመቃ ከጀርመን ልምድ ለማግኘት የተደረገውን ሙከራ አሳውቆናል፡፡ በመጨረሻም በቴክኒካዊ አገላለጽ በሞዴል ማነፃፀሪያ በሥዕላዊ መግለጫ ያለውን ችግርና የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቁሟል፡፡

እንየው (ዶ/ር)ን በቅርብ አውቀዋለሁ፡፡ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በምርምር፣ በማስተማርና በአመራር ደረጃ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የማውቅ ሲሆን፣ እንደ እሱ ያሉ በምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተማሩና የሠለጠኑ ሙያተኞችን የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚገባ የተጠቀመባቸው አይመስለኝም፡፡ ተሳስቼም ከሆነ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ታዲያ ይህ አገራዊ ሙያተኞችን ከፖለቲካ ባሻገር ባለ ምልከታ ያለመጠቀም አባዜ ሁሌም ሰለ አገራችን ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና በማስብበት ወቅት የሚገርመኝና የማዝንበት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከተነሳንበት ከምግብ ዘይት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወቅታዊ ችግሮች አንፃር የሚመለከታቸው የመንግሥትና ሕዝባዊ ተቋማት (ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ቢሮዎች፣ ኮሚሽኖች፣ ኤጀንሲዎች) እንየውን (ዶ/ር) እና መሰል ሙያተኞች ከመጠቀም ይልቅ፣ ትንሽ ዶላራ ይዘው በጥናትና ማማከር ሥራ ስም፣ አለፍ ሲልም ፕሮጀክት ይዘን መጣን በሚል ዘርፉን ምስቅልቅሉን እያወጡት እንዳሉ መረጃዎች ሳገኝ፣ ይህ ዓይነቱ አገራዊ በሽታ መቼ ለቆን በአገሪቱ ዕውቅ ሙያተኞች፣ ቢያንስ የአመራር ጥላ ሥር፣ የአገሪቱን የተለያዩ የአምራች ዘርፎችን አወቃቀርና ሥራ እንቀስቃሴ ችግሮች በአገራዊ ጥቅም ላይ አንተርሰን እንደምናስጠና እየናፈቀኝ መጥቷል፡፡

በምግብ ዘይት ማምረት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም እንደ አገሬ ሰው አባባል ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ… ይቆጠራል›› ይሉ ዘንድ የራሳችን ሙያተኞችን አገራቸው ሳትሆን፣ እንመራታለን የሚሉ ፖለቲከኞች ጣል ጣል ቢያደርጓቸውም፣ በመላው ዓለም ከአደጉ እሰከ ታዳጊ ባሉት አገሮች ውስጥ ግን በማማከርና ጥናት ላይ በተመሠረተ ምክረ ሐሳባቸው ትልቅ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ አዘነ በቀለ (ዶ/ር) በሩዋንዳ ባዶ የሆነ መሬትን በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና እንክብካቤ ሳይንስ ላይ በተመሠረተ ጥናትና ትግበራ ምርታማና ውብ የቱሪስት መስዕብ አድርገው ዓለም አቀፍ ትኩረት ማግኘታቸው፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት ደግሞ ኢትዮጵያዊው አቶ ይልማ፣ ቬትናሞች ከምንም ተነስተው ዛሬ ላይ በቡና ከዓለም ሦስተኛ አምራች የሆኑበትን ስትራቴጂካዊ ጥናትና ምክር ሰጥተው ለዚህ እንዳበቋቸው መጥቀስ ይቻላል፡፡ ታዲያ ቢያንስ በአገር ውስጥ እንደ እነ እንየው (ዶ/ር) ዓይነቱን በምግብ ዘይት ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ችግር አጥንተው መፍትሔ ሊያቀርቡ ሲችሉ፣ ከእሱ ጽሑፍ እንደተረዳሁት ከውጭ አገር አገራዊ ዕውቀቱና ልምዱ የሌላቸውን በትመህርትና ሥልጠናውም ከእሱ ዓይነቶች ኢትዮጵያውያን ሊማሩ የሚችሉ ሰዎች በፕሮጀክት፣ በሞዴል፣ በልምድ ልውውጥ አመክንዮ ዶላር ይዘው ስለመጡ ብቻ ዘርፉ ዛሬም በችግር ውስጥ ተዘፍቆ እንዲገኝ እንዳደረጉት ተገንዝቤያለሁ፡፡ በሞዴል ግርግርና ክርክርም አገራዊ የምግብ ዘይት ማምረትና አቅርቦት ችግር መፍትሔ በሌለው ምክረ ሐሳብ እየታመሰ እንዳለ ከእንየው (ዶ/ር) ጽሑፍ ስለሸተተኝ ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማጻፍ ተነሳሳሁ፡፡

ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ችግሩ ገዝፎ መፍትሔ አጥቶ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ በኋላም በደርግ ዘመን በአገራዊ ዕውቀትና ጥበብ ላይ በተመሠረተ በጎጆ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተር ፕራይዞች (Cottage, Small and Medium Enterprises) በምግብ ዘይት መጭመቅና አቅርቦት ረገድ ለሕዝቡ በቂ በሆነ መጠን ይቀርብ የነበረው የምግብ ዘይት አቅርቦት ሥራ ልምድና ተሞክሮ ለምን ከዚያ በኋላ የመጡት የመንግሥትና ሕዝባዊ ተቋማት ኃላፊዎች በኢትዮጵያውያን ሙያተኞችና የልማት ሥራ ኤክስፐርቶች አስጠንተው ሊማሩባቸው እንደማይሹ ከእንየው (ዶ/ር) ጽሑፍ ባሻገር የዓይን ውጋት ስለሰጠኝ ነው፡፡

የእንየው (ዶ/ር) ጽሑፍ የጀመረው በ2001 ዓ.ም. ከተደረገ ጥናት ሆኖ ወደ ኋላ በንጉሡ ሆነ በደርግ ጊዜ የነበረውን አላስቃኘንም፡፡ በንጉሡ ዘመን የተጀመሩ፣ በደርግ ጊዜ በሠራተኞች አያያዝና አደረጃጀት በኩል መሻሻል እንዲደረግባቸው ተደርገው በዘይት ማምረት ሥራቸው በቀጠሉት አነስተኛ/የጎጆ ኢነዱስትሪዎች (Small and Cottage Industries) ልምድና ተሞክሮ ላይ የእሱ ጽሑፍም አልተንደረደረም፡፡ ለምን የሚለውን ጥያቄዬን ወደፊት እንየው (ዶ/ር) ይመልሰዋል ብዬ በመገመት፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጋዜጦችና ሬዲዮ ጣቢያዎች በተደረገልኝ ቃለ ምልልስ ለመግለጽ፣ እንደሞከርኩት ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የነበሩ አነስተኛ/የጎጆ ኢነዱስትሪ የምግብ ዘይት ማምረቻ  ተቋማት  አስተዋጽኦ ምን ድረስ እንደ ነበር፣ ለምን እንዲከስሙ እንደተደረገ፣ ዛሬ ከእነ አካቴውም ወደ መረሳት የመጡም ስለመሰለኝ በእነዚህ ጭብጦች ዙሪያ አስቀድሜ የእኔን ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የሥራ ልምዴንና የማማከር ሥራ አስተምህሮት ለማጋራትና ብሎም ከመነሻ ጽሑፉ ጋር በማያያዝ ተገቢ ነው ብዬ ያመንኩበትን ግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት በማስተላለፍ ይህችን ጽሑፍ ለውይይት መነሻነት አቅርቤያለሁ፡፡ የእኔን ልምድና ተሞክሮ ያቀረብኩት ለኤሌክትሮኒክስም ሆነ ለኅትመት ሚዲያው ቅርብ ስለሆንኩና፣ በአብዛኛው ስለኢኮኖሚ በተለይም ስለግብርናው ዘርፍ የዕድገትና ብልፅግና ፖሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች ስለምጽፍና ስለምናገር፣ ደግሞ ምን አውቃለሁ ብሎ ነው ደምስ ስለምግብ ዘይት ፋብሪካና ችግሮቹ የሚጽፈው ብለው ሊጠይቁ ለሚነሱ አንባቢያን ትንሽ የማሳወቂያ መግቢያ መጻፍ አስፈላጊ መስሎ ስለታየኝ ነው፡፡

