Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቸገረ ነገር!

ያጠበቁት እየላላ፣ ያላሉት እየጠበቀ፣ በ‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ› ግራ መጋባት የሄድንበትን መንገድ ደግመን ልንሄድበት ታክሲ ተሳፍረናል። ከኮልፌ ወደ ቀራንዮ። ቁጭት፣ ሰቀቀን፣ ተስፋ ማጣት፣ ማግኘት፣ ጉጉትና ምንም የለሽነት ውስጥ ሆነው ብዙ ተሳፋሪዎች ቆዝመዋል። አንዱ አቀርቅሮ ስልኩን ይጎረጉራል። አንዱ ውልብታውን በመስኮት አነጣጥሮ እንደ ፊልም እያየ፣ ያለበትን ረስቶ አፍንጫው እስኪደማ ይጎረጉረዋል። በዚህ ቀልበ ቢስ የሚጠቋቆሙ ወጣቶች የማያስቀው ሁሉ አሳቀን እያሉ ይንከተከታሉ። ባለተራ ሆኖ ያሳቃቸው ቀስት ወደ እሱ እንዳይነጣጠር ሥጋት የገባው ርብትብት ደግሞ ምንም ሳይገባው ያጅባቸዋል። ታክሲያችን ጥቂት ሳብ ጥቂት ቆም እያለ ይወዛወዛል፡፡ ወሬ የተከለከለ ይመስል ተሳፋሪዎች እርስ በርሳቸው እየተፋጠጡ ቆይተው አንገታቸውን የደፉት ያቃናሉ። በአፍንጫ ጎርጓሪው ቀልበ ቢስነት ተመስጠው ፌሽታ ከፈጠሩት ወጣቶች ፊት ለፊት የተቀመጡ ወይዘሮ አንዴ ጆሯቸውን እየነካከኩ፣ አንዴ ወደ መንጋጋቸው ሌባ ጣታቸውን ሰደው የምግብ ስንቅር እየፈለጉ ነገረ ሥራቸው አልጥም ያላቸውን ወጣቶች ይታዘባሉ። ፈርዶባቸው!

ወያላው በተደጋጋሚ ብቅ እያለ፣ ‹‹ይኼ ሰላማዊ በረራ ነው። ማንም ሰው የነገር እሳት መለኮስና ማቀጣጠል አይችልም…›› እያለን ነው። ‹‹አቦ ይኼ ነገር ምንድነው? እኛ እኮ አትንኩን ባይ ነን። እንኳን ነገር ተደጋግሞብን እንዲሁም ጠርጥረን ዱር የምንመነጥር…›› ይላል አንድ አጭር ደንዳና። አዛውንቷ ፈገግ ብለው እያዩት፣ ‹‹አንተስ ብትሆን ስለነገር አዋቂነታችን ለማውራት ምን ይኼን ያህል ጉልበት ያስጨርስሃል? ‹ምሳር ላወቀበት ደን ይመነጥራል፣ አትቀደም ያለው በዓይን ይጠረጥራል› ብለህ ዝም አትልም?›› አሉት። ‹‹ይቅር ይበሉኝ እማማ። ጨዋታው የመቀደምና ያለ መቀደም መሆኑ አልገባኝም ነበር…›› ብሎ እንደ ቢጤው በዓይኑ ሲጠቅሳቸው እንዳላዩ አለፉት። ሳይገባው የገባው መስሎ የሚታየው በዝቶም ይሆናል እኮ ክልከላና ማስጠንቀቂያው የሚያጨናንቀን!

 ጉዞው ከተጀመረ ቆይቷል። ማንም እንዳይደረብብኝ ካለች አንዲት ሞጋች በስተቀር ሁሉም ወንበር ላይ ትርፍ ተገጥግጧል። ወያላው በዚህ መሀል ሒሳብ ካላመጣችሁ ብሎ ይነዛነዛል። ‹‹እባክህ ፋታ ስጠን? ገና ለገና ወደ ቀራንዮ ጫንኳቸው ብለህ መስቀል ታሸክመናለህ?›› ይለዋል አንዱ። ይኼኔ ሦስተኛው ረድፍ ከጎልማሳው አጠገብ የተሰየመች ወይዘሮ፣ ‹‹የራሱን መስቀል ያልተሸከመ ሰው ማን አለ? ይኼ እኮ በመፈጠር ዕጣ የሚታደልህ እንጂ፣ ታክሲ ስትሳፈርና ስትወርድ የሚጫንብህ አይደለም…›› አለችው። እንዲያ ስትለው ቀራኒዮን በመስቀል አዋዝቶ ያነሳው ተሳፋሪ ዝም ብሎ አያት። ዝም አለኝ ብላ ቀጠለች። ‹‹ይህች ዓለም እኮ ሰጥቶ በመቀበል ሒሳብ ብቻ ሳይሆን የምታምነው ሒሳብ በማወራረድም ነው። እያንዳንዳችን ሒሳብ ሳናወራርድ ከዚህች ሕይወት ውልፍት ማለት የለ…›› ትላለች። ‹‹እሱንማ እየያነው ነው፣ ብቻ ሒሳቡ አልቋል ብለው በሕዝብ ሕይወትና ንብረት የቀለዱትን ማወራረድ እንዳያቆሙ እንጂ…›› አለ ጎልማሳው ፈገግ ብሎ። ሊጀመር ነው!

