- 16 ክለቦች እያንዳንዳቸው 2.1 ሚሊዮን ብር አግኝተዋል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የ2015 ዓ.ም. የቴሌቪዥን መብት የመጀመርያ ክፍያን መፈጸሙን አስታወቀ፡፡
የ2015 ዓ.ም. የውድድር ዘመን በባህር ዳር የጀመረው አክሲዮን ማኅበሩ፣ የአምስት ሳምንት ጨዋታቸውን ካጠናቀቀ በኋላ ከ33 ሚሊዮን በላይ ክፍያን ለክለቦች መከፋፈሉን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት በሊጉ እየተካፈሉ የሚገኙ 16 ክለቦች እያንዳንዳቸው 2.1 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመላቸው፣ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ክለቦቹ ካገኙት የቴሌቪዥን የመብት ሽያጭ ክፍያ የኮሚሽነሮችና የዳኞችን ክፍያ መፈጸም መቻላቸው ተጠቅሷል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ከዲኤስቲቪ ጋር ውል ያሰረው አክሲዮን ማኅበሩ፣ ከቴሊቪዥን መብት ሽያጭና ከተለያዩ ማስታወቂያዎች ያገኘውን ገንዘብ ለክለቦች የአባልነት ክፍያ ይፈጽማል፡፡
ከዚህም ባሻገር በውድድሩ መጠናቀቂያ ላይ ባጠቃላይ ያገኘውን ክፍያና እንደ ደረጃቸው ለኮከብ ተጫዋቾችና አሠልጣኝ፣ ለኮከብ ዳኞችና ውድድሩን ላስተናገዱ ስታዲየሞች ክፍያ ይፈጽማል፡፡
የክፍያውን አሠራር አስመልክቶ ሊግ ካምፓኒው ተሳታፊ ክለቦች ከስፖንሰሮች ከሚገኝ ገንዘብ 60 በመቶ እኩል እንዲከፋፈሉ ከተደረገ በኋላ፣ 25 በመቶውን ባስመዘገቡት ውጤትና ደረጃ መሠረት፣ ቀሪውን 15 በመቶ ደግሞ ለጽሕፈት ቤት ሥራ ማስኬጃ እንደሆነ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ከዚህም ባሻገር ሊግ ካምፓኒው ክፍያ የሚፈጸመው ትክክለኛ የፋይናንስ ሪፖርት እንደቀረበለት ብቻ እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይህም ክለቦች ያገኙትን ክፍያ ምን ላይ እንዳዋሉትና በምን ዓይነት የፋይናንስ ሥርዓት እንደተጠቀሙት የሚያሳይ በውጭ ኦዲተር የተረጋገጠ፣ የፋይናንስ ሪፖርት ለሊግ ካምፓኒው ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
በሌላ በኩል ሁሉም ጨዋታዎች በቴሌቪዥን መስኮትን መተላለፍ ከጀመረ ሦስተኛ ዓመት ላይ ቢገኝም፣ ክለቦች የቀጥታ ሥርጭት ዕድልን በመጠቀም በማስታወቂያ የገንዘብ ምንጭ ማሳደግ የሚቻልበት ዕድል መጠቀም አለመቻላቸው ይነገራል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ክለቦች በዙር በሚያደርገው ውድድር ከከተማ ከተማ እየተዘዋወሩ ጨዋታ ሲያከናውኑ፣ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ እንደሆነ ቅሬታ ሲያሰሙ ይስተዋላል፡፡