በነገራችን ላይ አነስተኛ/ጎጆ ኢንዱስትሪ፣ የቤተሰብ፣ የጥቃቅን፣ ባህላዊ ወዘተ. መጭመቂያዎችን ደረጃና ምንነት ከሥራ ፈጠራና ገቢ እንዲሁም፣ ከሌሎች መሥፈርቶች አንፃር ትንታኔ ሰጥቶ ለማቅረብ የዚህች አጭር ጽሑፍ ክፍለ ዓላማ አካል ስላልሆነ፣ በይዘትም ከአገር አገር የተለየ መሥፈርትና መገለጫ ስለሚሰጣቸው በጥቅሉ ቢያንስ ከባለቤቶች በተጨማሪ ከ50 ያልበለጡ ቋሚ ተቀጣሪ ሠራተኞች፣ የመጭመቂያና የማጣሪያ ማሽኖችና ተጓዳኝ ቴክኖሎጂዎች ያሏቸው ሙሉ ለሙሉ አገር ውስጥ የሚመረቱ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችን አነስተኛ ማለት ሲቻል በጣም ጥቂት ሠራተኛ፣ በቤተሰብ ደረጃ የሚተገበሩት የጎጆ ኢንዱስትሪ ናቸው በሚል አንባቢያን ይረዱልኝ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡

በ1960ዎቹ አጋማሽ በተካሄደው አብዮት ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የተዘጉበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከቤተሰቦቼ ጋር እኖርበት ከነበረው አሰላ ከተማ በ1967/68 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጥቼ በጉለሌ አዲሱ ገበያ አካባቢ አነስተኛ ኢንዱስትሪ/ፋብሪካ ሊባል የሚችል የዘይት መጭመቂያና አምርቶ መሸጫ ፋብሪካ ካላቸው ዘመዶቼ ጋር እየኖርኩ በፋብሪካው ውስጥ ሠራሁ፡፡ ፋብሪካው የአበራና ልጆቹ ዘይት ፋብሪካ ተብሎ በአገሪቱ የንግድ ሕግ ተመዝግቦና ፈቃድ ይዞ የሚሠራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከግብዓት አቅርቦት (የቅባት እህሎችን ጨምሮ) እና ከምርት (በተለይም የምግብ ዘይት በበርሜል በብዛት ይሸጥ ስለነበር) ጋር ተያይዞ በማውረድና  በመጫን ረገድ ያለውን ሥራ፣ በመጋዘን (የጥሬ ዕቃና የምርት) የቅባት እህሎች ማበጠሪያ፣ በሞተር ክፍል ውስጥ የመጭመቂያ፣ በካልዳያ የሙቀት መስጫ (Boiler)፣ የማጣሪያ (Refiner)፣ የማሸጊያና ማከፋፈያ ክፍሎች ያሉትን ሥራዎች በሚገባ በተግባር ጭምር አውቄአቸው ነበር፡፡ ፋብሪካው ለልዩ ልዩ ማሽነሪዎች መጠገኛ የዘመናዊ ቶርኖ ክፍልም ነበረው፡፡ በጥቅሉ በፋብሪካው ውስጥ ከጉልበት ሥራው ጀምሮ እሰከ አመራር ባለው ተሳትፌያለሁ፡፡ በእውነት ይህን ዕድል ለሰጡኝ ዘመዶቼ በተለይ ለአቶ አበራ ገብረ ሕይወትና ቤተሰባቸው ዛሬ በገሃድ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡ በሕይወቴ ውስጥ በመደበኛው ትምህርት ካገኘሁት ዕውቀት፣ ልምድና የአመራር ጥበብ የማይተናነስ የሕይወት ዘመን ተሞክሮና የሥራ ባህል ስንቅ እንዳገኝ አድርገውኛልም፡፡ 

