ብርሃን ለሕፃናት የማኅበረሰብ ተሃድሶ መርህን መሠረት በማድረግ፣ በዋናነትም አካል ጉዳተኛና ሌሎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ለማገዝ ከ25 ዓመታት በፊት በጥቂት በጎ ፈቃደኞች የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡ ሰሞኑን ሩብ ምዕት ዓመቱን አክብሯል፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱትና በሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርነት የሚመሩት ወ/ሮ እቴነሽ ወንድማአገኘሁ ናቸው፡፡ በአካል ጉዳተኛ፣ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን በመንከባከብና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የ‹‹ብርሃን ለሕፃናት›› ሥራን ለመጀመር በተንቀሳቀሱበት ወቅት ዕገዛና ድጋፍ ያደረገልዎት ማን ነው?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው ከኖርዌይ ሕፃናትን አድን ድርጅት በተገኘ አነስተኛ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ የተቋቋመውም በቀድሞ ወረዳ 22 በአሁኑ በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች 285 አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን በመርዳት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በአፋር ክልሎች በሰባት ማስተባበሪያ ቢሮዎች አማካይነት እየሠራ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ አካል ጉዳተኛና ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት በመንከባከብ ረገድ እየተጫወተ ያለውን ሚና ቢገልጹልን?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- እስካሁንም ከ18,000 በላይ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ሕይወት በመቀየር በማኅበረሰቡ ውስጥ ተካትተው እንዲኖሩ አስችሏል፡፡ ከ4,500 የሚበልጡ ሌሎች ለችግር የተጋጡ ሕፃናት ሕይወት እንዲቃና ያደረገ ሲሆን፣ ከ3,135 በላይ ወላጆችን በገቢ ማስገኛ ፕሮግራም በቀጥታ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ለልጆቻቸውም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በዚህም የበርካቶችን ሕይወት ማሻሻል ተችሏል፡፡ የሕፃናት አካል ጉዳተኝነት እንዳይከሰትና ከተከሰተም በኋላ ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረገ የተሃድሶ ፕሮግራም በማዘጋጀት አካል ጉዳተኛ ሕፃናት እንደማንኛውም ጉዳት አልባ የዕድሜ እኩዮቻቸው እንዲኖሩ፣ እንዲማሩ፣ እንዲሠሩና ራሳቸውን እንዲችሉ ብሎም አገራቸውን እንዲያለሙ ለማብቃት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኞች ከሚቸገሩበት አንዱ ከግንባታዎች ጋር የተያያዙ፣ የተደራሽነት ችግሮች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ምን ትሠራላችሁ?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ድርጅታችን አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሥራዎች ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር ይሠራል፡፡ ከእነዚህም መካከል ድርጅታችን ከተመሠረተበት ከ1991 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ከቀድሞ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአሁኑ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች በሚያመች መልኩ ተደራሽ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ግንዛቤ እንዲያገኙ ብርሃን ለሕፃናት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በዚህም መነሻነት በተለይ ሕንፃዎች ሲገነቡ መውጫና መግቢያ በሮች እንዲሁም ደረጃዎች ለአካል ጉዳተኛው ተደራሽ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ሕግ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲወጣ ለማድረግ ተችሏል፡፡
ሪፖርተር፡- ሕግ መውጣቱ አንድ ነገር ሆኖ፣ ለተግባራዊነቱ ምን ያህል ተንቀሳቅሷል?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ሕጉ ዕውን እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንዛቤ የመፍጠር፣ የማስታወስና የመጎትጎት ሥራ እያከናወንን ነው፡፡ ለዚህ ‹‹ሐንዲካፕ ናሽናል›› የአሁኑ ብርሃን ለሕፃናት ሚናው ጉልህ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በትምህርት ዙሪያ ብርሃን ለሕፃናት ያበረከተውን አገልግሎት እንዴት ይገልጹታል?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ከትምህርት ጋር በተያያዘ ድርጅቱ ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ለመምህራን፣ ለርዕሰ መምህራን፣ በትምህርት ሥራ ላይ ለተሰማሩና በቀጥታ ሥራው ለሚመለከታቸው አካላት በልዩ ፍላጎትና በአካቶ ትምህርት ዙሪያ በተደጋጋሚ ሥልጠናዎች የሰጣቸው ይገኙበታል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ከ17,000 በላይ ተሳታፊዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እንዲሁም ድርጅቱ በሚሠራባቸው ክልሎች ውስጥ ያሉ 392 ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ምቹና ክፍት እንዲሆኑ አቅም በፈቀደ መጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በዚህም የተሻለ የትምህርት ጥራት እንዲኖርና መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሐዋሳ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ገንብቶ ለመንግሥት አስረክቧል፡፡
ሪፖርተር፡- ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት በትምህርት ቤት ዕጦት የተነሳ ፍላጎታቸው እንዳይስተጓጐል ብዙ ጥረት ማድረጋችሁ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ ቢሰጡን?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- የሕፃናት የማጠናከሪያ ፕሮግራም መጀመሩ ተማሪዎች በአካባቢያቸው እንዲማሩና በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ አስችሏል፡፡ በሌላ በኩል በቱላ ወረዳ ዕድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት የትምህርት ዕድል ያላገኙ ሕፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰባት መሠረታዊ አማራጭ የትምህርት ጣቢያዎችን በመገንባት ብዙ ሺሕ ሕፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ከተገበሩት የአማራጭ ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች መካከል አምስቱን መንግሥት ተረክቧቸው ወደ መደበኛ ትምህርት ቤትነት በማሳደግ ለማኅበረሰቡ ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በደሴ ከተማ ስምንት የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ አንድ ፎቅ የሪሶርስ ማዕከል ገንብቶ በከተማዋ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኛ፣ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
