ለመሬት ምልከታ የሚያገለግሉ ሳተላይቶችን ካመጠቀ ኩባንያ ጋር ውል በመግባት የኢትዮጵያን ሁለተኛ ሳተላይት አምጥቆ፣ በኅብረ ሳተላይት (satellite constellation) በጋራ መረጃ ለመሰብሰብ ማቀዱን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከሌሎች ሳተላይቶች ጋር በኅብረት የምትሠራ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በተያዘው የ2015 በጀት ዓመት ለማምመጠቅ ዕቅድ እንደያዘና የኢትዮጵያን ሳተላይት በህብረ ሳተላይት ውስጥ የሚያካትት ኩባንያ የሚመረጥበት ጨረታ ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደሆነ፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛዋን ሳተላይት ለማምጠቅ የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ጥናቱ አንድ ሳተላይት ከማምጠቅ ይልቅ በኅብረ ሳተላይት (satellite constellation) ውሰጥ መግባት ተመራጭ እንደሚሆን ማመላከቱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን 1.1 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት በአንድ ሳተላይት መሸፈን እንደማይቻል የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ላይ አንዴ ብታልፍ መልሳ በአዲስ አበባ ላይ ለማለፍ ሌላ 20 ወይም 30 ቀን ይፈጃል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያን ያህል የመሬት ስፋት ያላቸው ሌሎች አገሮች እስከ 40 የመሬት ምልከታ ሳተላይት እንዳለቸው ገልጸው፣ ሳተላይት ለማምጠቅ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅና አሁን ባለው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይኼንን ማድረግ የሚቻል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ኅብረ ሳተላይት ለአንድ ዓላማ ተልከው ምድርን የሚዞሩ ሳተላይቶች ስብስብ ሲሆን፣ ከአንድ የምድር አካባቢ መረጃ ለማግኘት አንድ ሳተላይት ዞሮ እስከሚመለስ ለመጠበቅ ሳያስፈልግ ተተኪ ሆኖ ያንን አካባቢ ከሚዞር ሌላ ሳተላይት መረጃ መቀበል ይቻላል፡፡
‹‹የእኛ ሳተላይትም አብሮ ተልኮ እንዲሠራ ይደረግና ከሌሎቹም ሳተላይቶች ቶሎ ቶሎ መረጃ የማግኘት አቅምን ይፈጥራል፤›› ያሉት አቶ አብዲሳ፣ ለመሬት ምልከታ የሚሠሩ ሳተላይቶችን በዚሁ መንገድ ያመጠቁ ኩባንያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ዓላም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ኩባንያዎቹን አወዳድሮ ለመምረጥ ማሰቡን አክለዋል፡፡
በጨረታ የሚመረጠው ኩባንያ የማምጠቅ ሥራውንም ያከናውን እንደሆን ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ዝርዝር ነገር ወደፊት ብንሰጥ እመርጣለሁ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ መንገድ የምትመጥቀው ሳተላይት ባለከፍተኛ ሪዞሉሽን እንደምትሆን ተገልጿል፡፡
ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነችው ETRSS-1 የመሬት ምልከታ ሳተላይት የመጠቀችው ከሦስት ዓመት በፊት ታኅሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከቻይና የመጠቀችው ባለ 72 ኪሎ ግራሟ ETRSS-1 ሳተላይት ግብርና በአካባቢ ጥበቃና በአየር ሁኔታ ዙሪያ መረጃ የምትሰጥና ኢትዮጵያ ለሳተላይት ኪራይ በዓመት ትከፍል የነበረውን ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደምታስቀር ተገልጾ ነበር፡፡
ሳተላይቷ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት የሚያገለግል ከ610 እስከ 640 ሜትር ስፋት ያለው ያለ የደን ምንጣሮ የሚካሄድበት ሥፍራን መለየትን አንስቶ የደን ሽፋን ክትትል፣ ለቱሪዝም መዳረሻዎች ልየታ ያገለገሉ መረጃዎችን ማስተላለፏ ተገልጿል፡፡
የመጀመሪያዋ ሳተላይት የተገመተላት የቆይታ ጊዜ ሁለት ዓመት ተኩል እንደነበር የገለጹት አቶ አብዲሳ፣ ይኼ ጊዜ የሚጠናቀቀው ሰኔ 2014 ዓ.ም. እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ሳተላይቷ ከታቀደላት ጊዜ አምስት ወራትን ጨምራ እስካሁን እያገለገለች መሆኑን ተናግረዋል፡፡