በፋብሪካው ውስጥ እንደ አቶ አበበ ደገፉ (ነፍስ ኄር) መሰሉ በቴክኒክ ሥራው ዕድሜ ጠገብ የነበሩ ሰዎች ዕውቀትና የሥራ ላይ ሥልጠና ሰጥተውኛል፡፡ ግዙፍ፣ የተወሳሰበ የብረት ጥርስ የበዛበትን ተሽከርካሪ የመጭመቂያ ማሽን ፈታትቼ መልሼ መግጠም እስከምችልበት ደረጃ ድረስ ያለውን አስተምረው፣ በተግባር ጭምር አሠልጥነው አብቅተውኛል፡፡ በዚያው ፋብሪካ ውስጥ እንደ አቶ አበባው አያሌው ዓይነቱ ያኔ የፋብሪካው ሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር የነበረ፣ ዛሬ ላይ አንቱ የሚባል በትራንስፖርቱ ንግድ ዘርፍ ተሰማርቶ በግሉ ትልቅ ስኬት ያገኘ በወቅቱ በፋብሪካው ውስጥ የሚሠሩትን ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን ከመምራት፣ ይሰጥ በነበረው የመሠረተ ትመህርት ማስተማር ላይ በመሳተፍ፣ በመመካከር የፋብሪካ ባለቤቶችና ሠራተኞች በአንድነት ተግባብተው ከሠሩ ጥሩ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል የማኔጅመንትና አስተዳደር ንድፈ ሐሳባዊ ሳይሆን፣ ተጨባጭ ዕውቀትና ጥበብ እንድጨብጥ አስችሎኛል፡፡ ይህን ጽሑፍ ስጽፍም ከማስታወስ አንፃር ክፍተት እንዳልፈጥር በረቂቁ ላይ አስተያየት ሰጥቶኛል፡፡ በአጠቃላይ በፋብሪካው ውሰጥ ቆይታዬ በዘመናዊው ትምህርቴና፣ በቅርብ ጊዜም አቶ አሰፋ ማመጫ ‹‹የጃፓን መንገድ›› ብሎ በጻፈው መጽሐፍ ጃፓን ከጦርነት ምስቅልቅል በኋላ ያደገችበትና የበለፀገችበትን ጎዳና እንድናውቅ ባደረገው ዓይነት ልምድና ተሞክሮ ያገኘሁበት ጊዜ ነበር ብል ማጋነን  አይደለም፡፡

ከላይ ብዙም በመደበኛው ትምህርት ባልገፋሁበት ጊዜ ካገኘሁት ዕውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ በተጨማሪ በመደበኛው ትምህርት እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ይዤ፣ በተለይ በግል የማማከር ሥራ ላይ ከሠራኋቸው ሥራዎች መሀል ከምግብ ዘይት ጋር የተያያዙ ጥናቶችም ነበሩ፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. 2008 (በ2000/2001ዓ.ም.) ለኢትዮ አግሪ ሴፍት (የሜድሮክ እህት ኩባንያ) አስዳ (ASDAA) በሚባል የማማከር ድርጅት በኩል የአኩሪ አተር ዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ ለማቋቋም የቴክኒክና የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት ሲደረግ የኢኮኖሚ አዋጪነት ጥናቱን ከሌላ የሥራ ባልደረባዬ ጋር በመሆን አጥንተነዋል፡፡ በዚህ ወቀት ለአንድ የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት የሚያስፈልግ ከግብዓት እስከ ማምረትና ሸጦ ትርፋማ ለመሆን እስከ መቻል ድረስ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በቁሳዊ ይዘትና መጠን እንዲሁም፣ ከዋጋ አንፃር ማሰባሰብ ግድ ሲል፣ አብሮም የበርካታ ዓመታትን የአገሪቱን የምግብ ዘይት የማምረትና አቅርቦት መራጃ ከተቋማት/ፋብሪካዎች አደረጃጀትና ይዘት ጋር አጣምሮ መሰብሰብ አስፈላጊ ነበር፡፡ መረጃው ሲሰበሰብም የአኩሪ አተር ብቻ ሳይሆን የኑግ፣ የጎመን ዘርና የተልባ ወዘተ. የቅባት እህሎችንም በተለይ ከአገር ውስጥ የአቅርቦት መጠን፣ ወደ ውጭ ከሚላክና ወደ አገር ከሚገባው ዓይነትና መጠን፣ በተጨማሪም የቅባት እህሎቹ የሚመረቱበትን አካባቢ መለየትና የማምረት አቅምን ወዘተ. ማሥላትና መተንተን የግድ ይል ነበር፡፡ በመስክ ሥራም በፍኖተ ሰላም አካባቢና ብር ሸለቆ፣ በምዕራብ ጎጃም በፓዊ ዙሪያ ብሎም በባህር ዳር ዙሪያ ሰፊ የመረጃ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ አድርገን ነበር፡፡ በመጨረሻም የጥናቱ ሪፖርት ተጠርዞ ለአስጠኝው አካል ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ ተሰጥቷል፡፡

