በአበበ ፍቅር
ለአንድ አገር የዕድገት መሠረት ከሆኑት መካከል ትምህርት ከቀዳሚዎቹ ይመደባል፡፡ የተሻለና ለሰው ልጅ ምቹ የሆነ ዓለም ለመፍጠርም ዋና መሣሪያው ነው። መንግሥትም በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የትምህርት ምኅዳሩን ለማስፋትና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ፣ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ሲገጥሙት ይስተዋላል። ከችግሮቹ መካከልም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ ሲያስተጓጉል የነበረውና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መፍትሔ እያገኘ የመጣው የተማሪዎች ምግብ አለመመገብና ረሃብ ይገኝበታል፡፡
ምንም እንኳን ችግሩ በዓለም ዙሪያ የሚያንዣብብ ቢሆንም፣ ባላደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች በስፋት ይስተዋላል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም በዓለም ላይ በምግብ ዕጦት በየዓመቱ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ። ሳይመገቡ የሚማሩ ተማሪዎችም ለተለያዩ የጤና ችድሮች ተጋላጭ በመሆናቸው፣ ለትምህርታቸው ትኩረት አይሰጡም፡፡ ውጤታቸውም ዝቅተኛ ሲሆን ትምህርትም ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡
የችግሩን አሳሳቢነት መነሻ በማድረግ ተማሪዎች ትምህርታችውን በአግባቡ እንዲከታተሉ በሚል የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ1954 በብራዚል መጀመሩን ተከትሎ በተለያዩ የዓለም አገሮች ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡
በአፍሪካም በ54 አገሮች ውስጥ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በዚህ የምገባ ፕሮግራም 65.4 ሚሊዮን ሕፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በኢትዮጵያ በንጉሡ ዘመን ለተማሪዎች ወተት፣ በደርግ ደግሞ ለሕፃናት የዱቄት ወተትና የፋፋ ድጋፍ የሚሰጥበት አሠራር የነበረ ቢሆንም፣ ከቅድመ መደበኛ እስከ መጀመርያ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች በቀን ሁለቴ እንዲመገቡ መደረግ የጀመረው በመንግሥት መዋቅር ገብቶ ከሦስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡
በተወሰነ መልኩ የተጀመረው በኢትዮጵያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ እያደረጉ ከሚገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መካከል ዓለም አቀፉ የሕፃናት አድን ድርጅት አንዱ ነው። ዓለም አቀፍ ትብብር ለትምህርት (ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኤጁኬሽን) ድርጅት ለትምህርት ሚኒስቴር ያበረከተውን የገንዘብ ድጋፍ መነሻ በማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሕፃናት አድንና ከክልል አጋር ተቋማት ጋር በመሆን፣ ሁሉን አቀፍ አገር በቀልና አካታች የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር በስኬት መጠናቀቁን አሳውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ከታኅሣሥ 1 ቀን 2020 እስከ መስከረም 30 ቀን 2022 ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ 223,301 ሕፃናትን በትምህርት ምግባ እንዲሁም ለ163,021 ለሚሆኑት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ከተጠቃሚዎቹ 68,261 የሚሆኑት ሴቶች እንደነበሩና ከተማሪዎች ባሻገር በሁሉም በፕሮጀክቱ በታቀፉ ትምህርት ቤቶች 5,558 ለሚሆኑ መምህራን የተለያዩ የአቅም ግንባታ ድጋፎች እንደተሰጠ ተጠቁሟል፡፡
ሁሉን አቀፍ አገር በቀልና አካታች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮጀክትን መጠናቀቅ ተከትሎ፣ ዓለም አቀፍ ትብብሩ በስድስት ክልሎች በሚገኙ በ13 ወረዳዎች፣ በ578 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ አገልግሎትና ሌሎች ተያያዥ ድጋፎችን ለማስቀጠል ተጨማሪ የ10 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደተፈራረመ በሚኒስቴሩ የመሠረተ ልማትና አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳዊት አዘነ ተናገረዋል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው በድርቅና በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ላይ ሲሆን፣ ከ200 ሺሕ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አቶ ዳዊት ለሪፖርተር አብራርተዋል።
አገር በቀልና አካታች የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ስኬታማ እንደነበር የገለጹት በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የትምህርት ትብብር ዳይሬክተር ሱብራታ ዳሃር (ዶ/ር) ናቸው። ዳይሬክተሩ ድርጅታቸው በ89 አገሮች እንደሚንቀሳቀስና ከእነዚህ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቅድሚያ የተሰጣት መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ናቸው። መንግሥት የምገባ ፕሮግራሙን እንደ ኢንቨስትመንት እንጂ እንደ ወጪ አይመለከተውም፡፡ በመሆኑም ከዓለም የምግብ ፕሮግራም አጋር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን በመላ ኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ምገባን የማስተባበሪያ ፖሊሲና ስትራቴጂ አዘጋጅቷል ብለዋል።
ስትራቴጂውን እስከ 2030 ድረስ ለመተግበር አቅጣጫ የተቀመጠለት ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።
በሕፃናት አድን ድርጅት የዓለም አቀፍ አጋርነት ለትምህርት የተሰኘው ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቢቲ ታደለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የተማሪዎችን ለረሃብ ተጋላጭነት በመቀነስ ሙሉ ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ በማድረግ ጥሩ የትምህርት አቀባበል እንዲኖራቸውና አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማስቻል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት የምገባ ፕሮግራሙ ዘለቄታዊ እንዲሆን ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠሩም አብራርተዋል። እየታየ ካለው ድርቅና ረሃብ አንፃር በፕሮጀክቱ የታቀፉ ትምህርት ቤቶች ቁጥራቸው ለምን አነሰ? ሲል ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ በገበያ ላይ ያለው የእህል ዋጋ መናር፣ ከነዳጅ መጨመር ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ወጪ መጨመርና ተያያዥ ጉዳዮች ተደራሽነታቸውን እንደገደበው ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከተመረጡ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሶማሌ፣ ከደቡብና ከሲዳማ ክልሎች የተገኙ ሲሆን፣ ከሶማሌ ክልል የመጡት አቶ ኢብራሂም አዴርሰው ከ12 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ እንደታቀፉና ተማሪዎችም በትምህርታቸው ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአማራ ክልል ዋግህምራ ልዩ ዞን የመጡት አቶ ጌታቸው ቢያዝን ደግሞ፣ ምገባ በጀመሩባቸው ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች መቅረት እንደቀነሰ ገልጸዋል፡፡