ሀገር ማለት ሰው ነው
ሕዝብ ማለት ሀገር
ያንድ ሳንቲም ተምሳል
የዘውድና ጎፈር
ይሉትን ምሳሌ … ወስኜ ላጣራ
ድብ ተጫወትኩኝ … ከንጉሤ ጋራ፡፡
እሱ ሀገር ወካይ… እኔ ያው ሕዝብ ነኝ
የማስፈነጥራት… ድምብሎም የሌለኝ፡፡
እሱ አሽቀነጠረ… ሽቅብ ወረወረ
መልሶ ቀለበ… ከመዳፍ አኖረ
ጥያቄው ይኼ ነው
ከጁ መሀል ያለው
ዘውዱ ነው? ጎፈር ነው?
ጥያቄው ይኼ ነው፡፡
ዘውዱን በአምበሳ… አጥሮ ለከበበው
ጥያቄም ጥያቄ… ጥያቄም መልሱ ነው፡፡
ብዬ ግጥም መጻፍ… መጻፍ ጀመርኩና
ጀምሬ አቋረጥኩት… ተደናገርኩና፡፡
- አንዱዓለም ጌታቸው ‹‹ዮሬካ››፣ 2008