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከላይ በሁለት አንቀጾች የተገለጹትን ልምዶቼንና ተሞክሮዎች ያቀረብኩት፣ በቀጣይ ለማብራራውና ለምሰጠው ምክረ ሐሳብ ለአንባቢያን ግንዘቤ ያስጨብጣል በሚል ነው፡፡

በፋብሪካ ሥራ ካገኘሁት ተግባራዊ ዕውቀት፣ ሙያዊ ክህሎትና በዘመናዊ ትምህርትና ሥልጠና ላይ ተመርኩዤ በማማከር ጥናት ላይ ከተገነዘብኩት፣ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ ዘይት ማምረትና አቅርቦት ረገድ ያለው ትልቁ ችግር በአብዛኛው የዕውቀትና የሕግ ክፍተት ብቻ ሳይሆን፣ በአንፃራዊ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ደርሳበት የነበረን የዕድገትና ልማት ደረጃ ያለማወቅ፣ ወይም አውቆ ላለመማር፣ ለግልና ለቡድን የፖለቲካና የሥልጣን ጥቅሞች ሲባል፣ ለማወቅ ካለመሻት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ በሽታ ብዙውን ጊዜ በሥልጣን ላይ ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናትን አገራዊ ሙያተኞችን ጠል፣ ለነጭ ሰጋጅ ሲያደርጋቸውም ይስተዋላል፡፡

በንጉሡ ዘመን፣ እንደ አሁነኛው ጊዜ ከውጭ አገር ያስፈልጋል የሚባል በፕሮጀክት ቀረፃና የመተግበር ግርግር ፈጠራ የታጀበ ብዙም ተሞክሮና ልምድ ልውውጥ ሳይሹ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ገዝተው በማስገባት፣ የምግብ ዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎችን በማቋቋም፣ ጥራቱን የጠበቀ ትኩስ ፈሳሽ የኑግ፣ ጎመን ዘርና ተልባ የምግብ ዘይት በቂ ሊሆን በሚችል መጠን ለሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ በቅርብ እንዲያገኝ አስችለው ነበር፡፡ ዛሬ የረጋ፣ ለጤና አዋኪ የሆኑ ናቸው ተብለው የሚገመቱ የምግብ ዘይት ዓይነቶችን በማስገባት፤ ወይም የፓልም ድፍድፍ በማስገባትና በማጣራት የምግብ ዘይቱ እንኳ በቅርብ በሠፈር ሊገኝ በትልልቅ ገበያ ማዕከላትም ለማግኘት ብርቅዬ የሚሆንባቸው ጊዜያት በርክተዋል፡፡

በዘርፉ በንጉሡና በደረግ ዘመን የተደረሰበት የዕድገት ደረጃና የልማት አቅጣጫ ሊጎለብትና ቀጣይነትም እንዲኖረው መደረግ ነበረበት፡፡ ግን አልሆነም፡፡ በዚህ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ልማት ዘርፎች፣ በአንፃራዊ ምልከታ፣ በዚያን ወቅት ተገኝተው የነበሩ አገራዊና ዘለቄታዊ መሠረት የጣሉ የልማት ሥራ አቅጣጫዎችን ተማርን፣ ሊቅ ሆንን የምንል በርካታ ኢትዮጵያውያን ለምን እንደምናደበዝዛቸውና ከመልካም ተሞክሮዎችና ሥራዎች ተምረን ለዛሬው ሥራችን ልንጠቀምባቸው እንደማንፈልግ ሳስተውል ይገርመኛል፣ የወደፊት የዕድገት መንገድ ዕይታችንም ያሳስበኛል፡፡ 

በንጉሡ ጊዜ የተቋቋሙትን በርካታ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን አጥፍተን፣ እንየው (ዶ/ር) እንዳመላከተው፣ በውጭ አማካሪዎች በፕሮጀክቶችና፣ ሞዴሎች በታጀበ ሴራዊ ጎዳና አገራዊ አቅምን መገንባት ሳይሆን፣ የማፍረስ ወጥመዳቸው ውስጥ የተዘፈቅን ይመስለኛል፡፡ በዚህ ሳቢያም የምግብ ዘይቱ የልማት ሥራ ባልተገባ አቅጣጫ ውስጥ ገብቶ እየተተራመሰ እንዳለ ከጽሑፉ ማሽተት ይቻላል፡፡ በንጉሡና በደርግ ዘመን በየአካባቢው ያለን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉንን የጎጆ/አነስተኛ/መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን አቀጭጨን በርካቶችንም ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ አድርገን፣ ከሥራ ፈጠራ አኳያ በቋሚነት ከ50 እስከ 300  የማያንሱ፣ በጊዜያዊነት ደግሞ ለመቶዎች የሥራ ዕድል የሚያስገኙ የነበሩትን ተቋማት አጥፍተን፣ ዛሬ የሥራ ዕድል ፈጠራ እያልን በእንብርክክና በእንፉቅቅ እንዳክራለን፡፡

በምግብ ዘይት መጭመቅና የተጣራ ዘይት አምርቶ ለተጠቃሚው በማቅረብ በኩል እንደ ምሳሌ አድርጌ እኔ በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ሠርቼበታለሁ ባልኩት በአበራና ልጆቹ ፋብሪካ ውስጥ ብቻ በሳምንት ሦስት፣ አራት ጊዜ ከ20 እስከ 30 በርሜል ከኑግ፣ ከጎመን ዘር አንዳንዴም ከተልባ የሚጨመቅና የተጣራ የምግብ ዘይት በወቅቱ ትሬንታ ኳትሮ ተብሎ በሚጠራ የጭነት መኪና ወደ ጠቅላይ ግዛቶች የተለያዩ አወራጃዎች፣ እንዲሁም በኦኤም ሎንቼና መኪና በአዲስ አበባ ውስጥ አከፋፋዮች እንሸጥ ነበር፡፡ ይህ በየቀኑ ለ12 ሰዓት ለአካባቢው ሆነ ከየትም መጥቶ ፋብሪካው ደጅ ባለን ሱቅ ከሚቸረችረው በተጨማሪ ነበር፡፡ ከዘይት መጭመቂያው ከሚገኙ ተረፈ ምርቶች መሀል ጭቃ መሰል ተረፈ ምርቱ አዲስ አበባ ውሰጥ ለፊልዶር ሳሙና አምራች ይሸጥ ነበር፡፡ ፋጉሎው ለአካባቢው ከብት አርቢዎች ከሚሸጠው ተርፎ፣ በትልቅ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ በዓመት አንድ ጊዜ በሺሕዎች በሚቆጠር ኩንታል ወደ ውጭ አገር ኤክስፖርት ይደረግ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ አነስተኛ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ ይከናወን የነበረ ሥራ ነው፡፡

ከላይ በምሳሌነት እኔ የሠራሁበትን የምግብ ዘይት ፋብሪካ አወሳሁ እንጂ፣ በዚያ ወቅት በርካታ አነስተኛ ፋብሪካዎች በንጉሡ ዘመን በኋላም በደርግ ጊዜ በመላ አገሪቷ ተስፋፍተው ነበር፡፡ እኔ ከሠራሁበት ፋብሪካ  በእግር ጉዞ ከአምስት እሰከ አሥር ደቂቃ በሚፈጅ ርቀት ላይ ሦስት ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ነበሩ፡፡ በነዚህ መሰል ፋብሪካዎችም የሕዝቡ የምግብ ዘይት ፍላጎት ከሞላ ጎደል ይሟላ ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው በርካታ ቋሚ ሠራተኞች ሲኖራቸው፣ በጫኝና አውራጅ ተጓዳኝ የቀን ሥራ የሚሠሩ በርካቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን መሰል አነስተኛ ፋብሪካዎችን ከማጠናከር፣ ከማሳደግና ከማስፋፋት ይልቅ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት እንዲቀጭጩና በርካታ ፋብሪካዎችም እንዲዘጉ ሆኗል፡፡ በምትኩ መካከለኛም ሆነ ከፍተኛ የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎችን በአገራዊ ጥናት ላይ በአገሬው ሙያተኞች አስጠንቶ በግሉ ዘርፍ ውስጥ ባሉ ኢትዮጵያዊ  ባለ ሀብቶች ግንባር ቀደምትነት እንዲቋቋሙና እንዲስፈፉ ከማድረግ ይልቅ የምግብ ዘይት ከውጭ የማስገባት፣ በተለይም ለጤና ጎጂ ናቸው ተብለው የሚነገርላቸውን የሚረጉ ዘይቶችን ማስገባት የፖሊሲ አቅጣጫ ሆኖ ከረመ፡፡

በቅርቡ ደግሞ ይህን ለማስቆም ተብሎ ትልልቅ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎችን ለመመሥረት ተብሎ በተደረገ የስትራቴጂ ለውጥ፣ ከድጡ ወደ ማጡ ይሉ ሁሉ፣ በቴክኖሎጂ ይዘታቸው ከአገር ዘላቂ የምግብ ዘይት የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ አንፃር ያልተፈተሹ፣ ከውጭ የሚመጣ ድፍድፍን የሚያጣሩ፣ ለድፍድፉ በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር የማያንስ የውጭ ምንዛሪ የሚሹ፣ በአገር በቀል የቅባት እህሎችና ተክሎች ላይ የመፈብረክ አቅማቸው ደካማ የሆኑትን ማቋቋም ተጀመረ፡፡ እነዚህም በእነ እንየው (ዶ/ር) ዓይነቱ ሙያተኞች ቢፈተሹ በርካታ የቴክኒክ ዘላቂነትና ኢኮኖሚያዊ ውጤታማነት ችግሮች ያላቸው እንደሚሆኑ እገምታለሁ፡፡ ስለሆነም የቅርቡ ጊዜ የፖለሲና ስትራቴጂ ክለሳውም መፈተሽ አለበት፡፡

ፍተሻውና ክለሳው ደግሞ በአገሪቱ ሙያተኞች የሚመራ መሆን አለበት፡፡ ቢያንስ ለዚህ ያህል የሚበቁ፣ በምግብ ዘይትም ሆነ በሌሎች የምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተማሩና የሠለጠኑ ኢትዮጵያውያን አሉንና፡፡ በተለይ ደግሞ በፕሮጀክት ስም ከላይ በምሕፃረ ቃል መጠሪያቸው የተጠቀሱት የመንግሥታቱ ድርጅት ወይም ሌሎች በሁለትዮሽና ብዝኃ ድርጅቶች በኩል በሚመጡ ፕሮጀክቶች ውስጥ በሚሰገሰጉ በዕውቀትም ሆነ በልምድ በአገር ውስጥ ካሉት በማይበልጡ መመራት የለበትም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ዕውቀታቸውና ችሎታቸው አጠያያቂ የሆኑ በአማካሪነት እንደሚመጡ በዘርፉ ውስጥ ካሉ ሙያተኞች ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በእነዚህ አማካይነት ወይም ለይስሙላ  በውጭ አገሮች ያሉ በዜጋ ኢትዮጵያዊ የሆኑትን ወጣት ምሩቃንን በግንባር አሠልፈው፣ ከኋላ በሚዘውሯቸው ኤክስፐርቶች በሚቀረፁ ፕሮጀክቶች በማማከር ጥናት ስም በሚቀርቡ ሞዴሎችና የልምድ ልውውጦች ጊዜ ከማባከንና፣ በውድቀት ጎዳና ከመጓዝም መቆጠብ አለብን፡፡

ኢትዮጵያውያን በንጉሡ ዘመን በምግብ ዘይት ማምረትና አቅርቦት አገልግሎት እንዴት የሚፈለገውን ዓይነት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ሊገነቡ ቻሉ፣ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ለምን ተዳከሙ የሚለው መጠናት አለበት፡፡ ከበስተኋላ የዚችን ሰፊ አገር የምግብ ዘይት ገበያ ለመያዝ የተደረገ አሻጥራዊ አካሄድ ካለም መመርመር አለበት፡፡ ከዚያም እነዚያን መሰሎች በማቋቋምና በማስፋፋት፣ ብሎም እንደ ባለሀብቱ አቅምና ፍላጎት በዘርፉ መካከለኛና ከፍተኛ የምግብ ዘይት መጭመቂያ ፋብሪካዎችን ዘመኑ ከዋጀው ቴክኖሎጂ ጋር አጣጥሞ አገራዊ በሆነ እሳቤና ጥናት ላይ ተመሥርቶ መገንባትና ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡

በተለይም አርሶ አደሮቻችን ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ እህሎችንና ተክሎችን አምርተው ለማቅረብ፣ ከኢንዱስትሪዎች ባለቤቶችና አመራሮች ጋር ተሳስረው በሚሠሩበት አቅጣጫ ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን መከለስና መተግበር አለበት፡፡ ለዚህም እንደ እነ እንየው (ዶ/ር) ዓይነት ሙያተኞችን፣ በአገር ውስጥ ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘርፉ ተሰማርተው ከነበሩና ዛሬም ላይ ካሉ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በማቀናጀት፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና ሕዝባዊ ተቋማትም ዕውቀቱ፣ ብቃቱና ልምዱ ያላቸውን በማቆራኘት ጥናትና ምክረ ሐሳብ እዲያቀርቡ ቢደረግ የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ በቅረቡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በፓርላማ የሥራ እንቅስቃሴው በሚገመገምበት ወቅት፣ በርካታ የፖሊሲ ክለሳዎችና ማሻሻያዎች የስትራቴጂ ልየታዎች ወዘተ. እንዳደረገ ያሳወቀ ቢሆንም፣ በእኔ በኩል በውጭ አካላት ፋይናንስ ተደርጎ በማማከር ሥራና ጥናት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ይህም እንደገና በሚገባ በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች በሚመራ ግብረ ኃይል መፈተሽ አለበት፡፡

በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በውጭ ዶላር ፍሰት እርባና ቢስ በሚሆን፣ በአገራችን ውስጥ ዘላቂ ልማትና ለውጥ እንዳናመጣና ችግሮቻችንን እንዳንፈታ ተደርጎ በውጭ አገር አማካሪዎች  መሪነት ከሚደረጉ የጥናትና የማማከር ሥራዎች፣ ብሎም ፕሮጀክት ቀረፃና ትግበራ መቆጠብ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች በሚመራ፣ አስፈላጊም ከሆነ የውጭዎቹ በሚገባ ዕውቀታቸውና ልምዳቸው እየተገመገመ፣ በቡድን ውስጥ እዲካተቱ እየተደረገ የኢንዱስትሪው ግንባታና ማስፋፊያ የፖሊሲና ስትራቴጂ ክለሳውና የልማት ሥራው እንዲሠራ መደረግ አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው demesec2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...