      ወይዘሮዋ፣ ‹‹ገና ምኑን ዓይተህ፣ ገና ብዙ እናወራርዳለን። ገና ብዙ እንመራመራለን፡፡ ያልተመረመረ ሕይወት ደግሞ ሕይወት ነው እንዴ?›› ስትለው፣ ‹‹ግን ኑሮንስ? ራሷ ሕይወትን እንዴት እናወራርዳት? እሱም አለ እኮ…›› አለ። ‹‹ኑሮ ማለት እኮ ምላስ ነው የእኔ ልጅ። ንግግርህን ሳትመረምርና ሳታወራርድ በረከትህን ከመርገምህ መለየት አትችልም። ዘረኝነት፣ ስድብ፣ ጥላቻ፣ በቀል የሚያጭሩና የሚያበረታቱ ያልታረሙ ንግግሮችን፣ ያልተገሩ አስተሳሰቦችን፣ እያራመድን መስሎኝ ደህና ተስፋ የሰጠን እንቅስቃሴ ሁሉ እንዲህ ውርጭ የወረሰው…›› አሉት ወይዘሮዋ። ፖለቲካ ሊናገሩት መስሎት በጥርጣሬ ዓይን አያቸውና ዝም አለ። ፍራቻ በሉት!

ሆላንድ ኤምባሲን እንደ ጨረስን አንጠጋጋም ያለችው ተሳፋሪ ከእነ ጓደኛዋ ወረደች። ወያላው፣ ‹‹ሁለተኛ እንዳላያችሁ እያለ…›› ይዝታል። ‹‹እንዴ ምን ሊላቸው ነው ይኼ ወያላ? በገዛ አገራቸው? በገዛ መሬታቸው?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ እባክሽ ሴትዮ ዝም በይ። ዝም ብለሽ መብቷ ነው ብቻ አትይም? አገር፣ መሬት፣ ቅብጥርስ ምን ያስብልሻል? ልታስወነጭፊብን ነው እንዴ?›› ብሎ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ወጣት ደነፋ። ‹‹በገዛ አፌ ምን አገባህ? አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ካማረህ አይቻልም…›› ብላ ዞራ ልትገጥም ስትል አዛውንቱ፣ ‹‹እናንተ ሰዎች እርቧችሁ ነው? ሆዳችሁ ባዶ ነው? ከሆነ ንገሩንና ምግብ እንዘዝላችሁ። በተረፈ ሆዳችሁ ካልጎደለ ምንድነው በትንሽ ትልቁ ሽቅብ ሽቅብ የሚላችሁ? እኛም እኮ በሰላም የመስተናገድ መብት አለን…›› ብሎው ሲቆጡ ጫጫታው ረጭ አለ። አጠገቤ እናትና ልጅ ተሰይመዋል። ሚሚ ቀልባችንን መሳብ ጀምራለች። እደጊ እንበላት!