ሪፖርተር፡- ልዩ ፍላጎት ካላቸው ዜጎች ለምልክት ቋንቋ ተጠቃሚዎች ምን ዓይነት ድጋፍ ተደርጓል?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች የተለያዩ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ድርጅታችን ከኮተቤና ከሐዋሳ መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጆች ጋር በመተባበር በቅርበት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በተለይ ከሐዋሳ መምህራን ማሠልጠኛ ኮሌጅ ጋር የአራት ዓመት የውል ስምምነት በመፈራረም ሁሉም ተመራቂ መምህራን የብሬል ጽሑፍና ንባብ እንዲሁም የምልክት ቋንቋ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በኮሌጁ የልዩ ትምህርት ክፍል በመክፈት የተጀመረው ሥራ በዘላቂነት ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ተችሏል፡፡ ለዚህ ውጤት የኮሌጁ አመራር፣ መምህራንና የትምህርት ቤቱ ኅብረተሰብ ጥረት የላቀ ነው፡፡ የብርሃን ለሕፃናት ድርጅት ያደረገው ድጋፍ ፍሬ በማፍራቱና በርካታ ሕፃናት ተጠቃሚ በመሆናቸው ዕርካታ ይሰማዋል፡፡ ይህም ውጤታማ ተሞክሮ በደሴና በጎንደር መምህራን ትምህርት ኮሌጆ በመተግበር ላይ ሲሆን፣ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ብርሃን ለሕፃናት ሲያራምደው የቆየው የአካቶ ትምህርትን የማስፋፋት ጥረት፣ በተለይም የብሬል ማንበብና መጻፍ እንዲሁም የምልክት ቋንቋ ክህሎት በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች እንዲሰጥ በትምህርት ሚኒስቴር ተወስኗል፡፡
ሪፖርተር፡- በአካል ጉዳት ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር የሚያስችል እንቅስቃሴ ይስተዋላል፡፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ድርጅታችን ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረምና በትብብር በመሥራት፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እንዲሁም የትምህርት አመራር አካላት ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን የአካቶ ትምህርት ማጣቀሻ መመርያ አዘጋጅተው ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ የተለያዩ ዓውደ ጥናቶች በማዘጋጀት በአካል ጉዳት ዙሪያ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር ማኅበረሰብ ተኮር የግንዛቤ ማስጨበቻ ፕሮግራሞችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴ ለማጠናከር በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞችን አቅርቧል፡፡ በዚህም ከሦስት ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መድረስ እንደተቻለ ይገመታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ጉዳይ በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እየተሰጠው በመሆኑ ደስተኞች ነን፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከውጭ ዕርዳታና ድጋፍ ለመላቀቅ ምን እየሠራ ነው?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ብርሃን ለሕፃናት አካል ጉዳተኝነትን የመከላከልና የተሃድሶ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው ቦታዎች ሁሉ ከጤና ኤክስቴነሽን ባለሙያዎች ጋር በጥምረት ይሠራል፡፡ ይህን ጥምረት አጠናክሮ በመቀጠሉ ክህሎት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲሸጋግር ከማድረጉም በተጨማሪ፣ በአንዳንድ የፕሮጀክት ቦታዎች የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ተደርጎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ በጎ ጥረትና ውጤት እንደ ትምህርቱ ሁሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፡፡ የብርሃን ለሕፃናት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ራሳቸውን እስኪችሉ የተሃድሶ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተጋ የሚገኝ ሲሆን፣ በሁሉም ሥፍራ የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ማዕከላት ገንብቷል፡፡ ይህም በትንሽ ወጪ ብዙ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ለመድረስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውጭ ዕርዳታና ድጋፍ ከመተማመን ይልቅ በሒደት የራሱን ገቢ በማመንጨት ራሱን ለመቻል እየተጋ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች ሁሉ የድርጅቱን ልፋትና ጥረት ከግምት በማስገባት፣ ከሊዝ ነፃ የሆነ ቦታ በመስጠት አካል ጉዳተኛ ሕፃናት በአስተማማኝ ሁኔታ የተሃድሶ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ድርጅቱ ራሱን ለመቻል የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የመንግሥት አካላት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተረፈ የሃያ አምስተኛ ክብረ በዓል የተዘጋጀበት ዋና ዓላማም ድርጅቱ እስካሁን ያከናወናቸውን በጎ ተግባራት በጥልቀት ለማጤን፣ የተለያዩ ድክመቶቻችንን ለማረም፣ በቀጣይ ዓመታት ተጠናክረን መቀጠል የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመላከትና ለአካል ጉዳተኛና ሌሎች ለችግር የተጋጡ ሕፃናትን እንዲሁም ለወላጆቻቸው የሚደረገውን የማብቃት ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል ድርጅታዊ ብቃታችንን የምናጎለብትበት ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ በቀጣይም በየክልሉ ዕገዛ የሚያገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመድረስ፣ በሥራ ሒደት ያከናወናቸውን የአሠራር ሥልቶች ወደ ሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለማስተላለፍ ጠንክረን የምንሠራበት ጊዜ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ዕገዛ አድርገዋል ብለው የሚገልጿቸው አሉ?
ወ/ሮ እቴነሽ፡- ብርሃን ለሕፃናት ላለፉት 25 ዓመታት ላከናወናቸው የሕፃናትና የማኅበረሰብ ተኮር አገልግሎቶችና ያስመዘገባቸው ውጤቶች፣ በተለይም በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ሕይወታቸው እንዲቀየር ላስቻላቸው በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ድጋፍ የሆኑን ለጋሽ ድርጅቶች፣ የመንግሥት አካላት፣ የድርጅታችን ጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ለችግር የተጋጡ ሕፃናትና ቤተሰቦች፣ የማኅበረሰቡ ተወካዮች ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