ከታክሲው ንጭንጭ ያለያየን ቢመስለንም መልሶ ስለታክሲ መሆኑ አልቀረም። ‹‹ማሚ ለምንድነው ሁሌ ብር መኪና ውስጥ ለሌላ ሰው የምትሰጭው?›› ጠየቀች ሚሚ። ‹‹እየሰጠሁ ሳይሆን እየከፈልኩ ነው እናትዬ። ካልከፈልን እኮ አይወስዱንም…›› እናት አባብላ ታስረዳለች። ‹‹ለምንድነው ሁሉም ነገር የሚከፈልበት?›› ብላ መልሳ ስትጠይቃት ተሳፋሪው እየተሳሳቀ ማደግን ይረግማል። እናት፣ ‹‹ይኼ ለእነሱ ሥራ ነው፣ እኔ ሥራ ሠርቼ ለአንቺ ብስኩት፣ ልብስ፣ ወተት እንደምገዛልሽ እነሱም ሰው በመኪና እየወሰዱ ለልጆቻቸው ልብስና ምግብ ይገዛሉ። ገባሽ?›› ገባት ብለን ስንጠብቅ ሌላ ጥያቄ መጣ። ‹‹ግን ወተትም፣ ብስኩትም፣ ልብስም፣ ምግብም፣ ታክሲም፣ ሁሉም ነገር ለምን ይከፈልበታል? ለምን ሁሉም በነፃ የፈለገውን እየበላ ደግሞ እየሰጠ አይኖርም?›› ብላ ብትጠይቅ ጥያቄና መልሱን መቋጫው የጨነቃት እናት፣ ‹‹እሱ ስታድጊ ይገባሻል…›› ብላ አለፈቻት። ከገባን ይልቅ የተምታታብን እንደማይብስ ሁሉ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንዱ፣ ‹‹አሁን ይኼ ምን የሚሉት ዓይን አውጣነት ነው…›› እያለ ስልኩን ይነካካል። ‹‹ማን ነው?›› አለችው ከጎኑ የተሰየመች። ‹‹አንድ ወዳጄ ነው እንጂ። ሥራ ሊቀጠር አንድ መሥሪያ ቤት ሄዶ ቀድመው ጥያቄና መልስ ያገኙ ናቸው የሚቀጠሩት ብሎኝ እኮ ነው…›› ሲል፣ ‹‹የመንገዱ ፀባይ ነው፣ ምንም ማድረግ አይቻለም። ይኼ መንገድ እንደሆነ ገና ብዙ ብዙ ያነጋግራል። እንዲያውም እኛ እኮ አንነጋገርም ያልነው…›› ብላ ጣል አደረገችበት። ‹‹ኤድያ! ተነጋገርን አልተነጋገርን ማን ሊያዳምጥ። ገና ሀ ብለን ሁ ሳንል በየፊናችን ዱላና ዕብሪት ሲቀድመን ነው የኖረው። ተጨነቁ ብሏችሁ…›› አለች ሌላዋ። ‹‹የለም! እንደዚያማ አይባልም። በአሥር ሚሊኒየም አንዴም ቢሆን መነጋገር ጥሩ ነው። ይህችን ታህል ያኖረን ምን ሆነና? ደህና ዋልክ፣ ደህና አደርሽ መባባላችን አይደለም እንዴ?›› ሲላት ከጀርባዋ የሚወዛወዝ ጎልማሳ፣ ‹‹እሱማ ሰሞኑን ነገር አብርዱ ተብሎ ሰው አገር ድረስ ሄደን የምንደራደረው ይህንን ወግ አናውቅበት ብለን አይደል እንዴ…›› ብላ መለሰችለት። እውነትም ማወቅ ተስኖናል!

‹‹ታዲያ የምን ንግግር ነው የናፈቃችሁ?›› ጠየቀ ጎልማሳው ግራ ገብቶት። ‹‹የአንተ ትብስ የአንቺ ትብስ ነዋ። ‹ይኼው ጥፋትህ እንዲህ ያደረግከው፣ እንደዚህ ቢሆን ነበር መልካም› ሲባል፣ ‹ልክ ነው ተቀብያለሁ፣ ተሳስቻለሁ› የምንባባልበት ንግግር ነው ያልንህ አይደለም እንዴ?›› ብላ ዙሪያ ገባውን ስትቃኝ አዛውንቱ፣ ‹‹እሱማ ፍቅሩን መቀባበል ስንጀምር መሆኑ አይቀርም። ነፍሳቸውን ይማረውና የድሮ ሰዎች እንዲህ ያለው ነገር ሲገጥማቸው፣ ‹የማይተካ ነገር የለም፣ ዋናው ቁም ነገር ሰው ሆኖ መገኘት ነው እንጂ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ግን በዋሉበት ማደር ብርቅ ሆኗል፡፡ ለቃል ታማኝ መሆን አልተቻለም፡፡ የሰላም ስምምነት ተፈራርመው የሚክዱ ጉዶችን እያዩ ነበር፡፡ ነገሩ ገና ይቀጥላል…›› ሲሉ ተሳፋሪዎች በኅብረት በአንድ ድምፅ ‹‹እንዴት ሆኖ ይቀጥላል?›› ብለው በጥያቄ ጮኹ። ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ወያላው በሩን ሲከፍት ከእነ ጥያቄያችን ወርደን ማዝገም ስንጀምር አዛውንቱ፣ ‹‹እስከዚያማ ከሰው የሚጠበቀው አስተዋይ መሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ማስተዋል ብርቅ ሆነ፡፡ ቃል አባይ መሆን ተስፋፋ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ነገራችን ሁሉ የቸገረ ሆኖ ግራ ያጋባናል…›› ብለውን መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት